በአሁን ወቅት ለዓለማችን ስጋት እየሆኑ ከመጡት ጉዳዮች መካከል የአየር ንብረት ለውጥ አንዱና ዋነኛው ነው፡፡ የዚህ ችግር ገፈት ቀማሽ የሆኑት ደግሞ ለችግሩ ትልቁን ድርሻ የሚወስዱት ያደጉት ሀገራት ሳይሆኑ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ በማደግ ላይ የሚገኙ ሀገራት ናቸው፡፡ ይህ አሳሳቢ ችግር ባላደጉ ሀገራት ላይ ይዞት የሚመጣው ጣጣ አስፈሪ እንደመሆኑ ከወዲሁ መፍትሄ ካልተበጀለትም ውስብስብ የሆነ ችግር እንደሚያስከትል ተደጋግሞ ተነግሯል፡፡
ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር ተያይዞ ከሚመጡ ችግሮች አንዱ ድርቅ ሲሆን በዚህም ሳቢያ የሰው እና የእንስሳትን ሕይወትን እየቀጠፈ ይገኛል፡፡ የአፈር መሸርሸር፣ የመሬት መራቆትን እንዲሁም የደን መመንጠርን ለመከላከል በቀዳሚነት ከሚጠቀሱ የመፍትሄ ሃሳቦች አንዱ ሲሆን ዛፎችን በብዛት በመትከል የምድርን ለምነት መጠበቅ ለነገ የሚተው የቤት ሥራ አይደለም፡፡
ኢትዮጵያ የዚህን ችግር አሳሳቢነት ቀድማ የተረዳች ብቻም ሳይሆን ቀድማ ሁነኛውን መፍትሄ ተግባራዊ ማድረግ የጀመረች ሀገር ናት፡፡ በዚህም ርምጃ ዘንድሮ አራት ዓመታትን አስቆጥራለች፡፡ ኢትዮጵያ በነደፈችው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር ባለፈው ሐምሌ 10 ቀን 2015 ዓ.ም ‹‹ነገን ዛሬ እንትከል›› በሚል መሪ ሃሳብ በአንድ ጀምበር አምስት መቶ ሚሊዮን ችግኞችን ለመትከል አቅዳ ከዚያም የላቀ ስኬት ማስመዝገባ ይታወቃል፡፡
የአየር ንብረት ለውጥ ነገ ላይ ይዞት የሚመጣውን ችግር በማሰብ ዘር፣ ቀለም፣ ጾታ፣ ሃይማኖት እና ሌሎች ልዩነቶች ሳይገደቡ ችግሩ ሁሉንም የሚነካ መሆኑን በመረዳትም ከህፃናት እስከ አረጋውያን ሁሉም የማኅበረሰብ ክፍል ችግኞችን በመትከል የድርሻውን እየተወጣ ይገኛል፡፡ ከነዚህ የማኅበረሰብ ክፍሎች ደግሞ አንዱ አካል ጉዳተኞች ናቸው፡፡
የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ማህበራት ፌዴሬሽን የኮሙዩኒኬሽን ክፍል ኃላፊ አቶ ታደሰ መሸሻ፣ አካል ጉዳተኞች እንደሌሎች የሕብረተሰብ ክፍሎች በማህበራዊ፣ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ተሳትፎ በማድረግ ላይ እንደሚገኙ ያስረዳሉ፡፡ አረንጓዴ ዐሻራን ከተጀመረበት ቀን ጀምሮም በፌዴሬሽኑ አስተባባሪነት፣ በተለያዩ አደረጃጀቶች፣ በግል እና በማህበራቸው አማካኝነት ችግኝ ተከላው ላይ ንቁ ተሳትፎ እያደረጉ ይገኛሉ፡፡
እንደ ኃላፊው ማብራሪያ፣ ፌዴሬሽኑ ለአካል ጉዳተኞች መብት መከበር የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን ጨምሮ የተለያዩ ሥራዎችን ይሠራል። መንግሥት አካል ጉዳተኞችን አስመልክቶ ይዞት በሚወጣው ፖሊሲ እና ሌሎች ጉዳዮችን ያማክራል። መብት ከመጠየቅ ባለፈም አካል ጉዳተኞች የዜግነት አስተዋጽኦቸውን እንዲያበረክቱ ኃላፊነቱን ይወጣል፡፡ ስለሆነም በዚህ አረንጓዴ ዐሻራን በማኖር መርሃ ግብር ላይ አካል ጉዳተኞች እኩል ተሳትፎ ለማድረግ ጥረት አድርገዋል፡፡
ከኢትዮጵያ ማየት እና መስማት የተሳናቸው ብሔራዊ ማሕበር በችግኝ ተከላው ላይ ከተሳተፉት መካከል አቶ መላኩ ጎለጬ አንዱ ሲሆኑ፣ የተለያዩ አካል ጉዳተኞች በችግኝ ተከላ መርሃ ግብሩ ላይ ‹‹እችላለሁ›› የሚለውን ሃሳብ በንቃት ይዘው የራሳችን ዐሻራ ማስቀመጥ እንደቻሉ ተናግረዋል። አካል ጉዳተኞች በዚህ መርሃ ግብር ‹‹ምንም ነገር አይበግረንም እንችላለን›› የሚለውን መንፈስ በመያዝ ብርድ እና ዝናብ ሳይበግራቸው ዐሻራቸውን ማስቀመጥ መቻላቸውንም በኩራት ይገልጻሉ፡፡
ይህም አካል ጉዳተኞች ከሌላው ማኅበረሰብ እኩል መሆናቸውን ያሳዩበት ዕድል የፈጠረ ሲሆን፣ በችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ላይ እንዲሳተፉ ፌዴሬሽኑ የተለያዩ የቅስቀሳ እና የግንዘቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን ሰርተል፡፡ እነርሱም በሀገር አቀፍ ደረጃ በተለያዩ ቦታዎች በተመቻቸላቸው ዕድል ተጠቅመው ተሳትፎ ማድረጋቸው የሚበረታታ መሆኑንም አቶ ታደሰ ተናግረዋል፡፡
ይሁን እንጂ አካል ጉዳተኞቹ እንደማንኛውም ኅብረተሰብ ክፍል አሻራቸውን በቀላሉ ማሳረፍ ችለዋል ብሎ ደፍሮ መናገር ያዳግታል፡፡ ለወትሮም ቢሆን በማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና በዕለት ተዕለት እንቅስቃሴያቸው ብዙ ፈተናዎች ሳይገጥማቸው እንደማያልፍ የሚታወቅ ጉዳይ ነው፡፡ ከችግኝ ተከላ ጋር ተያይዞም የችግኝ መትከያ ቦታዎች ለአካል ጉዳተኞች አመቺ እንዳልነበሩ በመጠቆም ለወደፊት አካል ጉዳተኞችን ታሳቢ ያደረጉ እንዲሆኑ አቶ ታደሰ አስተያየት ሰጥተዋል፡፡ ተደራሽነትን በተመለከተም መስማት የተሳናቸውን በትክክል ለመድረስ እንኳን ውስን መገናኛ ብዙኃን ብቻ በምልክት ቋንቋ ሲሠሩ እንደነበርም አክለዋል፡፡ ይሁን እንጂ አካል ጉዳተኞች ባሉበት አካባቢ፣ ማህበራቸው በሚገኘው ቅጥር ግቢ ውስጥ ችግኞችን በመትከል የድርሻቸውን ተወጥተዋል፡፡
እንጦጦ ፓርክ አካባቢ ዐሻራቸውን ያሳረፉት አቶ መላኩ እንደሚናገሩት፣ አካል ጉዳተኞች የሁሉም ጉዳይ ላይ በሆነው የችግኝ ተከላ ዐሻራቸው ማሳረፍ መቻላቸው ጥሩ ሆኖ ሳለ ዐሻራቸውን ለማኖር ፍላጎት ኖሯቸውን ቦታዎች ምቹ ባለመሆናቸው ችግኝ ሳይተክሉ የተመለሱ ሰዎች እንደነበሩም ጠቁመዋል፡፡
ምንም እንኳን ከላይ የተነሱት ችግሮች ይኑሩ እንጂ አካል ጉዳተኞች ዐሻራቸውን ከማሳረፍ አላገዳቸውም፡፡ ጎታች የሆኑ ሥራዎች ቢኖሩም በልማት ሥራዎች ላይ በንቁ መሳተፍ እንደሚችሉም አሳይተዋል፡፡
ፌዴሬሽኑ የተቋቋመው የአካል ጉዳተኞችን መብት ለማስከበር በመሆኑ በተለያዩ ዘርፎች ላይ የአካል ጉዳተኞችን ተሳትፎ እንዲጨምር እና ተጠቃሚዎች እንዲሆኑ ከመንግሥት ጋር በጥምረት በሚሠሩ ሥራዎች ላይ ጠንክሮ መሥራት እንደሚገባም አቶ ታደሰ ገልጸዋል፡፡ አካል ጉዳተኞች በሁሉም ዘርፍ ያሉባቸው እንቅፋቶች ተወግደው ተሳታፊነታቸው እንዲጨምርም ብዙ ሥራ መሥራት እንደሚገባ አያይዘው ገልጸዋል፡፡
ችግኝ ለመትከል ለአካል ጉዳተኞች ምቹ ሁኔታዎች መፈጠር አለባቸው የጠቆሙት አቶ መላኩ እሳቸው ዐሻራቸውን ለማሳረፍ በተገኙበት አካባቢ ከፍታ ቦታ መኖሩ፣ ቁፋሮው ለአካል ጉዳተኞች ምቹ አለመሆኑ እና ስለቦታው ቀድሞ መረጃ አለመሰጠቱ ችግር እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡ ይህም እንዳሳዘናቸው በመግለፅ ፤ ለአካል ጉዳተኞች ተደራሽ የሆነ ነገር እንደሚያስፈልግ እና እንዲህ ዓይነቱ ክፍተት በቀጣይ መስተካከል እንዳለበት አብራርተዋል፡፡
በመጨረሻም እንዲህ ባለው እና የሁሉንም ተሳትፎ በሚፈልግ ሀገር አቀፍ መርሃ ግብር አካል ጉዳተኞችን ታሳቢ ያደረጉ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን መሥራት እንደሚገባ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
በእየሩስ ተስፋዬ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 13/2015