በአንድ ጀምበር 500 ሚሊዮን ችግኞች በመትከል ለሀገራችን ፍቅራችንን፣ ለዓለምም ጽናታችንን እናሳይ!

የአየር ንብረት ለውጥ ዓለም አቀፍ ተግዳሮት ከሆነ ዓመታት ተቆጥረዋል:: ምንም እንኳን ለዚህ ችግር እንደ ኢትዮጵያ በማደግ ላይ ያሉ ሀገራት አበርክቶ እዚህ ግባ የሚባል ባይሆንም፤ የአየር ንብረት ለውጡ እያሳደረ ያለው ከፍ ያለ ጉዳት ግን በእጅጉ ፈታኝነቱን ቀጥሏል:: ድርቅ፣ ጎርፍ፣ ሰደድ እሳትና ሌሎችም ክስተቶች ደግሞ በእነዚህ ሀገራት ለሚኖሩ ሕዝቦች የረሃብ፣ የስደትና ሞት ምክንያት ሆነው ሕይወትን ፈታኝ አድርገውባቸዋል::

ይሄን ችግር ከመቋቋምና ከመከላከል አኳያ ሀገራት በየፊናቸው የየራሳቸውን ጥረት እያደረጉ ሲሆን፤ ዓለም በተባበሩት መንግስታት ድርጅት በኩል በ2030 እንዲሳካ የሚጠበቅ የዘላቂ ልማት ግብ፤ አፍሪካም በአፍሪካ ሕብረት በኩል በ2063 እንዲሳካ የሚጠበቅ አጀንዳ ቀርጸው እየሰሩ ይገኛሉ::

ኢትዮጵያም የዘላቂ ልማት ግቡንም ሆነ አጀንዳ 2063ትን ለማሳካት ብቻ ሳይሆን፤ ከዚህ ከፍ ባለ ከራሷ አልፎ የአየር ንብረት ለውጥን ተቋቁሞ ለመሻገር ለሌሎች በጎ ተምሳሌት የሆነን ስራ እያከናወነች ትገኛለች:: በተለይ ባለፉት አራት ዓመታት በዐረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር ስታከናውነው የቆየችው ተግባር በእጅጉ ውጤታማ እና የአካባቢ ጥበቃ ሥራ ከፍ ያለ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ እንዳለው የተረጋገጠበት ነበር::

በእነዚህ አራት ዓመታት 20 ቢሊዮን ችግኝ ለመትከል ታቅዶ በተሰራው ሥራ 25 ቢሊዮን ችግኝ መትከል ተችሏል:: ይሄ የአየር ንብረት ለውጥን ከመከላከል አኳያ ያለው ሚና እጅጉን የጎላ ሲሆን፤ ከዚህ በተጓዳኝ በአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር የተተከሉ ችግኞች በምግብ ራስን ለመቻል በሚደረገው ጥረት ውስጥ የራሳቸው አበርክቶ ያላቸው ፍራፍሬዎች ጭምር በስፋት የተተከሉበት እና ውጤታቸውም የታየበት ሆኗል::

በስኬት በተጠናቀቀው የመጀመሪያው ምዕራፍ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር ታዲያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የሃሳቡ አመንጪ ይሁኑ እንጂ፤ እሳቸው ከፊት ቀድመው በጀመሩትና ባስቀጠሉት ተግባር መላ ኢትዮጵያውያን ሥራውን የራሳቸው አድርገው የከወኑት መሆኑ ለውጤቱ ትልቁን ቦታ ይይዛል:: ለዚህ ዐቢይ ማሳያው ደግሞ መርሃ ግብሩ በተጀመረበት በመጀመሪያው ምዕራፍ በአንድ ጀንበር ከ20 ሚሊዮን ሕዝብ በላይ የተሳተፈበት ከ350 ሚሊዮን በላይ ችግኝ በአንድ ጀንበር የተተከለ መሆኑ ነው ::

ይሄ ደግሞ መርሃ ግብሩ ምን ያህል ሕዝባዊ መሰረት እንደያዘ እና ኢትዮጵያውያን በሀገራዊ ፕሮጀክቶቻቸው ላይ የማያወላዳ አቋም እንዳላቸው ያረጋገጠ ተግባር ነበር:: በአንድ ጀንበር ከ350 ሚሊዮን በላይ ችግኝ ሲተከልም ሆነ በአራት ዓመታት ውስጥ ከእቅድ በላይ 25 ቢሊዮን ችግኝ ሲተከል በሂደቱ ተሳታፊ የነበረው ከ20 ሚሊዮን የላቀ ሕዝብ ማንም ጎትጓች በራሱ ፈቃደኝነትና ተነሳሽነት የፈጸመው ነበር:: ሕዝቡ ለሀገሩ በማገልገሉ፣ ኢትዮጵያን አረንጓዴ በማልበሱ የተጎናጸፈው ደስታና እርካታ ከፍተኛ ነው::

ይሄ ከፍ ያለ የሕዝብ መሰረት የያዘ መርሃ ግብር ታዲያ በምዕራፍ አንድ በታየው ስኬት ተወስኖ የሚቀር አልሆነም:: ይልቁንም ተጨማሪ 25 ቢሊዮን ችግኞችን በቀጣይ አራት ዓመታት ውስጥ በመትከል በ50 ቢሊዮን ችግኝ ኢትዮጵያን የማልበስ ጉዞውን በዚሁ ዓመት በሁለተኛ ምዕራፍ የአረንጓዴ ዐሻ ራ መርሃ ግብር ሌ ላ ታሪክ ለመስራት ጉዞ ተጀምሯል::

የሁለተኛው ዙር የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብርም ገና ከጅምሩ በውጤት እየሄደ ሲሆን፤ እንደ መጀመሪያው ምዕራፍ ሁሉ ሌላ ታላቅ ታሪክን ለመጻፍ እቅድ ተይዟል:: እሱም ሃምሌ 10 ቀን 2015 ዓ.ም በመላው ኢትዮጵያ በሰፊ የሕዝብ ተሳትፎ በአንድ ጀንበር 500 ሚሊዮን ችግኝ የመትከል ዕቅድ ነው::

ይሄንን እቅድ ይፋ ያደረጉት የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር ሃሳብ አመንጪና መሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፣ “ ሃምሌ 10 ቀን 2015 ዓ.ም በአንድ ጀንበር 500 ሚሊዮን ችግኞችን በመትከል ታሪክ እንድንሰራ ጥሪ አቀርባለሁ!” በማለት ባስተላለፉት መልዕክት፤ የዕቅዱ ዕውን መሆን ለትውልድ የሚተርፍ ታሪክ መስራት ስለመሆኑ አስገንዝበዋል::

“የኢትዮጵያ ትክክለኛ መልክ ልምላሜ ነው!” የሚል ገለጻን ተጠቅመው ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህ መልዕክታቸው እንዳሰፈሩትም፤ “አረንጓዴ ዐሻራ ለእኛ ብዙ ነገራችን ነው:: የግብርና ምርታችንን ከፍ የሚያደርግና በምግብ ራሳችን እንድንችል የሚያበቃን ነው:: ወንዞች እስከ ወሰናቸው እንዲሞሉ አድርጎ የመስኖና የመጠጥ ውኃ እንዳይቋረጥ የሚያደርግም ነው:: የደን ሽፋንን አሳድጎ የአየር ንብረቱን የሚያስተካክል ነው:: የሕዳሴ ግድባችንን ጤንነት የሚያስጠብቅ ነው፤…” ሲሉም ነው የመርሃ ግብሩን ታላቅ ሀገራዊ ፋይዳ ያስረዱት::

“ሐምሌ 10 ቀን ኢትዮጵያውያን የራሳችንን ሪከርድ እንሰብራለን:: ከዚህ በፊት ከ350 ሚሊዮን በላይ ዛፎች በአንድ ጀንበር ተክለን ዓለምን አስደምመናል:: ዘንድሮም 500 ሚሊዮን ችግኞችን በአንድ ጀንበር በመትከል የራሳችንን ሪከርድ እናሻሽላለን፤ ታሪክ ሰሪ ትውልድነታችንን በተግባር ለዓለም እንገልጣለን፤” የሚለው መልዕክታቸው ደግሞ የመርሃ ግብሩን ሕዝባዊነት የገለጡበት ብቻ ሳይሆን፤ ለመርሃ ግብሩ መሳካት የኢትዮጵያውያንን ቁርጠኝነት በልበ ሙሉነት የተናገሩበት ነው::

ምክንያቱም ኢትዮጵያውያን ስለ ሀገራቸው፤ ኢትዮጵያውያን ስለ ክብርና ልዕልናቸው፤ ኢትዮጵያውያን ስለ ብልጽግናቸውና ሕልውናቸው ያላቸውን ቅንዓት በልኩ ያውቁታልና ነው:: 20 ቢሊዮን አቅዶ 25 ቢሊዮን በመትከል ያሳየ ሕዝብ፤ 200 ሚሊዮን ችግኝ በአንድ ጀንበር ሊተክል ተነስቶ 350 ሚሊዮን የተከለ ሕዝብ መሆኑን በሚገባ ስለሚያውቁትና፤ የሚመሩት ሕዝብ ስለ ኢትዮጵያ ሲል ጊዜውን፣ ገንዘቡንና ጉልበቱን ብቻ ሳይሆን ለአንድያ ሕይወቱ የማይሳሳ ስለመሆኑ በእጅጉ ስለሚገነዘቡም፤ ስለሚተማመኑበትም ነው::

ከተደመርን በሁሉም መስኮች ኢትዮጵያውያን ያሰብነውን ማሳካት እንችላለን:: የሃምሌ 10 ቀን 2015 ዓ.ም ዕቅድም እንደሚሳካ እንዲሁ ጥርጥር የለውም:: ለዚህ ደግሞ ሃምሌ 10 ቀን 2015 ዓ.ም ጀንበር ወጥታ እስክትገባ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ቤቱ ሊውል አይገባም::

ምክንያቱም ይህ ኢትዮጵያን አረንጓዴ የማልበስ ፤ ኢትዮጵያን የመውደድ እና ለዓለም ሕዝብ ኢትዮጵያዊ ማንነትን የመግለጥ ጉዳይ ነውና:: በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ የራስን ዐሻራ የማኖር ጉዳይም ነው:: እናም በአንድ ጀምበር 500 ሚሊዮን ችግኝ ተክለን ለሀገራችን ፍቅራችንን፣ ለዓለምም ጽናታችንን ለመግለጽ እንዘጋጅ!

አዲስ ዘመን   ሐምሌ 4/2015

Recommended For You

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *