ዛፎች የተፈጥሮን ሚዛን ጠባቂዎች፣ ምግቦችና እስትንፋሶች

 በምድራችን ላይ ያሉ ሥነፍጥረታት እርስ በእርሳቸው እንዲተሳሰሩ የሚያደርግ ተፈጥሯዊ ሕግ አለ። በፍጡራን የእርስ በእርስ መስተጋብር ውስጥ አንዱ ካልኖረ ሌላውም ሊኖር የማይችልበት የህይወት ስንስል መኖሩ ግልጽ ነው። ለምሳሌ የእጽዋት ወይም የደኖች መኖር እርጥበት አዘል አየር እንዲፈጠር አስተዋጽኦ ያደርጋል። የእርጥበት አዘል አየር መኖር ደግሞ ደመና እንዲፈጠር ያደርጋል፤ እንግዲህ ምድራችን በልምላሜ የምትፈካውና አረንጓዴ የምትለብሰው ደመና ወደ ዝናብነት ሲቀየር ነው።

እንስሳትም ይሁኑ የሰው ልጆች ከምድሪቱ ልምላሜ በሚያገኙት በረከት በሕይወት ለመኖር ዋስትና የሚሰጧቸውን ትሩፋት ያገኛሉ። ሳር የሚግጡ፣ ቅጠል የሚበሉ፣ ፍራፍሬ የሚለቅሙ፣ አርሰው የሚቅሙ፣ ፍጥረታት በሙሉ ዝናብ ከሌላ ሕልውናቸውን ማረጋገጥ አይችሉም። ሌላው ቀርቶ ሳይንሱ ሥጋ በል ብሎ የሚጠራቸው ፍጡራንም ቢሆኑ ሳር በሎቹን ተመግበው የሚኖሩ በመሆናቸው በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ የዝናብ በረከቱ ተቋዳሾች ናቸው።

ዋናው ቁምነገር እጽዋት ሲኖሩ ዝናብ ይኖራል፤ ዝናብ ሲኖር እጽዋት ይኖራሉ፤ የእጽዋት መኖር ሕይወት ላላቸው ፍጡራን ዋስትና ይሠጣል የሚለውን እውነታ እንድንይዝ ነው። የሰው ልጅ ከእጽዋት የሚያገኘው ምግቡን ብቻ አይደለም። የተቃጠለውን አየር (ካርቦንዳይ ኦክሳይድን) ባስወጣ ቁጥር እስትንፋሱን የሚያስቀጥልለትን ኦክሲጂንን ከእጽዋት ይቀበላል። ከዚህ አንጻር እጽዋት የአተነፋፈሳችን ሥርዓት ሳይዛነፍ በሕይወት እንድንኖር የማድረግ ሚናም ያላቸው ናቸው።

እንግዲህ በተፈጥሮና በፍጡራን መካከል ያለው ትስስርና መሳሳብ ከተገለጸውም በላይ ብዙ መልክ ያለው ነው። ይህ ተደጋግፎና ተመሳጥሮ የመኖሩ ሁኔታ ቀጣይነት የሚኖረው ተፈጥሮ ሚዛኗን ጠብቃ መጓዝ የቻለች እንዲሁ ነው። የደኖች መመናመን ተፈጥሮ ሚዛኗን ጠብቃ እንዳትጓዝ ሥጋት እየሆነ የመጣ የዓለማችን ግንባር ቀደም ችግር ሆኗል።

ከኢንዱስትሪዎች የሚለቀቁ በካይ ጋዞችን መጥጠው ማስቀረት የሚችሉ ደኖች ስለተመናመኑ ዓለማችን ለሙቀት መጠን መጨመርና ለአየር ንብረት ብክለት ተጋላጭ የመሆኗ ጉዳይ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቷል። ይህን ዓለማችን ላይ የተጋረጠውን አደጋ ለመቆጣጠር አገራት በየጊዜው በሚያደርጉት ውይይት የየራሳቸውን ድርሻ ለመወጣት ቃል እየገቡ ቢለያዩም የችግሩን አሳሳቢነት ተረድተው ቁርጠኛ ርምጃ እየወሰዱ ያሉት ግን ጥቂቶች ናቸው።

በተለያዩ ትልልቅ ዓለም ዓቀፍ ጉባኤዎች ላይ የአየር ንብረት ለውጥ ሥጋቱን ለመቀነስ ከኢንዱስትሪዎች የሚለቀቀውን በካይ ጋዝ መቀነስና ችግኞችን መትከል እንደመፍትሔ ቢጠቀስም ተተግባሪነቱ ግን በሚወራው ልክ ሲሆን አይታይም። በተለይም ያደጉ አገራት ታዳሽ ኃይሎችን በመጠቀም ከኢንዱስትሪዎቻቸው የሚለቁትን በካይ ጭሶች ለማስወገድ ቁርጠኛ ሲሆኑ አይስተዋልም።

የኦዞን ሌየር መሳሳት፣ ጎርፍ፣ የዝናብ እጥረት ወይም ድርቅ፣ ሰደድ እሳት፣ የበረዶ ግግሮች መናድ፣ የሙቀት መጠን ማሻቀብ ወዘተ በተፈጥሮ ሚዛን መዛነፍ ምክንያት እየተከሰቱ ያሉ የዓለማችን ችግሮች ናቸው። ከሰሞኑ የአሜሪካ የአካባቢ ትንበያ ብሄራዊ ማዕከል ባቀረበው መረጃ ባለፈው ሰኔ ወር የተመዘገበው ሙቀት አስከዛሬ ድረስ በዓለማችን ታይቶ የማይታወቅ ነው። ይህም ዓለምን ያስደነገጠና ያነጋገረ ዜና ሆኗል።

ይሄኔ ታዲያ ‹‹ፊቱን ነበር እንጂ ቀምሞ መደቆስ፤ አሁን ምን ያደርጋል ድስቱን ጥዶ ማልቀስ ›› የሚለው የአበው ቢሂል ትውስ ሊለን ይገባል። ይህን ስል ከዚህ በኋላ ሠርተን የምንለውጠው ጉዳይ የለም፤ ወቅቱ አልፏል፤ ማለቴ እንዳልሆነ ያዙልኝ። አስቀድመን ለችግሮቻችን መፍትሄ መስጠቱ ላይ ግን ዘግይተናል። የአየር ንብረት ተለዋዋጭነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየፈጠነ ሲሄድ እኛ ግን ወደዝች ምድር ስንመጣ የነበረውን አየር አሁንም እየማግን የምናስወጣ እየመሰለን ባለንበት ቆመናል፤ ዓለም ተኝቷል ማለት ፈልጌ ነው።

ዓለም ለእንዲህ አይነት ችግር ተጋላጭ እየሆነች እንደመጣች የተነገረን ዛሬ አይደለም። ሳይንቲስቶች የመጪውን ዘመን ስጋቶች ሲያስረዱንና ማድረግ ያለብንን ጥንቃቄ ሲነግሩን ጆሮ ዳባ ብለን ዛሬ በምንሰማው ዜና ልንደነግጥ አይገባም። በተለያዩ ዓለም አቀፍ መድረኮች ላይ ስለአየር ንብረት ለውጥ የሚደረጉ ውይይቶችና ማሳሰቢያዎችም የአንድ ሰሞን አጀንዳ ከመሆን አልፈው በትኩረት፣ በጥብቅ ቁጥጥርና ክትትል ለውጥ ሲመዘገብባቸው አይታይም።

እንግዲህ ስለ አየር ንብረት ለውጥ ስናስብ ወደድንም ጠላንም ያሉን ሁለት አማራጮች ብቻ ናቸው። አንደኛው አማራጭ እጃችንን አጣጥፈን በመቀመጥ በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት የሚመጡብንን ማናቸውንም ተጽዕኖዎች ሁሉ ተቋቁመን መኖር ለእንዲህ አይነቱ አኗኗር ደግሞ ምናልባትም ጊዜያዊ ካልሆነ በስተቀር ዘለቄታዊ ዋስትና ሊሰጠን እንደማይችል የሚታወቅ ነው። ጊዜያዊ ቆይታችንም ቢሆን ልክ አሁን እያየን እንዳለነው በፈተና ታጅቦ ነው የሚዘልቀው።

ሁለተኛው አማራጭ ግን በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት ለሚመጡት ችግሮች አስቀድሞ መፍትሔ መስጠት ነው። ሰው በተሰጠው የማሰብ ጸጋ ያለፈውን፣ የአሁኑን እና የመጪውን ሁኔታ እያነበበ፤ በሕይወቱ ውስጥ ጎጂና ጠቃሚ ነገሮችን እየለየ አኗኗሩን ማስተካከል ይኖርበታል። ከሚጎዳውና ከሚጠቅመው አንጻር መጪውን ዘመን እየዋጀ መኖሩም ከአንስሳት የሚለይበት አንዱ ባህሪው ነው። ለዚህም ነው ከርሞ ስለሚመገበው ምግብ አስቀድሞ በማሰብ ዘንድሮ ላይ ቆሞ ከጎተራው አውጥቶ የሚዘራው።

ሰው ሁልጊዜም መጪውን እያሰበ ስለሚኖር ችግሮችን አሻግሮ በመመልከት መፍትሔ እያስቀመጠላቸው መሄድ ይኖርበታል። ተፈጥሮን በማከም እና በመንከባከብ የአየር ንብረት ለውጥ ተጋላጭነትን በመቆጣጠር ዓለምን እና የአየር ንብረቷን ለሰው ልጆች አኗኗር ምቹና ተስማሚ አድርጎ ማቆየት ይጠበቅበታል። ለአየር ንብረት ለውጥ ታጋላጭ ከሚያደርጉ ጉዳዮች አንዱ የደኖች ወይም የእጽዋት መመናመን በመሆኑ የዓለምን የደን ሽፋን ማሳደግ ከአገራት የሚጠበቅ ቁልፍ ጉዳይ መሆኑ ለሰከንድ እንኳ መረሳት የለበትም። ስለዚህ እያንዳንዱ የዓለም አገር፤ እያንዳንዱ ሰው ለራሱና ለመጪው ትውልድ የምትሆን ነገን ዛሬ መትክል ይኖርበታል።

ኢትዮጵያ በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ አቅጣጫ ሰጪነት የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ-ግብርን ይፋ አድርጋ ወደ ሥራ ከገባች አራት ዓመታትን አሳልፋለች። በነዚህ ዓመታት 25 ቢሊዮን ችግኞችን በመትከል የመጀመሪያው ምዕራፍ ዘመቻዋን ማሳካትዋን ከሰሞኑ በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ይፋ ተደርጓል። በምዕራፍ ሁለት ዘመቻም እንዲሁ 25 ቢሊዮን ችግኞችን የመትከል እቅድ እንደተያዘና በዘንድሮ ዓመት በአገር አቀፍ ደረጃ “ነገን ዛሬ እንትከል” በሚል መሪ ሀሳብ ከስድስት ቢሊየን በላይ ችግኞችን መትከል እንደታሰበ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል።

በምዕራፍ ሁለት 5ተኛው ዙር የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ-ግብር ንቅናቄም “500 ሚሊየን ችግኞችን በአንድ ጀምበር ለመትከል እንደ አገር ሰኞ ሀምሌ 10 ቀን 2015 ዓ.ም ቀጠሮ ተይዞ ተፈጻሚ ሆኗል። የዘንድሮው የችግኝ ተከላ አሁንም እንደቀጠለ ይገኛል። ችግኞችን መትከል ‹‹በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ ›› ከሚባለውም በላይ ስኬቱ ብዙ ነው።

የመጀመሪያውና የተነሳንበት ጉዳይ የደን ሽፋናችንን በማሳደግ በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት ዓለም የተጋረጠባትን ስጋት መቀነስ ወይም መከላከል የሚለው ሊሆን ይችላል። ከዚህ አንጻር ኢትዮጵያ በአጭር ጊዜ ውስጥ ያስመዘገበችው ውጤትና በቀጣይም ልትደርስበት ያሰበችው ስኬት እንደ አገር ታሪካዊ ድል ከመሆን አልፎ ለሌሎች የዓለም አገራትም ተጠቃሽ የሚሆን ታላቅ ገድል ሆኗል።

የችግኝ ተከላ ዘመቻው ማህበረሰቡ ስለ ደኖች ጥቅም ተጨባጭ ግንዛቤ እንዲኖረውና ስስ ስሜት እንዲጋባበት ያደረገ፤ ለበርካታ ዜጎቻችን የሥራ እድል የፈጠረ፤ በግድየለሽነት ሲጨፈጨፉ የነበሩ አገር በቀል ዛፎቻችንም እንክብካቤና ትኩረት እንዲያገኙ ያስቻለ ነው። ዓለም በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት የተጋረጠባትን ስጋት ለመቀነስ የምታደርገውን ጥረት ተከትሎ ኢትዮጵያ እንደአገር የተጣለባትን አደራ በሚገባ እየተወጣች እንዳለች በአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ-ግብሯ በሚገባ አሳይታለች። በዚህ የችግኝ ተከላ ንቅናቄዋ ሌሎች ዓይናቸውን የከደኑ የዓለም አገራትም ከተኙበት እንዲነቁ ቀስቅሳቸዋለች።

በቅርቡ በአገራችን መተከል የተጀመሩት ችግኞች የዛፍ አግልግሎት ያላቸው ብቻ ሳይሆኑ ለምግብነት የሚውሉ ፍራፍሬዎችም መሆናቸው ሌላው ስኬት ነው። በአንድ በኩል የተፈጥሮ ሚዛንን ለማስጠበቅ ሲያገለግሉ በሌላ በኩል የምግብ ዋስትናችንን ለማስጠበቅ በእጅጉ የሚረዱ ናቸው። ፍራፍሬዎች በተለያዩ ቫይታሚኖች የበለጸጉ ስለሆኑ ከተለመደው ባህላዊ የአመጋገብ ሥርዓት የተላቀቀና ጤናው የተጠበቀ ማህበረሰብን ከመፍጠር አንጻርም አበርክቶ አላቸው።

በአመዛኙ አመጋገቡ በሰብል ምርቶች ላይ የተንጠለጠለው ማህበረሰባችን ፊቱን ወደ ፍራፍሬዎች በማዞር በደጃፉ ላይ ባለችው ክፍት ቦታ ሁሉ እየተከለ እንዲመገብ የሚያበረታታ አዲስ ባህልን የሚያለማምድም ነው። ችግኞችን የመትከሉ ንቅናቄ ለበጋው ግብርናችን የሚያበረክተው አስተዋጽኦ ሌላው ስኬት ነው። ወንዞችና ምንጮች አቅም የሚኖራቸው፤ እርጥበት አዘልና ውሃ-ገብ መሬቶች የሚኖሩት፤ ዝናብ ሲኖር ነው። ለዝናብ መኖር ደግሞ የደኖች አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው። ስለዚህ ችግኞችን መትከል በግብርናው ዘርፍ ስኬታማ ሆነንና በምግብ ራሳችንን ከመቻል አልፈን ኤክስፖርት የማድረግ ግብ ላይ የሚያደርሰን ነው።

ኢትዮጵያ ግብርናን ከኢንዱስትሪ ጋር እያመጋገበች ለማደግ በምትከተለው የእድገት መስመር ውስጥ የኤሌክትሪክ ኃይል ትልቁ ግብዓት ነው። ይህ በመሆኑም ታላቁ የህዳሴው ግድብን ጨምሮ በርካታ የውሃ ኃይል ማመንጫ ጣቢያዎችን ገንብታለች፤ እየገነባችም ነው። ወንዞች እንዲሞሉና ኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች የሚጠበቅባቸውን ኃይል እንዲያመነጩ ደግሞ ዝናብ መዝነብ አለበት፤ ከዚህ አንጻር የሚተከሉት ችግኞች የሚያበረክቱት አስተዋጽኦ ቀላል ግምት የሚሰጠው አይደለም፤

በተጨማሪም በወንዞች ዳርቻ የሚተከሉ ችግኞች ግድቦች በደለል እንዳይሞሉ የማድረግ ሚና ያላቸው ናቸው። ስለዚህ ችግኞችን መትከል ‹‹በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ›› ከሚባለውም በላይ ነው የምንለው በነዚህና በሌሎች ባልጠቀስናቸው በርካታ ጥቅሞች ነው። ስለዚህ ችግኝ መትከልን ለትውልዶች የሚተላለፍ ባህል አድርጎ ማስቀጠል ከዚህ ትውልድ የሚጠበቅ ትልቁ የቤት ስራ ነው።

 ኢያሱ መሰለ

አዲስ ዘመን ሐምሌ 14/2015

Recommended For You

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *