በአምቦ ከተማ የተወለደው ወጣት ዘላለም መርአዊ እድገቱ ከመዲናችን አዲስ አበባ 55 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ታሪካዊቷ አዲስ ዓለም ከተማ ነው። የአንደኛ ደረጃ ትምህርቱን በትውልድ አካባቢው ተከታትሎ ወደ ሀገሪቱ ዋና ከተማ አዲስ አበባ አምርቶ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን በሽመልስ ሀብቴ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት አጠናቋል።
በመቀጠል ወጣት ዘላለም፤ አንበሳ የኢትዮጵያ ቱሪዝም ኮሌጅን በመቀላቀል በቱሪዝም ማኔጅመንት የመጀመሪያ ዲግሪውን አግኝቶ ላለፉት ዓመታት በኢትዮጵያ ቱሪዝም ኢንዱስትሪ ውስጥ ንቁ ተሳትፎ ማድረግ ችሏል። ወጣት ዘላለም ለቱሪዝም ኢንዱስትሪው ያለው ፍቅር የጀመረው በአዲስ ዓለም ጋራዥ ውስጥ በመኪና መካኒክነት ሲሰራ በነበረበት ወቅት እንደነበረ ይናገራል።
በከተማዋ ያለው በቱሪስቶች የሚጎበኝ ቤተ ክርስቲያን እና ሙዚየም ነበር፤ በጊዜው አስጎብኚ ድርጅቶች መኪኖቻቸውን ሰርቪስ የሚያስደርጉት ወጣት ዘላለም፤ በጋራዥ በባለሙያነት በሚሰራበት ቦታ ነበር፡፡ በእዚህ አጋጣሚ ወጣት ዘላለም የጉብኝት እና የጉዞ ንግድ እንዴት እንደሚሠራ የማጥናት እድል አገኘ።
ወጣት ዘላለም 5 እና 6 ዓመታት በሹፌርነት እና በአስጎብኚነት በተለያዩ ድርጅቶች ካገለገለ በኋላ ዘላለም ቱር እና ትራቭል ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ድርጅት በማቋቋም ሥራውን መጀመር ቻለ። ኢንደስትሪው ካፒታል የሚፈልግ በመሆኑ እና ከሰዎች ጋር ግንኙነቶችን በመመስረት የሚሰራ መሆኑ አስቸጋሪ ሁኔታዎችን እንዲያሳልፍ እንዳደረገው በወቅቱ የነበረውን ሁኔታ አስታውሶ ይናገራል።
ዘላለም ለንግድ ሥራው የሚረዳው የገንዘብ አቅም ከሌለው ምስኪን ቤተሰብ የመጣ እንደመሆኑ እራሱን ለመለወጥ እና የተሻለ ደረጃ ላይ ለማድረስ በግንባታ ሰራተኝነት፣ በጫማ ጠራጊነት እና በመኪና መካኒክነት በርካታ ስራዎችን በመስራት፤ እዚህ ስለመድረሱ ተናግሯል።
የተለያዩ ሥራዎችን በትጋት ሰርቶ 70 ሺህ ብር ካጠራቀመ በኋላ ዘላለም አስጎብኝ እና የጉዞ ወኪል በአንድ አስጎብኚ መኪና አንድ ብሎ ስለመጀመሩ ያብራራል፡፡ ይህ ድርጅት ዛሬ ላይ 19 ዓመታትን አስቆጥሯል፡፡ በዚህ የ19 ዓመት ጉዞ ውስጥ በርካታ ስኬቶች እና ውድቀቶች አጋጥሞኛል የሚለው ወጣት ዘላለም፤ የስኬት ዓመታቱ የኢትዮጵያ ቱሪዝም በጥሩ እንቅስቃሴ በነበረበት እ.ኤ.አ ከ2010 እስከ 2015 ድረስ ጥሩ ገቢ አግኝቶ እንደነበር ይናገራል፡፡
በጊዜው የኢትዮጵያ ቱሪዝም በደንብ ያደገበት፤ ዓለም ላይ ያሉ ትልልቅ የቱሪዝም አስጎብኚ መፅሔት እና ዌብሳይቶች ኢትዮጵያን በዓለም ላይ መጎብኘት አለባቸው ከሚባሉ ከ10 ሀገራት ውስጥ ትጠቀስ በነበረበት ጊዜ ድርጅቱ ተሳክቶለት እንደነበር ያስታውሳል።
በዚህም መሰረት በየ6 ወሩ የሚታተም የኬር ኤዢ ኢትዮጵያ የቱሪስት መፅሄት እና የቱሪስት መመሪያ መጽሃፍ ስራ አስጀምሯል፡፡ በተጨማሪም የኢትዮጵያ የቱሪስት መዳረሻዎችን ለማስተዋወቅ የተሰራ ድረ-ገጽም የዘላለም አስጎብኚና የጉዞ ኩባንያ አበልፅጎ በመላው ዓለም ላይ በተዘረጋው ስርዓት ከ72 በላይ በሆኑ ቋንቋዎች ለተጠቃሚዎች ለጎብኚዎች መረጃን በመስጠት እያገለገለ ስለመሆኑ ተናግሯል።
ኩባንያው ማህበራዊ ሚዲያን በሙያዊ መንገድ በመጠቀም ምሳሌ መሆን እንደሚችል እና በኢትዮጵያ ቱሪዝም ዘርፍ ከዚህ ቀደም ያልነበሩ እንደ ኦንላይን ክፍያ እና የቦኪንግ ሲስተም ያሉ ልዩ ልዩ አሰራሮችን ተግባራዊ በማድረግ አገልግሎት ለመስጠት ጥረት ስለማድረጉ ወጣት ዘላለም ገልፆል።
ከአስጎብኝና የጉዞ ኩባንያው በተጨማሪ ዘላለም፤ የኬር ኤዢ ኢትዮጵያ አስጎብኚ መጽሔትና የድረ-ገጽ ማውጫ ቡድንን በማርኬቲንግ፣ በአይቲ እና በይዘት ፈጠራ በሚገባ የተደራጁ ቡድኖች አቋቁሟል።
የድረ-ገጹ ማውጫ ከ400 በላይ አስጎብኚዎች እስከ 1000 የሚደርሱ ሆቴሎች በመረጃ ማከማቻውን ከውስጥ በመያዝ ቱሪስቶችን እና አገልግሎት ሰጪዎችን በቱሪዝም ዘርፍ የእሴት ሰንሰለት ውስጥ ለማስተሳሰር ያለመ እንደመሆኑ በቱሪዝም ዘርፍ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ትልቅ አስተዋፅኦ አድርጓል ይላል።
የድረ-ገፁ ማውጫ ስራ በተሳካ ሁኔታ በመጠናቀቁ ወደ 7 ነጥብ 5 ሚሊየን የሚጠጉ ቱሪስቶች መረጃ ለማግኘት ድረገፁን ጎብኝተው እንደነበር ወጣት ዘላለም ያብራራል። ዘላለም የኢትዮጵያን ቱሪዝም ለማስተዋወቅ ባደረገው ጥረት ከአሜሪካ ሂዩስተን እና ስዊዘርላንድ የክፍለ-ዘመኑ ዓለም አቀፍ የጥራት ሽልማት ተሸላሚ መሆን እንደቻለ እና ዓለም አቀፍ ሽልማቱም እጩዎችን የሚሸልመው የገበያ ትስስር፣ ማህበራዊ ኃላፊነት እና የስራ እድል ፈጠራ ጥረቶቹን ከግምት ውስጥ በማስገባት እንደሆነ ተናግሮ ባገኘው እውቅናም ደስተኛ እንደሆነ ገልፆል።
ነገር ግን ባለፉት 6 እና 7 ዓመታት በሀገሪቱ በነበረው ግጭት፣ የኮቪድ ወረርሽኝ እና በቅርቡ ደግሞ የተከሰተው ጦርነት እና በሌሎችም ጉድለቶች ምክንያት የቱሪዝም ኢንዱስትሪው ተጎድቷል። በዚህም የጉብኝት እና የጉዞ ስኬት ተገድቧል። እነዚህ ተግዳሮቶች ተደማምረው ለማገገም አስቸጋሪ በሆነው የቱሪዝም ዘርፉ ላይ ከፍተኛ ጉዳት አስከትለዋል። በዚህም ምክንያት ቱሪስቶች በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ውስጥ ወደሚገኝ ሀገር ሲጓዙ የጉዞ ዋስትና ሊሰጣቸው ስለማይችል ሀገሪቱን ለመጎብኘት ፈርተው ነበር ይላል፡፡
በቱሪዝም ንግዱ ላይ ከደረሰው ማሽቆልቆል ለማገገም በወሰደው እርምጃ፣ ወጣት ዘላለም ትኩረቱን ከቱሪዝም ጋር ተያያዥነት ወዳለው የቆዳ ኢንዱስትሪው ለመዞር እንደተገደደ ይናገራል። ነገር ግን የቱሪዝም ድርጅቱም አልተዘጋም፤ ለቱሪስት መረጃ መስጠት እና አልፎ አልፎ የኮንፈረንስ ቱሪዝሞችን ያስተባብራል፡፡ ከሀገር ውስጥ ወደ ውጭ ለሚሄዱ ኢትዮጵያውያን አገልግሎት ይሰጣል፡፡
ባሉት መኪኖች የሰርቪስ አገልግሎት ለተለያዩ የመንግሥት እና የግል ተቋማት እንደሚሰጥ የተናገረው ወጣት ዘላለም፤ አሁንም ኢትዮጵያ ከ12 በላይ በዩኔስኮ የተመዘገቡ ቅርሶች ያሉባት ሀገር መሆኗን አስታውሶ፤ አሁን ላይ ደግሞ ብዙ የቱሪስት መዳረሻዎች እየተሰሩ መሆናቸውንም በመጥቀስ ዘርፉ ተስፋ ያለው ነው፤ ይላል።
ድሮ የነበሩት የቱሪስት መዳረሻዎች የሀይማኖት ቦታዎች እና ሙዚየሞች በመሆናቸው አስጎብኚዎች የሚሄዱት ታሪካዊ እና ሀይማኖታዊ ቦታዎችን ለማሳየት ብቻ ነበር የሚለው ወጣት ዘላለም፤ አሁን ግን ትልልቅ የቱሪስት መዳረሻዎች እየተገነቡ መሆናቸው ዘርፉን እንደሚያግዘው የሚያስረዳው በቅርቡ ያለቀው ሀላለ ኬለ፣ ጣና ሀይቅ ላይ እየተሰራ ያለው የጎርጎራ ፕሮጀክት እና በመሠራት ላይ ያለውን ወንጪን በመጥቀስ ነው፡፡
እንደወጣት ዘላለም ገለፃ፤ አዲስ አበባም ቢሆን ቱሪስቱ እንቅስቃሴ የሚያገኝበት ቦታ አልነበረም። የቱሪስት መዳረሻዎች ሙዚየሞች ብቻ ነበሩ። አሁን ግን እንጦጦ እና ሌሎቹም መሠራታቸው ለከተማዋ የቱሪዝም ዘርፍ ዕድገት ትልቅ አስተዋፅኦ ይኖራቸዋል፡፡
የኢትዮጵያ የቱሪስት መዳረሻ ገና ተገኝቶ አላለቀም፤ ገና ብዙ ነገሮችን መስራት እና መፍጠር ይቻላል የሚለው ዘላለም፤ ‹‹ የቱሪዝም ሥራን አልተውንም፤ ልንተወውም አንችልም፤ ለወደፊት እያሰብን ያለነው በችግር ውስጥም ቢሆን ቱሪስት መምጣት የሚቻለው እንዴት ነው? የሚለውን እያሰብንበት ነው፡፡›› ይላል።
የማኑፋክቸሪንግ ኩባንያው የተቋቋመው በአዲስ አበባ በሚገኙ የቱሪስት ሱቆች ውስጥ ባለ የምርት ጥራት መጓደል ምክንያት ነው የሚለው ወጣት ዘላለም፤ እንዲሁም የአዲስ አበባን ግዙፍ የቆዳ ኢንዱስትሪ አቅም የመጠቀም ራዕይ አንግቦ እንደሆነ ይናገራል።
ኬር ኤዢ የቆዳ ማምረቻ ስያሜውን ያገኘው ከዘላለም የመጀመሪያ ልጅ ስም ሲሆን፤ ትርጉሙም “ደስ የሚል ነገር በኢትዮጵያ ላይ ይታይ” እንደ ማለት እንደሆነ ወጣት ዘላለም ይናገራል።
ኬር ኤዢ ከመመስረቱ በፊት ቱሪስቶች ከሌሎች የአፍሪካ ሀገራት እንደ ኬንያ፣ ታንዛኒያ እና ደቡብ ሱዳን ካሉ ሀገራት የሚገቡ የቤት ውስጥ ቅርሶችን ይሸምቱ ነበር፡፡ አሁን ላይ ይህ እንደሌለ እና በሀገር ውስጥ የተመረቱ የቆዳ ውጤቶችን እንደሚሸምቱ ወጣት ዘላለም ተናግሯል፡፡
በኢንዱስትሪው ውስጥ ወቅታዊ ዕውቀትን ለማግኘት በኬር ኤዢ የመጀመሪያ ደረጃ ላይ ከአሜሪካ፣ ህንድ፣ አውሮፓ እና ሌሎች አገሮች ዓለም አቀፍ ልምዶች ተወስደዋል የሚለው ዘላለም፤ የምርት ማሳያ ሱቆቹ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ከተከሰተበት ጊዜ አንስቶ 2 ሴት ሰራተኞችን ከቤታቸው የቆዳ ምርቶችን በመስራት ስራ ጀምሯል።
ከቆዳ ምርቶቹ መካከል ቀበቶዎች፣ አነስተኛ እና የጉዞ ቦርሳዎች፣ የመኪና መቀመጫዎች፣ አልባሳት፣ ጫማዎች እና ሌሎችም ምርቶች እንደሚጠቀሱ ተናግሯል።
የሰራተኞች ቁጥር ብዛት ከ20 ተነስቶ ዛሬ ወደ 125 ደርሷል ያለው ወጣት ዘላለም፤ ከዚህ በተጨማሪ 20 ለሚሆኑ በሌዘር ምርት ለተሰማሩ እና ከ15 እስከ 35 ሰራተኛ ላላቸው ኩባንያዎች ስልጠና በመስጠት አብረው የሚሠሩ መሆኑን ተናግሯል፡፡ ከዚህ ሌላ ”ከውጭም ከሀገር ውስጥም ትልልቅ ትዕዛዞች ሲቀርቡልን ስልጠና ከመስጠት በተጨማሪ የጥሬ ዕቃ እና የማሽነሪ ድጋፍ በማድረግ እንዲያመርቱ እና ለእኛ እንዲያስረክቡ እናደርጋለን” በዚህም ተጨማሪ የሥራ ዕድል መፍጠር ችለናል ይላል።
ሌሎችም በየቤታቸው የሚሰሩ ከ150 በላይ ሴቶችን ቤታቸው ሆነው እንዲያመርቱ በማድረግ በወር እስከ 15 ሺህ ብር ገቢ ማግኘት እንዲችሉ የሚያደርጉ መሆኑን የተነገረው ወጣት ዘላለም፤ ይህንን የሰራተኛ ቁጥር በሚቀጥሉት ጥቂት ዓመታት ሁለት ሺህ ለመድረስ እየተሰራ እንደሆነ ይናገራል።
የሰራተኞቹን እውቀት ማዘመን አስፈላጊ ነው የሚል እምነት ያለው መሆኑን የሚናገረው ዘላለም፤ ለዚህም ከቤልጂየም፣ ከጣሊያን፣ ከህንድ እና ከቻይና የተውጣጡ ዓለም አቀፍ የቆዳ ባለሙያዎችን በመጋበዝ የበጎ ፈቃድ ስልጠናዎችን እንዲሰጡ የሚጋብዙ መሆኑንም ተናግሯል፡፡ በኩባንያው ውስጥ ካለው አገልግሎት ወይም ሽያጭ ጋር የተመጣጠነ ደመወዝ እንደሚከፍሉ እና የዚህ ምክንያት ደግሞ ድርጅቱ የሰራተኞቹን ችሎታ እና እውቀት ስለሚያደንቅ እንደሆነ ተናግሯል።
ኬር ኤዢ በተለያዩ የዓለም ሀገራት በርካታ መዳረሻዎች እና ገበያዎች አሉት። ስምንት ሱቆች አሉት፡፡ እንዲሁም በኬንያ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ እንግሊዝ እና አሜሪካ ካሉ አጋር ድርጅቶች ጋር የሚሰራ የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ፍራንቺዝ ብራንድ ነው፡፡ ኩባንያው ከፍተኛ የቱሪስት ትራፊክ ባለበት በኢትዮጵያ አየር መንገድ ሁለት የቆዳ ምርቶች ማሳያ በመክፈት እየሰራ እንደሆነ የገለፀው ወጣት ዘላለም፤ ይህም በዓመት ከፍተኛ ገቢ እና የውጭ ምንዛሬ እንደሚያስገኝ ተናግሯል።
ኤክስፖርትን በሚመለከት በአሜሪካ ገበያ ላይ ትልቅ ኤክስፖርት እያደረገ መሆኑን የገለፀው ወጣት ዘላለም፤ በዓመት ውስጥ ከአምስት መቶ ሺህ ዶላር በላይ ከውጭ ዜጎች በሀገር ውስጥ ብቻ የሚሰበስቡ መሆኑን እና በውጭ ኤክስፖርት ደግሞ በአሜሪካ ገበያ ብራንድ በመሸጥ በአሜሪካ ሀገር የኬር ኤዢ ሱቆች መከፈቱን እና በተለያዩ የአሜሪካ ከተሞች ምርቶቹን እየሸጠ መሆኑንም ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ቆዳ መሸጥ ብቻ ሳይሆን ብራንድም መሸጥ ትችላለች የሚለው ወጣት ዘለለም፤ በሚቀጥሉት ዓመታት በስፋት የሚሄድበት መሆኑን እና አሁን በእንግሊዝ፣ ኔዘርላንድ፣ ደቡብ አፍሪካ እና ኬንያ ላይም የብራድን ሱቆች ለመክፈት ስራ ላይ መሆኑን ጠቁሟል፡፡ በሚቀጥሉት ስድስት ወራት ሁሉም ሀገሮች ላይ በተመሳሳይ ሰዓት አልቆ እንዲከፈት በማድረግ፤ በዚህም ዓለም አቀፍ ዕውቅናው የሚያድግበት ሁኔታ እንደሚኖርም ተናግሯል።
ኬር ኤዢ በቅርቡ ደግሞ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ የከበሩ ማዕድናትን ጥሬውን ሳይሆን እሴት ጨምሮ ጌጥ በማድረግ በውድ ዋጋ መሸጥ ይቻላል የሚለውን ሀሳብ ለኢንዱስትሪው ማስተማር በሚቻልበት ሁኔታ ኬር ኤዢ የከበሩ ማዕድናት እና የጌጣጌጥ ማምረቻ በማቋቋም ከቆዳ ኢንዱስትሪው በተጨማሪ ለመስራት የታሰበ መሆኑንም ተናግሯል።
በተጨማሪ በቡና ኤክስፖርት ያለቀለት ብራንድ ውድ ዋጋ ያለው ቡና ወደ ዓለም ገበያ ለማቅረብ እየሰሩ መሆኑን ጠቅሷል፡፡ ኢትዮጵያ ተወዳዳሪ መሆን ያልቻለችው ሁሉንም ነገር በጥሬው ኤክስፖርት ስለምታደርግ መሆኑን አስታውሶ፤ ስለዚህ ምርቶችን እሴት ጨምሮ በመሸጥ እራስን እና ሀገርን ተጠቃሚ ለማድረግ እየሰሩ እንደሆነ ወጣት ዘላለም ገልፆል።
የወደፊት እቅዱን ወጣት ዘላለም ሲናገር፤ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር በቅርበት በመስራት አውሮፕላን ውስጥ የሚሸጡ ምርቶችን ለማምራት፤ ከውጪ የሚገቡ ምርቶችን ሀገር ውስጥ በማምረት ያለቀላቸውን የፋሽን ኢንዱስትሪው ምርቶች ለመስራት፤ እንደ ጣልያን፣ ህንድ፣ ቬትናም ወደ መሳሰሉ አገራት በቆዳ ምርት ትልልቅ ስራዎች ከኢትዮጵያ የሚወጡበትን ዕድል ለመፍጠር ማቀዳቸውን ይናገራል፡፡ በዋናነት ግን ወጣት ዘላለም ዕቅዱም በዓለም የፋሽን ኢንዱስትሪ ውስጥ ያለውን የገበያ ድርሻ ኢትዮጵያ እንድታገኝ ማድረግ እንደሆነ ተናግሯል።
ወጣትነት መውደቅ ቢኖርም መነሳት እና ማሸነፍ የሚቻልበት የዕድሜ ክልል ነው የሚለው ወጣት ዘለለም፤ ይህንን የዕድሜ ክልል መጠቀም የሚችል ሰው የጉልምስና እና የእርጅና ወራቱ የተስተካከለ ይሆናል። ልጆቹ የተጎሳቆለ ኑሮ እንዲኖሩ የሚፈልግ ማንም የለም፤ እርሱ የሚፈጥረው ትውልድ ጭምር ያማረ ህይወት እንዲኖር ያደርጋል ሲል ምክሩን ይለግሳል፡፡
‹‹ኢትዮጵያ ሚሊዮን ዕድሎች ያሏት ሀገር ናት፡፡ ሁላችንም ፖለቲከኞች እና የፖለቲካ ተንታኝ መሆን አይጠበቅብንም፡፡ ብዙዎቻችን ለፍቶ የሚያድር ሰራተኛ፣ ህይወቱን፣ ቤተሰቡን፣ ሀገሩን የሚለውጥ ትውልድ መሆን አለብን፡፡››ብሏል።
በመጨረሻም በአጠቃላይ በተለይ ለወጣቱ ለትውልድ የሚጠቅም ስራ ለመስራት ወድቆ መነሳት እና ተነስቶም ማሸነፍ በሚችልበት ዘመን በመጣር መስራት እንዳለበት መልዕክቱን ያስተላልፋል።
ክብረአብ በላቸው
አዲስ ዘመን ሐምሌ 14/2015