ከ2008 እስከ 2012 ዓ.ም ኢኮኖሚው በአማካይ በየዓመቱ 11 ነጥብ 1 በመቶ ያድጋል የሚለውን ታሳቢ በማድረግ ዕቅድ ተዘጋጅቷል። ግቡም ሁሉም የኢኮኖሚ ዘርፎች የሚያስመዘግቡት ፈጣን ዕድገትን ግምት ውስጥ ያስገባ እንደነበር የፕላንና ልማት ኮሚሽን የ2010 በጀት ዓመት የእቅድ ግምገማ ሪፖርት ያመለክታል። ሆኖም በ2010 ዓ.ም የበጀት ዓመት የተመዘገበው የኢኮኖሚ ዕድገት 7 ነጥብ 7 በመቶ ብቻ ነው፡፡
ለእዚህ የኢኮኖሚ ዕድገት ማነስ ምክንያቱ ከጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት 19 ነጥብ 4 በመቶ ድርሻ ይኖረዋል ተብሎ የተተነበየው የኢንዱስትሪው ክፍለ-ኢኮኖሚ ተጨማሪ ዕሴት በ12 ነጥብ 2 በመቶ ብቻ በማደጉ በበጀት ዓመቱ ለተመዘገበው የ7 ነጥብ 7 በመቶ የኢኮኖሚ ዕድገት የ3 ነጥብ 1 መቶኛ ብቻ አስተዋጽኦ ማበርከቱ አንደኛው ምክንያት መሆኑን ታህሳስ 2011 ዓ.ም ላይ የፕላንና ልማት ኮሚሽኑ ይፋ ያደረገው ሪፖርት ያመለክታል፡፡
የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ዘርፉ በበጀት ዓመቱ ያስመዘገበው የ5 ነጥብ 5 በመቶ ዕድገትም፤ ዘርፉ ያስመዝግባል ተብሎ ከተጠበቀው የ22 በመቶ ዕድገት እና በ2009 በጀት ዓመት ካደገበት የ24 ነጥብ 7 በመቶ ተጨማሪ እሴት ዕድገት ጋር ሲነጻጸር ያነሰ አፈጻጸም የታየበት እንደነበር በሪፖርቱ ተገልጿል፡፡
በበጀት ዓመቱ ይጠበቅ ለነበረው የ11 ነጥብ 1 በመቶ ጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት ዕድገት የ1 ነጥብ 3 መቶኛ አስተዋፅኦ እንደሚያበረክት ግብ ተቀምጦ የነበር ቢሆንም፤ በበጀት ዓመቱ ለተመዘገበው ጠቅላላ የአገር ውስጥ ዕድገት የነበረው አስተዋጽኦ የ0 ነጥብ 4 መቶኛ ብቻ ሆኖ መገኘቱ ለዕድገቱ መቀነስ አስተዋፅኦ እንዳለው ተቀምጧል፡፡
የተመዘገበው የ7 ነጥብ 7 በመቶ የጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት ዕድገት በበጀት ዓመቱ ይመዘገባል ተብሎ ከተቀመጠው የ11 ነጥብ 1 በመቶ አማካይ የኢኮኖሚ ዕድገት ግብ
ጋር ሲነፃፀር፤ የ3 ነጥብ 4 በመቶኛ ነጥብ ቅናሽ አሳይቷል፡፡ ለእዚህም በመነሻነት የቀረበው በበጀት ዓመቱ በአብዛኛው የአገሪቱ ክፍሎች ተከስቶ ከነበረው ፖለቲካዊ አለመረጋጋት ጋር ተያይዞ በአጠቃላይ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ አሳድሯል የሚለው ጉዳይም ተጠቃሽ ነው፡፡
በተጨማሪም በበጀት ዓመቱ የተመዘገበው ከዕቅድ በታች የሆነ የወጪ ንግድ ገቢ አፈጻጸም ከገቢ ንግድ ወጪ በእጅጉ ያነሰ መሆን ጋር ተያይዞ የአገሪቱ የውጭ ምንዛሪ የማፍራት አቅም ውስን መሆን ሌላው በአገሪቷ የኢኮኖሚ ዕድገት መቀነስ ላይ የራሱን አሉታዊ ሚና ተጫውቷል። ይህ በተጨማሪ የአገሪቱን አጠቃላይ የውጭ ምንዛሪ አቅርቦት ከአጠቃላይ ፍላጎት ጋር ያልተመጣጠነ እንዲሆን አድርጎታል፡፡
በተመሳሳይ በበጀት ዓመቱ የተመዘገበው የታክስ ገቢ አፈጻጸም በተለይም አጠቃላይ አገራዊ የታክስ ገቢ ከጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት ያለው ድርሻ ከበጀት ዓመቱ ዕቅድም ሆነ ካለፉት ዓመታት አፈጻጸም አኳያ ሲታይ ደካማ ነው፡፡ ይህም በበጀት ዓመቱ የተቀመጡ የልማት ፕሮጀክቶችን በበቂ ሁኔታ ፋይናንስ ከማድረግ አኳያ ትልቅ ክፍተት የፈጠረ መሆኑንም ሪፖርቱ ያመላክታል፡፡
የፕላንና ልማት ኮርፖሬት ኮሙኒኬሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተሩ አቶ ዘላለም ብርሃኔ እንደሚገልጹት ደግሞ ፤ ኢትዮጵያ ባለፉት 27 ዓመታት አገራዊ የመካከለኛ ዘመን የልማት ዕቅዶችን በረጅም ዘመን ዕይታ የሚመሩበት ማዕቀፍ አልነበረም። ይህም ባለፉት ዓመታት ተግባራዊ የሆኑ አገራዊ የመካከለኛ ዘመን የልማት ዕቅዶች ውጤታማነት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ አሳድሯል፡፡
ከዚህ ጋር ተያይዞ በኢኮኖሚው ውስጥ ያለው የአቅርቦትና የፍላጎት አለመጣጣም ተከስቷል። በተጨማሪም የኢኮኖሚ ዕድገትና መዋቅራዊ ለውጥ ሂደትን በረጅም ጊዜ ዕይታ በአግባቡ መምራት አለመቻልና የልማት ኃይሎችን በማቀናጀት በተመረጡ የልማት ዘርፎች ላይ ያለማሰማራት ችግሮች ተስተውሏል፡፡
የፕላንና ልማት ኮሚሽን እነዚህንችግሮች በዘላቂነት ለመፍታት የሚያስችል አገራዊ የአስር ዓመት መሪ የልማት ዕቅድ በማዘጋጀት ላይ ይገኛል። ዕቅዱ በዋናነት የኢኮኖሚና ማህበራዊ ጉዳዮችን በጥቅል የሚያመላክት ሲሆን፤ በተለይም ዋና ዋና የማክሮ ኢኮኖሚ ጉዳዮች፣ የአምራች ዘርፎች፣ የኢኮኖሚ መሠረተ ልማት፣የከተማ ልማትና ቤቶች፣ የሥነ-ሕዝብና ልማት፣ የሰው ሀብት ልማት እና ሌሎች ቁልፍ ጉዳዮች በዝርዝር የሚቃኙበት እንደሚሆን ገልፀዋል፡፡
ከዚህ አኳያ ኮሚሽኑ ባለፉት ጊዜያት ለአስር ዓመት መሪ የልማት ፕላን ዝግጅት መነሻ ግብዓት የሚሆኑ በማክሮ ኢኮኖሚ ማዕቀፍ፣ በኢንዱስትሪ ልማት፣ በግብርና ትራንስፎርሜሽን፣ በሠው ሀብት ልማት፣ በኢነርጂ መሠረተ ልማት፣ በትራንስፖርት መሠረተ ልማትና አገልግሎት፣ በከተማ ልማትና ቤቶች፣ በሥነ- ሕዝብና ልማት፣ በውሀ ሀብት ልማት እና በግሉ ዘርፍ ልማት ዙሪያ የሚመለከታቸውን ባለድርሻ አካላት በማስተባበር ጥናቶችን እንዳከናወነ ይገልፃሉ፡፡
በቀጣይ የአስር ዓመት የልማት መሪ ፕላን ዝግጅት ሂደቱ ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል ማለትም የግል ባለሀብቱን፣ የሲቪክ ማህበራት፣ አርሶ/አርብቶ አደሮችን፣ ሴቶችን እና የተለያዩ የሕብረተሰብ ተወካዮችን ባሳተፈ መልኩ የሚዘጋጅ ይሆናል ይላሉ፡፡ ከዚህ አንጻር የመሪ ፕላኑ ዝግጅት አካሄድ በዋናነት ከታች ወደ ላይ ነው፡፡
ይህም ማለት ሁሉም የመንግስት አስፈጻሚ ተቋማት በሚመለከታቸው ዘርፎች ከታችኛው የህብረተሠብ ክፍል አንስቶ የአስር ዓመት የመሪ ፕላን ዕቅድ የሚያዘጋጁ ሲሆን፤ ፕላኑ ሁሉም የአገሪቱ ዜጎች የባለቤትነት ስሜት እንዲኖራቸውና ዜጋው ዕቅዱን በአግባቡ አውቆ የቅርብ ክትትል የሚያደርግበት እንዲሆን ከፍተኛ ዕገዛ እንደሚኖረውም ነው የገለፁት፡፡ ይህም ባለፉት ዓመታት ይዘጋጁ ከነበሩት የመካከለኛ ዘመን የልማት ዕቅዶች የተለየ እንዲሆን ያደርገዋል፡፡ በአጠቃላይ የአስር ዓመት የልማት መሪ ፕላኑ በቀጣይ ዓመት ሰኔ ወር ላይ የሚጠናቀቅ እንደሚሆንም ነው የሚናገሩት፡፡
ጨምረውም በአገሪቷ ከዚህ ቀደም በልማት ዕቅድ አፈጻጸም ዙሪያ ግልፅ የሆነ እና ተጠያቂነትን ሊያሰፍን የሚችል የአሰራር ሥርዓት አልነበረም። ይህም ባለፉት ዓመታት በልማት ዕቅድ አፈጻጸም ዙሪያ ለተመዘገቡ ጉድለቶች ዋነኛ ምክንያት ሆኗል፡፡ በተጨማሪ በክትትልና ግምገማ ዙሪያ የመረጃ አስተዳደር ሥርዓት ደካማ መሆን፣ የአቅም ውስንነት መኖር፣ ወጥ፣ የተቀናጀና ተመጋጋቢ የክትትልና ግምገማ አሠራር አለመኖር ዋና ዋና ምክንያቶች እንደነበሩ ይጠቅሳሉ፡፡
አገራዊ የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ አፈፃፀም የሚኒስትሮች ምክር ቤት የክትትልና ግምገማ መመሪያ በጥቅምት 24 ቀን 2010 ዓ.ም መፅደቁ ይታወቃል። ከዚህ አኳያ የፕላንና ልማት ኮሚሽን ከላይ የተጠቀሱትን ተግዳሮቶች በዘላቂነት ለመፍታት የክትትልና ግምገማ መመሪያውን ተግባራዊ ለማድረግ የሚያግዙ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን በማከናወን ላይ እንደሚገኝም ነው የገለፁት፡፡
የክትትልና ግምገማ መመሪያውን ተግባራዊ ለማድረግ የተለያዩ ማንዋሎች እየተዘጋጁ መሆናቸውን ጠቁመው፤ በተጨማሪ የመንግስት አስፈጻሚ ተቋማትን ተጠያቂ ለማድረግ የሚያስችል አሠራር ለመዘርጋት ቁልፍ የውጤት መስኮች እና ቁልፍ የውጤት አመልካቾች በማዘጋጀት ላይ ይገኛል፡፡ እነዚህን አመልካቾች በመምረጥ ሂደት ውስጥ ከሁሉም የመንግስት አስፈጻሚ ተቋማት ጋር የሚደረግ ተከታታይ ውይይትና ስምምነት ይካሄል፡፡ በዚህም ሁሉም የመንግስት አስፈጻሚ ተቋማት በቀጣይ የሚገመገሙበትና ተጠያቂነት የሚሰፍንበት አሠራር ይኖራል፡፡
በተጨማሪ ልማዳዊ ከሆነው በአብዛኛው ተግባርና ሂደት ላይ ከሚያተኩር የክትትልና ግምገማ አሠራር ሥርዓት ወደ ውጤትና ፋይዳ ላይ የሚያተኩር የክትትልና ግማገማ ሥርዓት ሽግግር ለማድረግ የተለያዩ ሥራዎች በመከናወን ላይ ናቸው። ከዚህ አንጻር በቀጣይ በሁሉም የመንግስት አስፈጻሚ ተቋማት ይህንን የአስተሳሰብ ለውጥ በአገር አቀፍ ደረጃ ለማምጣት በተከታታይ ከአመራሮች እስከ ባለሙያዎች ተሳትፎ የሚደረግበት የሥልጠና እና የውይይት መድረኮች በመዘጋጀት ላይ ናቸው፡፡ ይህም በአጠቃላይ በልማት ዕቅድ ዝግጅት እንዲሁም በክትትልና ግማገማ ዙሪያ ከፍተኛ የሆነ የአፈጻጸም ለውጥን እንደሚያመጣ ይጠበቃልም ነው ያሉት።
አዲስ ዘመን ግንቦት 2/2011
በምህረት ሞገስ