ሊበረታታ የሚገባው የብሪክስ  የአባልነት ጥያቄ!

መንግስታት ያሉበትን ዘመን የሚዋጁ፤ የሕዝቦቻቸውን ተጠቃሚነት የሚያጸኑ የተለያዩ ውሳኔዎችን ይወስናሉ፤ ይህ ትልቁ እና ዋነኛ ኃላፊነታቸው እንደሆነ ይታመናል። ዓለም በተለያዩ ፍላጎቶች ተሞልታ መሳሳቦች በበዙበት ባለንበት ወቅት የመንግስታት ትልቁ አቅምና ስኬታማነት የሚለካው ዓለም አቀፍ እውነታዎችን በብዙ አማራጮች በመመልከት የሚደርሱበት ውሳኔና ውሳኔው ለሕዝባቸው የሚያስገኝላቸው ተጠቃሚነት ነው።

በተለይም የሕዝቦቻቸውን የትናንት የድህነትና ኋላቀርነት ታሪኮች በመለወጥ አዲስ ታሪክ ለመስራት የሚንቀሳቀሱ መንግስታት፤ ፍላጎታቸው መሬት ረግጦ ተጨባጭ ታሪክ እንዲሆን ከሁሉም በላይ፤ ዓለም አቀፍ ሁኔታዎችን በአግባቡ መረዳትና ወቅቱን በሚመጥን መንገድ እያንዳንዷን ርምጃቸውን በጥንቃቄ መራመድ ይጠበቅባቸዋል።

መንግስታት ከዓለም አቀፍ መርሆዎችና ህግጋት ባፈነገጠ መልኩ፤ ከፍ ባለ ራስ ወዳድነት በተገራ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እሳቤዎች ትንፋሽ እያጡ በመጡበት ዓለም፤ በተለይም በማደግ ላይ ያሉ ሀገራት የችግሩ ዋነኛ ገፈት ቀማሽ እየሆኑ ባሉበት፤ አማራጮችን ከመፍጠር ጀምሮ መማተር የማደግ ፍላጎት ያላቸው ሀገራት የውዴታ ግዴታ ነው።

ከዚህ ዓለም አቀፍ አሁናዊ ተጨባጭ እውነታ በመነሳትም የኢትዮጵያ መንግስት ድህነትን ታሪክ በማድረግ የዜጎችን ሕይወት ለመለወጥ የጀመረው የለውጥ መንገድ በስኬት እንዲጠናቀቅ፤ ዘመኑን የሚዋጁ የተለያዩ አማራጮችን ለመጠቀም እየተጓዘበት ያለው መንገድ፤ በብዙ መልኩ ሊበረታታ እና እውቅና ሊሰጠው የሚገባ ነው።

በተለይም ለዘመናት በተለያዩ አካላት ጫና ውስጥ ያለው የታዳጊ ሀገራት የማደግ ፍላጎት ፈተናን ተሻግሮ ለማለፍ፤ ሀገር በቀልና ሌሎች አማራጮችን መፍጠር ካልሆነም በተፈጠሩት ተጠቃሚ ለመሆን መንቀሳቀስ የግድ ነው፤ ለዚህ የሚሆን ሁለንተናዊ ዝግጁነትና ቁርጠኝነት መፍጠርም ለነገ የማይባል ወሳኝ የዛሬ ሥራ ነው።

ከዚህ አንጻር መንግስት የብሪክስ አባል ለመሆን ያቀረበው ጥያቄ፤ ጥያቄው እንደ ሀገር ለጀመርነው ድህነትን ታሪክ የማድረግ ሀገራዊ ንቅናቄ ሊኖረው ከሚችለው አቅም አንጻር ሊበረታታ የሚገባ ትልቅ ውሳኔ ነው። ለጀመርነው ልማት ስኬትም ተጨማሪ አማራጭ መፍጠር የሚያስችል ነው።

ጥያቄው በብዙ አስገዳጅ ሁኔታዎች ከተወሳሰበው የዓለም የፋይናንስ አቅርቦት/ብድር እና ድጋፍ/ ጫና በተወሰነ መልኩ አማራጭ ለማግኘት የሚረዳ፤ በብሄራዊ ጥቅሞች ላይ መደራደር የሚያስችል ተጨማሪ እድል መፍጠር የሚያስችል ነው። አሁን ያለውን ዓለም አቀፍ ፖለቲካ በመዋጀት አቅም መገንባት የሚያስችልም ነው።

ሀገሪቱ ካላት የሕዝብ ቁጥር ብዛት፣ እያስመዘገበችው ካለው ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት፤ ከዚህም በላይ ለማደግ ካለው ሰፊ ዕድል፤ በአፍሪካና በሌሎች ሀገራት ያላት ተሰሚነት በተለይም የአፍሪካውያንን ድምጽ ከፍ አድርጎ ከማስተጋባት አንጻር የአባልነት ጥያቄ ማቅረቧ ተገቢና አስፈላጊ ነው። በዓለም አቀፍ መድረክ ያላትን አቅምም የሚያጎለብት ነው።

እንደ ሀገር ቀደም ባለው ጊዜ ከብሪክስ አባል ሀገራት /ብራዚል፣ ህንድ፣ ቻይና፣ ሩሲያ፣ ደቡብ አፍሪካ / ጋር ያላት መልካም የዲፕሎማሲ ግንኙነት ጥያቄዋ ተቀባይነት እንዲያገኝ እንደ አንድ መልካም ዕድል የሚቆጠር ነው። እንደ ሀገርም ከአባል አገራቱ ጋር ተደምሮ ድምጽን ማሰማት መቻልም ለጀመረችው ድህነትን ታሪክ የማድረግ የልማት ጉዞ ስኬት ተጨማሪ ጉልበት ተደርጎ ሊወሰድ የሚችል ነው።

ብሪክስ የዓለምን የፋይናንስ ተቋማት ጣልቃገብነት በመቆጣጠርና ፍትሃዊነትን በማስፈን ለታዳጊ አገራት ካለው ሁለንተናዊ ጥቅም አንጻር፤ ሀገሪቱ ከተዛባው ዓለም አቀፍ የግብይት ሥርዓትም ሆነ ከምዕራባውያን የፋይናንስ ፖሊሲ የሚደርስባትን ጫና ለማቅለል የሚረዳ ነው። ብሄራዊ ጥቅሞችን በተሻለ መንገድ ለማስጠበቅም አማራጭ ዕድል የሚፈጥር ነው !

አዲስ ዘመን ሐምሌ 14/2015

Recommended For You

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *