የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ተቋርጦ የቆየውን የኢትዮጵያ ዋንጫ በመጪው ዓመት ሊያስጀምር መሆኑን አሳውቋል:: ፌዴሬሽኑ ከሰሞኑ ባደረገው የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ስብሰባ የተለያዩ ቁልፍ ውሳኔዎችን አሳልፏል::
በአዲስ አበባ ከተማ ክለቦች መካከል በ1937 ዓ.ም መካሄድ የጀመረው የኢትዮጵያ ጥሎ ማለፍ ዋንጫ ለ16 ዓመታት ተካሂዶ ተቋርጦ የነበረ ሲሆን፣ በድጋሚ በሀገሪቱ የሚገኙ ክለቦችን በማካተት ዳግም መካሄድ ጀምሮም በድጋሚ መቋረጡ ይታወቃል:: በዚህ ምክንያትም ክለቦች በየዓመቱ የሚያደርጓቸው ውድድሮች መጠን እንዲቀንስ እንዲሁም ፌዴሬሽኑም የሚያገኘውን ገቢ ሊያጣ ችሏል:: በመሆኑም ፌዴሬሽኑ ቀደም ብሎ ‹‹የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የጥሎ ማለፍ ዋንጫ›› በሚል ስያሜ የሚታወቀውን ውድድር፤ ‹‹የኢትዮጵያ ዋንጫ›› በሚል በ2016 ዓ.ም የውድድር ዓመት እንደሚያካሂድ አስታውቋል::
በዚህ ውድድር ተሳታፊ የሚሆኑት ክለቦችም በፕሪሚየር ሊጉ እንዲሁም ከፍተኛ ሊግ ተሳታፊ የሆኑ ክለቦች መሆናቸው ታውቋል:: ቀድሞ በፕሪሚየር ሊጉ ሁለተኛ ሆኖ የሚያጠናቅቀው ክለብ በአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ በቀጥታ ተሳታፊ እንደሚሆን ይታወቃል:: ከቀጣይ ዓመት ጀምሮ ግን ይህ ቀርቶ የኢትዮጵያ ዋንጫን በሚያነሳው ክለብ የሚተካ ይሆናል:: ሌሎች ዝርዝር አፈጻጸሞች በቀጣይ የሚገለጹ ሲሆን፤ ክለቦችና የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አክሲዮን ማህበርም ይህንኑ ታሳቢ በማድረግ ዝግጅት እንዲያደርጉ ፌዴሬሽኑ ባወጣው መግለጫ አሳስቧል::
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ከሰሞኑ በነበረው ስብሰባ ሌሎች ውሳኔዎችንም ያሳለፈ ሲሆን፤ ከእነዚህም መካከል አንዱ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግን የሚመለከት ነው:: በፕሪሚየር ሊጉ ተሳታፊ ከሆኑት 16 ክለቦች መካከል በየውድድር ዘመኑ ሶስት ክለቦች ወደታችኛው የውድድር እርከን ወርደው በምትካቸው ሌሎች ሶስት ክለቦች ከከፍተኛ ሊግ ሲያድጉ ቆይተዋል:: ከቀጣይ ዓመት አንስቶ ግን ይህ ቁጥር በአንድ ቀንሶ ሁለት ክለቦች ብቻ ወጪና ወራጅ እንዲሆን ፌዴሬሽኑ ወስኗል:: ይህም ለውድድር ጥራት የተሻለ አሰራር ከመዘርጋት አንጻር አስፈላጊ መሆኑም በሥራ አስፈፃሚው ታምኖበታል:: ከከፍተኛ ሊግ ወደ ፕሪሚየር ሊግ የሚያድጉ ክለቦች በውድድር አቅም እና በአደረጃጀት የተሻሉና ተፎካካሪ መሆን ስለሚገባቸው፤ በፌዴሬሽኑ መተዳደሪያ ደንብ መሠረት ሥራ አስፈጻሚው ሊወስን ችሏል:: በመሆኑም ውድድሩን የሚመሩት አካላትም ይህንኑ በደንባቸው የሚያካትቱ ይሆናል::
ሌላው በሥራ አስፈጻሚው ውሳኔ የተሰጠበት የትግራይ ክልል የእግር ኳስ ክለቦችን የሚመለከት ጉዳይ ነው:: በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል ተከስቶ በነበረው ጦርነት ምክያት በትግራይ ክልል የነበሩ ክለቦች ከሚሳተፉባቸው ውድድሮች ርቀው ቆይተዋል:: ይህንን ተከትሎም የክልሉ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ስር በሚካሄዱ ውድድሮች ላይ ተሳታፊ የነበሩ ክለቦች ወደ ተሳትፎ ይመለሱ ዘንድ ድጋፍ እንዲደረግለት ጠይቋል:: በዚህም በፌዴሬሽኑ የመተዳደሪያ ደንብ ክፍል 11 ማጠቃለያ ድንጋጌዎች አንቀጽ 91 መሠረት ከውሳኔ ላይ ደርሷል::
የፊፋ እና የካፍ ደንቦችን ከግምት ያስገባው የፌዴሬሽኑ መተዳደሪያ ደንብ ክለቦች ከውድድር ከራቁ ከአንድ ዓመት በኋላ ቢመለሱ በነበሩበት መቀጠል እንደሚችሉ የሚጠቁም ሲሆን፤ የትግራይ ክለቦች ደግሞ ከተቀመጠው የጊዜ ገደብ በላይ ከውድድር ውጪ ሆነው ቆይተዋል:: በመሆኑም ክለቦቹ እንደ አዲስ ከክልል ክለቦች ቻምፒዮና መጀመር ይኖርባቸዋል፤ ነገር ግን ኮሚቴው ጉዳዩን በአንክሮ በመመልከት እና የክልሉን እግር ኳስ በማነቃቃት ወደ ተፎካካሪነታቸው ለመመለስ ከነበሩበት በአንድ ደረጃ ዝቅ ብለው እንዲወዳደሩ ወስኗል:: ኮሚቴው በየትኛውም የሊግ ውድድር ላይ የሚሳተፉትን፣ የሚወጡትንና የሚወርዱትን ክለቦች ብዛትና አጠቃላይ ሁኔታ እንዲሁም አዳዲስ የውድድር ሊጎችን ለማቋቋምና ለማፍረስ ውሳኔ ለመስጠት ባለው ሥልጣን መሠረት ውሳኔውን አስተላልፏል::
በዚህም መሠረት በመጪው የ2016 የውድድር ዘመን በፕሪሚየር ሊጉ ሲወዳደሩ የነበሩ ክለቦች ወደ ከፍተኛ ሊግ፣ ከፍተኛ ሊግ ላይ የነበሩ ወደ አንደኛ ሊግ፣ አንደኛ ሊግ ላይ ሲጫወቱ የቆዩት ደግሞ ወደ ትግራይ ክልል ሊግ ውድድር ዝቅ ብለው እንደሚወዳደሩም ፌዴሬሽኑ በመግለጫው አብራርቷል::
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ረቡዕ ሐምሌ 5 ቀን 2015 ዓ.ም