በዋና ኦዲተር መስታወት የሚገለጠው፣ ግን የማይፀዳው የተቋማት ጓዳ

 መነሻ ሃሳብ

ከሰሞኑ በተለያዩ መገናኛ ብዙሃን የተሰራጨው ዜና ቀልቤን ሳበው። ዜናውም ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት በኦዲት ምርመራው የደረሰበትን እና ተመላሽ እንዲሆን አስተያየት የሰጠበትን ከስድስት ነጥብ ስምንት ቢሊዮን ብር በላይ ሂሳብ ተመላሽ አለመሆኑን ስለመናገሩ የሚገልጽ ነበር። ይሄንን ዜና ሳይና ስሰማ በአእምሮዬ የሚመላለሰውን ‘የመንግሥት በጀት እና አጠቃቀሙን በተመለከተ ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት በየዓመቱ የሚያወጣቸው የኦዲት ግኝት ሪፖርቶች እና የሚያቀርባቸው ምክረ ሃሳቦች ምን ያህል ተፈጻሚ ናቸው?’ የሚለውን ጉዳይ የበለጠ እንድፈትሽ አነሳሳኝ።

በዚህች አጭር ጽሑፍም ምልከታዬም ሆነ ዳሰሳዬ የማተኩረው ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤቱ ይፋ ባደረጋቸው የፋይናንስ እና ሕጋዊነት ኦዲት ግኝቶች ላይ ብቻ ይሆናል። ለዚህም የ2012፣ የ2013 እና የ2014 የኦዲት ግኝቶችን ከነ ምክረ ሃሳቦቻቸው ከዋና ኦዲተር የየዓመቱ የሪፖርት ሰነዶች ላይ በመቀነጫጨብ ለመጠቋቆም የምሞክር ሲሆን፤ በእነዚህ ዓመታት የተከናወኑ የኦዲት ተግባራት ውጤትስ ስለ ተቋማት የበጀት አጠቃቀም፣ እንዲሁም የዋና ኦዲተር ግኝቶች ላይ ተመስርቶ በሕግ በተቆጣጣሪውም ሆነ በፍትህ አካል እየተወሰደ ያለው የእርምት ርምጃ ምን ይጠቁማል የሚለውን ግላዊ ሃሳብም ለመሰንዘር እሞክራለሁ።

የ2012 ኦዲት እና ግኝት

የፌዴራል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት ሰኔ 22 ቀን 2013 ዓ.ም ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረበው ዓመታዊ የኦዲት ሪፖርት መሠረት፤ 117 የመንግሥት ባለበጀት መሥሪያ ቤቶች ላይ የኦዲት ሥራ አከናውኗል። በዚህም ወቅት 77 ሺህ 392 ብር የጥሬ ገንዘብ ጉድለት አግኝቷል። ያልተጠቀሙበትን በጀት ለገንዘብ ሚኒስቴር ፈሰስ መደረግ ሲገባው ያልተደረገ 39 ሚሊዮን 178 ሺህ 285 ብር ፈሰስ ሳይደረግ መቅረቱን አረጋግጧል። የውዝፍ ተሰብሳቢ ሂሳብን በተመለከተም በተደረገው ምርመራ በ90 መሥሪያ ቤቶች እና በ12 ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች በድምሩ ሰባት ቢሊዮን 480 ሚሊዮን 256 ሺህ 624 ብር የተሰብሳቢ ሂሳብ ሳይወራረድ ተገኝቷል።

ከዚህ በተቃራኒው ደግሞ 390 ሚሊዮን 26 ሺህ 874 ብር ገቢ ለመሰብሰብ በሚያስገድዱ አዋጆችና ደንቦች መሠረት ሳይሰበሰብ መቅረቱ፤ 70 ሚሊዮን 329 ሺህ 574 ብር ከሕንጻ ሥራ ተቋራጮች እና እቃ አቅራቢዎች በገቡት ውል መሠረት ባለመፈጸማቸው ሳይሰበሰብ መቅረቱ፤ 31 ሚሊዮን 64 ሺህ 249 ብር ወጪያቸው ተሸፍኖ የተማሩ ሠራተኞች የውል ግዴታቸውን ባለመወጣታቸው መሰብሰብ የነበረበት ሂሳብ ሳይሰበሰብ መቅረቱም በኦዲት ግኝቱ ተረጋግጧል። በመሆኑም በገቢ መሥሪያቤት መሰብሰብ የነበረበት ከሰባት ነጥብ 77 ቢሊዮን ብር በላይ በወቅቱ ያልተሰበሰበ ውዝፍ ገቢ መኖሩም ተረጋጧል።

በአንጻሩ 475 ሚሊዮን 11 ሺህ 10 ብር የተሟላ የወጪ ማስረጃ ሳይቀርብ በወጪ ተመዝግቦ የተገኘ፤ 34 ሚሊዮን 767 ሺህ 546 ብር ለተለያዩ ግንባታ፣ ግዢዎችና ለውሎ አበል፣ እንዲሁም 28 ሚሊዮን 718 ሺህ 783 ብር የግንባታ ሥራ ትዕዛዝ የውል ስምምነት ያልቀረበበትና ሕጉ ከሚፈቅደው በላይ በብልጫ (ያለአግባብ) ተከፍሎ የተገኘ፤ አንድ ቢሊዮን 209 ሚሊዮን 949 ሺህ 196 ብር የመንግሥት ግዥና መመሪያን ባልተከተለ መልኩ ግዢ ተፈጽሞ የተገኘ፤ ከ800 ሚሊዮን ብር በላይ ንብረቱ ገቢ ለመሆኑ ማስረጃ ሳይቀርብ ወጪ የሆነ ሂሳብ፣ እንዲሁም ከ37 ነጥብ 48 ሚሊዮን ብር በላይ በተሰብሳቢ ሂሳብ መመዝገብ ሲገባው በወጪ ተመዝግቦ የተገኘ ስለመሆኑም ነው የዋና ኦዲተር ሪፖርት የሚያመለክተው።

የ2013 ኦዲት እና ግኝት

የዋና ኦዲተር መሥሪያቤቱ ሰኔ 14 ዓ.ም ቀን 2014 ዓ.ም ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረበው ሪፖርት መሠረት፤ በ2013 በጀት ዓመት ሂሳብን በተመለከተ የ171 የፌዴራል መንግሥት ባለበጀት መሥሪያቤቶች የህጋዊነት ኦዲት ተጠናቅቆ ሪፖርቱን አቅርቧል።

በዚህ ሪፖርት እንደተመላከተውም ፤ በበጀት ዓመቱ፡- አንድ ሚሊዮን 513 ሺህ 651 ብር የጥሬ ገንዘብ ጉድለት፤ አንድ ሚሊዮን አንድ ሺህ 318 ብር በክፍያ መመሪያ ከተወሰነ የገንዘብ መጠን በላይ ወጪ የተደረገ፤ 87 ሚሊዮን 909 ሺህ 298 ብር ለገንዘብ ሚኒስቴር ፈሰስ መደረግ ሲገባው በባንክ ውስጥ የተጠራቀመ የገቢ ሂሳብ፤ አንድ ሚሊዮን 134 ሺህ 396 ብር በጉድለት ተሰብሳቢ መያዝ ሲገባው በእጅ ቆጠራ ሳይታይ በእጅ ያለ ጥሬ ገንዘብ ተብሎ ሲንከባለል የቆየ የጥሬ ገንዘብ ጉድለት ታይቷል። ይሄን መነሻ በማድረግም በጉድለት የታየው ጥሬ ገንዘብ ተገቢው ርምጃ ተወስዶ እንዲተካ እና የታዩ ድክመቶችም እንዲታረሙ ዋና ኦዲተር አሳስቦ ነበር።

የውዝፍ ተሰብሳቢ ሂሳብን በተመለከተም፤ በ133 መሥሪያ ቤቶች እና በ26 ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች በድምሩ 13 ቢሊዮን 100 ሚሊዮን 235 ሺህ 836 ብር፣ እንዲሁም ከአራት የሥራ ተቋራጮች የሚፈለግ ያልተወራረደ ወይም ያልተሰበሰበ የቅድመ ክፍያ 10 ሚሊዮን 183 ሺህ 865 ብር በደንቡ መሠረት ሳይወራረድ ተገኝቷል። በዚህ መልኩ ውዝፍ ያልተወራረደ ሂሳብ የተገኘባቸው ተቋማትም ሆነ የገንዘብ ግኝቱ ከ2012 አንጻር ጭማሪ ማሳየቱን ነው ሪፖርቱ ያመላከተው። ለምሳሌ፣ ከገንዘብ አንጻር የአምስት ቢሊዮን 619 ሚሊዮን 979 ሺህ 211 ብር ወይም 75 በመቶ ጨምሯል።

በዚህ ረገድ ከፍተኛውን ድርሻ የያዙ ተቋማት ተብለው የተቀመጡትም፤ ጤና ሚኒስቴር ከአራት ቢሊዮን ብር በላይ፣ የብሔራዊ አደጋ ስጋትና ሥራ አመራር ኮሚሽን ከአንድ ነጥብ ዘጠኝ ቢሊዮን ብር በላይ፤ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ፣ ባህርዳር እና ጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲዎች እያንዳንዳቸው ከ420 ሚሊዮን ብር በላይ፣ እንዲሁም የቀድሞው የውሃ ልማት ፈንድ ጽ/ ቤት ከ378 ሚሊዮን ብር በላይ ይገኙበታል።

ከገቢ ሂሳብ አኳያም፤ በገቢ ግብር፣ በቀረጥና ታክስ መልኩ በተለያየ አግባብ መሰብሰብ ሲገባው ያልተሰበሰበ 410 ሚሊዮን 894 ሺህ 750 ብር፤ የጉዳት ካሳ ቅጣት መሰብሰብ ሲገባው ያልተሰበሰበ 43 ሚሊዮን 601 ሺህ አንድ ብር፤ እንዲሁም መንግሥት ወጪ ሸፍኖላቸው በውጭ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የተማሩ የውል ግዴታቸውን ባለመወጣታቸው መሰብሰብ ሲገባው ያልተሰበሰበ አንድ ሚሊዮን 973 ሺህ 328 ብር ገቢ ሳይሰበሰብ ተገኝቷል።

በዚህ መልኩ ከሚገለጹ አሃዞች በተጓዳኝ፣ የተለያዩ የወጪ አሰራር ጉድለቶች ስለመገኘታቸውም ነው ሪፖርቱ የሚያሳየው። በዚህም መሠረት በ41 መሥሪያ ቤቶች እና አንድ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት የተሟላ ማስረጃ ሳይቀርብ 139 ሚሊዮን 723 ሺህ 599 ብር በወጪ ተመዝግቦ ተገኝቷል። በ87 መሥሪያ ቤቶች እና በሁለት ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች ከደንብና መመሪያ ውጪ 89 ሚሊዮን 238 ሺህ 375 ብር ያለአግባብ ክፍያ ተፈጽሟል።

በ16 መሥሪያ ቤቶች እና በአንድ ቅ/ጽ/ቤት በመሥሪያ ቤቱ ለሌሉ እና ከሥራ ለተሰናበቱ ሠራተኞች 341 ሺህ 382 ብር ደመወዝ ተከፍሏል። እንዲሁም በ18 መሥሪያ ቤቶች በሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ያልተፈቀደ ሠራተኞችን በመቅጠር 77 ሚሊዮን 855 ሺህ 816 ብር ተፈጽሟል፡፡ በ12 መሥሪያ ቤቶች ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ሳይፈቅድ 30 ሚሊዮን 743 ሺህ 565 ብር የትርፍ ሰዓት ክፍያ ተፈጽሟል፡፡

በሌላ በኩል፣ ተቋማት ላገኙት አገልግሎት ክፍያ በሚፈጽሙበት ወቅት 42 ሚሊዮን 638 ሺህ 192 ብር በብልጫ መክፈላቸው፤ 583 ሚሊዮን 877 ሺህ 663 ብር ከግዥ አዋጅና መመሪያ ውጪ ግዢ መፈጸሙ፤ 10 ሚሊዮን 95 ሺህ 985 ብር በተሰብሳቢ ሂሳብ መመዝገብ ሲገባው በወጪ ተመዝግቦ መገኘቱንም ነው የኦዲት ሪፖርቱ ያረጋገጠው፡፡

የ2014 ኢዲት እና ግኝት

በፌዴራል መንግሥት መሥሪያ ቤቶች እና ድርጅቶች ሂሳብ ላይ የተከናወኑ የፋይናንስ እና ሕጋዊ ኦዲት፣ የፌዴራሉ መንግሥት ለክልሎች ለአስቸኳይ ጊዜ ርዳታ፣ ለመልሶ ማቋቋምና ለልማት ማስፋፊያ ለሚያስፈልጋቸው ወጪ የሚያደርገውን ድጎማ ያከናወነውን የኦዲት ሪፖርት ያካተተው የ2014 የኦዲት ተግባርም፤ እንደ ቀደሙት ሁሉ የተቋማትን የፋይናንስና ሕጋዊነት እንዲሁም የክዋኔ አቋማቸውን ያሳየ ነበር፡፡

ለምሳሌ፣ በጥሬ ገንዘብ ሂሳብ ላይ በተደረገ ኦዲት አንድ ሚሊዮን 306 ሺህ 863 ብር የጥሬ ገንዘብ ጉድለት የተገኘ ሲሆን፤ ስምንት ሚሊዮን 220 ሺህ 89 ብር ደግሞ ለባለመብቱ በቼክ መከፈል ሲገባው በጥሬ ገንዘብ ክፍያው መፈጸሙ ተረጋግጧል፡፡ በተመሳሳይ 94 ሚሊዮን 242 ሺህ 534 ብር ተቋማት በራሳቸው የውስጥ ገቢ እንዲሸፍኑ በአዋጅ ተፈቅዶላቸው ነገር ግን በዓመቱ እንዲጠቀሙ ከተያዘላቸው በላይ የሆነውን ተራፊ ገንዘብ ወደ ማዕከላዊ ግምጃ ቤት አለማስገባታቸው ታውቋል፡፡

በዚህ መልኩ በጥሬ ገንዘብ የታየው ጉድለት በአስቸኳይ ተመላሽ እንዲሆን፣ የተሰጣቸውን ኃላፊነት ዘንግተው ገንዘቡን ባጎደሉ ሠራተኞች ላይም አስተዳደራዊም ሆነ ሕጋዊ ርምጃ እንዲወሰድ፤ እንዲሁም ከመመሪያ ውጪ በቼክ መከፈል የሚገባውን በጥሬ ገንዘብ የመክፈል ሂደትም የመንግሥትን ገንዘብ ላልተገባ ዓላማ እንዲውል ምክንያት ሊሆን እንደሚችልም ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤቱ በወቅቱ አሳስቦ ነበር፡፡

ውዝፍ ተሰብሳቢ ሂሳብን በተመለከተም፣ ኦዲት በተደረጉ 131 መሥሪያ ቤቶች በድምሩ 15 ቢሊዮን 125 ሚሊዮን 179 ሺህ 526 ብር በወቅቱ ያልተወራረደ/ያልተሰበሰበ ሂሳብ መኖሩ ታውቋል፡፡ በዚህ ረገድ ከሚጠቀሱ ተቋማት መካከል ጤና ሚኒስቴር ከሁለት ነጥብ ስምንት ቢሊዮን ብር በላይ፣ የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ፣ የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ፣ የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ከ797 ሚሊዮን ብር በላይ እንዲሁም የትምህርት ሚኒስቴር ከ747 ሚሊዮን ብር በላይ በቀዳሚነት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡

ከገቢ ግብር፣ ቀረጥ እና ታክስን ከመሳሰሉ የሚሰበሰብን ገቢ በተመለከተም፣ ከ86 ሚሊዮን 611 ሺህ ብር በላይ በተለያዩ የገቢ ሰብሳቢ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች መሰብሰብ የሚገባው ገቢ ሳይሰበሰብ ቀርቷል፡፡ ሆኖም ይሄ ከተለያዩ ተቋማት መሰብሰብ የሚገባው ገቢ የመንግሥት ገቢ ሕግ በሚፈቅደው መሠረት መሰብሰብ እንዳለበት ነው ዋና ኦዲተር ያሳሰበው፡፡

ካልተሰበሰበ ውዝፍ የገቢ ሂሳብ ጋር በተያያዘም፤ ከጉሙሩክ ቀረጥና ታክስ፣ ከግብር እዳ እና መሰል ዘርፎች በድምሩ 13 ቢሊዮን 428 ሚሊዮን 501 ሺህ 194 ብር ከአንድ ዓመት እስከ ስድስት ዓመት ያልተሰበሰበ ውዝፍ እዳ መኖሩን ነው ዋና ኦዲተር ያረጋገጠው፡፡ ዋና ኦዲተርም ይሄ ሀብት ተሰብስቦ ቢሆን ኖሮ መንግሥት ለሚያከናውናቸው ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ መሠረተ ልማቶች የሚኖረውን ሚና በማመልከት፤ የገቢ አሰባሰቡ ትኩረት ተሰጥቶት እንዲከናወን፣ ያልተሰበሰበውም ውዝፍ እንዲሰበሰብ በጥብቅ አሳስቧል፡፡

ከዚህ በተቃራኒው ደግሞ፣ 142 ሚሊዮን 237 ሺህ 847 ብር ተቋማት የዋጋ ተመን ሳይኖራቸው ገቢ የሰበሰቡ መሆኑ የታወቀ ሲሆን፤ በአንጻሩ 52 መሥሪያ ቤቶች በድምሩ 307 ሚሊዮን 549 ሺህ 308 ብር የተሟላ የወጪ ማዘዣ ሳይቀርብ ወጪ ተመዝግቦ ተገኝቷል፡፡ ባልተሟላ መረጃ ወጪ ከመዘገቡ ተቋማት መካከል የንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር፣ የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን፣ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን እና ወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ይገኙበታል፡፡ በእነዚህ ተቋማት የታየው የአሰራር ክፍተትም በቀጣይ ሊታረም እና ያልተሟላ ማስረጃ ላልቀረበላቸው የወጪ ሂሳቦችም የተሟላ ማስረጃ እንዲቀርብላቸውም ነው ዋና ኦዲተር ያሳሰበው፡፡

በተመሳሳይ መልኩ ከደንብና መመሪያ ውጪ ክፍያን መፈጸም በ60 መሥሪያ ቤቶች የተስተዋለ ሲሆን፤ በዚህም 134 ሚሊዮን 289 ሺህ 678 ብር ከደንብና መመሪያ ውጪ ያለአግባብ ክፍያ መፈጸሙን ነው ዋና ኦዲተር ያረጋገጠው፡፡ ከዚህ በተጓዳኝ በ16 መሥሪያ ቤቶች 362 ሺህ 677 ብር ከሥራ የተሰናበቱና ተቋማቱን ለለቀቁ ሠራተኞች ያልሰሩበትን ደመወዝ ከፍለው ተገኝተዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ በ52 መሥሪያ ቤቶች 23 ሚሊዮን 225 ሺህ 360 ብር ከደንብና መመሪያ ውጪ አላግባብ በብልጫ ክፍያ መፈጸሙ፤ እንዲሁም ጉምሩክ ኮሚሽን ዋናው መሥሪያ ቤትን ጨምሮ በ82 መሥሪያ ቤቶች 592 ሚሊዮን 454 ሺህ 328 ብር የግዥ አዋጅና መመሪያን ያልተከተለ ግዢ መከናወኑን፤ በ14 መሥሪያ ቤቶች 42 ሚሊዮን 658 ሺህ 268 ብር ንብረቱ ገቢ ለመደረጉ ማስረጃ ሳይቀርብ ሂሳቡ በወጪ ስለመመዝገቡ፤ በዘጠኝ መሥሪያ ቤቶች 28 ሚሊዮን 623 ሺህ 796 ብር በተሰብሳቢ ሂሳብ መመዝገብ ሲገባው በወጪ ተመዝግቦ መገኘቱን ነው ዋና ኦዲተር ያረጋገጠው፡፡

በሌላ በኩል የመጀመሪያ እና ጠቅላይ ፍርድ ቤቶችን ጨምሮ በ16 መሥሪያ ቤቶች አንድ ቢሊዮን 888 ሚሊዮን 659 ሺህ 402 ብር በተከፋይ የተከፈለ ቢሆንም፤ መቼ በተከፋይነት እንደተመዘገበ፣ ተከፋይ ሂሳቡ ለማን እንደሚከፈል የማይታወቅና የቆይታ ጊዜውን የሚገልጽ ማስረጃ የሌላቸው ስለመሆኑም ተረጋግጧል፡፡ ይሄን መሰረት በማድረግም ማስረጃ ላልቀረበላቸው ተከፋይ ሂሳቦች ተገቢው ማስረጃ እንዲቀርብና ትክክለኛነቱ እንዲረጋገጥ ነው ዋና ኦዲተር ያሳሰበው፡፡

የኦዲት ሪፖርቶቹ ጥቁምታ

የዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤቱ በየዓመቱ በሚያቀርባቸው የኦዲት ሪፖርቶቹ መረዳት እንደሚቻለው፣ ባለበጀት ተቋማቱ ለየበጀት ዓመቱ የተመደበላቸውን በጀት የፋይናንስ አስተዳደር አዋጅ፣ ደንብና መመሪያ በሚፈቅደው መሠረት በትክክል ሥራ ላይ ማዋላቸውን ለማረጋገጥ የሚያስችለውን የኦዲት ተግባር አከናውኗል፡፡ በዚህም የሂሳብ አያያዝ ግድፈቶች፣ የውስጥ ቁጥጥር ድክመቶች፣ ከሕግና አሰራር ውጪ የሆኑ ተግባራት ስለመኖራቸው አረጋግጧል፡፡

የጥሬ ገንዘብ እና የባንክ ሂሳብ አያያዝ፣ ውዝፍ ሂሳቦች በወቅቱ አለመሰብሰብ እና አለማወራረድ፣ በብልጫ (አለአግባብ) የተከፈሉ ክፍያዎች፣ በገቢ ግብርና ታክስ ሕግ መሠረት ገቢዎችን አለመሰብሰብ፣ ደንብና መመሪያዎችን ያልጠበቁ ግዢዎች፣ የውስጥ ገቢ አሰባሰብና አጠቃቀም ጋር በተያያዘ የተስተዋሉ ጉድለቶች በኦዲት ግኝቱ የተረጋገጡ ናቸው፡፡

በመሆኑም ዋና ኦዲተር እነዚህን ከሕግ እና አሰራር ውጪ የሆኑ ተግባራት የፈጠሯቸውን የሂሳብ ግኝቶች ከማመላከት እና የማስተካከያ እርምት እንዲወሰድባቸው ከማሳሰብ በተጓዳኝ፤ ቀደም ሲል ምክረ ሃሳብና ማሳሰቢያ የሰጠባቸው ግኝቶች ተፈጻሚነትን መለስ ብሎ የሚፈትሽ መሆኑን መረዳት ችያለሁ፡፡

ለምሳሌ፣ የ2014 በጀትን ኦዲት ሲያከናውን በ2013 በጀት ዓመት እና ከዚያ በፊት በተከናወኑ የኦዲት ሪፖርቶች መሠረት ርምጃ የተወሰደ መሆኑን የማጣራት ተግባር አከናውኗል፡፡ ይሄንን ምርመራ እና ግኝት አስመልክቶም በ2014ቱ የኦዲት ሪፖርት ላይ እንዳሰፈረው (የመገናኛ ብዙሃኑ ሰሞንኛ ዜና ሆኖ ይሄን ጽሑፍ እንድጽፍ ምክንያት የሆነኝም ይሄው ነው)፤ በ86 መሥሪያ ቤቶች ተመላሽ እንዲደረግ ተብሎ አስተያየት ከተሰጠበት ስድስት ቢሊዮን 883 ሚሊዮን 555 ሺህ 669 ብር ውስጥ፤ 44 ሚሊዮን 995 ሺህ 283 ብር ተመላሽ መደረጉን ማረጋገጡን ገልጿል፡፡

ይሄንን ገንዘብ ተመላሽ ካደረጉ ተቋማት መካከልም፤ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ዘጠኝ ሚሊዮን 750 ሺህ 571 ብር፣ የፌዴራል ቴክኒክ ትምህርትና ሥልጠና ኢንስቲትዩት 14 ሚሊዮን 760 ሺህ 365 ብር፣ የቅዱስ ጳውሎስ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል አምስት ሚሊዮን 95 ሺህ 250 ብር ተመላሽ በማድረግ ተጠቃሽ ናቸው፡፡

ምንም እንኳን በዚህ መልኩ ተመላሽ ያደረጉ ተቋማት እና ይሄ እንዲሆን የተደረገው መጠነኛ ጥረት የሚበረታታ ቢሆንም፤ አፈጻጸሙ ሲታይ ግን አጥጋቢ ያልሆነ ብቻ ሳይሆን፤ እጅጉን ዝቅተኛ ነው፡፡ ምክንያቱም ተመላሽ እንዲሆን ምክረ ሃሳብ ከተሰጠበት ብር አኳያ ሲታይ ዜሮ ነጥብ 65 በመቶው ብቻ ሲሆን፤ ቀሪው ስድስት ቢሊዮን 838 ሚሊዮን 559 ሺህ 886 ብር ተገቢው ርምጃ ባለመወሰዱ ተመላሽ መሆን አለመቻሉም ነው የተመላከተው፡፡ ይሄንን ለማረጋገጥ ደግሞ ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤቱ ከ2009 ጀምሮ ባደረገው የኦዲት ምርመራ ሂደት ተመላሽ እንዲደረግ ተብሎ ማሳሰቢያ ከሰጠባቸው ሂሳቦች ስንቶቹ ተመላሽ ተደረጉ የሚለውን ማየቱ በቂ ይመስለኛል፡፡

ለምሳሌ፣ በ2009 ምርመራው 228 ሚሊዮን 717 ሺህ 664 ብር ተመላሽ እንዲሆን አስተያየት ሰጥቶበት፣ ተመላሽ የተደረገው 12 ሚሊዮን 536 ሺህ 323 ብር (5 ነጥብ 48 በመቶው) ብቻ ነው። በ2010 ደግሞ 726 ሚሊዮን 712 ሺህ 897 ብር ተመላሽ እንዲሆን አስተያየት የሰጠበት ቢሆንም፤ ተመላሽ የሆነው ግን 122 ሚሊዮን 344 ሺህ 802 ብር (17 በመቶው) ብቻ ነው፡፡ በተመሳሳይ በ2011 ምርመራው አንድ ቢሊዮን 787 ሚሊዮን 421 ሺህ 15 ብር ተመላሽ እንዲሆን አስተያየት የሰጠበት ሲሆን፤ ተመላሽ የሆነው ግን 216 ሚሊዮን 823 ሺህ 793 ብር (14 ነጥብ 64 በመቶው) ብቻ ነው፡፡

የተሻለ ሂሳብ ተመላሽ እንደሆነበት የሚገለጸው የ2012 ሂሳብም ቢሆን፤ ተመላሽ እንዲሆን አስተያየት ከሰጠበት ሁለት ቢሊዮን 471 ሚሊዮን 480 ሺህ 929 ብር ውስጥ፣ አንድ ቢሊዮን 29 ሚሊዮን 166 ሺህ 927 ብር (41 ነጥብ 64 በመቶው) ነው መመለስ የቻለው፡፡ በ2013 ምርመራ እንዲመለስ አስተያየት የሰጠበት የስድስት ነጥብ 88 ቢሊዮን ብር ሂሳብም ቢሆን፤ ቀደም ሲል እንደተገለጸው ከ44 ነጥብ 99 ሚሊዮን ብር (ዜሮ ነጥብ 65 በመቶው) የዘለለ ሊመለስ አልቻለም፡፡ የ2014ን ጉዳይ ደግሞ በቀጣዩ የዋና ኦዲተር ሪፖርት ላይ በ2016 ሲወጣ የምናየው ጉዳይ ይሆናል፡፡

ይሄ የሚያስረዳው ደግሞ በየዓመቱ ተመላሽ እንዲሆን አስተያየት የሚሰጥበት ሂሳብ ቁጥር እጅጉን እያሻቀበ መምጣቱን ሲሆን፤ ከዚህ በተጓዳኝ ግን ተመላሽ የሚሆነው ሂሳብ (ምንም እንኳን ፐርሰንቱ ከፍና ዝቅ ቢልም፣ እንዲመለስ ከተባለው ሂሳብ አንጻር) ሲታይ እዚህ ግባ የማይባል መሆኑን ነው፡፡ በአንጻሩ ተመላሽ ሳይሆን ከዓመት ዓመት እየተንከባለለ የዘለቀው ሂሳብ ብዙ መሆኑ ብቻ ሳይሆን፤ ጊዜው እየረዘመ በመጣ ቁጥር ሳይመለስ የመቅረቱ ጉዳይ ሰፊ አየሆነ ይሄዳል፡፡

እንደ መውጫ

በወፍ በረርም ቢሆን በሪፖርቱ መመልከት እንደተቻለው በየዓመቱ የጥሬ ገንዘብ ጉድለት፣ ያልተወራረደ ውዝፍ ሂሳብ እንዲሁም በገቢ ሂሳብ ላይ የሚታዩ ችግሮች በየዓመቱ እያደጉ ከመሄዳቸውም በላይ፤ ችግሮቹን ለማረም እየተወሰደ ያለው ርምጃ ከችግሩ ስፋት አኳያ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም። ይልቁንም በጊዜው ተመላሽ መሆን ያልቻሉ ጥሬ ብሮችም ሆኑ፣ በወቅቱ መወራረድም መሰብሰብም ያለባቸው ውዝፍ ሂሳቦችና ገቢዎች በጊዜያቸው መከወን ባለመቻሉ በቆይታ ብዛት ያለመሰብሰብ እድላቸው እየሰፋ ነው፡፡

በመሆኑም ዋና ኦዲተር በየዓመቱ እንደሚለው ሁሉ፣ የሚታዩ የጥሬ ገንዘብ ጉድለቶች፣ እየጨመሩ ያሉ ውዝፍ የተሰብሳቢ ሂሳቦች፣ እንዲሁም ገቢ ሂሳቦች ሕጉ በሚፈቅደው መሠረት እንዲከወኑ ማድረግ ይገባል፡፡ በተለይም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣው የውዝፍ ተሰብሳቢ ሂሳብን ተከታትሎ ገንዘቡ እንዲመለስ ወይም እንዲወራረድ ማድረግ በእጅጉ አስፈላጊ ነው፡፡

ምክንያቱም፣ ይሄን ማድረግ ሲቻል በየዓመቱ የሚመደብ በጀት ለታለመለት ዓላማ እንዲውል ያስችላል፤ ለሕግና አሰራሮች መተግበርም እድል ይሰጣል፡፡ ከዚህ በተጓዳኝ ተጠያቂነትን በማስፈን ሀገርም ከሀብቷ ተጠቃሚ፣ ዜጎችም ከልማት ተቋዳሽ እንዲሆኑ ያግዛል፡፡ ይሄን ማድረግ ካልተቻለ ግን የሀገር ሀብት ለልማት ሳይሆን ለብክነት ይዳረጋል፤ ተጠያቂነትን ማስፈን ስለማይቻልም የብዙሃኑ ሳይሆን የጥቂቶችን ተጠቃሚነት ይፈጥራል፤ በጥቅሉ ሕግና አሰራር ተፋትተው የሀገር በጀት ላልተፈለገ ዓላማ እንዲውል እድል ይሰጣል፡፡

ይሄ እንዳይሆን ደግሞ የዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤቱ በየዓመቱ የሚያወጣቸውን የፋይናንስም ሆነ የክዋኔ ኦዲቶችን በወጉ መመልከት እና ተገቢውን እርምት መውሰድ ከሚመለከተው አካል ይጠበቃል። በተለይ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና የሕግ ተርጓሚው ወይም የፍትህ አካላት ይሄን የማድረግ የሕግም፣ የሞራልም ግዴታ እንዳለባቸው አውቀው ለሕጎች ተፈጻሚነት በቁርጠኝነት መንቀሳቀስ ይኖርባቸዋል፡፡

 ማሙሻ ከአቡርሻ

 ይህ አምድ በተለያዩ ፖለቲካዊ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ዜጎች ነፃ ሀሳባቸውን የሚሰጡበት ነው።በዓምዱ ላይ የሚወጡ ጽሁፎች የዝግጅት ክፍሉን አቋም አያመለክቱም።

አዲስ ዘመን ሰኞ ሐምሌ 3 ቀን 2015 ዓ.ም

Recommended For You

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *