ኢትዮጵያ ከሰሞኑ ‹‹ብሪክስ››ን ለመቀላቀል ይፋዊ ጥያቄ ማቅረቧን የኢፌዴሪ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር መለስ አለም በሳምንታዊ የፕሬስ መግለጫቸው አስታውቀዋል:: ይህንንም ተከትሎ ጉዳዩ የብዙዎችን ትኩረት ስቧል::
‹‹ብሪክስ›› የሚለውን መጠሪያ የያዘው ይህ ምህጻረ ቃል፤ የአባል ሀገራቱን የመጀመሪያውን ፊደል ይዞ የተመሠረተ ሲሆን፣ እነዚህም ሀገራት ብራዚል፣ ሩሲያ፣ ህንድ፣ ቻይና እና ደቡብ አፍሪካ ናቸው:: መረጃዎች እንደሚያመለክቱትም ይህን ስያሜ የሰጡት እ.ኤ.አ በ2001 የጎልድማን ሳክስ የምጣኔ ሀብት ባለሙያው ጂም ኦ’ኔል እንደሆኑ ይነገራል::
በወቅቱ የብራዚል፣ ሩሲያ፣ ህንድ እና ቻይና ኢኮኖሚ ከፍተኛ እምርታ ማሳየቱን ተከትሎ የዓለምን ኢኮኖሚ የሚለውጥ አቅም እንዳለው በመገንዘባቸው በጉዳዩ ላይ ውይይት ማድረግ አስፈላጊ መሆኑ ግንዛቤ የተወሰደበት ነበር::
ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ የባለብዙ መድረኩ ብሪክስ አባል ሀገራት የዓለምን ህዝብ 42 በመቶ እና የዓለምን የሀገር ውስጥ ጥቅል ምርት 31 ከመቶ ይሸፍናሉ:: የብሪክስ ዋናው ግቡ ቀጣይነት ያለው፣ ፍትሃዊ እና ለሁሉም የሚጠቅም እድገትን ለማስፈን በአባል ሀገራቱ መካከል ያለውን ትብብር ማሳደግ፣ ማጠናከር እና ማስፋት እንደሆነም ይነገራል::
ኢትዮጵያ ይፋዊ ጥያቄ ያቀረበችው ይህን ድርጅት ለመቀላቀል ነው:: ኢትዮጵያ የአባልነት ጥያቄዋ ተቀባይነት ለማግኘት ከሌሎች ተመሳሳይ ጥያቄ ካቀረቡ 20 ከሚበልጡ ሀገራት ጋር ጠንካራ ፉክክር ሊገጥማት እንደሚችል ይገመታል:: ኢትዮጵያ ለዓለም አቀፍ ተቋማት በአባልነት እና መስራችነት የረጅም ጊዜ ታሪክ እና ልምድ ስላላትና ይህ ልምዷ በ‹‹ብሪክስ››ም ዘንድ ተፈላጊ ሊያደርጋት እንደሚችል ይታመናል::
ብሪክስ የተቋቋመበት አንዱ ዓላማም ኢኮኖሚዊ ዕድገትን የተመለከተ ሲሆን፣ ኢትዮጵያ፣ ከአፍሪካ በህዝብ ብዛት ሁለተኛ መሆኗ እና ተከታታይ እድገት እያስመዘገበች ያለች መሆኗ የ‹‹ብሪክስ›› አባል ሀገራት ከተሰባሰቡበት ዓላማ ጋር የተሰናሰለ መሆኑ ወደ ብሪክስ ለምታደርገው ጉዞ አቅም እንደሚሆናት ይታመናል::
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአፍሪካ እና እስያ ጥናትና ምርምር ማዕከል መምህሩ ዶክተር ሳሙኤል ተፈራ እንደሚናገሩት፤ ብሪክስ ውስጥ ያሉ ሀገራት የዓለም ኢኮኖሚ ድርሻቸው 31 ነጥብ 7 በመቶ የሚሆነውን ይይዛሉ:: በተቃራኒው የቡድን ሰባት አባል ሀገራት 30 ነጥብ 5 በመቶ ኢኮኖሚ ይዘው ነው ዓለምን በመዘወር ላይ የሚገኙት::
የብሪክስ ሀገራት ከ30 ትሪሊዮን ዶላር በላይ ጂ.ዲ.ፒ (GDP) ያላቸው ናቸው:: ሳውዲ ዓረቢያ፣ የተባበሩት አረብ ኤሚሬትስ፣ ናይጄሪያ፣ ግብፅ ፣ኮሪያ ፣ቱርክ ሁሉ ወደዚህ ህብረት ለመቀላቀል ጥያቄ ያቀረቡ ሀገራት ናቸው::
እርሳቸው እንደሚሉት፤ እነዚህ ሳይጨመሩ ሶስት ቢሊዮን የሚጠጋ የዓለም ህዝብ የሚኖረው በህብረቱ ሀገራት ውስጥ ነው:: በተጨማሪም እነዚህ ቡድኖች በምዕራቡ ዓለም በአይነ ቁራኛ የሚታዩ ሀገራት ናቸው:: በተለይ ‹‹ዓለም በዶላር ከመገበያየት መውጣት አለበት፤ ሌሎች አማራጮች መስፋት አለባቸው›› ብለው የሚያስቡ ናቸው:: በምዕራብ ብቻ የሚመራው የዓለም ሥርዓት እንዲኖር አይፈልጉም:: አዳዲስ ሀገራት ወደፊት እንዳይመጡ መንገድ አይዘጉም:: ባለብዙ አስተዋጽኦ ዓለም እንዲኖር የሚፈቅዱ ናቸው።
የ‹‹ብሪክስ›› ህብረት ውስጥ አንድ ሁለት ተብሎ የተቀመጠ ስምምነት የለም:: የፖለቲካ ፍላጎታቸውን የሚያስኬዱት በተናጠል ነው:: ነገር ግን በጋራ ደግሞ የሚስማሙባቸው ለምዕራቡ ዓለም እንደ ስጋት የሚታይ እንቅስቃሴ አላቸው:: ትልልቅ ነዳጅ አምራች አገራት ሳውዲ ዓረብያ ፣ኢራን እንዲሁም ናይጄሪያ ደግሞ ፈቅደው ወደዚህ ህብረት ከገቡ በዓለም ከግማሽ በላይ ነዳጅ የሚያመርቱ ሀገራት በእነርሱ ስር ይሆናሉ ማለት ነው። ይህ ደግሞ ተፅዕኖው ከፍተኛ ነው፤ የዓለምን የሃይል አቅርቦት መወሰን የሚያስችል አቅም ይፈጥርላቸዋል:: ይህም ትርጉሙ ብዙ ነው ሲሉ ዶክተር ሳሙኤል ተናግረዋል።
እንደ እርሳቸው ግምት፤ በሂደት ይህን ህብረት ለመቀላቀል ብዙ ሀገራት እያደረጉት ያለው እንቅስቃሴ እና ፍላጎት ሲታይ በምዕራብ የሚመራው ዓለም ያፈጀ እና ያረጀ ነው:: ጥቂት ሀገራት የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታ ምክር ቤት ድምፅን በድምፅ የመሻር መብት ይዘው ደቡብ የሚባለውን እያደገ ያለውን ኢኮኖሚ እና የፖለቲካ ፍላጎት የሚጨቁን እና የእነርሱ ፍላጎት ብቻ ማራመድ የሚያስችል ውሳኔዎች እንዲወሰኑ በማድረግ ተፅዕኖ ፈጣሪ ሆነው መቀጠል ይፈልጋሉ:: አዲስ ለሚመጡ ሃይሎች እና አስተሳሰቦች ቦታ የላቸውም ብለው መነሳታቸው የተባበሩት መንግሥታትን ሪፎርም ማድረግ እንዲችል አማራጭ መንገድ አድርገው ያያሉ:: እያደገ የሚመጣ ጠንካራ ስብስብ ለመፍጠር መንገድ የያዘም ይመስላል ብለዋል።
ፍላጎታቸው የንግድ ሥርዓትን መዘርጋት ስለሆነ በጊዜ ሂደት ጠንካራ ፖለቲካዊ አቋም እየፈጠሩ ቃልኪዳኖችንና ስምምነቶችን እየተፈራረሙ አሁን ባላቸው በዚህ አካሄድ ከቀጠሉ ምዕራቡን የሚያሰጋ ይሆናሉ ሲሉ ጠቅሰው፤ በራሳቸውም ደግሞ ተፅዕኖ ፈጣሪ ሆነው የዓለም ፖለቲካዊ ሥርዓትን በአማራጭነት የሚያመጣ ስብስብ ነው ብለን መውሰድ እንችላለን ይላሉ።
ከኢትዮጵያ አንፃር ሀገሪቱ እየደረሰባት ካለው ዓለም አቀፍ ጫና ለመግታት በተለይ በጦርነቱ ወቅት የነበሩ ፀረ ኢትዮጵያ የሆኑ ርምጃዎች፣ ማዕቀቦች፣ የርዳታ ዕገዳ፣ የገንዘብ ድጋፍ ተቋርጦ ነበር:: በዓለም አቀፍ ደረጃ በተከሰቱ ቀውሶች ምክንያት ደግሞ የገንዘብ ምንጭ እየደረቀ መጥቷል:: የሰብዓዊ ቀውሱ በሰፋ ቁጥር ይህንን ለመደገፍ የሚያስችል የፋይናንስ ድጋፍ እየቀነሰ ነው። ይህ ባለበት በዓለም አቀፍ ደረጃ ደግሞ መንግሥት ላይ ጫና በበረታበት ተፅዕኖ የሚፈጥሩ ሃይሎች በሀገሪቱ የውስጥ ጉዳይ ላይ እጃቸውን ባረዘሙበትና ይህ ሁሉ ግፊት ባለበት ሁኔታ ውስጥ ነው የኢትዮጵያ መንግሥት ጥያቄ ያቀረበው::
ኢትዮጵያ መቀላቀሏ ትርፍም ጉዳትም ሊኖረው ይችላል፤ የሚያመጣው ትርፍ ‹‹ብሪክስ››ን መቀላቀል ትልቅ የገበያ ሥርዓት ውስጥ የመግባትን ዕድል ይሰጣል:: በምዕራቡ ዓለም ብቻ ተወስኖ ያለው የፖለቲካዊም ሆነ የኢኮኖሚ ሥርዓት ሌላ አማራጭ እንዲያገኝ ዕድል ይሰጣል:: በመርህ ደረጃ ከሁሉም ጋር በሰላም የመኖር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ስትከተል የኖረች ናት:: ኢትዮጵያ እንደ ሀገር ወደዚህ ህብረት መግባቱ የኢኮኖሚ እና የዲፕሎማሲ አማራጭ ያሰፋል::
የህብረቱ መስራች ሀገራት ቻይና እና ሩሲያ በጦርነቱ ወቅት በተፈጠረ ጫና ጠንካራ አጋር እና ወዳጆች ሆነው ከብዙ ነገር የጠበቁን ናቸው:: በተለይ ድምፅን በድምፅ የመሻር መብታቸውን ተጠቅመው በዚህ መልኩ በኢኮኖሚ ተሰብስበው ጠንካራ ሆነው ሲመጡ ከፖለቲካ ድጋፋቸው ባሻገር በኢኮኖሚ ኢትዮጵያ ተጠቀሚ የምትሆንበትን ዕድል ያሰፋል ብለዋል።
ዶክተር ሳሙኤል እንደ ስጋት ያነሱት በኢትዮጵያ እና በህብረቱ አባል ሀገራት መካከል ያለው የንግድ ሚዛን የተመጣጠነ አለመሆኑን ነው፤ በዚህም ኢትዮጵያን ተጎጂ ሊያደርጋት ይችላል:: ቢሆን የምታገኘው ጠቀሜታ ሚዛን ይደፋል ብለዋል::
ወደፊት ሀገሪቱ ሰላም አግኝታ የተረጋጋ ኢኮኖሚ መዘርጋት ችላ በሃይል ልማት ዓባይን ጨምሮ አጠናቅቃ ሃይል ማመንጨት ጀምራ፤ ሰላም ተረጋግጦ ኢንቨስትመንት መሳብ ከቻለች በብዙ ተጠቃሚ ትሆናለች፤ ኢትዮጵያ ትልቅ ገበያ ናት::
በአፍሪካ የቻይና፣ የሩሲያና የህንድ ባለሀብቶች ኢትዮጵያ ውስጥ መጥተው ኢንቨስት ማድረግ እንዲችሉ ምቹ ሁኔታ በተፈጠረ ቁጥር ኢትዮጵያ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ምንጯን ታጠናክራለች:: የውጭ ምንዛሬ በተሻለ ሁኔታ የምታገኝበት ሁኔታ እንደሚፈጠር ዶክተር ሳሙኤል አስረድተዋል።
ኢትዮጵያ ያለችበት የጂኦፖለቲካ ሁኔታ በጣም ወሳኝ ነው። አየር መንገድን የመሰሉ ግዙፍ ተቋማት አሏት:: የቴሌኮም ሴክተሩ ሌብራላይዝድ መሆን የሚያመጣቸው ዕድሎች ይኖራሉ:: ኢንቨስትመንቶቻቸውን ወደ ኢትዮጵያ የሚልኩ ሀገራት ደግሞ ተጠቃሚ የሚሆኑበት ሥርዓት ይኖራል:: ምክንያቱም የተሻለ እና ጠንካራ የሃይል አማራጭ አለ:: የህዳሴ ግድብ አሁን ያለውን የሃይል መጠን ከእጥፍ በላይ የሚያመነጭ ስለሆነ ከውጭ የሚመጡ ኢንቨስተሮች ከሌላው ረከስ ባለ የሃይል አማራጭ ተጠቅመው ምርቶቻቸውን አምርተው ኤክስፖርት አድርገው እራሳቸውንም ኢትዮጵያንም መጥቀም የሚችሉባቸው መንገዶች ይስፋፋሉ:: ስለዚህ የጋራ የሆነ የገበያ ዕድል የማስፋት ዕድል ይኖረዋል ሲሉ ዶክተር ሳሙኤል ገልጸዋል።
በተጨማሪ ኢትዮጵያ 120 ሚሊዮን ህዝብ አላት፤ የአፍሪካ ህብረት መቀመጫ ናት:: ያለችበት የጂኦፖለቲካ አቀማመጧ ጠቃሚ ነው። በቀጣናው ያላትን ተፅዕኖ ፈጣሪነት ማስቀጠል ከቻለች ደግሞ የፖለቲካ ትርፍ ስለሚኖረው በብሪክስ ኢትዮጵያን ተመራጭ ያደርጋታል ብለዋል።
በዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ እና ዲፕሎማሲ መምህሩ አቶ ሙሉዓለም ሃይለማርያም በበኩላቸው፤ የ‹‹ብሪክስ›› አባል ሀገራት ህብረቱን የመሠረቱበት ዓላማ ሁለት ነው ይላሉ፤ አንደኛው ኢኮኖሚያዊ ሲሆን፣ ሌላኛው ደግሞ ፖለቲካዊ ዓላማ ያለው ነው። ከኢኮኖሚ አንፃር የህብረቱ አባል ሀገራት በዓለም ኢኮኖሚ ላይ እየመጡ እና በከፍተኛ ፍጥነት እያደጉ ያሉ መሆናቸው ይታወቃል:: የዓለም 42 ከመቶ የሚሆነውን የህዝብ ቁጥር የሚሸፍኑ ናቸው:: የዓለምን የሀገር ውስጥ ጥቅል ምርት 31 ከመቶ ይሸፍናሉ:: የ‹‹ብሪክስ›› ባንክ የሚል ስያሜ የተሰጠው ባንክ አላቸው:: ይህ ባንክ በባለፈው ዓመት እኤአ 2022 በአምስቱ ሀገራት መካከል ወደ 65 የሚሆኑ የመሠረተ ልማት እና ዘላቂ ልማት ፕሮጀክቶችን 21 ቢሊዮን ዶላር በማውጣት ሰርቷል:: ስለዚህ አቅሙ ከፍተኛ ነው ብለዋል::
በአሁኑ ወቅት ብሪክስን ለመቀላቀል የሚጠይቁ ሀገራት ከፍተኛ የሆነ የነዳጅ ክምችት ያለባቸው ሀገራት ናቸው፤ ይህ ደግሞ በዓለም ኢኮኖሚ ውስጥ ያለው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው። ሌላው ፖለቲካዊ ምክንያት ከቀዝቃዛው ጦርነት መጠናቀቅ በኋላ ዓለምን የሚመራው ሀገር ከአንድ ወደ ሁለት እና ሶስት ሀገር የመቀየር ዕድሎች ይዞ እየመጣ ነው:: ወደፊት እየመጡ ያሉ ሀገራት በከፍተኛ ደረጃ ኢኮኖሚያቸውን እያሳደጉ ነው:: በዓለም ፖለቲካ ደግሞ ሁልጊዜ የኢኮኖሚ የበላይነት ነው የፖለቲካ የበላይነትን የሚያመጣው:: ስለዚህ ‹‹ብሪክስ›› በምዕራባውያን እና አሜሪካ እየተዛወረ ያለውን የዓለም ፖለቲካ የሚገዳደር ዓለም አቀፍ ጥምረት ነው ብለን መውሰድ እንችላለን ይላሉ::
አቶ ሙሉዓለም እንደተናገሩት፤ የ‹‹ብሪክስ›› አባል ሀገራት በከፍተኛ ደረጃ ኢኮኖሚያቸውን እያሳደጉ ስለሆነ የዓለም ፖለቲካ የሃይል ሚዛኑን በመቀየር ደረጃ ትልቅ አስተዋጽኦ አላቸው፤ አሜሪካ እና ምዕራባውያን ያሉትን ብቻ የዓለም አገራት ‹እሺ› ብሎ ከመቀበል በዘለለ በብዙ ጉዳዮች በልዩነት የቆሙባቸውን ብዙ መድረኮች ነበሩ:: ስለዚህ ጥምረቱ የአንድ ወገን የበላይነትን በመገዳደር ሚናው ከፍተኛ ነው።
የዓለም አቀፍ ተቋማት ባስቀመጡት ግምት መሠረት ኢትዮጵያ በየዓመቱ የኢኮኖሚ ዕድገት እያስመዘገበች ያለች ሀገር መሆኗ ይታወቃል፤ በመሆኑም በዚህ ህብረት ውስጥ ብትካተት በርካታ የኢኮኖሚ እና የፖለቲካ ጥቅሞች እንደምታገኝ ስለምታውቅ ነው ጥያቄ ያቀረበችው፤ የ‹‹ብሪክስ›› ባንክ የሚባለው በአምስቱ የህብረቱ ሀገራት ብቻ በከፍተኛ ገንዘብ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን በአንድ ዓመት ብቻ እንዲሰሩ ማድረግ ችሏል፤ ስለዚህ ወደ ህብረቱ መግባት ይዞት የሚመጣው ለአባል ሀገራቱ የሚሰጥ ማንኛውም አይነት የልማት፣ የኢኮኖሚ እና የፖለቲካ ጥቅም በሙሉ ይዞ የሚመጣ ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ እያደገች ያለች ሀገር እንደመሆኗ ወደዚህ ጥምረት መግባቷ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላትን የመደራደር አቅም ከፍ ያደርግላታል:: ከፖለቲካ እና ኢኮኖሚ አንፃር ፋይዳው የጎላ ነው ይላሉ፤ ኢትዮጵያ ያላት የህዝብ ብዛት ለጥያቄዋ አዎንታዊ ምላሸ እንድታገኝ ይረዳታል ሲሉም የዶክተር ሳሙኤልን ሃሳብ ይጋራሉ:: ሀገሪቱ ወደውጭ ለምትልካቸው ምርቶች ተጨማሪ የገበያ አማራጭ ያስፈልጋታል:: በእነዚህ እና ሌሎች መሰል ምክንያቶች የጥምረቱ አባል መሆን ጠቀሜታው እንደ ሀገር ከፍተኛ ነው ብለዋል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የ‹‹ብሪክስ›› አባል ሀገራት ቁጥር ከፍ ማለት አለበት ብለው መስራች አገራቱ ያስባሉ፤ የተለያዩ የዓለም ሀገራት ደግሞ ለመቀላቀል ጥያቄ እያቀረቡ ነው:: የእንቀላቀል ጥያቄያቸው ዋናው ምክንያትም የዚህ ህብረት አባል በመሆን ውስጥ የሚገኘውን የላቀ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን ታሳቢ አድርገው ነው። ሌላው በዓለም መድረክ ላይ ያላቸው የመደራደር አቅም ከፍ እንደሚል ከግምት በማስገባት ነው:: ለብቻ ከመሆን ይልቅ እንደ ህብረት መደራደር ከፍተኛ ፋይዳ አለው ተብሎ ስለሚታስብም ጭምር ነው ብለዋል።
ከኢትዮጵያ አንፃር ሲታይ ወደ ህብረቱ ለመቀላቀል ቀጣይነት ያለው ኢኮኖሚያዊ እድገት ማስመዝገብ አለባት:: ይህ እንደ ቅድመ ሁኔታም ስለሚታይ መንግሥት እና ህዝቡ የሚችለውን ሁሉ በማድረግ ተረባርቦ የኢኮኖሚ እድገቱ በተሻለ ሁኔታ እንዲቀጥል መሥራት መቻል አለባቸው ብዬ አምናለሁ ብለዋል:: በተጨማሪ የህብረቱን አባል አገራትን ለማሳመን ከፍተኛ የዲፕሎማሲ ሥራ መስራት ያስፈልጋል:: ወደ ህብረቱ ኢትዮጵያ ብትገባ ሊኖራት ስለሚችለው አስተዋፅኦ እያንዳንዱን አባል ሀገር በምንችለው ሁሉ ለማሳመን ጥረት ማድረግ እና መግባባት አስፈለጊ እንደሆነ ተናግረዋል::
በአጠቃላይ ምሁራኑ እንደተናገሩት፤ የኢትዮጵያ ወደ ጥምረቱ የመቀላቀል ፍላጎት ምክንያት ሁለት ነው:: ይህም ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ነው:: በዋናነት አሁን የዓለም ፖለቲካ እና አሰላለፉ እየተቀያየረ እየሄደ ነው:: በተፈጥሮውም ተቀያያሪ ነው:: በአንድ ቦታ የሚቆም አይደለም፤ ተለዋዋጭ ነው:: በዚህ ተለዋዋጭ የዓለም ፖለቲካ ኢትዮጵያ የራሷን ብሔራዊ ጥቅም ማስጠበቅ የምትችልበትን አማራጭ ሁሉ መጠቀም አለባት፤ ከአንድ ወገን ጋር ብቻ ህብረት በማድረግ የሚፈለጉ ብሔራዊ ጥቅሞች ማሳካት የሚቻል አይደለም:: ስለዚህ ዕድሎች ካሉ በዓለም ደረጃ ካሉ ጥምረቶች ጋር አጋርነት በመፍጠር እንደ አገር ማግኘት ያለባትን ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ጥቅም ሁሉ ማግኘት ከተፈለገ እንደ ‹‹ብሪክስ›› ካለ ጥምረት ጋር ህብረት በመፍጠር በብዙ አማራጭ ብሔራዊ ጥቅሟን ማስጠበቅ እንዲያስችላት ህብረቱን መቀላቀሏ ፋይዳው የጎላ ነው።
ክብረአብ በላቸው
አዲስ ዘመን ሐምሌ 4/2015