የአትሌቲክሱ መንደር የቤት ስራ

በሃንጋሪ መዲና ቡዳፔስት አዘጋጅነት 19ኛው የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና ሊካሄድ ከአንድ ወር ያልበለጠ ጊዜ ይቀረዋል። ዓለም ትልቅ ትኩረት በሚሰጠው በዚህ መድረክ ለመሳተፍ አገራት የሚወክላቸውን አትሌቶች መርጠው ወደ ዝግጅት ከገቡ ሰንብተዋል። በዚህ ታላቅ መድረክ ውጤታማ ይሆናሉ ተብለው ከሚጠበቁ አገራት መካከል አንዷ የሆነችው ኢትዮጵያም አሉኝ የምትላቸውን ጠንካራ አትሌቶች መርጣ የቅድመ ዝግጅት ስራዎችን እያጠናቀቀች ትገኛለች።

ኦሊምፒክን ጨምሮ የዓለም ቻምፒዮና እና ሌሎች ዓለም አቀፍ ውድድሮች ሲቃረቡ በኢትዮጵያ ስፖርቱን በሚመሩ አካላት፣ አትሌቶችና አሰልጣኞች መካከል የተለያዩ ውዝግቦች መነሳታቸው የተለመደ ነው። ይህም በትልቅ ዓለም አቀፍ መድረክ አገርን ምን ያህል ዋጋ ሲያስከፍል እንደነበር አይዘነጋም፡፡

አሁን ኢትዮጵያ በእንቁ አትሌቶቿ የምትደምቅበት ዓለም አቀፍ መድረክ እንደመቃረቡ የተለመዱ ውዝግቦች እንዳይፈጠሩ ከወዲሁ በትኩረት ሊሰራ የሚገባበት ወቅት ነው። ኢትዮጵያ ከኦሊምፒክ ያልተናነሰ የድል ድርሳኗን በዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና መድረክም ማጻፍ የቻለች አገር ነች። በአትሌቲክስ ስፖርት ትልቁ በሆነው በዚህ ውድድር ሃገርን መወከል ለአትሌቶች ታላቅ ክብር የመሆኑን ያህል ሜዳሊያ አስመዝግቦ ባንዲራን ማውለብለብም ልዩ ትርጉም አለው። በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ ስኬታማ ሀገር ስትሆን እአአ ከ1983 አንስቶ ባለው የቻምፒዮናው ዕድሜ 95 ሜዳሊያዎችን መሰብሰብ ችላለች። ይህም ከዓለም አገራት ስድስተኛ ደረጃን በመያዝ ገናና ስም እንድታገኝ አድርጓታል።

በመካከለኛ እና ረጅም ርቀት ሩጫዎች የምትታወቀው ኢትዮጵያ የውድድር መድረኩ ድምቀት ከሆኑ ሀገራት መካከል አንዷ ናት። የብርቅየ አትሌቶች ሀገር እንደመሆኗ ከ800 ሜትር እስከ ማራቶን ባሉት ርቀቶች አትሌቶቿ አስቀድመው ለአሸናፊነት ይጠበቃሉ። በቡዳፔስትም ተመሳሳይ ግምት አግኝተዋል። ባለፈው ዓመት በአሜሪካ ኦሪጎን በተካሄደው 18ኛው የዓለም ቻምፒዮና ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ቀዳሚ ከዓለም ደግሞ ሁለተኛዋ ሀገር ሆና ማጠናቀቋ የሚታወስ ነው። በታሪክ የመጀመሪያው የሆነው ይህ ደረጃ ሊገኝ የቻለው ደግሞ በ4 ወርቅ፣ በ4 ብር እና 2 ነሃስ በጥቅሉ 10 ሜዳሊያዎች በመመዝገባቸው ነው።

እነዚህ ሜዳሊያዎች እንዲመዘገቡ ኢትዮጵያም ስሟ በበጎ እንዲነሳ ምክንያት የሆነው ደግሞ በአጠቃላይ ቡድኑ በነበረው መናበብና የጋራ ስራ ነበር። ‹‹አረንጓዴው ጎርፍ›› መታወቂያው በሆነውና በተለይ በቡድን ስራው ተደናቂ የሆነው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ብሄራዊ ቡድን የቀድሞ ግርማውን ካጣ ከዓመታት በኋላ ዳግም አንሰራርቶ የታየበት ዓመትም ነበር። ከግል ውጤት ይልቅ ሀገርን በማስቀደም እንዲሁም ተግባብቶ በመስራትም ኢትዮጵያ የሳቀችበት ህዝቧም በደስታ ያነባበትን ውጤት ሊያመጣ ችሏል። ይህ ስሜት ሳይበርድ በዓመቱ ደግሞ በሌላኛው የዓለም ቻምፒዮና ተሳትፎ በማሟሟቅ ላይ እንገኛለን፡፡

ይህ የደስታ እና የድል ስሜት ሳይቀዛቀዝ በወራት ልዩነት ዳግም በመድረኩ ተሳታፊ መሆን እንዳለፈው ተመሳሳይ ውጤት እንዲጠበቅ ምክንያት ነው። በመሆኑም የቡድኑ አባላት ይህንን ተረድተው የኦሪጎኑን ድል ለመድገም አሊያም ተሽሎ ለመገኘት ዝግጅት እያደረጉ ይገኛሉ። ይህን አጠናክሮ ለመቀጠል አስቀድሞ በእቅድ መመራትና ውጤታማ የሚያደርገውን የቡድን ስሜት በብሄራዊ ቡድኑ አባላት ለማስረጽ ከወዲሁ መስራት ያሻል። ይሁንና ከሰሞኑ በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን እየወጡ የሚገኙ መረጃዎች ዓለም አቀፍ ውድድሮች ሲቃረቡ የተለመደውን ቅሬታ እንዳያጭሩና ውዝግብ እንዳያስነሱም የሚያሰጉ ናቸው

 በተለይ ከአትሌቶች ምርጫ ጋር ተያይዞ በርካታ አላስፈላጊና አሳዛኝ ሂደቶችን ከዚህ ቀደም የስፖርት ቤተሰቡ ተመልክቷል። ወጥ እና አሻሚ ያልሆኑ፣ አትሌቶችና አሰልጣኞቻቸውንም ሊያስማማ የሚችል የመምረጫ መስፈርት አለመኖሩ በተደጋጋሚ ለሚነሳው ቅሬታ ምክንያት ነው። ጥቂት ሳምንታት ብቻ በቀሩት የቡዳፔስቱ ቻምፒዮናም በየርቀቱ የተመረጡ እጩዎች ከነተጠባባቂዎቹ እነማን እንደሆኑ ታውቀዋል። ነገር ግን ይህ ምርጫ ከማራቶን እና በስፔን የሰዓት ማሟያ ውድድር ከተደረገበት የ10ሺ ሜትር ውጪ ባሉ ርቀቶች እንደሁኔታው ሊቀየር የሚችል መሆኑ ከመጀመሪያው አንስቶ በፌዴሬሽኑ ሲገለጽ ቆይቷል።

በዚህም መሰረት በ800 ሜትር፣ 1ሺ500ሜትር፣ 3ሺ ሜትር እና 5ሺ ሜትሮች በተለያዩ የዓለም ሀገራት የሚካሄዱ ውድድሮች መኖራቸውን ተከትሎ የዓለም አትሌቲክስ ባስቀመጠው መርሃ ግብር መሰረት ውድድሮች እስኪዘጉ በሚኖረው ጊዜ የተሻለ ሰዓት ማስመዝገብ የሚችል አትሌት በብሄራዊ ቡድኑ የመካተት እድል ይኖረዋል። ነገር ግን ፌዴሬሽኑ ከሰሞኑ አትሌቶች ተሰባስበው ወደ ሆቴል እንዲገቡ መመሪያ ማስተላለፉን ተከትሎ በ5ሺ እና 3ሺ መሰናክል ውድድሮች ላይ ተሳታፊ እንዳይሆኑና ውድድር የተዘጋ መሆኑን አሳስቧል። በአንጻሩ በ800 እና 1ሺ500 ሜትር በቀረው ጊዜ በተመረጡበት ምድብ ብቻ ተሳታፊ መሆን ይችላሉ።

እንደሚታወቀው የዓለም ቻምፒዮና እና ኦሊምፒክን የመሳሰሉ ታላላቅ ውድድሮች በሚካሄዱባቸው ጊዜያት የዓለም አትሌቲክስ የግል ውድድሮች ላይ የራሱን የጊዜ ገደብ እንደሚያስቀምጥ ግልጽ ነው። በዚህም መሰረት እስከተያዘው ወር መጨረሻ ድረስ ዳይመንድ ሊግን ጨምሮ በሚካሄዱ ውድድሮች ላይ አትሌቶች ተካፋይ መሆን እንደሚችሉ ከመርሃ ግብሩ መረዳት ይቻላል። የዳይመንድ ሊግ መርሃ ግብሩ እንደሚያሳየው ከሆነም በሁለቱም ርቀቶች የሚካሄዱ ውድድሮች በመኖራቸው ተጠባባቂ አትሌቶችን ጨምሮ ሰዓታቸውን ማሻሻል ለሚችሉ አትሌቶች ክፍት መሆን ሲገባው ተዘግቷል። ይህም የሆነው ቀድሞ አትሌቶች እንዲያውቁትና ራሳቸውን እንዲያዘጋጁ ከማድረግ አስቀድሞ በመሆኑ ለቅሬታ መነሻ ስለመሆኑ አያጠያይቅም። በመሆኑም መሰል የቅሬታ ምንጭ የሆኑ ጉዳዮች በአስቸኳይ ሊታረሙ ይገባሉ፡፡

በእርግጥ ተደጋጋሚ ውድድሮችን ማድረግ አትሌቶችን ሊያደክምና ወደፊት የሚኖራቸውን አቋም ሊፈታተን ይችላል። አትሌቶች በግል ውድድሮች ላይ አቅማቸውን አሟጠው በአገራዊ ውድድሮች ላይ ውጤት እንዳያጡ እንዲሁም በጉዳት ምክንያት በቡድኑ ጉድለት እንዳይፈጠር በፌዴሬሽኑ በኩል ሊታሰብበትና አስቀድሞ መላ ሊበጅለት ይገባ ነበር። በአንጻሩ አትሌቶችም ከሀገር የሚቀድም ነገር እንደሌለ መገንዘብና ከክብርም በላይ ለሆነው የሀገር ክብር እንዲቆሙ ነጋሪ ሳያስፈልጋቸው ራሳቸውን ሊያዘጋጁ ይገባል። በሌላ በኩል ፌዴሬሽኑ አትሌቶች ወደ ሆቴል እንዲሰባሰቡና ዝግጅታቸውን እንዲጀምሩ ማስታወቂያ ቢያወጣም አትሌቶች በማሳሰቢያው መሰረት ባለመገኘታቸው በድጋሚ ጥሪ ለማቅረብ ተገዷል። ይህም አካሄድ ተገቢ አለመሆኑንና ለራሳቸውና ለሀገራቸው ክብር ሲሉ በስነምግባርና በታዛዥነት ከአሰልጣኞቻቸው ጋር ሆነው ዝግጅታቸውን መጀመር አለባቸው።

በወራት ልዩነት በሚካሄደው የዓለም ቻምፒዮና ካለፈው ያነሰ ውጤት ማምጣት በእርግጥም የኢትዮጵያውያን አትሌቶችን ብቃት ጥያቄ ውስጥ ሊያስገባ ስፖርት ወዳዱን ህዝብም አንገት ሊያስደፋ ይችላል። መጪው ዓመትም የኦሊምፒክ እንደመሆኑ ያልተቋረጠ ዝግጅትና መሰናዶ ማድረግ ተገቢ በመሆኑ፤ በፌዴሬሽኑ፣ በአትሌቶች፣ አሰልጣኞችና የሚመለከታቸው አካላት ከወዲሁ ተናበውና ያሉባቸውን ክፍተቶች ተወያይተው ሊያርሙ ይገባል።

ብርሃን ፈይሳ

አዲስ ዘመን ሐምሌ 14/2015

Recommended For You

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *