የዘገባ ሽፋን በመንፈግ የኢትዮጵያን ስኬቶች ማደብዘዝ አይቻልም!

 መገናኛ ብዙኃን መረጃ በመሰብሰብ፣ በማደራጀት እና በተለያዩ መንገዶች በማሰራጨት፤ በመረጃ የበለጸገች ዓለም እና ማኅበረሰብ ለመፍጠር ከፍ ያለ ኃላፊነት የተጣለባቸው ናቸው፡፡ ይህንን ኃላፊነታቸውን ለመወጣት ከሁሉም በላይ ለሙያው ሥነምግባር የመገዛታቸው እውነታ ትልቅ ስፍራ የሚሰጠው ነው።

በተለይም በተለምዶ ዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙኃን በመባል የሚታወቁት የምዕራቡ ሀገራት የመገናኛ ብዙኃን፣ ከመጡባቸው ረጅም ዓመታት ተሞክሮ፣ ለጋዜጠኝነት ሙያ ካበረከቷቸው አስተዋፅዖዎች አንጻር በብዙዎች ዘንድ ትልቅ ከበሬታና ታማኝነት አትርፈዋል፤ ተመራጭነትንም አግኝተዋል፡፡

ከሙያ ነጻነት /የፕሬስ ነጻነት/ ጋር በቀደሙት ዘመናት ከነበራቸው የጎላ ታሪክ፤ ከሁሉም በላይ ደግሞ ራሳቸውም የነፃነቱ ሐዋርያ አድርገው በስፋት ከመስበካቸውጋር በተያያዘ በፈጠሩት ታማኝነት ለመረጃ ምንጭነት ተፈላጊም ሆነዋል። ከዚህ የተነሳም በዓለም አቀፍ ደረጃ በመረጃ ስርጭት ውስጥ ሊፈጥሩ የሚችሉት አሉታዊ ሆነ አዎንታዊ ተፅዕኖ ከፍ ያለ እንደሆነ ይታመናል።

መገናኛ ብዙኃኑ በቀደሙት ዘመናት ታሪካቸው ለዓለም አቀፉ ኅብረተሰብ መረጃዎችን በመዘገብ የተሻለ ስምና ዝና የማትረፋቸውን ያህል፤ ዛሬ ላይ ተለዋዋጭ በሆነው አሁናዊው ዓለም ከሚሰብኩት የሙያ ሥነ ምግባር ባፈነገጠ መንገድ ሲንቀሳቀሱ ማየት የተለመደ ሆኗል፡፡ በዚህም በተለያዩ ሀገራት እና ሕዝቦች ላይ ያልተገቡ ጫናዎችን በግልጽም፤ በስውርም ሲፈጥሩ ይስተዋላል።

በተለይም የምዕራቡን ዓለም ሀገራት መንግሥታት ፍላጎት ለማስፈጸም የሚሄዱባቸው ያልተገቡ መንገዶች፤ በየጊዜው በነበራቸው ዓለም አቀፍ ተቀባይነት ላይ ጥላ እንዲያጠላ አድርጎታል። የተቀሩት የዓለም ሀገራት ዘመኑን የሚዋጅ አማራጭ የመገናኛ ብዙኃን እንዲያማትሩም እያስገደዳቸው ይገኛል።

በብዙ ፍላጎቶች በተሞላች የዛሬዪቱ ዓለም፤ ነፃ ስለሆኑ የመገናኛ ብዙኃን በድፍረት ማውራትም ሆነ መስበክ፤ ከዚያም አልፎ በስብከቱ ታምኖ መመላለስ የዋህነት ነው፡፡ ከዚያም በላይ የዋህነት ሊያስከፍል የሚችለውን ያልተገባ ዋጋ ለመክፈል ራስን ከማዘጋጀት ያለፈ ትርጉም የሚሰጠው አይደለም።

ለዚህ ደግሞ እነዚህ የመገናኛ ብዙኃን ባለፉት አራትና አምስት ዓመታት ስለሀገራችን /ኢትዮጵያ/ በዓለም አቀፍ መድረኮች ሲያስተጋቧቸው የነበሩ የተዛቡ ድምፆችን፤ ድምፆቹ የተገዙባቸውን ግልጽና ስውር ፍላጎቶች ማጤን ተገቢ ነው። ስለ ሀገሪቱ የነበረውንና ያለውን እውነተኛ ገጽታ ለማጠልሸት የሄዱበትን ርቀት ማየት መልካም ነው።

ሀገርን እንደ ሀገር የማጽናት ፈታኝ ወቅት ውስጥ በነበርንበት በዚያ አስቸጋሪ ወቅት ፍጹም ተዓማኒነት የሌላቸው፤ የሙያውን ሥነምግባር ታሳቢ ያላደረጉ የተዛቡ ዘገባዎችን በመሥራትና በማሰራጨት ዓለም አቀፉ ኅብረተሰብ በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ የጠራ መረጃ እንዳይኖረው በስፋት ሠርተዋል።

ከዚህም ባለፈ አስቸጋሪ ወቅቶች ጨምሮ በሀገሪቱ እየተመዘገቡ ያሉ ኢኮኖሚያዊ ስኬቶችን የማሳነስ ዘመቻዎችን ሲያካሄዱ፤ ስኬቶቹ ዓለም አቀፍ እውቅና እንዳያገኙ በስፋት ተንቀሳቀስዋል። በዚህም ሀገርና ሕዝብን ብዙ ያልተገቡ ዋጋዎችን አስከፍለዋል።

ሌላው ቀርቶ በዓለም አቀፍ ደረጃ በምግብ ሰብል ራሳችን ለመቻል የምናደርገውን ሀገራዊ ጥረት፤ በተለይም በስንዴ ልማት ዘርፍ ያስመዘገብነውን፤ ለብዙዎች ተሞክሮ ሊሆን የሚችለውን ስኬት ለማሳነስ ፈጥረውት የነበረው ያልተገባ ትርክት የሚረሳ አይደለም ።

ከዚህም በላይ ዓለም በከፋ የአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት የተጋረጠባትን ስጋት እና አደጋ ውስጥ ባለችበት በዚህ ወቅት እንደ ሀገር የጀመርነው የአረንጓዴ አሻራ /ሀገርን አረንጓዴ የማልበስ ንቅናቄ/ እና ደማቅ የስኬት ታሪኮች በቂ ዓለም አቀፍ እውቅና እንዳያገኝ የዘገባ ሽፋን ከመንፈግ ጀምሮ እየሄዱበት ያለው የተሳሳተ መንገድ በሕዝባችን ዘንድ ትዝብትን የፈጠረ ነው።

ይህ የመገናኛ ብዙኃኑ ያልተገባ አካሄድ አንድም ለሙያው የነበራቸውን ከበሬታ/ታማኝነት ጥያቄ ውስጥ የከተተ፤ ከዚያም ባለፈ ዜጎች ለመገናኛ ብዙኃኑ የነበራቸውን ከበሬታና ታማኝነት በአደባባይ ያሳነሰ፤ አማራጭ ታማኝ የመረጃ ምንጮችን እንዲያማትሩ የሚያስገድድ ነው!

አዲስ ዘመን   ሐምሌ 13/2015

Recommended For You

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *