ድሮና ዘንድሮ

ነፍስ ድሮና ዘንድሮ ብራናና ወናፍ ናት..አንድ ዓይነት መስላ የተለየች። እንደ ጊዜ የሰው ልጅ ሠርግና ሞት የለውም። ከመኖር ወደአለመኖር ይወስደናል። ካለመኖር ወደመኖር ይመልሰናል። እናም ጊዜ አለቃ ነው..ትላለች የጠየፋት ራሷ በታወሳት ቁጥር። ጊዜን ታኮ፣ ሰውነትን ሽቶ በመኖር ውስጥ ያወቀችው ቀዳማይ እውቀቷ ይሄ ነው፡፡

በሴትነቷ ላይ የተለወሱትን አስር አመታት አትወዳቸውም። ኤጭ ትላቸዋለች። በተጸየፈ ፊት አክ ብላ እንትፍ የምትለው ያለፈችበትን ጎዳና ስታስብ ነው፡፡

ከአስር አመት በፊት እንዲህ ነበረች…

ክፋት ያላያት፣ ነጠላዋን ተከናንባ ቤተክሲያን ከመሳም ሌላ እውቀት የሌላት፣ ለጠየቃት ሁሉ ሌማቷ እስኪራቆት የምታበላ፣ በሰንበት በአዘቦት መሽቶ እስኪነጋ ማህሌታይ የምትቆም..ከአስር አመት በፊት እንዲህ ነበረች፡፡

ቀና ብላ ሰው የማታይ፣ በነፍሷ አትሮኖስ ላይ የቀራኒዮውን እየሱስ የተሸከመች፣ ግራዋን ለመታት ቀኝዋን የምታሳይ፣ አንደበቷ የማይቀጥፍ፣ ምላሷ የማይሸነግል..ከአስር አመት በፊት እንዲህ ነበረች፡፡

ጾማ ውላ ማታ የምትበላ፣ እከሊት ላላት እመይት የምትል፣ ጓዳዋ እንደሳራ ቤት ተከፍቶ የሚያድር፣ እዮብ ካልሆነ፣ ይስሀቅ ካልሆነ፣ አብረሀም ካልሆነ በእምነትና በቅንነት የማይበልጧት..ከአስር አመት በፊት እንዲህ ነበረች፡፡

ውብ ናት..ውብ ገጠሬ። ፈገግታዋ ከተሜነት ያልጎበኘው፣ በዓይንአፋርነት ከአፈር ያልተነሱ ዓይኖች ያሏት፣ በአለባበሷ እና በንግግር ዘዬዋ በየሄደችበት ሰዎች የሚያዩዋት ባላገር..ከአስር አመት በፊት እንዲህ ነበረች፡፡

ከአስር አመት በፊት ያለው ራሷ ለራሷ ይገርማታል። ከህልሟ አንዱ ያቺን እሷን መሆን ነው። አንዳንድ ጊዜ ራሳችን ለራሳችን አይገባንም አይረባም ብለን የተጸየፍነውን ራሳችን ከዓለም ምርጥ ሆኖ ይታወሰናል። የሆነ ጊዜ ላይ የምናፍርበት ማንነት የሆነ ጊዜ ላይ በምንም የማናገኘው የክብር ማማችን ሆኖ ትዝ ይለናል። ግን ምንም አናመጣም..ያን አይረባም ያልነውን ማንነት በመሻትና በመናፈቅ ዘመናችን ያልፋል። የማይረባ ሰው፣ የማይረባ ማንነት፣ የማይረባ ታሪክ፣ የማይረባ ስብዕና የለም። የማይረባው አስተሳሰባችን ነው። በማይረባው አስተሳሰባችን በኩል ነው የሚረባ ዋጋችን ዋጋ የሚያጣው። ይሄ እውነት ቶሎ አይገባንም..ዘግይቶ እና ምንም ሳለን፣ ምንምም ማድረግ በማንችልበት የሆነ ዕለት የሚገባን መረዳት ነው፡፡

ፈገግታዋ ያምራል። በመሽኮርመም ውስጥ የምትፈገው የሆነ ፈገግታ አላት። በማፈር ውስጥ የምትስቀው የሆነ ሳቅ አላት። በማንም ፊት ላይ ያልታየ ፈገግታና ሳቅ። የጥርሶቿ ልባስ ከናፈሯ ሲነቃነቅ ከደመና መሀል እንደምትወጣ ጣይ ዓይን የሚከዳ የውበት ብርሃን አላት። ጥብርብር..ድንብርብር የሚያደርግ። በጊዜ በትር ሳታድፍና ሳትቆሽሽ፣ ዘመናዊነት በሚሉት ራስን በሚያስክድ በሽታ ከመያዟ በፊት እንዲህ ነበረች፡፡

ሥራ ፍለጋ ከአንዱ ከሀገራችን ገጠራማ መንደር ነው ወደአዲስ አበባ የመጣችው። አራት ጊዜ አግብታ ፈታለች። አምስተኛውንና በዕድሜ የሚበልጣትን ከአባትነት ሸሽቶ አያቷ ሊሆን የሚዳዳውን አዛውንት ባሏ አድርገው ሊድሯት አሸወይኗ በሚሉላት የሠርጓ ቀን ነው ጥላው አዲስ አበባ ሽሽት የመጣችው። መንፈሷ ያልጠና፣ ሴትነቷ ያልቀና አንዲት የአስራ ሁለት አመት ጉብል አራት ጊዜ አግብታ ፈታለች ቢባል ለሰሚው ግራ ነው። ግን እውነተኛ ታሪኳ ነው..ለጠየቃት ሁሉ እህህ እያለች የምታወራው። አዲስ አበባን አታውቀውም። ለመጀመሪያ ጊዜ ወንድ ከሚሉት የተፈጥሮ እድፍና ሴት ከሚሏት የተፈጥሮ እውነት ራሷን ለማራቅ ስትል በወሰነችው ውሳኔ በኮንጎ ጫማዋ ረገጠቻት።

ትዝ ይላታል..አዲስ አበባ ጣይ ነበረች። ጣይ ውበቷ ላይ ጣይ ስትወጣ አልታዘበችውም። መንገደኛው ሁሉ ተገላምጦ ሲያያት ራሷን የተለየች አድርጋ ነበር። እውነትም የተለየች ነበረች። በዛ ስፍራ ተገላምጠው ካስተዋሏት እልፍ ዓይኖች ውስጥ ጥቂቱ ለእግዚቢትነት ቢጠየቁ ‹ጣይ መሳይ ፊት ላይ ፀሐይ መውጣቷ ይገርማል› የሚል መልስ ይሰጡ ነበር። በአደስና ቅቤ ርሶ፣ በእድፋም ሻሽ አመታትን የዘለቀው ጸጉሯ በሰባት ሰዓቷ ጀምበር ተዠልጦ ቀይ ፊቷ ላይ ሲንዠቀዠቅ ነበር። አንገቷ ላይ በተከናነበችው ነጠላ እያበሰችው ከነፌስታሏ አንድ ጥግ ላይ ተሰየመች። ወዴት እንደምትሄድ ግራ ገብቷት፡፡

ከቆመችበት ሳትንቀሳቀስ ማታ ሆነ። አዲስ አበባ ያን ቀን ማረፊያ አሳጥታ እዛው የቆመችበት እንድታድር አስገደደቻት። ጠዋት ላይ ከእንቅልፏ ስትነቃ ኮንጎ ጫማዋ እግሯ ላይ አልነበረም። ከሁለት ቀን ልፋት በኋላ እማማ ወይኗ ቤት በግርድና ገባች። ይሄ ሁሉ የሆነው መቼ ነበር? አዎ ከዛሬ አስር አመት በፊት ይሄ ሁሉ ሆኖ ነበር። አሁን ሌላ ናት..ዘመናዊነት በሚሉት እድፍ ያደፈች እና ከተሜነት በሚሉት ነውር የነወረች። ድሮና ዘንድሮን ፊቷ አምጥታ ፍርድ ጀመረች፡፡

አስር አመታት ወደሴትነቷ መጥተው ለወጧት። አሁን ራስወዳድ ናት። አንዲት ዘመናዊ ሴት አለኝ የምትለው እብሪትና ኩራት፣ ማንአለብኝነትና እብለት አንዱም አልቀረባትም። ሳትዋሽና ሳታስመስል መናገር አትችልም። ዘመናዊነትን የለካችበት እሳቤዋ ለማንም የማትሆነውን እሷን ፈጥሯታል። አሁን ትግል ላይ ናት..ከድሮዋና ከዘንድሮዋ እሷ ጋር። በማንነት ሚዛን ካልተቀበሉት ዘመናዊነት ሰንካላ ነው። በራስ እውነት ካልተራመዱበት ከተሜነት ጉስቁልና ነው የሚል በምንም የማትሽረው እውቀት አላት፡፡

በሕይወቷ ሁሌም አንድ ነገር ይቆጫታል ባላገርነቷን በከተሜነት መቀየሯ። ገጠሬነቷን በዘመናዊነት መለወጧ። ገጠሬ ሆኖ እና ባላገር ተብሎ ማንም በሌለው ከተሜነትና አራዳነት ውስጥ መቆም እንደሚቻል ሁሉን ካጣች በኋላ ነው የገባት። ባላገር መሆን ተመኘች። ማንም ያልሆነውን፣ ማንም የሌለውን ዓይናፋርነት..ጨዋነት። የድሮዋን እሷን ናፈቀቻት። ያቺን ለድሀ የምትራራውን፣ ቤተሰብ አክባሪዋን፣ አመሻሽና ሰርክ ቤተክሲያን የምታገድመውን እሷን። የድሮዋን እሷን ተመኘቻት..ያቺን ሌማቷ እስኪራቆት የምታበላውን፣ ጸሎተኛዋን፣ ጾማ ውላ ጀምበር ስታዘቀዝቅ የምትበላውን እሷን። የድሮዋን እሷን ከጀለቻት..ያቺን ከአስር አመት በፊት የምታውቃትን ሴት። ቅኗን..ደጓን፣ አዛኟን..

አሁን ያላት የሴትነት ሞገስ ምኑም ከድሮው እሷነቷ ጋር የማይነጻጸር ነው። ሳትዋሽ ኖራ፣ ሳታብል ተናግራ አታውቅም። ከአስመሳዮች ጋር አስመስላ እንድትኖር ከተሜነት ቀንበሩን ጫንቃዋ ላይ አሳርፏል። ከሁሉም በኋላ እግዜር ባላገር ነው ትላለች። እንዴትም ብትኖር፣ እንዴትም ብታስብ ከዚህ የሚልቅ እውቀት አይኖራትም። እግዜር ይሄን ሁሉ ጸጋና በጎነት በባላገር ልብ ውስጥ ማኖሩ ባላገር እንደሆነ እንድታምን አደረጋት። አዎ እግዜር ባላገር ነው። ኢትዮጵያ ራሷ ባላገር ናት። ማንነቱን በውሸት እውቀት ሸጦ እንጂ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ባላገር ነው። ከተሜነት ከእውነተኛው ማንነት መሸሽ እና ከእውነተኛው እግዜር መራቅ እንደሆነ የገባትን ያክል ምንም ገብቷት አያውቅም፡፡

ከሁሉም በኋላ ይሄ ገባት..

ከተሜነት ብዙ ባላገርነት፣ ጥቂት ዘመናዊነት እንደሆነና ቢሆን የሚል፡፡

 በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)

አዲስ ዘመን ሐምሌ 14/2015

Recommended For You

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *