በክረምቱ በረከት – አረንጓዴ ዐሻራን

እነሆ ! ዘንድሮም ክረምቱ ባለ ቃል ሆኗል፡፡ መምጫ ቀጠሮውን አልሳተም ፣ መድረሻ ጊዜውን አልረሳም ።ጥቂት ጊዜያት ቀድሞ ከሰዓቱ ፈጥኖ ቢታይም ፤ ከተጠበቀው ወር ተራው አልዘገየም። ቀድሞ በመምጣቱ ፣ ፈጥኖ በመታየቱ ጊዜውን አልተወም ፡፡

የዘንድሮውም ሰኔ የባተው ከዝናቡ በረከት ጋር ነው። ከእርጥበቱ ሳያጎድል፣ ከልምላሜው ሳያሳንስ ጊዜውን አጠናቆ በክብር ተሰናብቶናል። በሰኔ የብርቱ ገበሬ ጉልበት ይፈተናል።የልፋት ድካሙ ውጤት ይታያል። የክረምቱን ዝናብ፣ የወቅቱን በረከት የሚሹት ሁሉ በዚህ ወቅት ተደላድለው አይተኙም። ጊዜውን በወጉ ይጠቀሙታል፡፡ ለቁምነገር ያውሉታል፡፡

በክረምት የምድር ተፈጥሮ አይነጥፍም። ወንዞች ይሞላሉ፣ ዙሪያ ገባው ይለመልማል ። ጠብታን የተጠሙ፣ በሀሩር የከረሙ ስፍራዎች በዝናብ ውሀ ይረሰርሳሉ። በጋው ለክረምቱ ስፍራውን በለለቀ ጊዜ የተፈጥሮ በረከት በእግሩ ይገባል። አረንጓዴ ምድር ቦታውን ይረከባል። ይህኔ ልባም የሆነ ትውልድ አካባቢውን ማሰቡ አይ ቀርም ።ስለነገው መኖር ዛሬን በማቀድ ችግኞችን ይተክላል፡፡

ችግኞችን መትከል ስለነገ ማንነት ማሰብ ነው። ዛሬ ላይ ያቆየነው ጥሪት ከዘመናት በኋላ መልካም ፍሬውን ያቅመናልና። ዛሬ ዓለማችን ከምትፈተንባቸው የተፈጥሮ አደጋዎች አንዱ የጎርፍ መጥለቅለቅ ክስተቶች ናቸው። እንዲህ ለመሆኑ ዋንኛ ምክንያቱ መሬት በአግባቡ በዕፅዋት ያለመ ሸፈኗ በየጊዜው ደኖች የመጨፍጨፋቸው እውነታ ነው፡፡

የአየር ንብረት ቀውስ ሌላው የዓለማችን መከራ ሆኖ በርካታ ሀገራት እየተፈተኑበት ነው። ቋሚ ባልሆነ የአየር ንብረት መለዋወጥ ሚሊዮኖች ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል። ሀገር ጥለው ተሰደዋል፡፡ በአሁኑ ጊዜ የሰው ልጆች ሊቋቋሙት በማይቻላቸው ከመጠን ባለፈ ሙቀት፣ በከፍተኛ የበረዶ ክምርና ቅዝቃዜ ፣ እየተፈተኑ ነው፡፡

በአሁኑ ጊዜ በርካታ ስፍራዎች ወደ በረሀማነት በመቀየር ላይ ናቸው፡፡ ሙቀቱን ተከትሎ የሚነሳው የሰደድ እሳትም ደኖችን ያወድማል፡፡ በውስጡ የሚገኙ አራዊቶችን ለሞትና ስደት ይዳርጋል። በየጊዜው ድርቅ የሚከሰትበት የዓለም ክፍል ለሰው ልጆች በሕይወት መኖር ፈታኝ መሆኑን ይዟል።ከዚህ በተቃራኒም በአንዳንድ የዓለማችን ስፍራዎች ከፍተኛ የሚባል የዝናብ መጠን እያጋጠመ ነው፡፡

የሰው ልጅ ለኑሮው የሚጠቀማቸው የከሰል ፣ ጋዝና እንጨት ምርቶች የራሱን እስትንፋስ ለመመረዝ የፈጠኑ ናቸው። እነዚህ ጭስ ወለድ ግብአቶች የጥቅማቸውን ያህል አካባቢን በመ በከል፣ ጤናን በማወክ የሚያስከትሉት ጫና ቀላል አይደለም፡፡

እነዚህ ኃይል አመንጪ ንጥረ ነገሮች በሚለቁት ጋዝ የሚያስከትሉት ጉዳት በዚህ ብቻ አይገታም። ከተፈጥሮ ፀሐይ የሚመጣውን ብርሃን አምቆ በመያዝ የፕላኔታችንን የሙቀት መጠን እንዲጨምር ያደርጋሉ፡፡

በየጊዜው የሚያይለው የዓለም ሙቀት መጠን ለውቅያኖሶች መጠን መቀነስና ፣ ለግግር በረዶዎች መቅለጥ ምክንያት ይሆናል፡፡ ኃይለኛ ሙቀትና ከባድ ቅዝቃዜ ለሰውልጆችም ሆነ ለእንስሳ እጅግ ፈታኝ የሚባል ነው፡፡

መረጃዎች እንደሚጠቁሙት የዓለማችን የሙቀት መጠን 1 ነጥብ ሴልሺዬስ ላይ መቆየት ካልቻለ ድፍን አውሮፓ በከባድ ጎርፍ የመጥለቅለቅ ዕድሏ የሰፋ ነው።የመካከለኛው ምሥራቅ ሀገራትም ከፍተኛ የሚባለው የሙቀት መጠን ስለሚያገኛቸው የእርሻ ቦታዎቻቸው ወደበረሀማነት ይቀየራል።የውቅያኖሶች መጠን ሲጨምር በፓስፊክ ስር የሚገኙ ደሴቶች በማዕበል ሊዋጡ የግድ ይሆናል፡፡

በዚህ ወቅት በርካታ የሚባሉ የአፍሪካ ሀገራት በከፋ ድርቅ ይቀጣሉ፡፡ ከፍተኛ የሚባል የምግብ እጥረትና ርሀብም ሊጎበኛቸው ይችላል፡፡ ምዕራባዊው የአፍሪካ ክፍል ድርቅ ሲያገኘው የተቀረው ክፍል ደግሞ ነጎድጓድ ባጀበው ከባድ ዝናብ የመመታት ዕድሉ ከፍተኛ ነው፡፡

የአካባቢን ብክለት ጨምሮ አሳሳቢውን የዓለም ሙቀት መጠን መቀነስ ለሰው ልጆች ህልውና በእጅጉ አስፈላጊ ነው።ይህ ይሆን ዘንድም ምድር በአረንጓዴ ተክሎችና በተፈጥሮ ደን ልትሸፈን የግድ ይላል፡፡

በተለያዩ ጊዜያት በሚደረጉ ዓለምአቀፍ ጉባኤዎች የአየር ንብረት ለውጥ ትኩረት የሚሰጥበት አጀንዳ ሆኖ ቆይቷል።የካርበን ልቀትን ለመቆጣጠር የሚያስችሉ መርሆች ተነድፈውም የስምምነት ውል ታስሮበታል፡፡

በዩናይትድ ኪንግደም እንደ አውሮፓውያን አቆጣ ጠር በኅዳር 2030 በሚደረገው ጉባኤ የካርበን ልቀትን መቀነስ በሚቻልባቸው ነጥቦች ላይ ጠቃሚ ሀሳብ ይቀረጻል ተብሎ ይጠበቃል። እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2050 በርካታ ሀገራት የካርበን ልቀትን ዜሮ የሚባል ደረጃ ለማድረስ ከስምምነት ደርሰዋል ፡፡

በሀገራችን ወቅቱን ጠብቆ በዘመቻ የሚካሄደው የችግኝ ተከላ መሬት እንዳይሸረሸር ፣ የአካባቢ ልማት እንዲጠበቅና የጎርፍ አደጋዎች እንዳይከሰቱ የሚያበረክተው ድርሻ የጎላ ነው፡፡ ችግኝን ከመትከል ባለፈ የመንከባከቡ ጉዳይ ትኩረት የሚያሻው ሆኖ ይህ ጠንካራ ተሞክሮ ለሀገራችን መልካም የሚባል በረከትን እያተረፈ ይገኛል፡፡

እስከዛሬ በሀገራችን በነበረው የችግኝ መትከል እንቅስቃሴ ውጤታማ የሚባል ተግባራት ተከናውኗል። በርካታ ደረቅ ስፍራዎች አረንጓዴ ለብሰው በዛፎች ተሸፍነዋል፡፡ ይህን ውጤት ተከትሎም የብዝሀ ሕይወት ገጽታ ጤናማ ሆኖ እንዲቀጥል ምክንያት ሆኗል፡፡ የጠፉ፣ የደረቁ ምንጮች እንደአዲስ ፈልቀዋል፡፡ በርሀ የነበሩ አካባቢዎች በአረንጓዴ ምድር ተተክተዋል።ችግኝ በመትከል፣ ዛፍ በማሳደግ የአየር ንብረትን ለመጠበቅ ተችሏል፡፡

ከችግኝ መትከልና አረንጓዴ ዐሻራ ጋር ተያይዞ ሰሞኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በመጪዎቹ ሦስት ዓመታት የሚኖረውን የመዲናዋን የአረንጓዴ ሽፋን ዕቅድ ይፋ አድርጓል፡፡ በከተማዋ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ይፋ የሆነው ይህ ዕቅድ ቀድሞ የነበረውን የአስራአምስት በመቶ የአረንጓዴ ሽፋን ወደ ሰላሳ በመቶ ለማሳደግ በትኩረት የሚሠራ ነው።ከንቲባዋ በመግለጫቸው እንደጠቆሙት በነዚህ ዓመታት በመዲናዋ በሚኖረው የአረንጓዴ ልማት እንቅስቃሴ በርከታ ተግባራት ይከወናሉ፡፡

እንደከንቲባዋ ገለፃ የከተማዋን አረንጓዴ ሽፋን ከነበረበት 2 ነጥብ 8 በመቶ ወደ 15 በመቶ ከፍ በማድረግ ተመዝግቧል፡፡ ባለፉት አራት ዓመታት የነበ ረውን ታሪክ ለመቀየርም ዘንድሮ 17 ሚሊዮን ችግኞችን በመትከል በሚቀጥሉት ሦስት ዓመታት የከተማዋን የችግኝ ሽፋን 50 ሚሊዮን የማድረስ ዕቅድ ተይዟል፡፡

በዚህም የመዲናዋን የአረንጓዴ ልማት ከአስራ አምስት በመቶ ወደ 30 በመቶ ከፍ ለማድረግ በትኩረት የሚሠራ ይሆናል፡፡ በሁለተኛው ምዕራፍ የአረንጓዴ ዐሻራ የሀገር በቀል ዛፎችን ጨምሮ ለምግብነትና ለውበት አገልግሎት የሚውሉ ችግኞች የሚተከሉ መሆኑን ከንቲባዋ በመግለጫቸው አክለው ገልጸዋል፡፡

ሀገራችንን አረንጓዴ በማድረግ የተሰጠንን ድንቅ የተፈጥሮ ሀብት በወጉ መጠቀም ከቻልን ድህነትን በመዋጋት ታሪካችንን መቀየር ይቻለናል፡፡ ክረምቱን ብቻ ጠብቀን የምንተክለውን የችግኝ ዛፍ በአግባቡ ጠብቀን ከያዝነው ቆይቶ ለራሳችን ይከፍለናል፡፡

 መልካምሥራ አፈወርቅ

አዲስ ዘመን   ሐምሌ 2/2015

Recommended For You

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *