የላቁ ትምህርት ቤቶች ለላቀች ኢትዮጵያ!

ትምህርት የሰው ልጅ ከፍ ያለ የማሰላሰል እና የመፍጠር አቅም፣ ዕውቀትና ክሒሎትን ከለውጥ አስተሳሰብ ጋር አቀናጅቶ የሚያጎናጽፍ ማዕድ ነው። ይሄ ማዕድ ደግሞ ሙሉ ሆኖ ተሰናድቶ የሚቀርበው በትምህርት ቤቶች ውስጥ ነው። ይሄ ለሰው ልጆች ምጡቅ አዕምሮ የሚያጎናጽፉት የትምህርት ማዕድና የማዕዱ ማቅረቢያ ትምህርት ቤቶች የሚኖራቸው ገጽታ ደግሞ የትምህርትን ማዕድነት ውጤታማ የማድረግም ሆነ ያለማድረግ አቅማቸው ከፍ ያለ ነው።

ምክንያቱም የትምህርት ቤቶች ሁኔታ ለተማሪዎች የሚቀርበውን የእውቀት ማዕድ በአግባቡ እንዲቀስሙት አልያም እንዳይቀስሙት ያደርጋልና ነው። በዚህ ረገድ በኢትዮጵያ ትምህርት ቤቶች ውስጥ የሚከናወን የመማር ማስተማር ሂደት ውጤታማነት ከዓመት ዓመት እያሽቆለቆለ ስለመሄዱ በርካቶች ሲናገሩ ቆይተዋል።

ባለፈው ዓመት በተሰጠው የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና የተገኘው ውጤት ደግሞ ይሄንን ብሂል ተጨባጭ እውነት ስለመሆኑ ማረጋገጫ የሰጠ ሆነ። እናም በኢትዮጵያ የሚታየው የትምህርት ጥራት ችግር ከምን የመነጨ ነው የሚለውን ለማወቅ በተደረገ ጥናት መሠረት አንዱና ቀዳሚው ጉዳይ ሆኖ የተለየው የትምህርት ቤቶች ደረጃ ዝቅተኝነት ነው።

የትምህርት ሚኒስቴር መረጃ እንደሚያመለክተው፣ በኢትዮጵያ ከ249 ሺህ በላይ ትምህርት ቤቶች ያሉ ቢሆንም፣ ከእነዚህ ውስጥ አንድም የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የትምህርት ሚኒስቴርን መመዘኛ አሟልቶ (ለመማር ማስተማር ሥራ ብቁ ሆኖ) አልተገኘም።

የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ እንዳሳወቁት ደግሞ፤ ከእነዚህ 249 ሺህ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ለትምህርት ብቁ ሆነው የተገኙት ዜሮ ነጥብ ዜሮ አንድ በመቶ (0.01%) የሚሆኑ በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ብቻ ናቸው። ከ86 በመቶ በላይ የሚሆኑት የአንደኛ እና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች፣ እንዲሁም ከ71 በመቶ በላይ የሆኑት የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ለትምህርት ቤትነት የማይመጥኑ ወይም ፍጹም ከደረጃ በታች ናቸው።

በመሆኑም ይሄንን ገጽታቸውን ለመለወጥ እንዲቻል «ትምህርት ለትውልድ» በሚል መሪ ሃሳብ የትምህርት ቤቶችን ደረጃ ለማሳደግ እና ትምህርት ቤቶች የተማሪዎች ውሎ መግቢያ ሳይሆን እውነተኛ እውቀት ማግኛ አውድ እንዲሆኑ በማስቻል ሂደት ውስጥ ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል የራሱን ዐሻራ እንዲያኖር ዕድል የሚሰጥ ሀገራዊ የትምህርት ንቅናቄ በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ አማካኝነት ይፋ ሆኗል።

ይሄ የንቅናቄ መርሃ ግብር ታዲያ፣ ከደረጃ በታች ያሉ እና ለመማር ማስተማር ሂደት ምቹና ብቁ ያልሆኑ ትምህርት ቤቶችን ደረጃ በማሳደግ ረገድ መንግሥት ብቻውን ሊወጣ የሚችለው ባለመሆኑ፤ በሂደቱ ሁሉም ዜጎች የበኩላቸውን እንዲያበረክቱ የሚያደርግ ነው። ለዚህም ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ በወቅቱ ባስተላለፉት መልዕክት «የላቀች ኢትዮጵያን ለመገንባት፤ ቀድመን የላቁ ትምህርት ቤቶችን አብረን እንገንባ!» ሲሉ ያሳሰቡት።

እርግጥ ነው በእውቀትም ሆነ በአመለካከቱ የበቃ ትውልድ መፍጠር የመንግሥት ኃላፊነት ብቻ አይደለም። ይልቁንም ወላጆች፣ ትምህርት ቤቶች፣ መምህራን፣ ባለሀብቶች፣ የተለያዩ ተቋማት፣ በጥቅሉ የመላውን ኅብረተሰብ ሚና የሚጠይቅ ነው። በዚህ ሂደት ግን አንዱ ጎድሏል፤ ትምህርት ቤት። በመሆኑም ዛሬ ላይ የትውልድ ዕውቀት አውድ መሆን የተሳናቸውን ትምህርት ቤቶች ወደ ግብራቸው ለመመለስ በጋራ መሥራት የግድ የሚልበት ጊዜ ላይ ተደርሷል።

«በትምህርት ላይ የምንሠራቸው ሥራዎች ወጣቶቻችን በተለዋዋጭ ዓለም ውስጥ ለመጓዝ የሚያስፈልጋቸውን ዕውቀት እና ክህሎት እንዲያገኙ የሚያደርግ ነው፤ በመሆኑም በየትኛውም የኢትዮጵያ ጫፍ የተማራችሁ ሁሉ ትናንት የተማራችሁባቸው ትምህርት ቤቶች ዛሬ የእናንተን ድጋፍ ይሻሉ፤» ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ማሳሰባቸውም ይሄንኑ ሃቅ የሚያረጋግጥ ነው።

ይሄ ዛሬ የኢትዮጵያ እና ትምህርት ቤቶቿ ድምጽ ነው፤ የተማሪዎቿም ህልምና ምኞት ነው፤ የዜጎቿም የወደፊት መዳረሻ ለመድረስ አቅም ለመገንባት ጡብ የማኖር ጅማሮ ነው፤ ስለ ሁሉን አቀፍ የዜጎች መብትና ተሳትፎ (የሴቶች፣ አካል ጉዳተኞች፣ ልዩ ድጋፍ የሚሹ ዜጎች፣…) እውን መሆን ብቻ ሳይሆን በሀገር ግንባታ ሂደት ውስጥ በእውቀትና አቅም ላይ የተመሠረተ ሚናቸውን እንዲያበረክቱ የማስቻል መንገድ ነው።

ይሄ እውን ይሆን ዘንድ ደግሞ የሁላችንንም ሃሳብ፣ ገንዘብ፣ ጉልበት፣ በጥቅሉ ባለንና በምንችለው ሁሉ ለትምህርት ቤቶች ደረጃ ዕድገት ሁሉን አቀፍ ሚናችንን ማበርከት ይጠበቅብናል። ይሄን ስናደርግ ሀገራችንን፣ ይሄን ስናደርግ ሕዝባችንን፣ ይሄን ስናደርግ ልጆቻችንን ወደ ከፍታ እያሻገርን መሆኑንም ልንገነዘብ ይገባል። ምክንያቱም ጉዞው የላቀች ኢትዮጵያን ለመገንባት፤ ቀድመን የላቁ ትምህርት ቤቶችን አብሮ የመገንባት እንደመሆኑ፤ ትምህርት ቤቶችን በማላቅ የላቀች ኢትዮጵያን እንገንባ!

አዲስ ዘመን ሰኞ ሐምሌ 3 ቀን 2015 ዓ.ም

Recommended For You

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *