በሌማት ትሩፋት የተከፈተ እንጀራ

ጓደኛሞቹ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ከፋ ዞን ፤ ጊምቦ ወረዳ ጎጀብ ቀበሌ ውስጥ ነው የሚኖሩት። ከትምህርታቸው ጎን ለጎን አንዱ ሽንኩርት በመነገድ ሌላው ደግሞ ልኳንዳ ቤት በመሥራት ኑሮአቸውን ይደጉማሉ። ከሚያገኙት ገቢም በየወሩ እቁብ ይጥላሉ። እቁብ ሲደርሳቸው ተጨማሪ ሥራ መፍጠር እንዳለባቸው ጓደኛሞቹ ይመክራሉ።

ገበያውን ሲያጠኑም ወተት ለተጠቃሚው ማቅረብ አዋጭ ሆኖ አገኙት። ወስነውም አንዲት ላም ከነጊደሯ ስድስት ሺ ብር ገዝተው ሥራ ጀመሩ። በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥም ውጤት አገኙበት። ጠዋትና ማታ ታልቦ ለገበያ ከሚያቀርቡት ወተት ዘጠኝ ሺህ ስድስት መቶ (9600) ብር አገኙ። በአንድ ላም የተገኘው ውጤት ወደ ሁለተኛ እቅድ አሸጋገራቸው።

ጓደኛሞቹ ከስድስት ዓመት በፊት ጀምረው ውጤታማ ያደረጋቸውን የወተት ልማት የላሞች ቁጥር በመጨመርና ሌሎች ጓደኞቻቸውንም በማሳተፍ የበለጠ ቢያጠናክሩት ትርፋማ እንደሚያደርጋቸው አቀዱ። እቅዳቸውንም ወደ ተግባር ለመቀየር በእንቅስቃሴ ላይ እያሉ በማህበር ተደራጅተው በመረጡት የሥራ መስክ ለመሰማራት ፍላጎት ላላቸው ወጣቶች ለሥራ መነሻ ብድር ይመቻችላቸዋል የሚል ከሚኖሩበት ወረዳ መልካም ዜና ሰሙ። ለእቅዳቸው መሳካት መልካም አጋጣሚ ሆነላቸው።

ብድሩን ያመቻቸላቸው ኦ ማይክሮ ፋይናንስ የተባለ አበዳሪ ድርጅት ሲሆን፣ 74ሺ ብር ብድር ፈቅዶላቸው እቅዳቸውን ወደ መተግበር ሥራ ገቡ። በሁለት ጓደኛሞች የተጀመረው የወተት ልማት ሥራ አራት አባላትን አፍርቶ ወደ ኢንተርፕራይዝ ከፍ አለ። በየጊዜው ለውጥ እያስመዘገቡ፣ ወደ ኢንዱስትሪ ለመሸጋገር ሩቅ አልመው መጓዝ ጀመሩ።

እኛም የአካባቢያቸውን ፀጋ ለይተው እየተጠ ቀሙበት ያሉትን የነዚህን ባለራዕይ ወጣቶች የሥራ እንቅስቃሴ በሥፍራው ተገኝተን ለማየት እድሉን አግኝተናል። መነሻ ሃሳቡን ከማፍለቅ ጀምሮ ኢንተርፕራይዙንም በመምራት እስካሁን በሥራው ውስጥ ከሚገኘው ወጣት በረከት ደገፉ ጋር ነበር ቆይታ ያደረግነው። ለኢንተርፕራይዛቸውም መጠሪያ ‹‹ኑኒ ከፈቾ›› የሚል ስያሜ ሰጥተውታል። ስያሜው ወደ አማርኛ ሲመለስ ‹‹እኛ የከፋ ልጆች›› ማለት እንደሆነም ወጣት በረከት ነግሮናል።

ወጣት በረከት እንደገለጸልን፤ ከጓደኛው ጋር ሆነው የጀመሩትን ሥራ ለማሳደግ ሁለት አባላትን ጨም ረው አራት በመሆን ወደ ኢንተርፕራይዝ የተሸጋገሩ ቢሆንም አንዱ አባላቸው በሞት ስለተለያቸው ቀሪዎቹ ናቸው ሥራውን የቀጠሉት። ከአባላቱ መካከልም አንድ ሴት ትገኛለች። ኢንተርፕራይዙ ከኦ ማይክሮ ፋይናንስ አበዳሪ ድርጅት ባገኘው ብድርም ሶስት የወተት ላሞች ከነጥጆቻቸው ገዝቶ ሥራውን ያሰፋ ሲሆን፣ የወጣቶቹን ትጋት የተገነዘቡ የአባላቱ ቤተሰቦች ደግሞ ለሥራ የሚሆን ቦታ በመስጠት ትብብራቸውን አሳይተዋል። የአካባቢው ማህበረሰብ የአገዳና የሩዝ ተረፈ ምርት መኖ በመስጠትም አበረታትቷል። ለዚህም አባላቱ ትልቅ ምስጋና አላቸው።

ላሞቹ ያለ ማቋረጥ ለስድስት ወር ያህል ነበር የታለቡት። ተሸጦ ከሚገኘው ገቢም ተጠራቅሞ ለከብቶቹ በረት (ማደሪያ) ተሰራ። ላሞቹ ሲነጥፉም ተሽጠው ተጨማሪ ገበያ አስገኝተዋል። በአሁኑ ጊዜም የወተት ምርታማነትን በመጨመር ገቢን ለማሳደግ በተሻሻሉ ዝርያዎች ለመተካት ጥረት በማድረግ ላይ እንደሆኑ ነው ወጣት በረከት የነገረን።

እንደ ወጣት በረከት ገለጻ፤ ላሞቹ ሲነጥፉ ከሥር ከሥር እየተሸጡ በመሆኑ ቁጥራቸው በየጊዜው ይለያያል። አሁን ላይ 14 የወተት ላሞች ናቸው ያሉት። የኢንተርፕራይዙ አባላት እንደ ሀብት (ካፒታል) የሚቆጥሩት ያሏቸውን ከብቶች፣የሰሩትን በረት፣ እስከዛሬ ባገኙት ገቢ በኑሮአቸው ላይ ያመጡትን ለውጥ ጭምር ነው።

እያንዳንዱ አባል፣ የራሱን መኖሪያ ቤት ሰርቷል። ቤተሰብም መሥርቶ እየመራ ይገኛል። ይሄ ለአባላቱ ትልቅ ለውጥ ነው። ወጣት በረከት ‹‹ሁላችንም የኢተርፕራይዙ አባላት አንድ እርምጃ ተራምደናል›› ሲል ነው ስኬታማነታቸውን የገለፀው። ለኢንተርፕራይዙ ህልውና የሚሆን በባንክ መጠነኛ ቁጠባ መኖሩንም ነግሮናል።

በኢንተርፕራይዝ ተደራጅተው በዚህ ሥራ ውስጥ ባይሆኑ ኖሮ እጣ ፈንታቸው ለቤተሰብ ሸክም መሆን፣ አልባሌ ቦታም የሚውሉበት አጋጣሚ ይፈጠር እንደነበር ነው ወጣት በረከት ያጫወተን። ሥራው ጥንካሬንና ትዕግሥትንም እንደሚጠይቅ ይገልጻል። ‹‹ውጤት የሚገኘው በሂደት ነው። ተስፋ የሚያስቆርጡ ነገሮች ያጋጥማሉ። በትዕግሥት ከታለፈ ግን ውጤት ይገኛል። ውጤቱን እያዩ ሲሄዱ ደግሞ የመሥራት ፍላጎት ይጨምራል። በዚህ መንገድ ውስጥ አልፈን ነው በሥራው ላይ የቆየነው›› ሲልም የሥራ ቆይታቸውን አጫውቶናል። ኢንተርፕራይዙ የራሱን አባላት ብቻ ሳይሆን፣ ለስድስት ወጣቶችም የሥራ እድል በመፍጠር አስተዋጽኦ ማበርከቱንም አመልክቷል።

ከብቶችን የሚያጠቃ ገንዲ የተባለ ዝንብ በአካባቢው ላይ በስፋት መኖሩን የገለፀልን ወጣት በረከት፤ የእንስሳቱን ጤና መጠበቅ ወሳኝ እንደሆነም ይገልጻል። በዚህ በኩል ወረዳው በከፍተኛ ሁኔታ እገዛ እያደረገላቸው እንደሆነ ነው የነገረን። ለገንዲ ዝንብ መከላከያ የሚሆን መድኃኒትና ህክምና በነፃ እንዲያገኙ እንዳመቻቸላቸውና ይህም ከፍተኛ ድጋፍ እንደሆናቸው ነው የገለጹልን። የተሻሻለ ዝርያ ያላቸው ከብቶችን የሚያገኙበት መንገድ ወረዳው እያመቻቸላቸው መሆኑን ነግሮናል። እርሱ እንዳለው አካባቢው ላይ የተሻሻለ ዝርያ ያላቸው ከብቶችን የመጠቀም ልምድ ባለመኖሩ በወተት ላምም ሆነ በሥጋ ምርታማነት ላይ መቀነስ ይስተዋላል።

ምርታማነታቸውን ለማሳደግ በወረዳው በኩል እየተፈጠረላቸው ያለው ምቹ ሁኔታ የበለጠ እንዲሰሩና ወደፊት ወደ ኢንዱስትሪ የማሳደግ እቅዳቸውን ለማሳካት ጉልበት እንደሚሆናቸው የሚናገረው ወጣት በረከት፤ ከወተት ምርት በተጨማሪ የሥጋ ከብቶችንም በማቅረብ፣ ንብ በማነብ ሥራቸውን የማስፋት፣ አቅርቦቱን በኢንዱስትሪ ደረጃ በማሳደግ የዓለም ገበያ ውስጥ መግባት፣ በሥራቸውም ከአካባቢያቸው አልፈው የሀገራቸውንም ስም ለማስጠራት ሰፊ እቅድ ይዘው እየሰሩ እንደሆነ ነው የገለፀው።

መንግሥት በሌማት ቱሩፋት በግብርናው ዘርፍ በእንስሳትና ወተት ልማት፣ በንብ ማነብ፣ በዓሣ ልማት፣ የሰጠውን ትኩረት ለመጠቀም መልካም አጋጣሚ እንደሆነም ያስረዳል።

በተለያየ ምክንያት ሥራ መፍጠር ያልቻሉ ወጣቶች ከእነርሱ ኢንተርፕራይዝ ምን ተሞክሮ ማግኘት ይችላሉ ብለን ላቀረብንለት ጥያቄ ወጣት በረከት የሚከተለውን መልሶልናል። ‹‹በአካልም በስልክም የሚጠይቁት ወጣቶች መኖራቸውንና አንድ ሥራ ሲጀመር ስኬት ብቻ ሳይሆን፣ ውጣ ውረዱንም ለመቋቋም በሥነ ልቦና ዝግጁ መሆን እንደሚያስፈልግ፣ ሥራ ለመጀመርም መፍራት እንደሌለባቸው፣ ውጤት ከመውደቅ መነሳት የሚገኝ መሆኑን ገልጾልናል። ›› በተለይ ደግሞ እነርሱ ያሳለፏቸው ችግሮች እንዳይገጥሟቸው በቀላሉ ለስኬት የሚበቁበትን መንገድ በማሳየት ምክሩን እንደሚለግሳቸውም ነው የገለፀው።

የሚሰሩ እጆች በሚያስፈልጉበት በዚህ ወቅት ሥራ ለመሥራት ጥረት ለማያደርጉ ወጣቶችም ወጣት በረከት መልዕክት አለው። ‹‹ሥራ መሥራት ለመንፈስ እርካታ፣ ለአካልም ጥንካሬ ነው። አንድ ሰው በዚህ ምድር ላይ ሲኖር በሚችለው ሁሉ ለሀገሩ አንድ ነገር ስርቶ ማለፍ ይኖርበታል።

ይህን ሳይገነዘቡ ሀገርንና ሕዝብን በሚጎዳ ተግባር የሚሰለፉ ወጣቶች ቆም ብለው ያስቡ ነው የምለው። ከጥፋት ሳይሆን ከልማት ነው ትርፍ የሚገኘው። ጊዜን በሥራ ከማሳለፍ ይልቅ አልባሌ ቦታ ላይ መዋልን የሚመርጡ ወጣቶች መኖራቸውን በአካበቢዬም እታዘባለሁ። በምክር ለመመለስ ጥረት አደርጋለሁ። ግን የብዙዎች ትብብር ነው የሚያስፈልገው።

እባካችሁ ወጣቶች እንስራ ነው የምለው። ወላጆቻችን ብዙ መሬት ኖሯቸው ግን እንዴት ምርታማ መሆን እንደሚችሉ በቴክኖሎጂ ባለመታገዛቸው በግብርናው ዘርፍ የሚፈለገውን ውጤት ማምጣት አልቻሉም። ኑሮአቸውም አልተለወጠም። እኛም እነርሱ ባለፉበት መንገድ ሳይሆን ግብርናውን በማዘመን ለለውጥ መነሳት ይኖርብናል። እኛ ለመሥራት ፍላጎቱ ካለን ለማደግ እድሉ አለን። እንጠቀምበት ነው የምለው›› ሲልም መልዕክቱን አስተላልፏል።

እንዲህ በትጋት እየሰሩ ላሉ ኢንተርፕራይዞች ክልሉ እያደረገላቸው ስላለው እገዛና ድጋፍ በከፋ ዞን ጊምቦ ወረዳ ሥራ ክህሎትና ገበያ ልማት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጌታቸው ዘውዴ እንደገለጹልን፤ በክልሉ በማህበር ተደራጅተው ወደ ሥራ ለሚገቡ ወጣቶች በግብርና፣ በአገልግሎት፣ በግንባታና በሌሎችም በመረጡት ዘርፎች የሥራ ዕድል ተመቻችቶላቸዋል።

በወረዳው በሚገኙ 30 የገጠር ቀበሌዎችና አምስት ማዘጋጃ ቤቶች ከሶስት መቶ በላይ የሚሆኑ በተለያየ የሥራ ዘርፍ የተደራጁ ኢንተርፕራይዞች መኖራቸውንና እያንዳንዱ ኢንተርፕራይዝም በቁጥር የተለያየ አባል ይዞ እንደሚንቀሳቀስ የጠቆሙት አቶ ጌታቸው፤ ከ2005 ዓ.ም ጀምሮ ሰፊ ቁጥር ላላቸው ዜጎች የሥራ እድል መፍጠር መቻሉን አመልክተዋል። ጎጀብ በማዘጋጃ ቤት ሥር ከሚገኙ አምስቱ መካከል አንዱ መሆኑንና ሰፊ የሥራ ዕድል የተፈጠረላቸው ወጣቶች የሚገኝበት አካባቢ እንደሆነም አመልክተዋል።

እንደ አቶ ጌታቸው ገለጻ፤ በጎጀብ ብቻ በከተማ ግብርና የተሰማሩ 28፣በማኑፋክቸሪንግ 3፣ በአገልግሎት 22 ኢንተርፕራይዞች ይገኛሉ። ይህን ያህል ኢንተርፕራይዝ ማፍራት የተቻለው ማዘጋጃ ቤቱ ትኩረት ሰጥቶ በመንቀሳቀሱና የወጣቶች የሥራ ተነሳሽነት በመጨመሩ ነው። በወተት ልማት ተሰማርተው ውጤታማ የሆኑት ‹‹ኑኒ ከፈቾ›› ኢንተርፕራይዝም የዚሁ አካባቢ ናቸው። ኢንተርፕራይዙ በሥራም ሆነ የተበደረውን ፈጥኖ በመመለስ በአርአያነት ይጠቀሳል። ተጨማሪ ብድር በማመቻቸትና የተለያዩ እገዛዎችንም እንዲያገኙ በማድረግ ኢንተርፕራይዞቹን ማበረታታት ያስፈልጋል። ወረዳው በሚችለው ሁሉ እያገዛቸው ይገኛል።

እንደ አቶ ጌታቸው ገለጻ፤ የድጋፍ ማዕቀፎችን ለይቶ በተሻለ እንቅስቃሴ ውጤታማ የሆኑትን ማበረታታት፣ ወደኋላ የቀሩትንም ክፍተቶቻቸውን ፈትሾ ማብቃት ያስፈልጋል። እየተሰራ ያለውም በዚህ መንገድ ነው። ‹‹ኑኒ ከፈቾ›› ኢንተርፕራይዝ የመሥሪያ ቦታ ችግር ነበረበት። አባላቱ ቤተሰብ በሰጣቸው ቦታ ላይ ነው እየሰሩ ውጤታማ የሆኑት። ይህን ጥረታቸውን በማየት ወረዳውና ማዘጋጃ ቤቱ በጋራ ተነጋግረው አሁን ላይ ለበረት የሚሆንና የግጦሽ ቦታ እንዲሰጣቸው አድርገዋል። ለአካባቢው ወጣቶች አርአያ በመሆኑም በተለያየ መንገድ ድጋፍ እየተደረገለት ነው።

የኢንተርፕራይዙን እንቅስቃሴ የሚያዩ የአካባቢው ወጣቶች ለሥራ እየተነሳሱ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ጌታቸው፤ ጎጀብ ውሽውሽ ከተማ ላይ በወተት ላም ልማት ወጣቶች ተደራጅተው ሥራ መጀመራቸውንና በተቀሩት ጊምቦ ወረዳ አካባቢዎችም በንብ ማነብ፣ ዳቦ ቤት በመክፈት ውጤታማ ሆነው በአርአያነት የሚጠቀሱ መኖራቸውን አመልክተዋል።

ወጣቶቹ በወተት፣ በማር፣ በዳቦ አቅርቦቶች ነዋሪውንም ተጠቃሚ ማድረጋቸው ሌላው በመልካም ጎን የሚጠቀስ እንደሆነም ገልጸዋል። በዓሣ ልማትም ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ መኖሩን አመልክተዋል። በገበያ ትስስር በኩልም በአካባቢው ላሉ ትላልቅ የእርሻ ድርጅቶችና አገልግሎት ሰጪ ተቋማት በማቅረብ ተጠቃሚ የሚሆኑበት እድል መኖሩንም አመልክተዋል።

ጥቅሙ ዘርፈ ብዙ መሆኑ ግንዛቤ ተይዞ ተሞክሮው ሰፍቶ የበለጠ ውጤት እንዲመዘገብ ማገዝ ያስፈልጋል ያሉት አቶ ጌታቸው የመንግሥት ድጋፍና ክትትል ብቻውን በቂ እንዳልሆነና መንግሥታዊ ያልሆኑ ባለድርሻ አካላትም በትብብር ቢሰሩ በሀገ። ደረጃ ትልቅ ስኬት ማስመዝገብ እንደሚቻል ገልጸዋል። እየተሰራ ያለው ሥራ ኢንተርፕራይዞቹ በድጋፍ ብቻ እንዲቀጥሉ ሳይሆን፣ ሀብት አፍርተው ለሌሎችም የሥራ እድል መፍጠር እንዲችሉ፣ በሀገር ኢኮኖሚ እድገትም አስተዋጽኦ እንደሚያበረክቱ ማስቻልም ጭምር እንደሆነ ግንዛቤ ሊያዝ ይገባል ብለዋል።

ከሥራ ዕድል ፈጠራ ጋር ተያይዞ መታረም አለበት ያሉትንም አቶ ጌታቸው እንዲህ አንስተዋል። ለሥራ የተበደሩት ብድር ተመላሽ ሲሆን፣ መልሶ አዲስ ለሚደራጁ ኢንተርፕራይዞች መዋል ሲኖርበት ለመደበኛ የብድር አገልግሎት ተግባር ይውላል። ይሄ ደግሞ ሥራ በሚፈጠርላቸው ወጣቶች ላይ መጉላላት እያስከተለ ነው። ገንዘቡ በሥራ እድል ፈጠራ አካውንት (ማጠራቀሚያ ሂሣብ) ውስጥ ነው መቀመጥ ያለበት።

አንዳንዶቹ ግንዛቤ በመፍጠር የሚፈቱ በመሆናቸው እንደ ችግር ላይነሱ ይችላሉ። ክትትልና ድጋፍን አጠናክሮ መቀጠል ከተቻለ የወጣቱን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ እንደሚቻልም አቶ ጌታቸው ተናግረዋል።

ለምለም መንግሥቱ

 አዲስ ዘመን መስከረም 10/2017 ዓ.ም

 

Recommended For You