ኢትዮጵያ በቱሪዝም ሀብትነት የምትጠቀማቸው በርካታ ታሪካዊ ቅርሶች፣ ታሪካዊ ቦታዎች፣ ጥብቅ የማኅበረሰብ ሥፍራዎች፣ ብርቅዬ የዱር እንስሳት እና የማይዳሰሱ ደማቅ የማኅበረሰብ በዓላት ያሏት ሀገር ናት። እነዚህን ሀብቶች ለመጎብኘት ከተለያዩ የዓለም ሀገራት ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡ ቱሪስቶች ከሚያስገኙት የውጭ ምንዛሬ በተጨማሪ፣ ለበርካቶች የሥራ ዕድል መፍጠር የሚያስችሉ ናቸው።
ሀገሪቱ ካላት እምቅ የቱሪዝም አቅምና መዳረሻዎች አንፃር እያገኘችው ያለው ጥቅም እጅግ አነስተኛ መሆኑ ግን ድብቅ አይደለም። ለዚህ ደግሞ አንዱና ትልቁ ችግር በቱሪስት መዳረሻ ስፍራዎች ያሉ የመሠረተ ልማትና ደረጃቸውን የጠበቁ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት እጥረቶች ናቸው።
መንግሥት ነባራዊ ሁኔታውን ለመቀየርና ዘርፉ በኢኮኖሚው ውስጥ ተገቢውን ድርሻ እንዲይዝ አስቻይ የሪፎርም ሥራዎችን እያከናወነ ይገኛል። ለዘርፉ ዕድገት ምቹ መደላድል ለመፍጠር ፖሊሲዎችንና የሕግ ማዕቀፎችን ከማሻሻል ባለፈ ቱሪዝምን ከማኅበራዊ ዘርፍ ወደ ኢኮኖሚ ዘርፍ ማሸጋገር እየቻለ ነው።
ሀገሪቱ አሁን ላይ ተግባራዊ እያደረገች በምትገኘው የ10 ዓመት የልማት ዕቅድ (2013-2022) ውስጥ ከተቀመጡት ሰባት ዘርፎች ቱሪዝም አንዱ መሆኑ ይታወሳል። በዕቅዱም የቱሪስት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ብዛት በ2012 በጀት ዓመት ከነበረበት አንድ ሺህ 348፣ በ2022 ወደ ሁለት ሺህ 696፣ እንዲሁም በዚሁ ጊዜ የጎብኝዎችን እርካታ መጠን ከ50 በመቶ ወደ 75 በመቶ ለማሳደግ ግብ ተይዟል።
እነዚህን ዕቅዶች ተግባራዊ በማድረግ በተደራራቢ ችግሮች እየተፈተነ የሚገኘውን የኢትዮጵያ ቱሪዝም ከገጠመው ችግር እንዲወጣ አስቸኳይ የማገገሚያ ሥራዎችን መሥራት እንደሚገባ ግልጽ ነው። ይህንን ታሳቢ በማድረግም በአሁኑ ወቅት በመንግሥት እየተከናወኑ ያሉ ሰፋፊ የመሠረተ ልማት ፕሮጀክቶች የቱሪዝም ሀብቶችን ማዕከል ያደረጉና ለዘርፉ ዕድገት መሠረት እየጣሉ እንደሚገኙ በርካታ ማሳያዎች አሉ።
ለዚህ ደግሞ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የተጀመሩ እንደ ገበታ ለሀገር ፤ ገበታ ለሸገር፤ ገበታ ለትውልድ ዓይነት ኢኒሼቲቮችና በርካታ ፕሮጀክቶች ዓይነተኛ ሚና እንደሚጫወቱ ይታመናል። እነዚህ ፕሮጀክቶች ሲጀመሩ ሀገር በርካታ ችግሮች እያሉባት በዚህ ወቅት ሊተገበር አይገባም ወይም ቅድሚያ ሊሰጣቸው የሚገቡ ጉዳዮች አሉ የሚሉ ውዥንብሮች በርክተው ነበር። እነዚህ ትልልቅ ፕሮጀክቶች በርካቶቹ ከመጠናቀቃቸው ጋር ተያይዞ በቱሪዝም ዘርፉ ላይ ምንያህል ለውጥ እንዳመጡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ሰሞኑን የሕዝብ ተወካዮች ምክርቤት ቀርበው በሰጡት ማብራሪያ አስረድተዋል።
እውነት ነው ኢትዮጵያ ብዙ ቀዳዳ አለባት፣ በትኩረት ሊሠራባቸው የሚገቡ አያሌ ወቅታዊ ችግሮችም አሉ። ያ ግን ለቱሪዝም ዘርፉ ሞተር የሆኑ መሰል ፕሮጀክቶችን እየገነባች ከመሄድ ሊያግዳት አይገባም። የአንድ ሀገር ልማትና እድገት ‹‹አንዱን ጥሎ ሌላውን አንጠልጥሎ›› ሊሆን አይችልም። ሁሉንም አቅም በፈቀደ መጠን አቻችሎ መጓዝ ያስፈልጋል።
ዛሬ ላይ በዓለም እጅግ ተመራጭ የቱሪስት መዳረሻ የሆኑት ዱባይን የመሳሰሉ ሀገራት ቱሪዝም የመጪው ዘመን የኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት መሆኑን ቀደም ብለው በመገንዘብ ሙሉ ትኩረታቸውን ወደዚያው ማዞራቸው ይታወቃል። እነሳውዲ አረቢያም ቢሆኑ ተመሳሳይ መንገድ ጀምረዋል። ኢትዮጵያም ከነዚህ ሀገራት የተሻሉ የተፈጥሮ ሀብቶችን አጉልታ ለማሳየት አንድና ሁለት ሳይሆን በሺዎች የሚቆጠሩ ፕሮጀክቶችን አቅዳ መተግበር አለባት።
ቱሪዝም ለሀገር ኢኮኖሚ ብቻ ሳይሆን በሥራ ዕድል ፈጠራ ላይ ለሚሊዮኖች እንጀራ የሚፈጥር ዘርፍ ከመሆን ባለፈ፤ የአድናቆት ገበያ መሆኑን በመገንዘብ የኢትዮጵያን ቱሪዝም ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት የሚያሳድጉ እንደነ ኮይሻ፣ ሃላላ ኬላ፣ ወንጪ፣ ጎርጎራና ዓይነት ሌሎች ትልልቅ ፕሮጀክቶች ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል። ወደትግበራ እየገባ ያለው ገበታ ለትውልድ ፕሮጀክትም በሁሉም ወገን ድጋፍና ርብርብ ለስኬት ሊበቃ ይገባዋል።
ለዚህ ደግሞ ባለሀብቱ ያሳየውን ተነሳሽነት ከማሳደግ ጎን ለጎን ዲያስፖራውም ልክ እንደ ዓባይ ግድብ ዐሻራውን የሚያሳርፍበት ዕድል ሊመቻች ይገባል። ሕዝቡም የእነዚህን ፕሮጀክቶች ዘላቂ ጥቅም በአግባቡ በመረዳት ድጋፉን አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል!
አዲስ ዘመን ሐምሌ 2/2015