ኢትዮጵያ ለላቀ የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ መዋል የሚችል መጠነ-ሰፊ የከርሰ-ምድርና የገፀ-ምድር የውሃ ሀብት እንዳላት ይታወቃል፡፡ ይህን ሀብት በዘላቂነትና በፍትሃዊ ለመጠቀም እንዲቻል የውሃ ሃብት አስተዳደር ፖሊሲ ተቀርፆ ተግባራዊ እየተደረገ ሲሆን ይህንን ፖሊሲ መሠረት በማድረግ የኢትዮጵያ የውሃ ሀብት አስተዳደር በሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 115/1997 እና አዋጅ ቁጥር 197/1992 ጸድቆ መውጣቱ ይታወቃል፡፡
የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መንግስት የሁለተኛውን የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድን በተሻለ መልኩ ለማሳካት እንዲቻል በአዋጅ ቁጥር 1097/2011 አስፈጻሚ አካላት በአዲስ መልክ እንዲደራጁ በተደረገው መሠረት ለውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር ተጠሪ ሆኖ ከዚህ በፊት የአዋሽ፣ የአባይና የስምጥ ሸለቆ ኃይቆች ባላስልጣናት እንዲሁም ከውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር አምስት ዓላማ ፈፃሚ የሥራ ሂደቶችን ወይንም የተፋሰስ አስተዳደር፣ የወሰንና ወሰን ተሻጋሪ ወንዞች፣ የውሃ ፈቃድና አስተዳደር፣ የከርሰ-ምድር ጥናት፣ የሃይድሮሎጂና ውሃጥራት ዳይሬክቶሬቶችን በመያዝ የተፋሰሶች ልማት ባለስልጣን በአዲስ መልክ ተቋቁሟል፡፡
ይህ አደረጃጀትም ኢትዮጵያ ያላትን የውሃ ሀብት በአግባቡ በመጠቀምና ፍትሃዊ አጠቃቀም በማስፈን የተረጋጋ ሥነ-ምህዳር እንዲኖር በማድረግ የዜጎቿን ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ጉልህ ድርሻ እንዳለው ይታመናል፡፡ በዛሬው ዕለት በተፋሰሶች ላይ በተለይም በአዋሽ ተፋሰስ ነባራዊ ሁኔታ እና ጎርፍ ለመከላከል እየተከናወኑ ያሉ ተግባራትን አስመልክቶ ከአዋሽ ተፋሰስ አስተዳደር ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አንድነት ጌታቸው ጋር ቆይታ አድርገናል፡፡
አዲስ ዘመን፡- አዋሽ ቤዝን መነሻውና የሚያካልለው መልክዓ ምድራዊ ገፅታ እስከየት ነው?
አቶ አብነት፡- በኢትዮጵያ ካሉት 12 ተፋሰሶች ውስጥ አንዱና ዋነኛው አዋሽ ተፋሰስ ሲሆን የተፋሰሱ ስም የሆነው የአዋሽ ወንዝ መነሻውን ከመሀል ኢትዮጵያ ኦሮሚያ ክልል ከምዕራብ ሸዋ ዞን ከዳንዲ ወረዳ ከአዋሽ ቦሌ ቀበሌ እዚህም እዚያም ጭልጭል ከሚሉ ትናንሽ ምንጮች ተነስቶ በተለያዩ ገባር ወንዞች ዓማካኝነት በመጠኑና በስፋቱ እየጨመረ 1ሺ280 ኪሎ ሜትር ተጉዞ መጨረሻውን በአፋር ክልል ዞን አንድ አፋምቦ ወረዳ አቤ ሐይቅ ያደርጋል፡፡
አዋሽ ቤዝን ሰፊ ቦታ ያቀፈ ነው፡፡ አፋር፣ አማራ፣ ኦሮሚያ፣ ሶማሌ እና ጥቂት ወረዳዎች ደግሞ ከደቡብ ክልል ብሎም የድሬዳዋ እና አዲስ አበባ ከተማ መስተዳድርን ያካትታል፡፡ በአጠቃላይ 138 ወረዳዎችን የሚያካልል ሲሆን፤ ገባሮቹ ሲጠቃለሉ ስፋቱ 114ሺ ስኩየር ኪሎ ሜትር ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- የተፋሰሱ ዋነኛ ግልጋሎቶች ምንድን ናቸው?
አቶ አብነት፡- ይህ ተፋሰስ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎች አሉት፡፡ ለመስኖ፣ መዝናኛ፣ ለኤሌክትሪክ ኃይል ለማመንጭት፣ ዓሣ እርባታና ለመሳሰሉት ከፍተኛ ግልጋሎት እየሰጠ ነው፡፡ ከማዕከላዊ ኢትዮጵያ ተነስቶ ወደ ሰሜን ምስራቅ ነው የሚፈሰው፡፡ በተለይም ዘመናዊ መስኖም እንደ አገር የተጀመረው በዚሁ ተፋስስ ነው፡፡ ለወደብም ቅርብ ነው፡፡ ለአገር ውስጥ እና ለአገር ውጭ ገበያ ምርት ለማቅረብም አመቺ ቦታ ላይ ይገኛል፡፡ በመሆኑም የመስኖ ልማት በሰፊው እየተካሄደበት ያለ ተፋሰስ ነው፡፡ ከአገሪቱ አጠቃላይ ምርት 24 ከመቶ የሚሸፍነውም ከዚህ ተፋሰስ ነው፡፡ በአገሪቱ የግብርና ምርትም ስምንት በመቶ በዓመቱ ያድጋል በዚህ ተፋሰስ ሳቢያ፡፡ ስለዚህም ይህ ተፋሰስ በኢትዮጵያ የግብርና ምርት ዕድገት ላይ ከፍተኛ ድርሻ ያለው ነው፡፡
በሌላ መልኩ በኢትዮጵያ ካሉት 12 ተፋሰሶች ውስጥ አዋሽ ተፋሰስ አጠቃላይ በውሃ አቅም ሰባተኛ ደረጃ ላይ የሚገኝ ነው፡፡ 4ነጥብ6 ቢሊዮን ሜትር ኪዮብ ዓመታዊ የገፀ-ምድር ውሃ ፍሰትም አለው። በውሃ ሃብቱ የሚቀድመው ደናክል፣ አይሻና የመሳሰሉትን ደረቅ ተፋሰሶችን ነው የሚቀድመው፡፡ በቆዳ ስፋት ደግሞ አራተኛ ደረጃ ነው፡፡
የአዋሽ ተፋሰስ ብዙ መገለጫዎች አሉት፤ በርካታ ገባሮችም አሉት፡፡ ቀለጣ፣ ከሰም፣ አጣዬ፣ ቦርከና፣ ሚሌ፣ አርባ፣ አቦምሳ፣ ቀበና፣ አዋዲ፣ ነጄሶ፣ ጨለለቃ፣ ሎጊያ እና አቃቂ የአዋሽ ገባር ወንዞች ናቸው፡፡ በርካታ ሰው ሰራሽ እና የተፈጥሮ ሃይቆች በዚህ ተፋሰስ ላይ ይገኛሉ። ኩሪፍቱ፣ ቢሾፍቱ፣ በሰቃ፣ ሃይቅ፣ አርዲቦ፣ ገደባሳ፣ ኤርታሌ፣ አቤ ሃይቅ እና ሆራ አረሰዲ ደግሞ በተፋሰሱ ውስጥ የሚገኙ የተፈጥሮ ሃይቆች ናቸው። ገፈርሳ፣ ለገዳዲ፣ ድሬ፣ አባ ሳሙኤል፣ ቆቃ፣ ከሰም እና ተንዳሆ ደግሞ በተፋሰሱ ላይ የተገነቡ ሰው ሰራሽ ኃይቆች ናቸው፡፡
ይህ ተፋሰስ በቱሪስት መስህቦችም የታደለ ሲሆን፤ የአዋሽ ብሄራዊ ፓርክ፣ ሶደሬ መዝናኛ፣ ዶሆ ፍል ውሃ፣ ሃይቅ እስጢፋኖስ ገዳም፣ ኤርታሌ ሃይቅ፣ አፍዴራ የጨው ማዕድን፣ የኩሪፍቱና የሆራ ሃይቅ ዋንኞቹ ናቸው፡፡
አዲስ ዘመን፡- የአዋሽ ተፋሰስ የውሃ ይዞታና ህዝባዊ አሰፋፈሩስ ምን ይመስላል?
አቶ አብነት፡- የአዋሽ ተፋሰስ ካሉት ተፋሰሶች ውስጥ በህዝብ ብዛቱ ሁለተኛ ሲሆን 4ነጥብ6 ቢሊዮን ሜትር ኪዮብ ዓመታዊ የገፀ-ምድር ውሃ ፍሰት እና ከ10ነጥብ23 እስከ 18ነጥብ93 ቢሊዮን ሜትር ኪዮብ የከርሰ-ምድር የውሀ ሀብት እንዳለው መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡ ይህ የውሃ ሀብት በወንዞች፤ ሀይቆችና በረግረጋማ ስፍራዎች የሚገኝ ነው፡፡ የአገሪቱ 65 ከመቶ ኢንዱስትሪ የሚገኘውም በዚሁ ተፋሰስ ነው። ይህ ደግሞ ከውሃ ጥራት ጋር በተያያዘ የራሱ የሆነ ትርጉም አለው፡፡ ከአገሪቱ ህዝብ ውስጥም ከ18 እስከ 20 ሚሊዮን ህዝብ የሰፈረው በአዋሽ ተፋሰስ ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- በአዋሽ ተፋሰስ የሚስተዋሉ ተግዳሮቶች ምንድን ናቸው?
አቶ አብነት፡- በሌሎች ዓለማት ተፋሰሶችን የሚጋጥመው ችግር አዋሽ ተፋሰስ ላይም ይስተዋላል። የአገሪቱ 65 ከመቶ ኢንዱስትሪ ብሎም እስከ 20 ሚሊዮን የሚሆነው ህዝብ የሰፈረው በአዋሽ ተፋሰስ ነው፡፡ ስለዚህ እነዚህ ጉዳዮች በአዋሽ ተፋሰስ ላይ ተፅዕኖ አላቸው፡፡
በዚህ አካባቢ የውሃ እጥረት፣ የተፈጥሮ ሃብት መመናመንና መራቆት፣ የውሀ ጥራት ችግር፣ የውሀ እጥረት፣ ጐርፍ፣ የደለል ክምችት፣ የአፈር ጨዋማነት፣ የአፈር መከላት የመሳሰሉት ተጠቃሽ ናቸው፡፡ የአዋሽ ተፋሰስ ከፍተኛ የሆነ ድርቅም ጎርፍም የሚያጠቃው ነው፡፡ ያለው ውሃ አሁን ከአቅም በላይ ጥቅም ላይ እየዋለ ነው፡፡ 4ነጥብ6 ቢሊዮን ኪዮቢክ ሜትር ውሃ በላይ ጥቅም ላይ እየዋለ ነው፡፡ በዚህ ላይም ቆቃ፣ ከሰምና እና ተንዳሆ ሦስት ትልልቅ ግድቦች አሉ። በቀጣይ ውሃ እጥረቱንና ድርቁን ለመቀነስ በዚህ ተፋሰስ ላይ ለመገንባት የታሰቡ ሁለት ግድቦች አሉ። አንደኛው ሎጊያ አፋር ክልል የታሰበ ሲሆን ሁለተኛው በተፋሰሱ መካከለኛ ክፍል አዋሽ ሰባት የሚባለው አካባቢ የተጠና ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- የአገሪቱን 65 ከመቶ የሚሆኑ ኢንዱስትሪዎች መገኛ በዚህ ተፋሰስ ከሆነ የውሃ ብክለት እንዳያስከትሉ ምን እየተሰራ ነው?
አቶ አብነት፡- የውሃ ሃብት ችግሮችን ብዛት ለመቆጣጠር የሚያግዙና በአስተዳደራዊ ዓይን የሚታዩ ጉዳዮች አሉ፡፡ ችግሮችን መቀነስና ዘለቄታዊ ጥቅም ማስጠበቅ ቅድሚያ ይሰጠዋል፡፡ ይህ ተቋም ከአምስት ዓመት በፊት ያስጠናው ጥናት አለ፡፡ አንዱ መንገድ ክፍያ ነው፡፡ ለመስኖ ግልጋሎት ይሁን እነዚህ ኢንዱስትሪዎች የታከመ ፈሳሽ እንዲለቁ የሚያስችል ታሪፍ ተጠንቷል። ይህም በህግ ሂደት ወደሚመለከተው አካል የሄደ ቢሆንም እስካሁን በሚኒስትሮች ምክር ቤት ፀድቆ ተግባራዊ አልሆነም። እነዚህ የማስገደጃ አካሄዶች በጥናትና በሂደት ላይ ናቸው፡፡ በብዛት ወደሚመለከተው አካል ደርሰው በመፅደቅ ሂደት ላይ ናቸው፡፡ ይህ ተግባራዊ ሲደረግ የታከመ ፍሳሽ መልቀቂያ ታሪፍ ስላው በዚህ መሰረት መቆጣጠር የሚያስችል አቅም ሊኖር ይችላል፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ ግን በህግ ማዕቀፍ አስገዳጅ ሁኔታ የለውም፡፡
የውሃ ጥራት ተፅኖን ለመቀነስ እኛ ዳሰሳ እናደርጋለን፡፡ የትኛው አካባቢ ምን ዓይነት ብክለት ደረጃ ላይ ነው የሚለው ተለይተው የሚታወቁ አሉ፡፡ ስልጣኑ ለአካባቢ ጥበቃ ስለተሰጠ በእነርሱ ዓማካኝነት ቢያንስ ዓለም አቀፍ ደረጃን ጠብቆ ፍሳሽ እያጣሩ እንዲለቁ የማስገደድ ጥረቶች አሉ። ሆኖም እነዚህ ጥረቶች በአስገዳጅ የህግ ማዕቀፎች መደገፍ አለባቸው። ይህ ከሆነ ለማስፈፀም አስቸጋሪ አይሆንም፡፡ አሁን የተሟሉ የህግ ማዕቀፎች የሉም፡፡
አዲስ ዘመን፡- በተፋሰሱ ላይ በሚለቀቁ የተለያዩ ያልተጣሩ ፍሳሾች የሚያደርሱዋቸው ጉዳቶች በአሃዝ ተሰልቷል?
አቶ አብነት፡- የጉዳቱን መጠን ለማወቅ ሰፊ ጥናት ይፈልጋል፡፡ ወደ ውሃ ውስጥ ከገባ በኋላ በተጠቃሚው ጤና ላይ፣ በሥነ ምህዳርና በመሳሰሉት ላይ ያደረሰውን ጉዳት ለማወቅ ጥልቅና ሰፊ ምርመራ ይፈልጋል፡፡ እኔ በዚህ ላይ በጥልቀት የማውቀው መረጃ የለም፡፡ ዋናው ነገር ወደ ውሃ ውስጥ የሚገቡ ያልተጣሩ ፍሳሾች በዓለም አቀፍ ደረጃ በዓለም ጤና ድርጅት የተቀመጡ ውሃ ጥራት መመዘኛዎች አሉ፡፡ ለመስኖም የሚውል ውሃ ጥራት መጠን የራሱ ገደብ አለው፤ ይህንንም የዓለም ምግብ ድርጅት አስቀምጦታል፡፡ ስለዚህ እነዚህን መሰረት በማድረግ ናሙናዎች ይሰበሰባሉ፡፡ ተተንትነው የሚደርሱትም ጉዳት ይቀመጣል፡፡ እኛ በዚህ ደረጃ ሙሉ ለሙሉ ጥናት አላደረግንም፡፡ ነገር ግን ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጥናት አካሂደው ሊሆን ይችላል፡፡
አዲስ ዘመን፡- ጉዳቶቹንስ መጠቆም ወይንም መዘርዘር አይቻልም?
አቶ አብነት፡– ከተለያዩ ተቋማት ጋር የተገናኘ ነው፡፡ ይህ ከጤና ጋር የሚገናኝ ጉዳይ አለው፡፡ ይህን ውሃ የተጠቀመ ሰው ምን ሆነ የሚለውን ለማወቅ የጥናት ውጤት በማየትና ሰፊ መረጃ በመውሰድ የሚታወቅ እንጂ እንዲሁ ጉዳት አለው ብሎ ማስቀመጥ አስቸጋሪ ነው፡፡ ይህ በዝርዝር እና በጥልቀት ማየት ይፈልጋል፡፡ በባህሪው ውስብስብ ነው፡፡ ይሁንና ግን ጉዳዩ ሰው ላይ የሚያርፍ በመሆኑ ትኩረት የሚሰጠው ጉዳይ መሆኑን መካድ አይቻልም፡፡
አዲስ ዘመን፡- በተፋሰሱ የሚገኙ አካባቢዎች በድርቅም በጎርፍም በከፍተኛ ደረጃ የሚጠቁት ለምንድ ነው?
አቶ አብነት፡- ይህን ያመጣው የወቅቶች መፈራረቅን መሰረት አድርጎ ነው፡፡ በተፋሰሱ ከፍተኛ የሆነው የዝናብ መጠን ወይንም 70 ከመቶ በላይ የሚሆነው ከሰኔ እስከ መስከረም ባሉት ወራት ነው፡፡ በዚህ ወቅት ከፍተኛ የሆነ ውሃ ፍሰት አለ፡፡ ተፋሰሱ 14 ገባሮች አሉት፡፡ እነዚህ ዋናው ወንዝ ላይ ሲጨመሩበት በጣም ከፍ ያለ የውሃ መጠን ይኖራል። ይህም ከፍተኛ ጎርፍ ያስከትላል፡፡ በዚህ ተፋሰስ ላይ በርከት ያሉ ግድቦች ቢገነቡ የውሃ መጠኑን በከፍተኛ ደረጃ የሚይዝ ይሆናል፡፡ በተጨማሪም ውሃው በግድቦች ውስጥ የሚቆይ ስለሚሆን ጎርፍ በከፍተኛ ደረጃ ለመከላከል ያስችላል፡፡
በዚህ ተፋስስ ከሰኔ እስከ መስከረም ያለው ከፍተኛ ውሃ መጠን ቢሆንም በዓመቱ ውስጥ ያሉት ቀሪ ወራቶች ጥቅም ላይ የሚውለው ውሃ በክረምቱ በግድቦች ላይ በተያዘ ውሃ ነው፡፡ ሰፊ ልማት የሚከናወንበት እና በ1956 ዓ.ም የተገነባው ቆጋ ግድብ ነው፡፡ እስካሁንም አገልግሎት እየሰጠ ነው። ወንዙ ከፍተኛ ውሃ አፈር ይዞ ስለሚመጣ እና ግድቡ በደለል እየተሞላ በመሆኑ የሚይዘው የውሃ መጠን ላይ ተጽዕኖ አለው፡፡ ክረምቱ ካለፈ በኋላ የተፋሰሱ ተጠቃሚዎችን ማዕከል ባደረገ መልኩ ውሃ ይለቀቃል፡፡ በመሆኑም በበጋው ብዙ ውሃ ስለማይኖር ውሃው ይከፋፈላል፡፡ ይህ ደግሞ የተጠቃሚዎችን ፍላጎት ያክል ላይሆን ይችላል፡፡
አንዱ ተፅዕኖ ይህ ነው፡፡ አንዳንድ ጊዜ ወንዙ ሊደርቅ ይችላል፡፡ በዚህ ተፋሰስ ደግሞ ለገበያ የሚቀርቡ ምርቶችና ሌሎችም ለፍጆታ የሚቀርቡ አትክልቶች የሚመረቱበት ነው፡፡ ወንጂ፣ መተሐራ እና ከሰም ሥኳር ፋብሪካዎችም መገኛቸው በዚህ ተፋሰስ ነው፡፡ በዚህ ተፋሰስ ውስጥ ትልቅ አገራዊ ትርጉም ያላቸው ልማቶች አሉ፡፡ ስለዚህ ክረምት ወቅት ላይ ያለውን ውሃ በሆነ ዘዴ መያዝ ቢቻል በክረምት ጎርፍ ለመከላከል፤ በበጋ ደግሞ ድርቅን ለማስቀረት ያግዛል፡፡ አብዛኛው የኢትዮጵያ ክፍል የዝናብ ስርጭት ከፍተኛ የሚሆነው በክረምት ነው። የአዋሽ ተፋሰስም በዚህ ተመሳሳይ ሁኔታ የሚገለፅ ነው፡፡ በተለይ በልግ በሌለ ሰዓት ዝናቡ ድርቁ ይበረታል። የውሃ አጠቃቀማችን 80 ከመቶ የሚሆነው መስኖ ነው፡፡ በመስኖ ላይ ያለን አፈጻጸም ደግሞ 45 ከመቶ አይበልጥም፤ 55 ከመቶ ይባክናል፡፡ ስለዚህ መስኖ ስንጠቀምም ዝም ብሎ ውሃን በማባከን ነው፡፡ ይህም መሬት ከሚፈልገው በላይ ነው የምንጠቀመው። ውሃ ቆጣቢ ቴክኖሎጂ የመጠቀሙ ጉዳይም ገና ነው። ለመጠጥ፣ ለሥነ ምህዳሩና ለመሳሰሉት ጥቅም ላይ የሚውለው 20 ከመቶ ነው፡፡ እነዚህ ተደምረው ለውሃ እጥረት ምክንያት ናቸው፡፡
አዲስ ዘመን፡- ተፋሰሱ ከድርቅ በተጨማሪ ከፍተኛ ጎርፍ የሚያጠቃው ነው። ይህን ለመከላከል ምን እየተሰራ ነው?
አቶ አብነት፡- የአዋሽ ቤዚን አስተዳደር ፅህፈት ቤት በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ስር ያለ ፅህፈት ቤት ነው፡፡ ከጎርፍ ጋር በተያያዘ ለእኛ ተቋም የተሰጠው ኃላፊነት የውሃ ፍሰቶችን አይቶ የቅድመ ጎርፍ ማስጠንቀቂያ ስራዎችን ያከናውናል የሚል ነው፡፡ ለዚህም ከገንዘብ ሚኒስቴር ገንዘብ ተበጅቶ መስራት ይቻላል፡፡ ግን ጎርፍን መከላከል በተመለከተ ለእኛ የተሰጠው ከሌሎች የሚመለከታቸው አካላት ጋር የሚሰራው ነው፡፡ ጎርፍ ሁሉንም አካል ይመለከታል። ጎርፍ አደጋ ስለሆነ በርካታ አካላት ጋር በቅንጅት ይሰራል ነው የሚለው፡፡ ሆኖም ጎርፍ እንዳይከሰት በመደበኛ ስራችን የምናከናውናቸው ተግባራት አሉ። የወንዝ አቅጣጫ አመራር ሥራ የሚባል ስራ አለ። ወንዙ በአቅጣጫው እንዲሄድ የሚሰራ ነው። ነገር ግን ጎርፍን እንደ አደጋ ይዘን ለመከላከል ይህን እንሰራለን ብለን በጀት መጠየቅም ማግኘትም አይቻልም፡፡
በቅንጅት ይሰራል የሚባለው ክልሎች የየራሳቸው አስተዳደራዊ ወሰን የሚከሰተውን የመጠበቅ ኃላፊነት አለ፡፡ ከእነርሱ ጋር በቅንጅት ይሰራል፡፡ ቅድመ ጎርፍ መከላከል ከፍተኛ መዕዋለ ንዋይ ይጠይቃል፡፡ የወንዝ ዳርና ዳር ግድቦች ይሰራሉ፡፡ ከላይኛው የወንዙ ተፋሰስ ክፍል እየመጣ የሚሞላውንና ውሃ የመያዝ አቅሙን የሚያሳንሰውን ደለል ከውስጡ በማሽን ማውጣት ይጠይቃል፡፡ ይህ ደግሞ በትንሽ ቦታ ላይ ትልቅ ገንዘብ የሚጠይቅ ነው፡፡ ይህ በመሆኑም በርካታ አካላት በቅንጅት ሊሰሩት የሚገባ ጉዳይ ነው። ይሁንና ሌሎች አካላት ከውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር፣ ከሌሎች የፌደራል ተቋማትና ከመሳሰሉት የመጠበቅ ዝንባሌ አለ፡፡
አዲስ ዘመን፡- እንደ ተቋም ምን ሰርታችኋል?
አቶ አብነት፡- በዚህ ዓመት ያደረግነው ችግሮችን ዳሰሳ አድርገን የመረጃ ምንጭ መሆን ነው፡፡ ቦታዎችን በመለየት ምን መሰራት እንዳለበት ይጠቁማል፡፡ ይህም በጥናት ላይ የተመሰረተ ነው፡፡ ስራዎችን ከለየን በኋላ በጀት አይኖርም፡፡ ሆኖም እኛ እንደሚኒስቴር በአዋጅ የተሰጠንን ተልዕኮ እየተወጣን ነው። ከበጀት አኳያ ችግር አለ፡፡ ክፍተቶች ከተለዩ በኋላ ከክልሎች ጋር ውይይት ይደረጋል፡፡ ሆኖም በጀት ማቅረብ ስለማይችሉም በተቻለ መጠን ሚኒስቴራችን በለያቸው ቦታዎች ስራዎች እየተሰሩ ነው፡፡ በጀት ባይኖርም ሥራውን ለመስራት ሲባል በአዋሽ ተፋሰስ ላይ ያለውን ችግር ለማቃለል ሲባል ጨረታ ወጥቶ ነበር፡፡ ይህም በላይኛው፤ በመካከለኛው እና በታችኛው ተፋሰስ ለሚሰሩ የጎርፍ መከላከል ሥራዎችን ያጠቃልላል፡፡ ሆኖም ግን በበጀት እጥረት የተነሳ የታሰበውን ያህል መስራት አልተቻለም፡፡
አዲስ ዘመን፡- በተፋሰሱ ላይ ጎርፍ ለመከላከል የሚደረገው ጥረቶች ምንድን ናቸው?
አቶ አብነት፡- የአዋሽ ተፋሰስ ከፍተኛ የሆነ ጠቀሜታ ያለው ቢሆንም በዚያው ልክ ከፍተኛ ጎርፍ እና ድርቅም የሚስተዋልበት ተፋሰስ ነው። የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴሩም የቅድመ ጎርፍ ማስጠንቀቂያ ሥራዎችን እየሠራ ነው፡፡ ጎርፍ መከላከል ከፍተኛ መዕዋለ ንዋይ የሚጠይቅ ነው፡፡ ከአዋሽ ከላይኛው ተፋሰስ ክፍል መሠራት ያለባቸው ሥራዎች በሰፊው እየተከናወኑ ነው፡፡ በመካከለኛው እና ታችኛው የተፋሰሱ ክፍልም ጎርፍ የሚደርሰውን አደጋ በከፍተኛ ሁኔታ ለመቀነስ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ልዩ ትኩረት በመስጠት እየሰራ ይገኛል፡፡
ከክልሎች ጋር በተናበበ መልኩ ዘርፈ ብዙ ተግባራትን እያከናወነ ነው፡፡ ይሁንና ከተፋሰሱ የሚገኘውን ጥቅም ላይ የሚደረገውን መረባረብ ያክል፤ በጎርፍ የሚደርሰው የመከላከል ሂደቱም ትኩረት የሚፈልግ ነው፡፡ በዚህ ዓመት ችግሮችን ለመለየት ጥረት አድርገናል፡፡ መከናወን ያላባቸውን ተግባራት በጥናት ለይተን ወደ ሥራም ገብተናል። በተቻለ መጠን የተሰጠንን ተልዕኮ እየተወጣን ነው፡፡ ከክልሎች ጋር ለመሥራትም ከፍተኛ ጥረት አድርገናል፡፡ በተፋሰሱ የሚደርሰው ጎርፍ ለመከላከል በመደበኛ ሥራም የምንሠራቸው ሥራዎች አሉ፡፡ ሌሎች አካላትን በማሳተፍም በጎርፍ የሚደርሰውን ጉዳት ለመቀነስ ዘርፈ ብዙ ተግባራት በመከናወን ላይ ናቸው፡፡
የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴርም ባደረገው ዳሰሳ ጥናት መሠረት ያለባቸውን ተግባራት ተለይተዋል። በመሆኑም በበጀት ዓመቱ ከታሰበው ውስጥ አንዱ የጎርፍ አደጋ የሚያስከትሉ ደለል እና መሰል ችግሮችን ለማስወገድ ማሽኖችን በጨረታ በማወዳደር ለሥራ ዝግጁ ማድረግ ነው፡፡ በዚህም በመካከለኛው አዋሽ ተፋሰስ ላይ በጨረታው አሸናፊ ተገኝቷል፡፡ ሆኖም የላይኛው እና የታችኛው የአዋሽ ተፋሰስ አካባቢዎች ይህን ማሳካት አልተቻለም፡፡ ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቅ ሥራ ነው፡፡
ይሁንና መንግስት ከአዋሽ ተፋሰስ በዘለለ በዓባይ እና ሥምጥ ሸለቆ ተፋሰሶች ጎርፍን ለመከላከል የሚያስችሉ የረጅም ጊዜ ዕቅዶች አሉት፡፡ በዚህም ረገድ በቀጣይ አምስት ዓመታት የሚተገበር ጎርፍ የመከላከል ሥራዎች ከወዲሁ ተጀምረዋል፡፡ ለዚህ ሥራም የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ከዓለም ባንክ ጋር የ300 ሚሊዮን ዶላር ሥምምነት ፈፅሟል፡፡ ይህ በአገር ደረጃ በጎርፍ የሚደርሱ አደጋዎችን በከፍተኛ ደረጃ ያቃልላል። በቀጣይ እንደ መንግስት በእቅድ የሚሰሩ ሰፋፊ ሥራዎችም ይኖራሉ፡፡
አዲስ ዘመን፡- ከዝግጅት ክፍላችን ጋር ለነበረዎት ቆይታ እያመሰገንኩ፤ ተጨማሪ ሃሳብ ካለ ዕድሉን መጠቀም ይችላሉ፡፡
አቶ አብነት፡– የአዋሽ ተፋሰስ ሆነ ሌሎች ተፋሰሶች ለአገሪቱ ኢኮኖሚ ዕድገት ከፍተኛ ጥቅም የሚሰጡ መሆኑን ማወቅ ይገባል። በተፋሰሱ ላይ የሚከናወኑ ማናቸውም ሥራዎች ደግሞ ጉዳት በማያደርስ መንገድ መሆኑን ማወቅና ኃላፊነት መውሰድ ይገባል፡፡ እነዚህን ሃብቶች በአግባቡ መጠቀም ካልተቻለ እና ከብክለት መታደግ የሚያስችል ጠንካራ አሰራር ካልተዘረጋ እንደ አገር ጉዳቱ የከፋ ነው። በመሆኑም ተፋሰሶች ላይ ያለን አተያይና የአስተዳደር ዘይቤያችን ከዘመኑ ጋር የተናበበ መሆን እንዳለበት አምናለሁ፡፡ እኛም እንደ ሚኒስቴር ብሎም እንደ አዋሽ ተፋሰስ አስተዳደር በርካታ ተግባራትን እያከናወንን ሲሆን፤ ሌሎች የሚመለከታቸው አካላትም በዚህ ጉዳይ ላይ በትኩረት መሥራት ይኖርባቸዋል እላለሁ፡፡
ክፍለዮሐንስ አንበርብር
አዲስ ዘመን ሰኞ ሐምሌ 3 ቀን 2015 ዓ.ም