‹‹በግብርናው በኩል የምንሠራው የወጪ ምርትን በማሳደግ ለሀገር አስተዋፅዖ ማበርከት ነው›› አቶ መምሩ ሞኬ የሲዳማ ክልል የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ መምሩ ሞኬ የሲዳማ ክልል የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ ኃላፊ

ግብርና የአገሪቱ ኢኮኖሚ ዋና መሠረት የሆነና ወደ ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ ለሚደረገው ሽግግር ድልድይ መሆኑ እሙን ነው፡፡ ከዚህ አኳያ ምርትና ምርታማነቱ እንዳይቀንስ ምቹ የአየር ንብረት ሊኖር የግድ ይላል፡፡ ስለዚህም የአፈር መሸርሸር እንዳይከሰትና የአፈር ለምነት እንዳይቀንስ የተለያዩ ተግባራትን ማከናወን ወሳኝ ነው፡፡

ለዚህ ደግሞ ካለፉት አራት ዓመታት ጀምሮ በስፋት እየተካሔደ ያለው የአረንጓዴ አሻራ መርሐግብር ዋንኛ ተግባር በመሆኑ አጠናክሮ መቀጠሉ ከግብርናው ዘርፍ ለመጠቀም ታላቁ ብልሃት ነው፡፡ በመሆኑም ከግብርናው ዘርፍ ምን ተሠርቶ ምንስ ውጤት ተገኘ በሚለውና በሌሎች የተለያዩ ጥያቄዎች ዙሪያ አዲስ ዘመን ከሲዳማ ክልል የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ ኃላፊ ከሆኑት ከአቶ መምሩ ሞኬ ጋር ያደረገውን ቃለ ምልልስ እንደሚከተለው አጠናቅሮ አቅርቦታል፡፡

አዲስ ዘመን፡- ቢሮው በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ትኩረት ሰጥቶ የሠራው ምንድን ነው? አፈጻጸሙስ ምን ይመስል ነበር?

አቶ መምሩ፡- በሀገር አቀፍ ደረጃ ትኩረት ተሰጥቶባቸው እየተተገበሩ ያሉ ዘርፎች እንዳሉ ይታወቃል። ከዚህ የትኩረት መስኮች ግብርና ቀዳሚውን ስፍራ ይይዛል። ሌሎቹ ደግሞ ማኑፋክቸሪንግ፣ የቱሪዝም ዘርፍ፣ አይ.ሲ.ቲ እንዲሁም የማዕድን ዘርፍ ተጠቃሾች ናቸው። እንደጠቀስኩት እነዚህ በሀገር ደረጃ ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቷቸው የሀገር በቀል ፖሊስን መነሻ በማድረግ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ሲሆኑ፣ ግብርና ትልቁን ድርሻ ይይዛል፡፡

ይህን መነሻ በማድረግ በእርሻው ዘርፍ በዓመቱ የተቀመጡትን ግቦች ለማከናወን እንደ ሀገርም እንደ ክልልም ሰፊ ሥራ እየተሠራ ነው፡፡ መነሻውም ቀደም ሲል የተዘጋጀው የአስር ዓመት እቅድ ነው፡፡ ይህን እቅድ መነሻ በማድረግ በአስር ዓመት መድረስ ወደሚገቡን ጉዳዮች ለመድረስ በየዓመቱ ከአስር ዓመቱ እቅድ እየተቀዱ የሚሠሩ ተግባራትን እየሠራንና እየፈጸመን እንገኛለን፡፡

በዚህ መነሻ እንደ ክልላችን ቅድሚያ የተሰጠው የሰብል ልማት ዘርፉ ሥራ ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ የቡና ልማት ሥራችን ነው፡፡ በሦስተኛ ደረጃ የያዝነው ደግሞ የአየር ንብረት ለውጥን የሚቋቋም ኢኮኖሚ በመፍጠር ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የተፈጥሮ ሀብት ልማት ሥራችንን ነው፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ የመስኖ ልማት ሥራዎች እና የተለያዩ የተፋሰስ ልማት ሥራዎች ከዚህ ጎን ለጎን የሚሠሩ ናቸው፡፡

ትኩረት ተደርገው የሚሠሩ ሥራዎች በዋናነት ሲስተዋሉ የመጀመሪያው ነገር የሆነው በምግብ ራስን የመቻልና የምግብ ዋስትናን የማረጋገጥ ግብ ነው፡፡ ሁለተኛው ግብ ገበያ ተኮር የሆነ ግብርናን በማካሔድ ለኢንዱስትሪ ጥሬ እቃ የሚሆኑ ግብዓቶችን የማግኘት ሥራ ነው፡፡ ሦስተኛው ደግሞ የኩታ ገጠም እርሻን መሠረት ያደረገ የምርታማነት ስኬት ማስመዝገብ ነው።

በተለይ በግብርናው በኩል የምንሠራው የወጪ ምርትን በማሳደግ በሀገር ደረጃ ከፍተኛ አስተዋፅዖ ማበርከት ነው። ይንን መነሻ በማድረግ አቅደን የምንሠራቸው አንደኛ በርካታ የሆኑ የአቅም ግንባታ ሥራዎች ናቸው፡፡ የአመራሩን፣ የባለሙያንና የአርሶ አደሩን አቅም በማሳደግ ተጠቃሚነትን ከፍ ማድረግ ነው። በዚህ መነሻ በዓመት ውስጥ ወደ 816 ሺ የኤክስቴንሽን ተጠቃሚዎች እንዲኖሩ የማድረግ ሥራ ተሠርቷል፡፡ ከዚህ ውስጥ ወደ 437 ሺ የሚሆነው አርሶ አደር የኩታ ገጠምን (ክላስተርን) ጨምሮ የሙሉ ፓኬጅ ተጠቃሚ ነው፡፡

በሚሰጡ የአቅም ግንባታ ሥራዎች ከጊዜ ወደጊዜ የኤክስቴንሽን የሙሉ ፓኬጅ ተጠቃሚነት እንዲሁም የኩታ ገጠም አጠቃቀም እየተሻሻለ መጥቷል፡፡ ለዚህ ማሳያው ሞዴል አርሶ አደሮችን በዓመቱ ውስጥ በሰብል ልማት፣ በመስኖ ልማትና በቡና ልማት ሙሉ ፓኬጅ እንዲጠቀሙ በማድረግ ተደራሽ መሆን ችለዋል፡፡

የኤክስቴንሽን ተደራሽነት እና ተጠቃሚነት አንደኛው ስለሆነ በቀጣይ የምንሠራቸው በርካታ ጉዳዮች እንደተጠበቁ ሆነው የአርሶ አደሮቻችንን ተጠቃሚነት ወደ እዛ ደረጃ ማድረስ ችለናል፡፡ ሁለተኛው እነዚህ አርሶ አደሮች የሚሰማሩባቸው የተለያዩ ዘርፎች ናቸው። የመጀመሪያው አስቀድሜ ለመጥቀስ እንደሞከርኩት የምንሠራው የሰብል ልማት ሥራ ነው፡፡ ይህን መነሻ በማድረግ በወቅቶች የተከፋፈሉ ተግባራት አሉን፡፡ እነዚህም የመኸር፣ የመስኖ፣ የበልግ እና ከዚህ ጎን ለጎን ደግሞ የቡና ሥራዎች ተያይዘው የሚሔዱ ናቸው፡፡

ከሰብል ልማት አኳያ ያቀድናቸው ሥራዎች አሉ፤ ይህ የሚጀምረው በዓመቱ የመኸርን ተግባር ከማሳካት አኳያ ነው፡፡ ማለትም 2014/15 የምርት ዘመን የመኸር ሥራ ማሳካት ነው፡፡ በመሆኑም ከ92 ሺ ሔክታር መሬት በላይ ምርት በማልማት ወደ ሁለት ነጥብ አንድ ሚሊዮን ኩንታል ምርት የማግኘት ሥራ ተሠርቷል፡፡ ይህም በብርዕ፣ በስራስር እና በጥራጥሬ ሰብሎች 85 በመቶ የዕቅዳችንን ማሳካት ችለናል። ይህ በየዓመቱ ሲታይ ለውጦች አሉት፡፡ ነገር ግን በእያንዳንዱ ሰብል ስንመጣ ምርታማነት የጨመረ ቢሆንም አሁንም ከምርታማነት አኳያ በእያንዳንዱ ሰብል የምንጨምራቸው ምርታማነቶች ገና ይቀሩናል። ይኸውም በምርትና ምርታማነት እንዲሁም የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ላይ የሚያስፈልገውን ከፍተኛ ሥራ መሥራት ነው፡፡

ሁለተኛው ተግባራችን የሆነው የመስኖ ልማት ሥራ ነው፡፡ ሁለት የመስኖ አሠራር ሥራ አለ፤ ይኸውም መደበኛ መስኖና የበጋ መስኖ ስንዴ ነው። በዚህ መሠረት የበጋ መስኖ ስንዴን ስንመለከት ወደ 67 ሺ ሔክታር መሬት ለማልማት በማቀድ በሁለቱም ዙር ወደ 64 ሺ ሔክታር የማሳካት ሥራ ተሠርቷል፡፡ ከዚህም እንደ አጠቃላይ ወደ አንድ ነጥብ 35 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ማግኘት ተችሏል፡፡ በተለያዩ የጓሮ አትክልቶችና በተለያዩ ስራስር ሰብሎች ላይም ተሠርቷል፡፡ ከዚህ ውስጥ በዋናነት ስንዴን በሚመለከት 2 ሺ 500 ሔክታር በማቀድ 1 ሺ 626 ሔክታር ማልማት ተችሏል፤ ከዚህም ወደ 29 ሺ 111 ኩንታል ምርት ተገኝቷል። ምርታማነቱንም በሔክታር ስናሰላው ወደ 31 ኩንታል መድረስ ችሏል፡፡

እንደሚታወቀው እንደሌሎች ክልሎች ሰፋ ያለ የመስኖ መሬት ባይኖረንም ባለን ቦታ የተሻለ ሥራ እየሠራን እንገኛለን። ለምሳሌ በበልግ ወቅት በቆሎን የሚያመርቱ አካባቢዎች ወደ መስኖ ሥራ እንዲገቡ ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራ ተሠርቷል። በሁሉም የአየር ጸባይ ማለትም በደጋ፣ በወይና ደጋና በቆላ አካባቢዎች ስንዴን የውሃ አማራጭ በማዘጋጀት እንዲያለሙ የተለያየ እንቅስቃሴ ተካሂዷል፡፡ በዚህም እንቅስቃሴ በ2014 ዓ.ም ወደ 1 ሺ 126 ሔክታር መሬት ማድረስ ተችሏል። በዚህም በሁሉም የሲዳማ አካባቢዎች ስንዴን አልምቶ ምርታማ መሆን እንደሚቻል ማረጋገጥ ተችሏል፡፡ ነገር ግን ከተቀመጠው ግብ አኳያ ብዙ መሥራት እንዳለብን ያሳየናል፡፡ በመሆኑም ትልቅ ትምህርት የተወሰደበት በመሆኑ በቀጣይም ትልቅ ውጤት የምናመጣበት መሆኑን ተረድተናል፡፡

ሦስተኛው ተግባር ደግሞ ከበልግ ሥራ አኳያ ያስቀመጥናቸው ግቦች አሉ፡፡ 105 ሺ ሔክታር መሬት በማቀድ ወደ 101 ሺ ሔክታር መሬት በዘር በመሸፈን በአሁኑ ወቅት የምርት እንክብካቤ ላይ እንገኛለን። ይህም በዘር መሸፈን ደረጃ ያቀድነውን ከ94 በመቶ በላይ ማሳካት ችለናል፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ ትልቁን ድርሻ የሚወስደው ሰብል በቆሎ፣ የስራስር፣ ቦለቄና ሌሎች ሰብሎች ናቸው። በአጠቃላይ ትልቁን ድርሻ በቆሎ የሚይዝ ቢሆንም በልግን በስፋት የምናለማው በአገዳ፣ በጥራጥሬና በስራስር ሰብሎች ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት እየሠራን ያለነው በቀጣይ ወደ ሁለት ነጥብ አምስት ሚሊዮን ኩንታል በአገዳ ሰብል ማግኘት የምንችልበትን ግብ ጥለን ነው፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ የምንገኘው በማሳ እንክብካቤ ላይ ሲሆን፣ የስራስርና የጥራጥሬ ሰብሎች በአሁኑ ወቅት በመድረስ ላይ ይገኛሉ። ይሁንና ምርቱን ስላልሰበሰብን ምን ያህል ነው የሚለውን ልንገልጽ አንችልም፡፡ ነገር ግን ማሳ ላይ ያለውን አያያዝ ስናይ በእጅጉ ተስፋ ሰጪ እንደሆነ ከወዲሁ ተረድተናል፡፡

አሁን ያለው የሰብል አቋም የተሻለ ነው እንደሆነ ብንረዳም ከዚህ በላቀ ሁኔታ አስፈላውን እንክብካቤ ካደረግን የተሻለ ውጤት ማግኘት የምንችልበት እድል አለን። እንደሚታወቀውም የግብርና ሥራ እንደ በጀት ዓመት አንዴ የሚጠናቀቅ ሳይሆን አንዱ ዓመት ከሌላው ዓመት እየተቀባበለ የሚሄድ ነው፡፡ ለምሳሌ የተያያዝነው የግብርና ሥራ ባለበት ዓመቱ በማለቁ የተሸጋገርነው ወደ መኸር ነው፡፡ መኸሩን በሚመለከት ከ125 ሺ ሔክታር መሬት በላይ አቅደን በአሁኑ ወቅት ወደተግባር ገብተናል። ለዚህም የሚሆን እንደ አቅም ግንባታ ሥራዎች እየሠራን ነው፡፡ ስለዚህ ዓመቱ ሳያልቅ የሚቀጥለውን ዓመት የመኸር ሥራ ጀምረናል ማለት ነውና ቅብብሎሹ በዚህ አይነት ሁኔታ የሚሠራ ነው፡፡

እንደ አጠቃላይ ይህን ለማሳለጥ ሁለተኛው ጉዳይ የቴክኖሎጂ አጠቃቀማችን ነው፤ በዋናነት በዓመቱ ትልቁን ድርሻ የሚይዘው የማዳበሪያና የምርጥ ዘር አቅርቦት ነው፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ የማዳበሪያ አቅርቦትን በሚመለከት እንደ አጠቃላይ ኤን.ፒ.,ኤስ. (NPS) የአፈር ማዳበሪያ ወደ 152 ሺ ኩንታል በማቀድ አሁን ባለው ሁኔታ 106 ሺ ኩንታል ጥቅም ላይ እንዲውል ተደርጓል። ዩሪያን በሚመለከት ወደ 113 ሺ ኩንታል በማቀድ አሁን ባለው ሁኔታ ወደ 50 ሺ ኩንታል ጥቅም ላይ ማዋል ተችሏል፡፡

ሌላው ሊጠቀስ የሚችለው ከቴክኖሎጂ አጠቃቀም አኳያ የመካናይዜሽን ሥራ ነው፡፡ ለአብነት የኩታ ገጠም ሥራውን ታሳቢ በማድረግ ወደ 28 የሚጠጋ ትራክተር ሥራ ላይ ለማሰማራት ታቅዶ 32 ትራክተሮች ሥራ ላይ እንዲሰማሩ ተደርገዋል፡፡ ከዚህ ውስጥ አራቱን የክልሉ መንግሥት በ2014 በጀት ዓመት ገዝቶ ያቀረባቸው ናቸው፡፡ ይህ በመሆኑ ወደ 50 ሺ ሔክታር መሬት በኩታ ገጠም ለማልማት በማቀድ 45 ሺ ሔክታር መሬት የኩታ ገጠም እርሻ ማካሔድ ተችሏል። በዋናነት የመኸር፣ የበልግ እንዲሁም የመስኖ ሥራው ከጊዜ ወደጊዜ እየጨመረ መጥቷል፡፡

በተለይም በበልግ አምራች የሆኑ እና በመስኖ አካባቢ ያሉ የኅብረተሰብ ክፍሎች እንዲሁም በመኸር አምራች የሆኑ በኩታ ገጠም የማልማት ልምዳቸው እያደገ መምጣት ችሏል፡፡ የቴክኖሎጂ አጠቃቀማቸውም እንዲሁ እየተሻሻለ በተጨማሪም ምርታማነትም እያደገ መጥቷል፡፡ ከዚህ በመነሳት ገበያንም ጭምር ለማሻሻል የተሠራው ሥራ መልካም የሚባል ነው፡፡ ለምሳሌ ከገብስ እና ከስራስር አኳያ ሲታይ ወደገበያው ማቅረብ ተችሏል። ነገር ግን በተወሰነ ደረጃ የገበያ ትስስር የተፈጠረ ቢሆንም አሁንም ገበያ ከማረጋጋት አኳያ ግን ክፍተቶች መኖራቸው አይካድም፤ በትልልቅ ከተሞች ላይ የታየውን የገበያ ሁኔታ ስናስተውል ታች በወረዳ አካባቢ እንዳለው ተረጋግቷል ብለን አንወስድም። ግን ምርቱ በሸማቾች የኅብረት ሥራ ማኅበራት በኩል እንዲቀርብ የማድረግ ሥራ ተሠርቷል። ስለዚህ ከገብስና ከድንች አኳያ በተቻለ መጠን ሁሉም ዘንድ ተመሳሳይ ባይሆንም ገበያን እንዲያረጋጉ የማድረግ ሥራ ከንግድ ጋር ተቀናጅቶ እየተሠራ ነው፡፡

አዲስ ዘመን፡- ከቡና ልማት አኳያ እየተሠራ ያለው ምንድን ነው? ምንስ ውጤት እያመጣ ነው?

አቶ መምሩ፡- መልካም፤ ሁለተኛው ሥራ አስቀድሜ ለመጥቀስ እንደሞከርኩት አንድም ከወጪ ንግድ ጋር ተያይዞ የሚነሳ ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ የሀገራዊ አስተዋፅዖን በሚመለከት ነው፡፡ የወጪ ንግድና ሀገራዊ አስተዋፅዖው ለሀገር ኢኮኖሚ በተለይ ለውጭ ንግድ ተሳትፎ አላቸው፡፡ ይኸውም አንደኛው የቡና ምርት ነው፡፡ ቡናን በሚመለከት ወደ 162 ሺ ሔክታር መሬት ይለማል፡፡ ከዚህ ውስጥ 139 ሺው ምርት የሚሰጥ ነው፡፡ ከተሰበሰበው ቡና ውስጥ 22 ሺ ቶን ለውጭ ገበያ ቀርቧል፡፡ ለውጭ ገበያ የመቅረቡን ያህል ለሀገር ውስጥ የሚሆን ፎጆታውም እንደተጠበቀ ነው። በእርግጥ ለውጭ ገበያ የማቅረብ እቅዳችን 29 ሺ ቶን ነበር፤ ስለዚህ 31 ሺ ቶን በመሰብሰብ 22 ሺ ቶን ቡና ወይም የእቅዳችን 76 በመቶ ቀርቧል፡፡ በተወሰነ ደረጃ አሁን ባለው ከዓለም የቡና ገበያ ጋር ተያይዞ ሁሉም ቡና ከእጃችን አልወጣም፡፡ እንዲያም ሆኖ ይህ የውጭ ንግድ አስተዋፅዖ ብቻ ሳይሆን ለሀገር ኢኮኖሚ የሚያበረክተው አስተዋፅዖም ጭምር ነው፡፡

በቡና ደረጃ ለምሳሌ በዚህ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት 27 ሚሊዮን የቡና ችግኝ ተዘጋጅቶ ወደ 26 ሚሊዮን የሚጠጋ የቡና ችግኝ ተተክሏል፡፡ ይህ ማለት የቡናን ልማት ለማሳለጥ የተደረገ ርብርብ ነው፡፡ በአንድ በኩል ያረጁ ቡናዎች በመኖራቸው በአዳዲስ የቡና ችግኝ የመተካት ሥራ ጭምር ነው። አብዛኛው ወይና ደጋ አካባቢያችን በቡና የተሸፈነ ነው፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ በዓመት ውስጥ አስቀድሜ ከጠቀስኩት ብቻ በቡና ገበያ ከ10 ቢሊዮን ብር በላይ ይንቀሳቀሳል። በዚያው ልክ ደግሞ የሥራ እድል ይፈጥራል። በተጨማሪም የውጭ ምንዛሪን የሚያስገኝ ዘርፍ ነውና ለኢኮኖሚ ያለው አስተዋፅዖ ከፍተኛ ነው። ስለዚህ ምርታማነቱን የማስፋፋቱን ሥራ በዚህ ልክ እየሠራንበት እንገኛለን፡፡

ሁለተኛው ደግሞ ይህ ብቻ ሳይሆን የቡናን ምርታማነት ሊያሳድጉ የሚችሉ ቴክኖሎጂዎች ላይ እየሠራን ነው፡፡ ቡናን ‹‹የቴክኖሎጂ መንደር›› ብለን ስድስት ወረዳ እና ከ30 ሺ ሔክታር መሬት በላይ በመለየት በኩታ ገጠም እያለማ ነው፡፡ በመሠረቱ ቡና በራሱ ኩታ ገጠም ነው፡፡ ግን ደግሞ የቴክኖሎጂ መንደር በሚል ኩታ ገጠሙን ተከትሎ እንዲሄድ የተለያዩ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም በስድስት ወረዳ በ30 ሺ ሔክታር መሬት እና በዚህ የሚሳተፉ አርሶ አደሮችን በመለየት የተለያዩ ፓኬጆች በአንድ ላይ እንዲሆኑ የማድረግ ሥራ እየሠራን እንገኛለን። ይህ ሥራ የቡና ምርታማነትን በሔክታር ይሰጥ ከነበረበት ከዘጠኝ ኩንታል ወደ 10 ነጥብ 2 ኩንታል ማሳደግ አስችሏል፡፡ ከአቅም አኳያ ግን ገና ብዙ ይቀራል፡፡

እንደሚታወቀው የሲዳማ ቡና በዓለም የቡና ገበያም የሚታወቀው በተፈጥሯዊ ይዘቱ (Organ­ic) ነው:: ላለፉት በርካታ ዓመታትም በዚህ ጣዕሙ የልሕቀት ጽዋ (Cup of Excellence) በተደጋጋሚ አሸናፊ መሆን ተችሏል፡፡ ስለዚህ ይህን የበለጠ ለማሳደግ በአንድ ዓመት ብቻ ከሦስት ሚሊዮን ቶን በላይ ኮምፖስት በማዘጋጀት በቡና ማሳ ላይ ጥቅም ላይ እንዲውል ይደረጋል፡፡ ስለዚህ ከአቅም አኳያ ምርታማነትን መጨመር ያስፈልጋል። ነገር ግን ከምርት አኳያ ብዙ ፍጆታ ቢኖርም ቢያንስ እስከ 31 ሺ ቶን ለዓለም ገበያ የማድረስ እና የማዘጋጀት ሥራ እየተሠራ ነው፡፡

ሁለተኛው ከውጭ ንግድ አኳያ ያለው የአቮካዶ ምርት ነው፡፡ አቮካዶን በሚመለከት ወደ ስምንት ሺ ሔክታር መሬት አለ፡፡ አንዱ ግባችን ለኢንዱስትሪ ጥሬ እቃ የሚሆኑ ምርቶችን ማምረት ነው፡፡ ስለዚህ ከይርጋለም የተቀናጀ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክ ጋር በማቀናጀት እየተሠራ ያለው አንደኛው አቮካዶ ነው። በዚህ ዓመት ብቻ ከ2 ሺ 900 ሔክታር መሬት በላይ የአቮካዶ ችግኝ ተከላ ተካሂዷል፡፡

በጥቅሉ ፍራፍሬን በሚመለከት ወደ 14 ሚሊዮን የአቮካዶ፣ ሙዝ፣ አናናስ፣ አፕልና ሌላውንም የችግኝ አይነት መትከል ተችሏል፡፡ እንዳልኩሽ ከዚህ ውስጥ ትልቁን ድርሻ የሚወስደው የአቮካዶ ምርት ነው። በመሆኑም የይርጋለም የተቀናጀ የግብርና አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክን ከአርሶ አደሩ ጋር በማስተሳሰር ገበያ መፍጠር ተችሏል፡፡ ከዚህም የተነሳ ተነሳሽነቱ ጨምሯል።

ይህ በመሆኑ በአሁኑ ወቅት የችግኝ ዝግጅቱ እየጨመረ ነው፡፡ ምርቱም ቢሆን በዛው ልክ እየጨመረ ይገኛል። በእርግጥ አቮካዶ የሚቀርበው ወደ ኢንዱስትሪ ፓርክ ብቻ አይደለም፡፡ ወደሌሎች ገበያዎችም እንደ አማራጭ ይሔዳል፡፡

እስካሁን ባለን መረጃ በአራትና በአምስት ዓመት ውስጥ ከአቮካዶ ምርት ከስምንት ሚሊዮን በላይ የአሜሪካ ዶላር መገኘት ተችሏል፡፡ በዚህ ዓመት ብቻ ደግሞ ወደ ከሁለት ነጥብ ስድስት ሚሊዮን በላይ ዶላር ተገኝቷል፡፡ በአሁኑ ወቅት የገበያ ትስስሩ በዛው ልክ ከፍ እያለ ይገኛል፡፡ ከዚህም የተነሳ አቮካዶ ለውጭ ገበያ ለማቅረብ በጣም ጥሩ አማራጭ የሆነ ምርት ነው። ይህ ከምግብ ዋስትና አኳያም የራሱ አስተዋፅዖ ያለው ነው፡፡

አዲስ ዘመን፡- ሀገሪቱ ከግብርና መር ወደ ኢኮኖሚ መር እየተጓዘች ነው፤ ይህን መሠረት በማድረግ በቢሮው በኩል እየተሠራ ያለው ምንድን ነው?

አቶ መምሩ፡- የቢሮው ትልቁ ተልዕኮ ምርትና ምርታማነት ላይ መሥራት ነው፤ በዚህ ሒደት ውስጥ የምግብ ዋስትና ይረጋገጣል፡፡ በዚህ ሒደት ውስጥ የኢንዱስትሪ ጥሬ እቃ ወይም ግብዓት ይገኛል። ብሎም የውጭ ምርት ያድጋል፡፡ ስለዚህ ከምግብ ዋስትና አኳያ የምግብ ዋስትናን የሚያረጋግጡ የብር፣ የአገዳ፣ የጥራጥሬና እንሰትን ጨምሮ የስራስር ሰብል ላይ ሰፊ ርብርብ እየተደረገ ነው፡፡ በመኸር፣ በበልግና በመስኖ በሚሠሩ ሥራዎች የምግብ ዋስትና በማረጋገጥ፣ የሀገር ውስጥ ገበያን በማረጋጋት በኑሮ ውድነት ላይ የሚፈጠረውን ጫና በመቀነስ ደረጃ ርብርብ እየተደረገ ነው፡፡ ይህ በአንድ በኩል በሀገር ኢኮኖሚ ላይ አዎንታዊ ተጽዕኖ ያሳድራል፡፡ ስለዚህ አንድም የአካባቢውን የምግብ ዋስትና መሸፈን አንድ ግብ ነው፤ በተጨማሪ ደግሞ ወደ ዘርፉ የሚደረገውን ጉዞ ያፋጥናል፡፡

ሁለተኛው አስቀድሜ እንደገለጽኩት የውጭ ንግድ (ኤክስፖርት) አስተዋፅዖ ነው፡፡ የኤክስፖርት አስተዋፅዖ ላይ ቡናም አቮካዶም የየራሳቸው ድርሻ አስተዋፅዖ አላቸው፡፡ ከጥራጥሬ አኳያ ደግሞ የቦለቄም አስተዋፅዖ ሌላው ተጠቃሽ ነው፡፡ ስለዚህ እነዚህ ሀገራችን በያዘችው ራዕይ ላይ ትልቁን ድርሻ ይወጣሉ ማለት ነው፡፡ እኛም ይህን ታሳቢ አድርገን እየሠራን ነው። ይሁንና ከአየር ንብረት ተፅዕኖ እና በሌላ በኩል ደግሞ ቴክኖሎጂውን በላቀ ደረጃ ወደ ሁሉም አርሶ አደር ከማድረስ አኳያ አሁንም በቤተሰብ ደረጃ የእያንዳንዱን ዋስትና አረጋግጠናል ማለት አንችልም፡፡ ግን ደግሞ እንደ አጠቃላይ ሲታይ የምግብ ዋስትናን፣ የገበያ መረጋጋትን፣ በውጭ ንግድና ወደ ሀገር ውስጥ የሚገባን ምርት ከመተካት አኳያ ላቅ ያለ አስተዋፅዖ አለው፡፡ በዚህ መሠረት ከሀገር ራዕይ ጋር ተጣጥመው የሚሄዱ ናቸው። ስለሆነም የሲዳማን እቅድ መፈጸም ማለት በሀገር ደረጃ ያለውን በአጠቃላይ አስተዋፅዖ ማድረግ ማለት ነው፡፡

አዲስ ዘመን፡- የተፈጥሮ ሀብት ልማቱ ላይ በተለይ በተፋሰሱ ላይ የተሠራው ሥራ ምን ይመስላል?

አቶ መምሩ፡– ከተፋሰስ እና ከአረንጓዴ አሻራ ጋር ተያይዞ ትልቅ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሠራ ያለ ተግባር ነው። በእኛ አገር ከእኛም አልፎ በጎረቤት አገራት ያልተሞከሩና ልምድ ሊሆኑ የሚችሉ ተሞክሮዎች እየተስተዋሉ ነው፡፡ ክልላችንም የዚህ ተሳታፊ ነው ብቻም ሳይሆን ተጠቃሚም ጭምር ነው፡፡ ለሀገር ኢኮኖሚ ወይም ደግሞ በሀገር ደረጃ የሚመጣውን አሉታዊ ተፅዕኖ ከመቋቋም አኳያ ላቅ ያለ ሚና ያለው ነው፡፡

ከዚህ የተነሳ በክልላችን በመጀመሪያው ዙር ማለትም ባለፉት አራት ዓመታት ወደ 850 ሚሊዮን ችግኞችን የተከልን ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ ከ90 በመቶ በላይ ሊጸድቅ ችሏል፡፡ ይህ መርሐግብር በየዓመቱ የራሱ የሆነ መሪ ሐሳብ ያለው ነው፡፡ ይህን መሪ ሐሳብ ታሳቢ በማድረግ የተተከሉ ችግኞች የአግሮ ፎረስተሪ፣ የደን፣ የፍራፍሬ፣ የእንስሳት መኖዎች እና ሌሎች ችግኞች በማሰባጠር ባለፉት ዓመታት ተተክዋል። ይህ አሠራር አንድም የተራቆቱ አካባቢዎችን የመሸፈን ዓላማን ሰንቆ የተካሄደ ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ በአየር ንብረት ተፅዕኖ የሚከሰቱ ተፅዕኖዎችን ለመቋቋም ነው። በመሆኑም በተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ የተጎዱ አካባቢዎች እንዲያገግሙ የማድረግ ሥራው ተጠናክሮ ቀጥሏል። ለምሳሌ በአፈር መከላት ወይም ደግሞ በደን መራቆት ጎርፍንና ናዳዎች የመከላከል ሥራ ላይ ትልቅ አስተዋጽፅዖ አበርክተዋል፡፡

ስለዚህ የምንተክላቸው ችግኞች በብዛት የደንን መራቆት፣ የአፈር መሸርሸር እና የአፈር መከላትን በዋናነት የሚከላከሉ ናቸው፡፡ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃንም የሚያጠናቅሩ ናቸው፡፡ ከዚህ መነሻ በክልል የደን ሽፋናችን 13 በመቶ ከነበረበት ወደ 22 በመቶ ማድረስ ችለናል፡፡ ስለዚህ የምንሠራቸው ሥራዎች በደን ሽፋን ላይ ትልቅ አስተዋፅዖ አላቸው፡፡ በተጨማሪም እንደ ሀገርም ሆነ እንደዓለም ስናይ ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር ተያይዞ የሚመጡ ተግዳሮቶችን መቋቋም የሚቻልበትን እድል ይፈጥራሉ፡፡

በዚህ መነሻ ወደ 546 የሚሆኑ ተፋሰሶች ተለይተው የተለያዩ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ ተሠርቷል፡፡ የጠረጴዛማ እርከን፣ ውሃ ማቀብና የተለያዩ ሥራዎች በዚህ ዓመት ከተሠሩ ሥራዎች መካከል ተጠቃሾች ናቸው፡፡ በቀጣይም የሚሠራ ይሆናል፡፡ በዚህ ዓመትም ወደ 306 ሚሊዮን ችግኞችን በማቀድና ወደ 301 ሚሊዮን ችግኞችን በማዘጋጀት 70 በመቶ ያህል ተከላውን አካሂደናል፡፡

አዲስ ዘመን፡- የከተማ ግብርና ልማትን በከተሞች ተግባራዊ በማድረግ ኅብረተሰቡን ከግብርናው ውጤት ተጠቃሚ ለማድረግ ምን እየተሠራ ነው?

አቶ መምሩ፡- የከተማ ግብርናን በሚመለከት ስማርት አግሪካልቸር ወይም ደግሞ እያንዳንዱ ሰው ከኑሮ ውድነት ጋር ያሉ ነገሮችን በራሱ ግቢ አልምቶ መሙላት ባይችልም ቢያንስ አትክልትና የተወሰኑ ፍራፍሬዎችን ባለው አነስተኛ ግቢ በመሥራት ተጠቃሚ ለማድረግ ሥራዎችን እየሠራን ነው፡፡ ቢያንስ በሌሎች አካባቢዎች ያለውን ጫና መቀነስ ይችላል በሚል ታሳቢ ተደርጎ ባለፉት ዓመታት የተለያዩ ተግባራትም ተከናውነዋል፡፡

ከአንድ ሺ ሔክታር በላይ መሬት በሚጠጉ ቦታዎች ላይ በተለያዩ ቁሳቁስ የአትክልት ሥራዎችን የማልማት ሥራ ተሠርቷል፡፡ እንዴት በማምረት ምርታማ እንደሚሆኑም ግንዛቤ በመሰጠቱ ውጤት እየተገኘበት ያለ ተግባር ሆኗል፡፡ ይህን አጠናክረን እንቀጥላለን፤ ይህ የተመራው በንቅናቄ ነው፡፡ ይህን ሥራ እንደ ሃዋሳ ከተማ ብቻ ሳይሆን በተለያዩ የክልሉ ትንንሽ ከተሞች ላይ ሁሉ በማካተት እየሠራን ነው፡፡

አዲስ ዘመን፡- ለሰጡን መረጃ ከልብ አመሰግናለሁ፡፡

አቶ መምሩ፡– እኔም አመሰግናለሁ፡፡

አስቴር ኤልያስ

አዲስ ዘመን   ሐምሌ 13/2015

Recommended For You

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *