“ካለምንም ጥርጥር የኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ፤ የኢትዮጵያ አንድነት ዛሬ ለኢትዮጵያ መንግሥት ስጋት አይደለም” – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)

በትናንትናው ክፍል አንድ እትማችን ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ኢትዮጵያ ማለት ምን ማለት እንደሆነ ትናንትናችንን በምን መልኩ ልናየው እንደሚገባ እንዲሁም በለውጡ ማግስት የፖለቲካ ሃይሎች ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገቡ እና በፖለቲካ አውድ ውስጥ እንዲሳተፉ የተደረገው ጥሪ ከተፈጠሩ አንዳንድ ችግሮች አኳያ ውሳኔው ምን ያህል ትክክል ነበር ለሚሉ ጥያቄዎች ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሰፊ ምላሽ ሰጥተዋል፣ በዛሬው እትማችን የቃለ መጠይቁን ሁለተኛውን ክፍል እንደሚከተለው አቅርበነዋል።

ኢቲቪ ፡- ምናልባት የሚገናኝ ይመስለኛል ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር የእነዚህ የፖለቲካ ሃይሎች ከእዚያ በኋላ በነበሩ ጊዜያቶች የአቋም መዋዠቅ የታዩባቸው የነበሩ አሉ:: ቀደም ሲል ተቋማት ግንባታዎቹ ሲሄዱ በየጊዜው ፊልተር እያደረጓቸው ይሄዳሉ የሚሉ ሃሳቦችን ሲያነሱ ነበርና የአቋም መዋዠቆች የታዩባቸው የፖለቲካ ሃይሎች አንዴ ደጋፊ አንዴ ተቃዋሚ የሚሆኑ የፖለቲካ ሃይሎች አሉና እንዲያው ከመነሻው ምንድነው ምክንያቱ ለዚህ ሊባል ይችላል?

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፦ አንዳንዴ መደገፍ አንዳንዴ መቃወም የሚለው ጉዳይ ጤነኛ እስከሆነ ድረስ የፖለቲካ ባህል መገለጫ ነው:: ሁልጊዜ ድጋፍ ወይ ሁልጊዜ ተቃውሞ መጠበቅ የለበትም ፖለቲካ ውስጥ:: ነገር ግን ፖለቲካን ማየት ያለብን በባሕር ላይ እንደመሻገር ነው:: በባሕር ላይ ስንጓዝ አንዳንድ ጊዜ ባህሩ ጸጥ ያለ ሊሆን ይችላል::

አንዳንድ ጊዜ ግን ወዝወዝታ ያለው፣ ማእበል ያለው የሚረብሽ በድምጸቱ በእንቅስቃሴው የሚያውክ፤ ሕይወታችንን እስኪወስድ ድረስ የሚያስደነግጥ ሊሆን ይችላል:: ማእበሉን ጸጥ ባለበት ሰዓት ያየው ሰው ወጀብ ሊነሳ እንደሚችል አስቦ በወጀብ ጊዜ ምን አይነት ቴክኒክ መጠቀም እንዳለበት ካላወቀ በድንጋጤ ነገሩ እዚያው ሊያበቃ ይችላል::

ወጀቦች ማእበሎች ግን ሁሌ ገዳይ ሁሌ አጥፊ ብቻ አይደሉም:: አንዳንድ ጊዜ ወደምንሄድበት አቅጣጫ ከኋላ የሚገፋ ንፋስ ሆኖ ካሰብነው ጊዜ አፍጥኖ ያደርሰናል:: ይሄ በአውሮፕላንም ይታያል፤ “ዊንድ ከኋላ” ነው ይላሉ አንዳንዴ ከጊዜው ፈጥነው ሲደርሱ፤ አንዳንዴ ደግሞ ከፊት ሆኖ በጣም አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል:: ያ የመጣው ማእበል ምን አይነት ነው የሚለውን ማስተዋል ያስፈልጋል::

ወደምንሄድበት አቅጣጫ ከኋላ የሚገፋ ነፋስ ሆኖ፤ ካሰብነው ጊዜ አፍጥኖ ያደርሰናል:: ይሄ በአውሮፕላንም ይታያል። ዊንድ ከኋላ ነው ይላሉ:: አንዳንዴ ፈጥነው ሲደርሱ:: አንዳንዴ ደግሞ ንፋሱ ከፊት ሆኖ በጣም አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል። ያ የመጣው ማእበል ምን አይነት ነው? የሚለውን ማስተዋል ያስፈልጋል። ይህ ለውጥ ፣ በዓለም ላይ ከፍተኛ ውዳሴ፣ ከፍተኛ ምስጋና፣ ከፍተኛ ድጋፍ ካስተናገዱ በጣም ጥቂት አፍሪካዊ ለውጦች አንዱ ነው።

ሰዎች መዘንጋት የለባቸውም ይሄንን ጉዳይ። ከኖብል የሰላም ሽልማት/ ከኖቤል ፒስ ፕራይዝ ጀምሮ ከ27 በላይ ዩኒቨርሲቲዎች እውቅና የሰጡት/ ሪኮግናይዝ ያደረጉት በጣም በርካታ ዓለም አቀፍ ተቋማት በተለያዩ ምክንያት የተሸለመ የተደነቀ የተወደሰ፣ በዓለምም በአፍሪካም በኢትዮጵያም ከፍተኛ ድጋፍ እና ውዳሴ ያገኘ ለውጥ ነው።

በዚያው ልክ ደግሞ የሚቃወሙት፣ ከጅምሩ የተቃወሙት፣ መሃል ላይ የተቃወሙ፣ ወጣ ገባ የሚሉ ሰዎችም ያስተናገደ ለውጥ ነው። ምንም አልጋ በአልጋ ተደርጎ አይወሰድም። ድጋፍ ያን ያክል የቸገረው እና ለድጋፍ የሚጠማ አይደለም፤ ከፍተኛውን ድጋፍ አስተናግዷል። ተቃውሞም እንደዛው አስተናግዷል፤ ሁለቱንም ባላንስ አድርጎ ለመሄድ ለውጡ የወሰነበት መንገድ፣ ንፋስ አቅጣጫውን ሊቀይር ይችላል፣ እኛ ግን መዳረሻችንን እናውቃለን፤ መርህ ያደረግነው መልህቃችንን ነው።

መርህን መልህቅ ካላደረግን በስተቀረ፤ መዳረሻ ግባችንን መልህቅ ካላደረግን በስተቀረ፤ንፋስ ወጀቡ በመጣ ቁጥር ወደ አሻው እንዲወስደን ከፈለግን ንፋሱ ይወስደናል ግን ከምናስበው አያደርሰንም። አንዳንዴ ወጀብ መጥቶ እኛ የምንሄድበትን ነጥብ/ ፖይንት ትቶ ሌላ ጫፍ ሊጥለን ይችላል። እዚያ ስንደርስ እንደደረስን ካሰብን ስተናል መዳረሻችን እርሱ አይደለም።

እኛ መዳረሻችን ብልፅግና ነው፣ መዳረሻችን የፀናች ኢትዮጵያን ማየት ነው። መዳረሻችን ልመና ያቆመች ኢትዮጵያን ማየት ነው። እሱን ስናስብ መሀል ላይ ውዳሴም እርግማንም ቢመጣም፣ ብዙ ሚዛን የሚያስት ጉዳይ አይደለም:: ሚዛናችንን የምንጠብቀው መልህቃችን መርህ ስለሆነ ማለት ነው።

በውዳሴ ውስጥም እምብዛም ስካር አልተሰማንም፤ በእርግማን ውስጥም እምብዛም አረበሸንም። ከእያንዳንዱ ውዳሴ እና ከእያንዳንዱ እርግማን ግን ለምን ብለን እንማራለን። ምን ፈጠረው፣ ምን አመጣው፤ የፖለቲካ ፓርቲዎች ለምንድነው ለብሄራዊ ትቅሞች /በናሽናል ኢንተረስት ጉዳይ ላይ የሚሰበሰብ፤ የሚፀና ሃሳብ መያዝ ያልቻሉት፤ ብለን እንገመግማለን።

አንደኛው ችግር የታዘብነው፤ በዚያ ጊዜ የነበሩ፤ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ለውጡን ያዩበት መንገድ ነው። እኛ ያየንበት መንገድ ብቻውን በቂ አይደለም። እኛ ያየንበትን መንገድ ለመገንዘብ መጋቢት 24 የነበረውን የፓርላማ ንግግር ማየት ነው። አንዲት አርፍተ ነገር /ስቴትመንት አልተዛነፈችም። ያቺ ንግግር ናት በየቀኑ በየዓመቱ የምትተገበረው። እኛ አልተቀየርንም። ዓላማችንን ተናግረነዋል፤ እየኖርነው ነው። ያ ንግግራችንን በየቀኑ እየኖርነው ነው።

ከውጪ ያሉት ሰዎች ግን የእኛን ንግግር የሰሙት ለእነሱ አዕምሮ እንዲመች አድርገው ነው። እኛ ያልነውን ሳይሆን የሚሹትን ነው የሰሙት። እንዴት ሰሙት ያልሽኝ እንደሆነ አንዳንዶች ችግር የለውም እነዚህ እምብዛም የማይታወቁ ሰዎች ስለሆኑ፤ ወጣ ብለን በሪሞት እናዘዋለን ለውጡን እኛ ወደምንዘውረው የሚጓዝ ለውጥ ይሆናል ብለው አሰቡ።

አንዳንዶች ደግሞ እነዚህ እምብዛም አይቆዩም ሁለት ሶስት ወር ነው ያሉም አሉ ባይዘዌ። በሁለት ሶስት ወር ውስጥ ተቀብለን እኛ እንቀጥላለን፤ እነዚህ አድራሽ ብቻ ናቸው እንጂ ዋንኞቹ እኛ ነን ብለው አሰቡ:: ይህንን ሃሳብ ከጅምሩ የገመትናቸውም አሉ፣ በሂደት የተማርናቸውም አሉ። ነገር ግን አብዛኛው እንደዚህ ያለ ሃሳብ የሚያስቡ ሰዎች መንግሥትን አያውቁም፤ መንግሥት መዘወር ግን ያስባሉ።

አንዲት ቀበሌ ለአንድ ዓመት አገልግለው /ሰርቭ አድርገው አያውቁም:: አንዲት ኤጀንሲ አገልግለው/ ሰርቭ አድርገው አያውቁም:: አንዳንዶቹ ፔሮል ላይ ፈርመው አያውቁም:: ማገልገል ምን እንደሆነ አያውቁም፤ግን መንግሥትን ማፍረስ መንግሥትን መምራት፤ መንግሥትን መዘወር እንደሚችሉ ያስባሉ:: ይህ ስለራሳቸው ያላቸው ግምገማ የፈጠረባቸው ቀውስ ይመስለኛል።

ሀገር ለመምራት ሶስት ጉዳዮች ያስፈልጋሉ:: አንደኛው እውቀት ያስፈልጋል። እውቀት ማለት የእውቀት መሠረቱ ኢንፎርሜሽን ነው፤ ዳታ ነው። አንድ ሰው ትምህርት ቤት ሄዶ የሚሰማቸው ማንኛውም ወሬዎች ፣ ኢንፎርሜሽኖች ሲደረጁ፤ በቻፕተር ሲደረጁ፤ በሴሚስተር ሲደረጁ፤ በዓመት ሲደረጁ፣ በሰርተፍኬት ሲረጋገጡ፤ እውቀት ይባላሉ::

ግን ወሬ ናቸው ኢንፎርሜሽን ናቸው:: አንድ ሀኪም ስለ ህክምና ኢንፎርሜሽን ሰምቶ ሰምቶ ከጨረሰ በኋላ ሂድና አክም ቢባል ማከም አይችልም። እየሰማ በሆነ ጊዜ ላይ መሞከር አለበት። ኖውሌጅ የሚባለው፤ እውቀት የሚባለው በሰማነው መረጃ/ ኢንፎርሜሽን፣ ባነበብነው መፅሐፍ ወይም ከሰዎች በሰማነው በትምህርት መልክ በተሰጠን ነገር ያከማቸነው ነገር ማለት ነው፤ እሱ ያስፈልጋል። እሱ ያስፈልጋል ግን በጣም ያለው ሼር በመንግሥት ውስጥ እነርሱ እንደሚያስቡት ሳይሆን ውስን ሼር ነው ያለው።

ከዚያ ቀጥሎ ክህሎት/ ስኪል ያስፈልጋል። ያ እውቀት የሚመነዘርበት፣ የሚተረጎምበት መሥራት የሚችልበት ክህሎት/ ስኪል ያስፈልጋል። ሶስተኛው ደግሞ ክህሎት/ ስኪል ለማምጣት አንዳንዴ እጅ ይቃጠላል፤ አንዳንዴ ይወደቃል፣ አንዳንዴ ጩኸት አለ፣ አንዳንዴ ድጋፍ አለ:: በዚያ ውስጥ ደግሞ ጥበብ / ዊዝደም እየተገነባ ይሄዳል፤ በጊዜ ውስጥ ማለት ነው። ሰው አውቀት ኖሮት ክህሎት/ ስኪል ከሌለው፣ ልምምዱ ከሌለው፣ በክህሎት/ በስኪል ውስጥ ደግሞ ጥበብ / ዊዝደም እየገነባ ካልሄደ ብቻውን እንኳን ባይሆን፤ እንደ ቡድን/ ቲም ይሄንን ብቃት መገንባት ካልቻሉ መንግሥት ያስቸግራል።

ብዙዎቹ በክፍል ውስጥ/ በክላስ ሩም ዋና እንዴት እንደሚዋኝ ተምረዋል፤ ስለ ዋና አልሰሙም አልልሽም ዋና ስትዋኝ መጀመሪያ ቀኝ እጅህን ትዘረጋለህ፣ ቀጥሎ ሁለት እግሮችህ ይንቀሳቀሳሉ፣ አየር የምትስብበት መንገድ ይሄ መሆን አለበት የሚል ንድፈ ሃሳብ/ ቲዮሪ ሰምተዋል፤ ግን ዋና ዋኝተው አያውቁም። አንድ ሰው ስለ ዋና አስተምረን ፣ አስተምረን ስናበቃ ሂድና ዋኝ ብለን ገንዳ ውስጥ ብንጥለው፤ ካልደረስንለት በቀር ሟች ነው።

ስለዋና ሰማ ማለት ዋና ቻለ ማለት አይደለም:: ወይም ሳይክል ለመንዳት ግራና ቀኝ እግርን እያፈራረቅክ ትነዳለህ ሚዛንህን ጠብቅ ብለን ለሰውዬ ብንነግረው ገብቶኛል ቢለንና ሳይክሉን ብንሰጠው ይፈጠፈጣል እንጂ ሳይክሉን አይነዳውም:: አብዛኛዎቹ እንደዚህ ናቸው::

ስለመንግሥት ወሬ የሰሙ ፣ ስለመንግሥት ያነበብ፣ ስለ መንግሥት በርቀት ያዩ ግን ደግሞ ቀበሌ ማለት ምን እንደሆነ በወጉ የማያውቁ ፣ ኤጀንሲ ማለት ምን ማለት እንደሆነ በወጉ የማያውቁ፣ ያልኖሩትና እኛ እኮ ስለዚህ ሰምተና ጉዳዩ እናውቃለን የሚሉ ናቸው:: አዎን ሰምተሃል መስማት ግን መኖር አይደለም:: ስትኖር ብዙ ከፍታና ዝቅታ በውስጡ አለ:: ይህንን ካለመገንዘብ ብዙዎቹ ሳቱ::

እኛ ለሁሉም እጃችንን ዘርግተን ጠበቅናቸው:: አውሮፓ፣ አሜሪካና በቅርብ ላለውም ለሁሉም እጃችንን ዘርግተ ነው የተቀበልነው:: አንዳንዶች ከእጃችን ላይ የግል ምንዳ ጠበቁ፤ ያንን የጠበቁትን ምንዳ ከእጃችንን ሲያጡ አኮረፉ:: ኑ ሲባሉ፤ግቡ ሲባሉ አብረን እንሥራ ሲባሉ ኑ የተባልነው አራት ኪሎ ነው ብለው ያሰቡ ሰዎች ሳቱ፤ አኮረፉ::

ሀገር ነው የምንፈልገው፤ ሃሳብ አለን መሥራት እንችላለን፤ እንፈልጋለን ያሉት ደግሞ ጸንተው ቀሩ:: እኛ ኑ ያልነው፤ ተመለሱ ያልነው አብረን እንሥራ ያለው ሃሳባችሁን ለመሸጥ አውድ ይገባቸዋል:: መዛኙ ሕዝቡ ካከበዳችሁ የምትፈልጉትን መሆን ትችላላችሁ ነው ያለው እንጂ፤ የጠራነው ሁሉ አራት ኪሎ ይገባ አላልንም:: እንዲዚያ ያሰቡ ሰዎች ሳቱ::

በሀሴት፣ በደስታ የተቀላቀሉ፤ ነገር ግን ቂም አርግዘው የገቡ በውስጡ ነበሩ:: በደስታ የመጣውም፣ እያለቀሰ የመጣውም ፣ ቂም አርግዞ የመጣው ተቀላቅሎ ስለመጣና ያንን የመለየት አቅም ስላልነበረ በሂደት ያ እሱ ያስቀመጠው መስፈርት፤ ይሆነኛል ይገባኛል ብሎ ያስቀመጠው መስፈርት ከፍና ዝቅ ሲል ድጋፉም ዋዠቀ፤ በኢትዮጵያ ፖለቲካ መቼም እንዴት እንደዋዠቀ ሁላችንም እንታዘባለን::

ዛሬ እነሳና የዛኛው ቡድን /ግሩፕ ደጋፊ እሆናለሁ፤ ካለምንም ችግር ደግሞ የሌላኛው ቡድን /ግሩፕ ደጋፊ እሆናለሁ፤ ሲጀመር መርህ አልነበርም:: የግል ፍላጎት እንጂ ብሔራዊ ጥቅም አልነበረም:: የግል ፍላጎት እንጂ፤ሃሳብ ሸጦ ተወዳድሮ ላሸንፍ እችላለሁ የሚል እምነትም አልነበረም:: እኔ ወሬ ስስማ ስለከረምኩ፤ እውቀት አለኝ ብዬ ስለማሰብ ቀጥታ መንግሥት መሆን ወይም መዘዋር እችላለሁ ብለው ብዙዎቹ አስበዋል::

እንግዲህ እኔ ያለኝ ምክር፤ መንግሥት ኢትዮጵያ ውስጥ ማንም ሰው፤ የተመኘ ሰው ከውስጥ ምኞት ያለው ሰው መሆን ይችላል:: እንደዚህ ቀደሙ ለምን መንግሥት መሆን ትመኛለህ የሚባልበት አይደለም:: ሰው ጠቅላይ ሚኒስትር፣ ጀኔራል፣ ሚኒስትር መሆንን መመኘትም ይችላል፤ ከበረታና ከተጋ መሆንም ይችላል::

የሚከለከል ሕግም፤ የሚከለከል አውድም አይደለም ያለው:: ብዙዎች ያንን እንዲመኙ ለዚያም እንዲተጉ እንፈልጋለን:: ግን ያለኝ ምክር ግን በከፍተኛው ቦታ ላይ ማገልገል የምናሰብ ማንኛውም ሰዎች ህልሙ ካለን ያ ህልም እንዳይጨናገፍና እንዲሆንልን ቀበሌን፣ ወረዳን ኤጀንሲን ማገልገል፤ ፒሮልን ማወቅ አለብን:: በወረቀት ፒሮል ላይ ፈርመን ደመወዝ መቀበል ሳንለማመድ ከዚያም ከዚህም ሞጭልፈን እየኖርን ከዚያ ላገልግል ካለን ያ ባህሪ ይከተለንና በፒሮል መኖር የምንቸገር ሰዎች እንሆናለን::

ፍላጎቱ ችግር የለበትም ፣ ምኞቹ ችግር የለበትም፤ ለዚያ መትጋቱም ችግር የለበትም:: ያ ግን በሰላማዊ፣ በሕጋዊ መንገድ፣ ሃሳብ ቆጥረን፣ በልፋትና በውጤት እንዲሆን ከሠራነው ከመራነው ለማንም ሰው ክፍት ነው:: እኛ ዛሬም እጃችን የተዘረጋ፤ ቤታችን የተከፈተ፣ ለሰላም፣ ለውድድር፣ ለንግግርና አብሮ ለመሥራት ለሚፈልጉ ማንኛውም ሰው ክፍት ነው ቤታችን፤ ዝግ አይደለም::

ባለፈው እንዲህ ስላደርግክ አሁን አትደርስብኝም የሚል አቋም የለንም:: አሁንም ሃሳብ ያለው ሰው፤ ሰላማዊ መንገድ የሚከተል ሰው፣ በመርህና በትጋት ሊያመጣ የሚሻ ሰው ካለ እሱ ለኛ ትርፍ ጥቅም ሀብት እንጂ ኪሳራ አይደለም::

ኢትዮጵያ ውስጥ አንዱም ችግራችን ጠንከር ያለ ሃሳብ ያላቸው፣ ሃሳብ ላይ ቆመው የሚሞግቱ ኃይሎች ጠፍተዋል:: እዚያም እዚያም የሚወራጨው ስሜት እንጂ ሃሳብ የለም:: እሱ ለኛም አይጠቅመንም፤ ለኢትዮጵያም አይጠቅማትም:: ምክንያቱም ሃሳብ እየደረጀና እየሞገትን ሲንሄድ እንማማራለን፤ አንዱ ከአንዱ ይማራል በዚህ ሂደት ውስጥ እናድጋለን:: አሁንም እኛ አልተዛነፈም ቦታችንን ክፍት ነው::

በመርህ ላይ የቆሙ ከመጀመሪያ እለት ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ በምንሠራው ሥራ መጋቢት 24 የተመለሱ እያገናዘቡ የሚደግፉ፤ በጎደለውም የሚመክሩ ሰዎች አሉ:: ሲደግፉንም ሆነ ሲቃወሙንም ያልገባቸው፤ አንድ ሳምንት ሲያወድሱ ሌላ ሳምንት ሲቃወሙ የሚታዩ ሰዎች አሉ፤ ይህንን ከኛ ይልቅ እነርሱ ሊሠሩበት ይገባል::

በእኛ በኩል ግን ውዳሴውንም ሆነ ወቀሳውም በሚዛን የምናየው ነው:: ከውዳሴውም ሆነ ከወቀሳው ትምህርት እንወስዳለን:: በውዳሴ ዘመን በጣም በርካታ ሽልማቶች፤ በጣም በርካታ ግብዣዎች ይቅርብን ብለን ትተናል:: መርጠን የወሰድናቸው አሉ፤ በጣም በርካታዎችን ግን አልተቀበልናቸውም:: ለምን ቢባል የውዳሴ መደጋገም በውጤትና በሥራ ካልተገለጠ ሊያዘናጋ እንደሚችል ስለምናውቅ የሚያስፈልገውን ያህል ካየን በኋላ አብዛኛውን እናመስግናለን ነው ያልነው::

በተቃውሞ ጎራም እንዲሁ ነው:: አንዳንድ ጊዜ መፈተሽ መመርመር ራሳችንን ማየት የሚገባን ጠቃሚ ሃሳቦች የሚነሱባቸው የተቃውሞ አይነቶች አሉ:: ያላየናቸው ያላስተዋልናቸው ልንማርባቸው የሚገቡ ጉዳዮች ሲኖሩ ሰክነን እንማርባቸዋለን:: አንዳንዴም የኢትዮጵያ ፖለቲካ በአብዛኛው ሽረባ ነው::

አንድ ሰው አጀንዳ ፈጥሮ አጀንዳውን ሠርቶ ይለቀዋል እሱ እየተነተነ ብሩን ይሰበስባል:: ለእንዲህ ዓይነቱ ጉዳይ ደግሞ የምንመልስበት የግብረ መልስ ሚዛን በንጽጽር ከዚያኛው ዝቅ ያለ ይሆናል:: ከተቃውሞውም፤ ከውዳሴውም እየተማሩ እያሻሻሉ፤ቃል በተግባር እየገለጡ መሄድ ጠቃሚ ነው ብዬ አስባለሁ::

ኢቲቪ ፡- በብዙ ቃለ ምልልሶችዎ ፈተና ውስጥ ትልቅ ነገርን መሥራት ወይም ማሳካት ይቻላል የሚሉ ሃሳቦችን ያነሳሉ፤ እነዚህ በማብራሪያ ብናያቸው? ምን ዓይነት ትልልቅ ስኬቶችን በፈተና ውስጥ ማሳካት ተችሏል?

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፦ ፈተና ያው ፈተና ነው። አቅልለን ጉዳት ወይንም ፈታኝ ሁኔታን አያመጣም ብለን የምናልፈው የምናቃልለው ጉዳይ አይደለም። ፈተና ፈተና ነው። ግን ያ ፈተና በውስጣችን የታመቀ ያልተለማመድነው ፣ በእለት ከእለት እንቅስቃሴያችን እምብዛም ያላወቅነው፣ የተደበቀ አቅም ደግሞ ያወጣል። ሰዎች ምን ይላሉ ፣ ሰው ሁሉም ሰው ተለክቶ ተሰፍሮ የማያልቅ ብቃት አለው ይላሉ።

ግን ያንን ብቃቱን አያውቀውም፤ ያን ብቃቱን አይመነዝረውም። ያንን ብቃቱን እንዲመነዝረው የሚያነሳሱ/ፕሮቮክ የሚያደርጉ ተግዳሮቶች አንዳንድ ጊዜ ከፍተኛ ውጤት ያመጣሉ። ለምሳሌ አሁን እዚህ አንደኛ ፎቅ ለይ ተቀምጠን እያለን ፣ አንደኛ ፎቅ ነው፣ ጉዳት አይደርስብሽም እስኪ ዝለይ ብልሽ ብትሞቺ አታደርጊውም። እሰበራለሁ፤ እጎዳለሁ አላደርገውም ነው የምትይው።

ነገር ግን በአቅራቢያችን ከፍተኛ ፍንዳታ ቢሰማ፤ ወደእዚህ ከፍተኛ ድምፅ የሚሰማ የሚመጣ አደጋ ቢሰማሽ፤ ኮንሸስ /ንቁ አእምሮሽ ሳያውቅ ፤ መቼ እንዴት እንደወሰንሽ ሳታውቂ ሰብ ኮንሸስ / አእምሮሽ መርቶሽ ከነበርሽበት ከዚህ ከፍታ ዘለሽ ትወርጂያለሽ። ያንን ዝላይ በኖርማል ጊዜ ድጋሚ ብትባይ ላትሞክሪው ትችያለሽ። ያ የመጣው አደጋ ነው የማታውቂውን ጉልበት የሰጠሽ። ያ የመጣው አስፈሪው ጉዳይ ከዚህ ፍርሃት በላይ ስለሆነ ሌላ የማታውቂውን ብቃትሽን አወጣው ማለት ነው።

በፈተና ጊዜ ትላልቅ ስኬት ያስመዘገቡ ሀገራት አሉ፤ ብዙዎቹም እንደዛ ናቸው። ለምሳሌ ደቡብ ኮሪያን ብንወስድ በዓለም ለይ ስኬታማ የአየር መከላከያ ሥርዓት ከፈጠሩ ሀገራት መከላል አንዷ ናት። ይህንን ምን አመጣው ካልን ሰሜን ኮርያ በማንኛውም ሰአት ሮኬት እና ሚሳእሎች ተኩሳ ልታጠፋን ትችላለች የሚል ስጋት ስላለ፤ ያንን ስጋት ለማስቀረት በጣም ተመራጭ እና ተወዳዳሪ የሆነ የአየር የመከላከያ ሥርዓት/ ሲስተም ሠርተዋል።

የፈጠሩት እነሱ ናቸው፤ መነሻው ግን ስጋት አለ ያስጋት ሊያጠፋን ይችላል የሚለው በውስጡ መኖሩ ነው። ጃፓን ጀርመን ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ሀገራቸው ፈርሶ ፣ ድህነት እና መፍረስ ያለውን አደጋ እንደ ማህበረሰብ አምነው ፣ ተገንዝበው፣ ጨክነው ሠርተው በጥቂት አሰርት ዓመታት ውስጥ ሀገሮቻቸውን የገነቡበት መንገድ፤ ያዩት ስጋት፤ ያዩት አደጋ ተመልሶ እንዳይመጣ ሀገር መገንባት እንዴት እንዳለበት አምነው ስለሠሩ ነው።

ሁላችንም ከፊታችን የሆነ ነገር እንዳለ ስናስብ፤ በተገራ መንገድ ፣ ፍረሃት መገራት አለበት ፣ ያልተገራ ፍርሃት ጥፋት ሊያመጣ ይችላል። እየፈራን ያንን ፍርሃት ለመከላከል የምንሠራው ሥራ ግን የማናውቀውን ብቃት ሊያወጣ ይችላል። ለምሳሌ በእኛ ሁኔታ ከለውጡ በፊት የነበረው አጠቃላይ ሕግ አስከባሪ ተቋማት፤ መከላከያው ደህንነቱ ሳይበር ሴኪዩሪቲ ተቋም የነበረውን ብቃትና ዛሬ ያለውን ብቃት ማወዳደር አይቻልም።

በጣም ከፍተኛ ልዩነት ያለው ነው። ዛሬ ያለው ሕግ አስከባሪ ምንም አይነት ስጋት ከዚህና ከእዛ ቢፈጠር ኢትዮጵያ ካለምንም ችግር እንደምትቋቋመው ምንም ጥርጥር የለውም። ከፍተኛ ብቃት ፈጥረናል። ያኔ ጥይት እንለምናለን አሁን ጥይት እናመርታለን። ያኔ በርካታ ነገሮች እንገዛለን አሁን እናመርታለን። ያኔ ስንገዛ ብዙ ወዳጅ ስላልነበረን ግዢውም ችግር ነው፤ ልመናውም ገንዘቡም ችግር ነው።

አሁን የተሻለ ገንዘብ የተሻለ ወደጅ የተሻለ የመግዛት አቅም አለን። መቶ ሰላሳ ሚሊዮን ሕዝብ ስላለን ብቻ ሳይሆን ሠልጥነን፤ ተደራጅተን በአዳዲስ እውቀትና ታክቲክ ሀገራችንን ሉዓላዊነታችንን ለመከላከል ያለን አቅም ለውድድር የሚበቃ ጉዳይ አይደለም። እውነቱን ለመናገር እነዛ ፈተናዎች ባይፈጠሩ ኖሮ በዛ ልክ እንደረጅ ነበር ወይ የሚለውን እንጠራጠራለን። መለስተኛ ሥራ እንሠራ ይሆናል፤ ግን በዛ ልክ መጠንከራችንን እጠራጠራለሁ።

የመከላከያን ብንተወውና የኢንሳን በንወስድ ከለውጡ በኋላ ሰፋፊ ቨርቹዋል ጥቃቶች ነበሩ በኢንተርኔት መብራት ሃይላችንን ቴሌኮሚዩኒኬሽናችንን ማጥቃት ነበር። የመሬት ብቻ ሳይሆን የቨርቹዋል ሉዓላዊነታችንን ለመጠበቅ በሳይበር ሴኪዩሪቲ የሚመጣን ጥቃት የመለየትና የመከላከል አቅም የገነባንበት ልክ በጣም ከፍተኛ ነው። ያኔ ጥቃቱ ባይመጣ ኖሮ በዚህ ልክ እንገነባው ነበር ወይ የሚለው ያጠራጥረኛል።

እና መከራ ነው ዋጋ አስከፍሏል፤ ሕይወት በልቷል ንብረት አውድሟል ብዙ ብዙ ጥፋት አጥፍቷል። በዚያው ልክ ደግሞ የማናውቀውን ብቃት፤ የማናውቀውን አቅም ፈጥሮ አልፏል። ጥፋቱ ቁስሉ አለ ጥቅሙ ግን ለልጆቻችንም ይሸጋገራል። ካለ ምንም ጥርጥር የኢትዮጵያ ሉዓላዊነት፤ የኢትዮጵያ አንድነት ዛሬ ለኢትዮጵያ መንግሥት ስጋት አይደለም። በተሟላ መንገድ ሉዓላዊነታችንን ከማንም ሃይል መጠበቅ እንችላለን። እንደዚህ ዓይነት ቁመና የፈጠርነው በሥራ ነው።

እንደ ሁለተኛ ምሳሌ ኮሮናን ልውስድ እንችላለን፤ ኮሮና ዓለምን የናጠ አደገኛ ተግዳሮት ነበር። እንደ ኢትዮጵያ ላለ ገና ለውጥ ለጀመረ ሀገር፤ እንደ ኢትዮጵያ ተቋም ላለመሠረተ ሀገር ሳይሆን ለትልልቆቹም፤ ገንዘብ ላላቸው የጤና ተቋማት ለገነቡትም ቢሆን ፈታኝ ነገር ነበር። ግን እኛ ልክ ኮሮና እንደመጣ አፍሪካውያኖች ይጎዳሉ ይሞታሉ ያልቃሉ የሚሉ ሟርቶች ነበሩ። ውይይት ስንወያይ እንደ መንግሥት አቋም ወስድን። ይሄ ሟርት ነው። ከዚህ ኮሮና ውስጥ በተቻለ መጠን ሕይወት እየታደግን፤ ለልጆቻችን ሀገር የምትቀጥልበትን መንገድ እንሥራ። በሽታ መጣ ብለን በራችንን ደጃችንን ዘጋግተን በረሃብ ማለቅ የለብንም። እንጠቀምበት ።

አንደኛ መሬት ጦም ማደር የለበትም አለን ሁሉም ሰው ይሥራ አልን ። መቼም መከራ ያሰባስባል ተሰባሰብን ሠራን ዛሬ በምርት የመጣው ውጤት ቀጣይ ሥራ የጠየቀም ቢሆን የዚህ ጊዜ መሬት ጦም ማደር የለበትም የሚለውና በዓመት ሁለት ጊዜ፤ ሦስት ጊዜ ማምረት ልምምድ መፍጠራችን በእጅጉ ለኢትዮጵያ አግዟል:: አየርመንገዳችንን ውሰጂ ኮሮና እንኳን በአየር እንቅስቃሴ ቀርቶ ሰው እርስ በእርሱም መገናኘት ያቆመበት ሲዝን/ ጊዜ ነው:: የእኛ አየር መንገድ ደግሞ አንድ ዓመት ስድስት ወር ከሥራ ውጪ ሆኖ ቢቆይ እንደሌሎች ሀብታም መንግሥታት ከፍተኛ ገንዘብ ኢንጀክት ስለማናደርግ ይወድቃል:: መቀጠል፤ ሰርቫይቭ ማድረግ ይቸግረዋል::

የለም ወንበር እንፍታና ካርጎ እናድርገው ብለን ዓለም ያገናኘ አየር መንገድን ከስድስት በመቶ በላይ እድገት አግኝቷል:: በኮሮና ውስጥ፤ በትልቁም በትንሹም ሀገር አየር መንገዶችን መንግሥታት ሳይደጉሟቸው ችግሩን የተሻገሩ የሉም:: ብዙ የወደቁ አሉ:: ሰርቫይቭ ያደረጉትም በመንግሥት ድጋፍ ነው:: እኛ አንድ ብር አልሰጠነውም::

ያንን ቻሌንጅ ወደሚመቸን መንገድ ቀይረን ተጠቀምንበት:: በጣም በርካታ ምሳሌዎችን ማንሳት እንችላለን:: ፈተናዎች፤ ኮሮናም ይሁን አንበጣ ጦርነትም ይሁን ሌላ መልክ ያለው ፈተኛ የራሱ የሆነ ኦፕርቺኒቲ ይዞ ይመጣል:: ያንን ለማየት የሰከነ ማንነት፤ የሚያስተውል ማንነት፤ ችግርን በችግርነቱ ብቻ ሳይሆን ከችግር ውስጥ የሚገኝ እድልን ፈልቅቆ የማውጣት ብቃት እስከተፈጠረ ድረስ በየአንዳንዱ ፈተና ውስጥ ጠቀሜታዎች አሉ፡።

ለምሳሌ አሁን ዓለም ላይ ያለው የታሪፍ ሁኔታ አስጊ ነው፤ አስጨናቂ ነው እንደ ኢትዮጵያ ላሉ ሀገራት ከባድ ነገር ነው:: ተቀምጠን ተወያየን:: እንጠቀምበት እድል አለው ችግሮች ብቻ አይደለም አልን ። እውነቱን ለመናገር ከፍተኛ ጥቅም እያገኘንበት ነው:: እናም ከማንኛውም ፈተና፤ ከማንኛውም ችግር በማስተዋል ተፈልቅቆ የሚወጣ ኦፖርችኒቲን ማየት እስከቻልን ድረስ ምንም ጥርጥር የለውም ፈተና የሚያመጣቸው እድሎች አሉ::

እነርሱን መጠቀም የሚያስችል ብቃት መፍጠር ደግሞ ያስፈልጋል:: በዚህ አግባብ ነው ኢዮጵያ ውስጥ ባለፉት ሰባት ዓመታት በጣም በርካታ ፈተናዎች ገጥመውን፤ለማመን የሚያስቸቸግሩ ድሎችን፤ ለማመን የሚያስደንቁ ተዓምር ሊባሉ የሚችሉ ድሎች ተመዝግበዋል::

እያንዳንዱን በየፈርጁ ማየት ይቻላል:: አስደማሚ፤ አስደናቂ ለማመን በእጅጉ የሚዳግቱ ተዓምራዊ ውጤት አይተንበታል:: መጋቢት 24 የተናገርነውን በእየለቱ እየኖርን፤ በየዕለቱ እየሳቅን፤ በእየለቱ እየተደመምን በውጤት ጉላት ወደምንፈልገው ሃሳብ እየተጓዝን ነው:: ያ ማለት ግን ማዕበል የለም ማለት አይደለም:: ማዕበሎች አሉ፤ ፈተናዎች አሉ:: እነርሱ ወደምንፈልገው ግብ የሚያደርሱን ጉልበት እንዲሆኑ አድርገን እንጠቀምባቸዋለን:: በዚያ መንገድ ነው እኔ የምገነዘበው::

ኢቲቪ ፡- የተለያዩ ትልልቅ ፕሮጀክቶች በሀገር ደረጃ ይከናወናሉ:: እነዚህን ፕሮጀክቶች ደግሞ እርስዎ በቅርብ በአካል ሄደው ይከታተላሉ:: ይህ ደግሞ በመሪ ደረጃ ብዙም የተለመደ አይደለም:: ይህንን ለምን ያደርጋሉ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፦ ስኬት መከናወን ፣ ጀምሮ መጨረስ ፣ካሰቡት ግብ መድረስ የማድረግ አቅምን ይፈልጋል:: ሳንተጋ፤ ሳንለፋ ከፈለግነው መዳረሻ ላይ መድረስ አይቻልም:: አቋራጭ መንገድ የምንፈልገውን ውጤት ሊያመጣልን አይችልም:: አንዳንዱ ጉዳይ በዚያ ትጋት ውስጥ ፣በዚያ መውጣት መውረድ ውስጥ ማለፍ ይጠይቃል::

በእርግጥ ይኸ በእኛ ሀገር ብቻ የሆነ ጉዳይ አይደለም። ማንኛውም ተቋም በወጉ ያልገነቡ ሀገራት፤ ሀገራቸውን ለማጽናት ፣ ለልጆች የሚሸጋገር መሠረተ ልማት ለመጣል፣ ፍላጎት የነበራቸው ሀገራት በሙሉ አመራሮች ወይም ኤጀንሲዎች፤ ቼንጅ አጀንቶች ከፍተኛ ሚና አላቸው። አሁን የምናየውን አውሮፓ ፣ያን መሠረተ ልማት ያን ሀገር የገነቡ የሆኑ ኤጀንቶች አሉ። ልክ አሁን እኛ በምናደርገው መንገድ ከዚያ በኋላ ያለው ትውልድ ያንን እየጠበቀ፤ እያሻሻለ፤ እያሳደገ የቀጠለ ሊሆን ይችላል::

ብዙ ሀገራት የምናየው ግን ወጣ ያለ ክትትል /ኢንተርቬንሽን በሚያስፈልግበት ሰዓትና በቂ ጠንካራ ተቋም በሌለበት ጊዜ ውስጥ ህልም ያላቸው ሰዎች ህልማቸውን ከውነው ለማየት ተጨማሪ ጉልበት/ ኤክስትራ ኢፈርት፤ ጥረት ይጠበቅባቸዋል:: ጥቂት ምሳሌዎችን /ኤግዛንፕሎች ማየት እንችላለን:: ለምሳሌ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ፈረንሳይ በጣም ጉዳት ከደረሰባቸው ሀገራት መካከል አንዷ ነች።

አውሮፓ አጠቃላይ ተጎድቷል፤ ፈረንሳም የዚያ ጉዳት ተቋዳሽ ነች። እና ቻርለስ ደጎል በወቅቱ የነበሩ አመራር፤የፈረንሳይ የያኔውን አውድ የማይገልጡ፤ የያኔውን ችግር የማይገልጡ አዳዲስ ሃሳቦች ይዘው ብቅ ብለው ነበር:: በእርግጥ ያኔ የነበሩ ዜጎች በቀላሉ የሚገዙት ሃሳብ አልነበረም:: ሁለቱን ምሳሌ ለማንሳት አንደኛው ፈረንሳይ ሀይ ስፒድ ሬል ዌ ያስፈልጋታል ብሎ ሬል ዌ መገንባት ጀመሩ:: በሃይ ስፒድ::

ሁለተኛው ክሊር ኢነርጂ ያስፈልገናል ብሎ ኒኩለር ክሊን ኢነርጂ መገንባት ጀመረ። ዛሬ በሁለቱ ሴክተሮች ከፍተኛ ተቃውሞ የነበረው ቢሆንም በወቅቱ፤በሬልዌ ብቻ ሳይሆን ሎጂስቲክ በአጠቃላይ በኮኔክቲቪቲ ፈረንሳይ በጣም ከአደጉት ከሚባሉ ሀገራት አንዷ ነች:: ሲጀመር እንደዚህ አልነበረም:: ዛሬ ያለውን ውጤት ዳጎል ላያየው ይችላል:: ግን በከፍተኛ ቅርብ ክትትልና አመራር ያንን ሥራ ለትውልድ አሳክቷል::

ኒኩለርን ብንወስድ ከራሽያና ከአሜሪካ ቀጥሎ ከፍተኛ አቅም ካላቸው ሀገራት ውስጥ የምትገባ ነች ፈረንሳይ። በአውሮፓ ፈረንሳይን የሚያክል የኒኩለር አቅም ያለው ሀገር የለም:: ያላቸው ሀገራት አሉ ግን ፈረንሳይን አያክሉም:: በብዙ መልኩ:: ያ የመጣው ያኔ በነበረው ኢንተርቬንሽን ነው ። ያ ኢንተርቬንሽን ግን ትዕዛዝ ብቸ አይደለም:: በጀት ብቻ አይደለም::

ያ የነበረው ኢንተርቬንሽን ቀጥተኛ አመራርን፤ ትጋትን፤ ክትትልን ይጠይቅ /ዲማንድ ያደርግ ነበር:: ምክንያቱም ፈርሷል ሀገሩ፤ ተቋም አልተገነባም ያኔ የፈረንሳይ ከፍተኛ አመራሮችና ጀነራሎች የሚጠበቁት ራሱ በሌላ ሀገር ወታደር ነው። በዚያ ልክ ሠራዊት/ አርሚ እንኳን አልገነቡም :: እንኳን እንደዚህ አይነት ቁምነገር ለማሰብ ተቋም አልነበራቸውም። ያ መሪ በቆረጠ መንገድ መከታተል መሥራት ነበረበት:: ውጤቱን ትውልድ ዛሬ ሀርቨስት እያደረገው ነው።

ከፈረንሳይ ወጥተን ሲንጋፖርን ብንወስድ የሲንጋፖር ጠቅላይ ሚኒስቴር ሊኳን ዩ፤ ሲንጋፖርን ከምንም ሀገር ያደረገ ሰው ነው:: ግን ከሁሉ የሚደንቀው እና ብዙ የተወቀሰበት አሁን የሚወደስበት አንዱ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ /የሀውሲንግ ኢንተርቬሽን ነው:: በሲንጋፖር ቤት ችግር ነበር፣ ቤት መገንባት አለበት የሚል እንደመንግሥት እምነት አለው:: ለዛ በጀት፤ ጊዜ ጉልበት ሰውቷል::

ግን የሚገርመው እሱ አይደለም በገነባው ቤት ውስጥ በአንዱ ህንጻ/ አፓርተመንት የወደፊቷ ሲንጋፖር በዘር በሃይማኖት እንዳትከፋፈል ብሎ ከተለያየ ጎሳዎች በግድ ነው እዚህኛው ፍሎር ላይ ኦሮሞ ካለ እዚህኛው ፍሎር ላይ አማራ ያኖረው:: አንድ ሰው አንድ ጎሳ ብቻ ተሰብስቦ ሊገባ አይችልም ቤቱ ውስጥ::

ይሄ ሰውዬ የቤታችን አይነት፤ አፓርተመንት ስለነበረ፣ የቤታችንን ሰፋት / ሳይዝ፣ ጎረቤቶቻችን ማን እንደሚሆኑ ጭምር የሚወስን ማነው እሱ? ከፈለግነው ጎረቤት ጋር እንዳንኖር ከእንትና ጋር ነው የምትኖረው እያልን የምንወስነው፤ ከፍተኛ ተቃውሞ፣ ከፍተኛ ቁጣ ነበር:: ከጥቂት ዓመታት በኋላ በዓለም ላይ ለዜጎቻቸው በቂ ቤት ካቀረቡ ሀብታም /ፕሮፐረስ ከሚባሉ ሀገራት አንዷ ናት ሲንጋፖር ማለት ሲጀመር ግን ዛሬ ሁላችንም የምንማርበት የምናከብረው ሰው ሆኗል::

እንዲህ አይነት ባህሪ ነበረው ሄዶ ሥራ የማየት፣ የመምራት፣ ነበረው:: ምክንያቱም ተቋም ጠንካራ ሳይሆን ግራንድ ሃሳብ ተይዞ እንዲሁ ሊከወን አይችልም:: አሜሪካንን ማየት እንችላለን በ1950ዎቹ መጨረሻ በ1960ዎቹ መጀመሪያ አካባቢ ጆሴፍ ኬኔዲ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት በነበረበት ጊዜ አፖሎን የስፔስ ሳይንስን ናሳን ፈጥሮ በስፔስ ሳይንስ ወደ ጨረቃ የመውጣት ህልም ነበረው፤ ያ ፕሮጀክት ወደ ሃያ አምስት ቢሊዮን ዶላር ገደማ ይጠይቃል::

የያኔው አሜሪካ ደግሞ የአሁኑ አሜሪካ አይደለም:: የሲቪል ራይት ሙቭመንት በስፋት ያለበት፣ ብዙ ሰልፎች ያሉበት፣ የዲሞክራሲ ጥያቄ የሚነሳበት፣ ሴቶች ጥቁሮች ይምረጡ የሚል ጩኸት የነበረበት፣ አክቲቪስቶች በጣም በስፋት የሚደመጡበት ዘመን ነው፤ ዘመኑ:: በዚያ ምክንያት የእሱ የሃያ አምስት ቢሊዮን ዶላር የአፖሎ ፕሮጀክት ኢንቨስትመንት እንደቅዱስ ሃሳብ የሚቀበሉት አልነበሩም::

ጊዜው አይመጥንም ነበር ለዛ ጉዳይ፤ ግን ጆን ኬኔዲ ናሳ ከኋይት ሀውስ ናሳ እየነዳ ሥራውን በቅርበት ይከታተል ነበር:: ከዚህ ጋር ተያይዞ የሚነገር ብዙ ታሪክ አለ፤ ለምሳሌ አንድ ጊዜ ለጉብኝት ሄዶ ሥራውን እያየ አንዷን ጽዳት ሠራተኛ አግኝቷት ሰላም ካላት በኋላ ምን እያደረግሽ ነው ሲላት አሜሪካ ከናሳ የምታደርገውን ጉዞ እየደገፍኩ ነው የሚባል በጣም ፕሮምነት የሆነ ንግግር አለ:: እያጸዳች ነው ግን የዛ ትልቁ ህልም አካል ነኝ አለች የሚለው ማለት ነው:: ይህ ሰው ማሰቡ ብቻ፤ በጀት አሎክት ማድረግ ብቻ ሳይሆን ሥራውን በቅርበት ይከታተል ነበር::

ወደህንድ መጥተን ጠቅላይ ሚኒስትር ኔህሩን ብንወስድ፤ ህንድ እንደ እኛ “ዳይቨርስ የሆነ ሶሳይቲ ” ያላት ነች:: ብዙ ድህነት ያለበት ሀገር ነው:: ምግብ ዋና ጉዳይ የሆነበት ሀገር ነው:: ግን ጠቅላይ ሚኒስትር ኔህሩ ከባድ ኢንዱስትሪ ላይ ኢንቨስት ማድረግ አለብን፣ በከፍተኛ ትምህርት / ሀየር ኢዱክሽን ፤ በተለይም አይቲ ላይ ኢንቨስት ማድረግ አለብን የሚል ሃሳብ ይዞ መጥቶ ብዙዎች ዳቦ ሳንበላ ከባድ ኢንዱስትሪ ምን ያደርግልናል ብለው ብዙ ጥያቄ አንስተዋል::

ዛሬ ህንድ ያላትን የኢኮኖሚ ለውጥ ያመጣ ግን ያ ኢንተርቬሽን ነው:: አንዳንዱ ኢንተርቬሽን የጊዜው ስለማይሆን ተቋማት በቀላል ወስደው አይተግብሩትም:: እነሱ እስኪለማመዱ ጊዜ ድረስ መሪዎች ወይም በየደረጃው ያሉ ሰዎች በቅርብ ክትትል ሥራውን መፈጸም አለባቸው:: ከተፈጸመ በኋላ የሚያይ ሰው ተምሮ መሰል ሥራ ሊሠራ ስለሚችል::

ለምሳሌ በእኛ ሁኔታ ዩኒቲ ፓርክ ሲሠራ እኔ እንደ ፕሮጀክት ማናጀር ነበርኩ:: ዶክተር ፍሰሀ፣ ዶክተር አብረሃም፣ ኢንጅነር ሀብታሙ ደግሞ ከኔ ስር የሚሠሩ ሰዎች ነበሩ:: ከኔ ጋር ሆነው ይከታተላሉ፣ ይገመግማሉ፣ ሥራ እንዴት እንደሚመራ አብረን እናያለን ልክ እንጦጦን ከጨረስን በኋላ ግን እያንዳንዱ የራሱን ፕሮጀክት እየያዘ ነው የወጣው::

ለምን ዶክተር ፍሰሀ ጅማን ይመራል፣ ዶክተር አብረሃም ሶማሌ ያለውን ፕሮጀክት ይመራል፣ ኢንጅነር ሀብታሙ አርባምንጭን ይመራል:: እኚህ ሰዎች ደግሞ በስራቸው በጣም በርካታ ሰዎች እየፈጠሩ ነው:: አሁን እኔ ዩኒቲን በምከታተልበት መልክ የአርባምንጩን ወይም የጅማውን ፕሮጀክት አላይም:: ባለቤት አለው፣ ሪፖርት ይቀርብልኛል፣ ቪዲዮ ይቀርብልኛል፣ ሲያስፈልግም ሄጄ አየዋለሁ::

እንደዚህኛው ግን በየቀኑ ከትትል አይጠበቅብኝም:: እዚህ አስፈልግ ነበር፤ ቲሙ እስኪሠራ ሃሳቡን የሚጋሩ፣ አብልጠው የሚሠሩ፣ ፓሽኑ ያላቸው፣ ልምድ ያካበቱ፤እውቀቱ ብቻ ሳይሆን ክህሎ ያላቸው፤ ተለማምደው ክህሎት / ስኪል ዴቭሎፕ ያደረጉ አመራሮች ሲፈጠሩ ደግሞ እኔ ወደሌሎች ሥራዎች ትኩረት እያደረኩ እሄዳለው::

ለምሳሌ አዲስ አበባ የመጀመሪያው ዙር ኮሪዶር ሲሠራ እያንዳንዱን ኮሪዶር የሚያስተባብሩ ሰዎች ኦልሞስት በየቀኑ፣ በየሳምንቱ አገኛቸዋለሁ፣ በየቀኑም ሥራውን አያለሁ፣ ኮሜንት አደርጋለሁ፣ ጨምሩ ቀንሱ እላለሁ በመጀመሪያው ዙር::

በሁለተኛው ዙር ቢያንስ በሃምሳ ፐርሰንት ቀንሷል ያነገር:: አሁንም እከታተላለሁ፣ አያለሁ ግን የክትትሉ ዴክስ ከአንደኛው ዙር አንጻር ቀንሷል:: ምክንያቱም በአንደኛው ዙር የአዲስ አበባ ከተማ አመራሮች እንደዚህ አይነት ሥራ ሠርተው አያውቁም:: ቢሮ ተቀምጠው የመገመገም፣ የተለመደውን የሥራ ባህሪ እንጂ ፊልድ ላይ ዎክ እያደረጉ መሥራት ብዙ አልተለመደም::

በአንደኛው ዙር አብረን ሠራን በሁለተኛው ዙር አብዛኛውን ራሳቸው ይሠራሉ፤እኔ ደግሞ ማየት ባለብኝ ልክ አያለሁ:: ይህ አሠራር እና አካሄድ አንድ ነገር አልቆ ለማየት፣ ጨርሰን ለማየት በእጅጉ የሚጠቅም ነገር ነው:: እኛ በዓይናችን ያላየንውን፣ ድጋፍ ያልሠጠነውን ነገር፣ በጀት ብቻ አሎኬት አድርገን ውጤት ልናገኝ አንችልም::

ለምሳሌ ህዳሴን መውሰድ ይቻላል፤ ህዳሴ እስከ አንደኛው ሁለተኛው ሙሌት ድረስ በየጠዋቱ አንድ ሰዐት፣ ለአንድ ሰዐት ሩብ ጉዳይ፣ አንድ ሰዐት ከሩብ አካባቢ ባለው ጊዜ ውስጥ በየቀኑ ለፕሮጀክት ማናጀሩ እደውልለታለሁ:: ከሴኩሪቲ ቀጥሎ የምከታተለው ውጊያ እያደረግኩ እደውልለታለሁ በውጊያ ቦታ ላይ::

ምክንያቱም ይፈልግ ነበረ:: አሁን ደግሞ መጠኑ እየቀነሰ፣ እየቀነሰ ሄደ ማለት ነው:: ለምን ነገርዬው መስመር እየያዘ ሲሄድ የእኔ ኢንቮልቭመንት እየቀነሰ ሲሄድ ሌሎች እየተረከቡት ይሄዳሉ፤ እኔ ደግሞ ወደአዲሱ ነገር ፊቴን ዞር አደርጋለሁ::

በዚህ መንገድ ልክ ካልሄድን በቀር ጀምረን መጨረስ፣ አስበን መከወን ፣ መከናወን ከባድ ነገር ነው:: ድካምን ፈርተን፣ ድካምን ሸሽተን ውጤት መመኘት ተገቢ አይደለም:: በእኛ ሁኔታ ደግሞ ተቋም የለም ብቻ ሳይሆን የተለመደው አሠራር መሪዎች ከቢሮ ሳይወጡ፣ ነገርየውን በዓይን ስለማያዩ በጣም በርካታ የውሸት ሪፖርቶች ይቀርባሉ::

ሌሎች ሰዎች መጥተው ሲያዩ እኮ ነው ህዳሴን ባዶ መሆኑን ያወቅነው፣ ሌላውንም ፕሮጀክት ያወቅነው እንጂ ቁጭ ብለን ሪፖርት ብንሰማ እንደዛ ላይመስለን ይችላል:: ስናየው ግን ብዙ ጣጣ በውስጡ አለ፤ እና ማየት ያስፈልጋል::

አሁን ሲወረድ አስር ቀበሌ ካለ ከአስሩ አምስቱ ስድስቱ በደንብ ወርደ,ው በየሰው ጓሮ እየሄዱ ስንት ዶሮ እንዳለ፣ ስንት ላም እንዳለ፣ ስንት ቤተሰብ እንዳለ፣ ምን ያክል አቅም/ ፖቴንሻል እንዳለ የሚያውቁ የቀበሌ ሊቀመንበር ባሉበት ቦታ የተሟላ መረጃ/ ዳታ አለ፣ የተሟላ ሥራ አለ፣ ሰላም አለ:: ቀበሌ ሊቀመንበር ብዙ በማይወርዱበት፣ በማይከታተሉበት፣ ማን እንደገባ ማን እንደወጣ እነሱ ሰፈር በማያውቁበት ሁኔታ ውስጥ ችግር አለ::

ክትትል በቀበሌም ደረጃ ያስፈልጋል:: በክፍለ ከተማም ብናስብ ወርደው ሥራን የሚመሩ ክፍለ ከተማ አመራሮች ባሉበት ክፍለ ከተማ እና ቢሮ ተቀምጠው በሚሠሩ ሰዎች አንድ አይደለም:: አንድ አይደለም ሥራው:: በየትኛውም ቦታ ብናይ ወርዶ ሥራውን እያዩ የሚመሩ ሰዎች ካሉ ሥራ ይፈጥናል፣ ይከወናል:: ያንን ልምምድ ማሳደግ ያስፈልጋል:: ደግሞም ትምህርት ይገኝበታል::

እውነት ለመናገር በማናውቃቸው የሥራ መስኮች ውስጥ ከባለሙያ ስንነጋገር ለምን ሆነ ስንል፣ ለምን አታፈርስም ስንል፣ ለምን አትቀጥልም ስንል ብዙ ነገር እንማራለን:: ከውድቀት እና ትምህርትም ይገኝበታል ሥራም ይቀላጠፋል፣ ደግሞ እንደዛ አይነት ጉልበት ሰጪ ክትትል ሠብዓዊ ባህሪ ነው::

ሰው ቁጥጥር ይፈልጋል፤ ለዛም አስፈላጊ ስለሆነ ነው እንደዛ የማደርገው:: አድካሚ ነው ግን ደግሞ በጣም ደስተኛ ነኝ:: ጀምሬ ያልጨረስኩት ነገር የለም:: ጀምሬ፣ አስቤ ያልሠራሁት ፕሮጀክት የለም:: ብዙ ጉዳይ የማይመስሉ ነገሮችን እናስባለን:: በእኛ አቅም የማይታሰቡ፣ ግን ያልቃሉ፤ ክትትል ስላለ ያልቃሉ::

አሁንም እንደዛ ነው ምንም ስጋት የለኝም:: ኢትዮጵያን ለማበልጸግ መሠረት እንጥላለን ብለን ቃል የገባንውን ነገር ምንም ጥርጥር የለውም መሠረት እንጥላለን:: እናደርገዋለን:: ሃሳቡ አለን፣ የሃሳብ ግልጽነት /ክላሪቲ ኦፍ ቶውት አለ፣ መሰጠቱ / ዲቮሽኑ አለ:: ሃሳብ ብቻ ሳይሆን ለመከወን የሚያስችል ጉልበት/ ኢነርጂ አለ:: በዚያ ምክንያት ሕዝባችንን ይዘን በጣም ሰፊ ጉልበት አግኝተናል:: ብዙ መሥራት የሚችሉ ሰዎች እየመጡ ስለሆነ ምንም ጥርጥር የለውም:: የኢትዮጵያን ብልፅግና መሠረት እስክንጥል ድረስ ትጋቱም ውጤቱም ይቀጥላል::

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ግንቦት 30 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You