ክረምትና ልጆቻችን

 ክረምት መጣ ክረምት!

ክረምት የበረከት ምንጭ ነው። ክረምት ፀጋ ነው። ክረምት የሥራም የማረፊያም ወቅት ነው። ለጊዜው የማረፊያነቱን ጉዳይ ወደኋላ ግድም ስለምንመለስበት በሥራ ወቅትነቱ ላይ ጫን ብለን በክረምታችን ትሩፋት ላይ ጥቂት ሃሳቦች እንፈነጣጥቃለን። የክረምትና የአርሶ አደሩ ወገኔ፣ ቁርኝቱና ዝምድናው ይህ ልኩ ተብሎ ወሰን የሚበጅለት አይደለም። እያንዳንዱን የክረምት ወራት ደቂቃና ሰኮንዶች ገበሬው “እንደ ርሃብ ቀን ሰብል” በጉጉት የሚያየውና የሚጠብቀው ሲሆን የሚመለከተውም ልክ “እንደ ዓይኑ ብሌን” እየተጠነቀቀ ነው። የዝናብ ወቅቱ እንዲባክንበት አይዘናጋም፤ እንደ አዘቦት ቀን “ትርፍ ቀናት” በአልባሌ ውሎዎች ዕለታቱ እንዲበላሹበትም አይፈቅድም።

እርግጥ ነው ሀገራዊ ምክክር ተደርጎባቸው አርሶ አደሩን ከሥራውና ከእርሻው የሚያዘናጉና ሊሻሻሉ የሚገባቸው አንዳንድ የሃይማኖትና የባህል ኩነቶች መኖራቸው አሌ የሚባል አይደለም። ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከታቸው አባቶችና አዋቂዎች ሥር ሰደው አሉታዊና አዘናጊ ልምምዶች በሆኑት እምነቶችና ባህሎች ላይ ሊመክርባቸው እንደሚገባ ማሳሰቡ ክፋት የለውም።

ከተሜው ሕዝባችን የክረምቱን ጠል እየሸሸ ወደ መጠለያዎች ሲጣደፍ ገበሬውና በሬው ግን የዝናቡ ውሽንፍር እየገረፋቸውም ቢሆን ወደ እርሻና የዘር ተግባራቸው የሚጣደፉት መንፈሳቸው በሀሴት ለምልሞ፣ ተስፋቸውም “አሽቶ” እርስ በእርስ እየተሞጋገሱ ነው። ገበሬው በሬውን “ጌታዬ በሬዬ በአንተ ነው ማማሬ!” እያለ ሲያደናንቀው በሬውም “በቋንቋው” እምቧ እያለ ምላሹን ይሰጣል። ይህ እውነታ የነገር ማሳመሪያ አድናቆት ሳይሆን ለዘመናት የፀና ምስክርነት ነው።

ለጥቁምታ ያህል ከአንጋፋዎቹ የሀገራችን የልጆች መጻሕፍት ደራስያን መካከል ያሬድ ገ/ሚካኤል “የእንስሳት አገልግሎት” በሚል ርዕስ ባሳተሙት መጽሐፍ ውስጥ በሬን እንደ ሰው እያናገሩ የተራቀቁበት ተወዳጅ የግጥም ሥራቸው ቢነበብ ይበልጥ ሃሳባችንን ፍንትው አድርጎ እንደሚያሳይ አስታውሰን እናልፋለን።

«ክረምት መጣ ክረምት፣

የእረኛ ወተት፤ የገበሬ እሸት

የአሮጊት ወዘተ፤ ክረምት መጣ ክረምት።»

በጨቅላ ዕድሜዬ የሰማሁት የትልቋ አያቴ የእማማ ይርገዱ ብሩ በዜማና በእንቅስቃሴ የታጀበ እንጉርጉሮ ዛሬም በጎልማሳነት ዕድሜዬ በፍጹም ከእዝነ ሕሊናዬ ውስጥ ደብዝዞ ሊጠፋ አልቻለም። በቀጣዮቹ የክረምት ወራትም ዜማቸውና እንጉርጉሯቸው ይዘነጋኛል ብዬ አልሰጋም።

ከተሜው ወገኔም ልክ እንደ ገጠሩ አርሶ አደር ሁሉ “ከዘመናት የክረምት ሽሽትና የመጠለያ ፍለጋ ጥድፊያ” አርነት ወጥቶና “የክረምቱ ዝናብ እንዳይደበድበኝ” ከሚል ፍርሃት ነጻ ሆኖ እርቅ በመፍጠር “የቆረበው” ከቅርብ ዓመታት ወዲህ መሆኑን ስናስተውል በእርግጥም “እርቅ ኩርፊያን አድርቅ” መሆኑን በገሃድ እንረዳለን። እንዴውን በጥቂቱ እናብራራ።

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ገጠር ከከተማ ልዩነት ሳይደረግ በየክረምቱ ሕዝበ ኢትዮጵያ በአጭሩ ታጥቆ በችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ላይ ሲሳተፍ ማስተዋል የተለመደ ሀገራዊ ባህላችን ሆኗል። እንኳንና ኢትዮጵያዊው ዜጋ ቀርቶ ለተለያዩ ጉዳዮችና ተልእኮዎች ሀገራችንን የሚጎበኙ መራሄ መንግሥታት፣ ዲፕሎማቶችና ድንበር ዘለል ዓለም አቀፍ ልዑካን፣ ነጋዴዎችና ባለሀብቶች ሳይቀሩ በተገኙባቸው የሀገራችን አካባቢዎች በሙሉ “እባካችሁን ችግኝ በመትከል ዐሻራችሁን አኑሩ” እየተባሉ ሲጋበዙና እጃቸው አፈር እየነካ ችግኞችን ሲተክሉ እያስተዋልን ነው።

በዚህ ጸሐፊ እምነት ከተፈጥሮ ጋር የተፈጠረው መስማማትና ተሃድሶ መገለጽ ያለበት ችግኞችን በመትከልና በመንከባከብ ብቻ ተደርጎ መቆጠሩ አግባብ አይመስለንም። ይልቅስ በጠብ ከተኳረፍናት “ከመጋቤ እናታችን ምድር ጋር” በይቅርታ የመታረቅ ያህል ዋጋ ሊሰጠው ይገባል። ተመናምኖ “ጥርሱን በማግጠጥ” የተራቆተው የሀገሬ ተራራ፣ ሸንተረር፣ ሜዳና ሸለቆ በእጽዋቶች ለምልሞ “ሲስቅና ሲፈነጥዝ” መመልከት ባለራዕዩን የሀገሪቱን መሪም ሆነ ራዕዩን በአሜንታ የተቀበለውን ሕዝብ በእኩልነት የሚያስመሰግን ነው።

“ኢትዮጵያ በየዓመቱ በቢሊዮኖች የሚቆጠር ችግኝ ተከለች” የሚለው ዜና ለእኛ ለባለጉዳዮቹ ቀላል መስሎ እየታየን “የጸደቁትን ሳይሆን የደረቁትንና የጠወለጉትን ችግኞች አሀዝ ብቻ እያጣቀስን” ጥረቱን ባናደንቅም፤ ከድርቅና ከበረሃማነት ጋር እየተጋሉ “ለመተንፈስ የተቸገሩት” ሀገራት እንዴት እንደሚቀኑብንና የእኛን የተፈጥሮ ሀብትና ጥረት በማየት “ምን በደልንህ” ብለው ፈጣሪን እንደሚሞገቱ ልብ ብለን ብናስተውል “የእጃችንን ወርቅ” ባላራከስን ነበር።

ይህ ጸሐፊ ከጥቂት ዓመታት በፊት የሰሃራ በረሃ በፈጣን ሁኔታ እየጋለበ በቻድ ብሔራዊ አውሮፕላን ጣቢያ ጥግ (N’Djamana International Airport) መድረሱን ያስተዋለው በልቡ እያማተበ፣ ስለ ሀገሩ ፀጋም በለሆሳስ ፈጣሪውን እያመሰገነ ነበር። የኢትዮጵያን ስፋት ስምንት ተኩል ጊዜ ያህል የሚያስከነዳውና (የበረሃው ስፋት 9,200,000 ስኩዬር ኪሎ ሜትር ነው) ፍጥረታት እንዲሰደዱ፣ ነፍስ ያለው እንዳይንቀሳቀስ ቀጣናውን በአቧራማ ጭጋግ እየሸፈነና ፍጥረታትን እያሰቃየ ያለው የሰሃራ በረሃ የብዙ ሀገራትን ታሪክ ወደ “ዶግ አመድነት” እንደለወጠና ሊለውጥ እንደሚችል ክፉኛ እየተተነበየ ይገኛል።

የትንቢቱን ሟርት አክሽፎ ፈጣሪ ይታደግን እንጂ ሀገራችን በተያያዘቸው የአረንጓዴ ልማት ጠንክራ ራሷን ካልተከላከለችና ጎረቤት ሀገራትንም አስተባብራ ከጎኗ በማሰለፍ በአረንጓዴ ዘመቻው እንዲረባረቡ ካላደረገች በስተቀር ተግዳሮቱ በምሥራቅ አፍሪካና በቀንዱ ቀጣናዎች ደጃፍ ደርሶ “ከሰሃራ በታች ያሉ ሀገራት” በሚል የሚታወቀው ስያሜቸው ተቀይሮ “የሰሃራ አካል” ተብሎ የማይለወጥበት ምክንያት አይኖርም። ምክንያቱን በተጨባጭ መረጃዎች እናብራራ።

እንደ ሰሃራ (በአብዛኛው ሰሜን አፍሪካ)፣ ካላሃሪ እና ካሮ (በደቡብ አፍሪካ)፣ ደናክል (በአፋር ትሬያንግ፡- በሰሜን ምሥራቅ ኢትዮጵያ፣ በደቡባዊ ኤርትራ፣ በሰሜን ምዕራብ አፋር)፣ ቻልቢ (በምሥራቃዊ ኬንያ)፣ ናሚቢ (ከደቡብ አፍሪካ የአትላንቲክ ውቂያኖስ ዳርቻ ተነስቶ በስፋት የተንሰራፋ) እና ጉባን (በሰሜን ሱማሊያ) የተዘረጉት በረሃዎች ለአህጉራችን አፍሪካ ትልቅ የድርቅ ምክንያት ሆነው ተፈጥሮን እንዳያዛቡ ሥጋት ካሳደረ ሰነባብቷል።

በመፃኢነት የተተነበየውና ከላይ የተጠቀስነው የበረሃዎች መስፋፋትና አስደንጋጭ ተፈጥሮ ነክ ሥጋት ያነሰ ይመስል የሰው ሠራሽ የደን ጭፍጨፋዎችና የበካይ ጋዞች የትነት ተግዳሮት እየናጣት እርቃኗን እንዳትቀር በሚያሰጋት የአፍሪካ አህጉር ሀገሬ በቢሊዮን የሚቆጠሩ ችግኞችን ተክያለሁ ወደፊትም ቢሊዮኖችን እጨምራለሁ በማለት ምሳሌ መሆኗ ያስመሰግናታል። አፍሪካዊያን ወንድም እህቶቻችን አርአያዋን እንዲከተሉ አጥብቃ ማበረታታቷ የማይዋጥላቸው አንዳንድ የራሳችን ወላጆች ሪፖርቱንና ቁጥሮችን እያጣጣሉ ሲያሾፉና ሲዘባበቱ መመልከት “ታዘብኩሽ ምንትሴ” እንዲሉ በራስ አረም እባብ ይዞ ከማስፈራራት የሚተናነስ አይደለም።

ሐምሌ 10 ቀን 2015 ዓ.ም የተተከሉት ከአምስት መቶ ስልሳ ሚሊዮን በላይ ችግኞችም መቶ በመቶ ይጽደቃሉ ተብሎ ባይገመትም በተወሰነ መጠን ሥር ሰደው ቢጸድቁ ለምድራችን ልምላሜ፣ ለመሶባችን ትሩፋት፣ ለአየር ንብረታችን ፈውስ ሊሆኑ እንደሚችሉ መገመቱ ከባድ አይሆንም። ከእኛም አልፎ ተርፎ ፀጋው ለሌሎችም መትረፉ አይቀርም። ስለዚህም ለተከላው የተረባረቡት እጆች ይባረኩ፣ ያስተባበሩ ተቋማትና ባለሙያዎች ይከበሩ፣ በክረምቱ ዝናብ ጠል ያጠገብ አምላክ ይመስገን ብሎ ማድነቁ ተገቢ ይመስለናል።

ዓረቦች በብሂላቸው “It is good to know the truth, but it is better to speak of palm tree” ትርጉም፡- “እውነትን ማሰስ መልካም ነው፤ የበለጠ የሚሻለው ግን ስለ ዘንባባ/የቴምር ዛፎቻችን መመስከር ነው።” እንዳሉት አንዲት ዛፍ እንኳን መጽደቋን መመስከር ትልቅ ማስተዋል ነው። ምክንያቱም “አንድ ትውልድ የሚተክለው ዛፍ ለቀጣዩ ትውልድ ጥላ ብቻ ሳይሆን እርሻም ጉርሻም ሆኖ ስለሚያገለግል” -የቻይኖች አባባል ነው። “እስከ ህልፈተ ሕይወታችን በምንተነፍሰው እያንዳንዷ ሰከንድ ዛፎችን እናመስግን የሚባለውም ከሕይወት የምንሰናበተው የእነርሱ በረከት ሲጎድልብን ነው።” በብዙ ሀገራት የሚነገር አባባል ነው። ስለ አረንጓዴው ትሩፋታችን ይህንን ያህል ካልን ዘንድ በዋናው የጽሑፋችን ርዕስ ላይ ከክረምት ጋር አዳብለን ስለጠቀስነው ስለ “ሕያዋኑ ችግኞቻችን” ስለ ልጆቻችን ጥቂት ሃሳቦችን እንፈነጣጥቅ።

ክረምቱና ልጆቻችን፤

ምድር በችግኞች እንደምትለመልመው ሁሉ ልጆቻችንም ነገ “በዛፍ በሚመሰል ደረጃ ላይ ደርሰው” ለሀገር ጥላ እንደሚሆኑ ጥርጥር አይገባም። የዝናብ ወቅት ጠብቀን ችግኞችን እንደምንተክል ሁሉ ልጆቻችንንም በማረፊያቸው የክረምት ወራት በቅርብ እየተከታተልን ጥበብና እውቀትን፣ ርህራሄና ለሌሎች ማሰብን፣ ለሀገርና ለሕዝብ መቆርቆርን፣ ከጥላቻና ከቂም ውርስ ይልቅ ፍቅርን ልንዘራባቸውና ልንተክልባቸው ይገባል።

ቀደም ባሉት ዘመናት ልጆቻችን የክረምት እረፍታቸውን በቁም ነገር ላይ እንዲያውሉ በስማቸውና በግብራቸው በተመሰገኑ በርካታ ተቋማት ልዩ ልዩ ፕሮግራሞች እየተነደፉ በተለያዩ ጠቃሚ ጉዳዮች ላይ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ይበረታቱ ነበር።

ለአብነት ያህልም ይህ ጸሐፊ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቱ የነበረውና ሕይወቱንና የዛሬ ማንነቱን የቀረጸው የወጣቶች ወንዶች ክርስቲያናዊ ማኅበርን (ወወክማ) እና የወጣት ሴቶች ክርስቲያናዊ ማኅበር (ወሴክማ) የመሳሰሉ ተቋማት ልጆችን በሥነ ምግባር በመቅረጹ ረገድ ትተውት ያለፉት ደማቅ ዐሻራ ይህ ልኩ የሚባል አይደለም።

በየአካባቢው ተቋቁመው በነበሩ በእነዚያ ተቋማት አማካይነት በየክረምት ወራት ይሰጡ የነበሩ ልዩ ልዩ ስፖርታዊ ሥልጠናዎች፣ ወጣ ያሉ የካምፕ ቆይታዎችና የማሕበረሰብ አገልግሎቶች ከቶውንም የሚረሱ አይደሉም። በከፍተኛ ደረጃ ሀገሪቱን የመሩና እየመሩ ያሉ የያኔው ታዳጊ ወጣቶች የዛሬ ጎልማሶችና አዛውንቶች ተሞክሯቸውን አካፍሉ ቢባሉ ብዙ የሚመሰክሩት እውነታ አለ። በዚህ ጉዳይ በርካታ የሀገሬ ሚዲያዎች ስለምን ንቃት እንዳነሳቸውና አርቆ ማሰብ እንደተሳናቸው ሳስብ ይከፋኛል።

ለምሳሌ ከላይ በተጠቀሰው ተቋም ውስጥ አብረውት የተማሩትና በየክረምቱ ውሃ እየተራጩና ጭቃ እያቦኩ ብቻ ሳይሆን ዕድሜያቸው የሚፈቅድላቸውን ያህል በበጎ ሥራዎች ክረምታቸውን ያሳልፉ የነበሩ ዘመነ አቻዎቹ ሁሉም በሚያሰኝ ቁጥር ዛሬ በሀገርና በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ተጽእኖ ፈጣሪዎች በመሆን ስማቸው ይጠቀሳሉ።

እርግጥ ነው ዛሬም ቢሆን በርካታ የሀገሪቱ ታዳጊና ወጣቶች ችግኝ ተከላን በመሳሰሉ ሀገራዊ ፕሮግራሞች በንቃት መሳተፋቸው አልቀረም። ነገር ግን ክረምታቸውን በውጤታማነትና በቋሚነት ለማሳለፍ መንገዱና ዘዴው ይሄ ብቻ ነው ወይ? ምንም እንኳን ቀጥተኛ ባለጉዳዮቹ እኛ ወላጆች መሆናችን ባይካድም መንግሥትስ “ሕያዋን ችግኞቻችን” በመልካም ዜግነት እንዲበቅሉልን ኃላፊነት የለበትም ይሆን?

የክረምቱ መምጣት ለብዙ ወላጆች ሥጋት እንደሆነባቸው በግልጽ ይታወቃል። “ደግሞ ያ ትምህርት ቤት ተዘጋ ልጆቼ እንዴትና የት ይከርሙ ይሆን?” የሚለው መሳቀቅ የየቤቱ ጭንቀት ከሆነ ሰነባብቷል። በተለይም የማሕበራዊ ሚዲያው ሱስ ልጆቻችንን ተቆጣጥሮ ካስገበራቸው ውሎ አድሯል። የሱሱ መጠንና ተጽእኖ በቀላሉ የሚታይ ሳይሆን በነገው ሕይወታቸውም ላይ ትቶት የሚያልፈው ቁስል በቀላሉ ሊፈወስ የማይችል እንደሆነ ብዙ ማሳያዎች አረጋግጠውልናል።

ስለዚህ ክረምት በመጣ ቁጥር ስለ ልጆቻችን እያማጥን እስከ መቼ እንገፋዋለን። አንድ ተጎራባቼ እናት የልጆቻቸውን ነገር ባነሱ ቁጥር “ስወልዳቸው ካማጥኩት በበለጠ እየቃተትኩ ያለሁት በዛሬ የታዳጊነት ዕድሜያቸው ላይ ነው” ብለው ብለው የተናገሩት ብዙ ወላጆች የሚጋሩ ይመስለናል።

ለመሆኑ በየቀበሌው፣ በየወረዳውና በየክፍለ ከተማው የወጣቶች ማዕከል እየተባሉ የተፈጠሩት እጅግ በርካታ ተቋማት ከምን ደረሱ? ካሉስ እየዋሉባቸው ያሉት እነማን ናቸው። ለመልካም ወጣቶች ማፍሪያ ተብለው በሕዝብ ገንዘብ የተቋቋሙት እነዚያ የወጣቶች ማዕከላት በውኑ ለምን ተግባር እየዋሉ እንዳሉ በግልጽ የሚከታተላቸው አካል ይኖር ይሆን? ጉዳዩን ሆድ ይፍጀው ብለን ብቻ ማለፉ ተገቢ አይመስለንም። “ነገን ዛሬ እንትከል” በሚል መርህ ክረምቱን በችግኝ ተከላ እንደምንረባረበው ሁሉ “ለሕያዋን ችግኞቻችንም” ማበልጸጊያ ማዕከላት ሊታሰብላቸው ይገባል የማጠቃለያ መልእክታችን ነው። ሰላም ለሕዝባችን፤ ለዜጎችም በጎ ፈቃድ።

 (በጌታቸው በለጠ /ዳግላስ ጴጥሮስ)

gechoseni@gmail.com

አዲስ ዘመን   ሐምሌ 12/2015

Recommended For You

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *