የኢትዮጵያን ይግዙ – ምርቶችን ማስተዋወቅና ትስስር መፍጠር ያስቻለ መድረክ

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ኢትዮጵያ በተለያዩ አካላት የሚዘጋጁ በርካታ ዓለም አቀፍ እና ሀገራዊ የንግድ ትርኢቶችን /ኤግዚቢሽኖች/ን እያስተናገደች ትገኛለች። በዚህ አመት ብቻ አመት በዓሎችን ምክንያት በማድረግ ከተካሄዱ የንግድ ትርኢቶች ውጭ እንደ የኢትዮጵያን ይግዙ፣ የቆዳና ቆዳ ውጤቶች ዓለም አቀፍ ኢግዚቢሽን ያሉ በርካታ ዓለም አቀፍ ኢግዚቢሽኖች በሀገሪቱ ተካሂደዋል። ኢግዚቢሽኖቹን በተመለከተ በሚመለከታቸው አካላት ከተሰጡ መግለጫዎች፣ ከመገናኛ ብዙኃን ዘገባዎችና ማስታወቂያዎች መረዳት የሚቻለውም ይህንኑ ነው።

በሀገሪቱ የንግድ ኢግዚቢሽን በማዘጋጀት ከሚታወቁት መካከል የኢትዮጵያ የንግድና የዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ይጠቀሳል። ምክር ቤቱ ዘንድሮም ባለፈው ሚያዚያ ወር ዓለም አቀፍ የንግድ ትርኢት አዘጋጅቷል። የምክር ቤቱ ዋና ጸሐፊ አቶ ውቤ መንግሥቱ እንደሚሉት፤ ምክር ቤቱ ዘንድሮ ያዘጋጀውን ጨምሮ 13 ዓለም አቀፍ የንግድ ትርኢቶችን አዘጋጅቷል። ምክር ቤቱ ‹‹የኢትዮጵያን ይግዙ› ›(Buy Ethiopian) በሚል መሪ ቃል የንግድ ትርኢቱን እያዘጋጀ ይገኛል።

‹የኢትዮጵያን ይግዙ›› የሚለው ትልቅ መልዕክት ያለው መሪ ቃል እንደሆነ የሚናገሩት አቶ ውቤ፣ የንግድ ትርኢቱ ዓላማም አንደኛው የኢትዮጵያን ምርቶች እኛው ራሳችን አምርተን፤ እኛው ራሳችን እንጠቀም የሚል መሆኑን ያመለክታሉ። መሪ ቃሉ ሀገር ሊያድግ የሚችለው የራስን ሀብት በመጠቀም እንጂ የውጭውን ሀብት በመጠቀም አይደለም የሚል መልዕክትን ያየዘ መሆኑንም ነው ዋና ፀሐፊው ይገልጻሉ። ሁለተኛው ‹‹የኢትዮጵያን ይግዙ› መልእክት ባህላዊ አስተሳሰብን( ኢትዮጵያውነትን) በማምጣት አምርቶ ከመጠቀም ባለፈ የኢትዮጵያን ግብዓቶች ተጠቅሞ በማምረት በአግባቡ መጠቀም እንዲቻል ለማነቃቃት የተደረገ መሆኑንም ይናገራሉ። ሦስተኛው የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪዎች እንዲያድጉ በማነቃቃት ለማገዝ የሚያስችል ዓላማን ያነገበ ነው ይላሉ።

ዋና ፀሐፊው እንዳብራሩት፤ ዘንድሮ በተካሄደው ‹የኢትዮጵያን ይግዙ› የንግድ ትርኢት ላይ በርካታ የውጭ ተሳታፊዎች ይገኛሉ ተብሎ ተጠብቆ ነበር፤ ነገር ግን የተገኙት የተወሰኑ ሀገሮች ተሳታፊዎች ብቻ ነበሩ። የሩሲያ፣ የተባበሩት አረብ ኤሚሬት፣ የሱማሌላንድና የሱማሊያ ተሳታፊዎች በንግድ ትርኢቱ ተሳትፈዋል። ከሱዳን በርካታ ተሳታፊዎች እንደሚመጡ ቢጠበቅም፣ በሀገሪቱ በተፈጠረው ግጭት ሳቢያ ተሳታፊዎቹን ማግኘት አልተቻለም።

የዘንድሮው የንግድ ትርኢት በጣም ደማቅ ሆኖ ከአነስተኛ ጀምሮ እስከ ከፍተኛ ደረጃ ያሉት ኢንዱስትሪዎች በከፍተኛ ሁኔታ ምርቶቻቸውን እንዲያስተዋውቁ የተደረገበት መሆኑንም ጠቅሰው፣ በዚህ የንግድ ትርኢት ላይ 172 ኩባንያዎች መሳተፋቸውን ይጠቅሳሉ። ከእንደ ኢትዮ ቴሌኮም አይነት ኩባንያዎች አንስቶ ማር አምራቾች ድረስ ያሉ አካላት በንግድ ትርኢቱ እንዲሳተፉ መደረጉን ገልጸው፣ በዚህም ውጤታማ ሥራ መሥራት እንደተቻለም ገልጸዋል። በንግድ ትርኢቱ ላይ የኢትዮጵያን ምርቶች ለሌላው ዓለም ልናስተዋወቅ የምንችለውን ሥራ ሰርተናል ብለን እናምናለን ሲሉም አቶ ውቤ ተናግረዋል።

የንግድ ትርኢቱ ለንግዱ ማህበረሰብ ምርቶችንና አገልግሎቶችን ለማስተዋወቅ ያስቻለ ነው የሚሉት አቶ ውቤ፤ ኢንዱስትሪዎች የተሻለ ማምረት እንዲችሉ፣ ከተለያዩ ሀገራት ከመጡ አቅራቢዎች በተለይ ከግብዓት አቅራቢዎች ጋር የአቻ ለአቻ ትስስር እንዲፈጠሩ የሚያስችል ተግባር መከናወኑን አስታውቀዋል። ከንግድ ትርኢቱ ጎን ለጎን በተሰጡ ስልጠናዎች ወደ ዓለም ገበያ ለመግባት የሚያስችሉ ፤ የንግዱ ማህበረሰብን የተሻለ ተጠቃሚ የሚያደርጉ ዘዴዎችን በመጠቀም ምቹ ሁኔታዎች ለመፍጠር መሰራቱንም ይናገራሉ።

የንግድ ትርኢቱ ‹የኢትዮጵያን ይግዙ› እንደመሆኑ መጠን በዘንድሮው የንግድ ትርኢት ለኢንዱስትሪዎቻችን ግብዓት ይዘው በመምጣት ይሳተፋሉ ተብለው የሚጠበቁትን ያህል ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ከዓለም አቀፍ ሁኔታው ጋር በተያያዘ አልመጡም ሲሉ ዋና ፀሐፊው ይገልጻሉ። በዚህ የተነሳ ከንግድ ትርኢቱ የተጠበቀውን ያህል ውጤት ማግኘት እንዳልተቻለ ጠቅሰው፣ እንዲያም ሆኖ ሙሉ ለሙሉ ግን ተሳክቷል ባይባልም 80 በመቶ ያህሉ እቅድ ተሳክቷል ብለው እንደሚያምኑ አስታውቀዋል።

እሳቸው እንዳሉት፤ የንግድ ትርኢቱ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ በመሀል ላይ ኮቪድና የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ኢኮኖሚውን በመቀዛቀዛቸው ሳቢያ የሚፈለገውን ያህል እንቅስቃሴ ማድረግ ሳይቻል ቀርቷል፤ ከኮቪድ ወዲህ ባሉት ሁለት ተከታታይ ዓመታት ግን በሚገርም ሁኔታ የተሳኩ የንግድ ትርኢቶች ማዘጋጀት ተችሏል።

አሁን መጀመሪያ የተቀዛቀዘውን የንግድ ትርኢት ወደ ነበረበት ሁኔታ እየመለስን፣ የንግዱ ማኅብረሰብም እንዲነቃቃ እያደረግን ምርቶቻችንን በማስተዋዋቅ የንግድ ትርኢቱ በተሻለ መንገድ እንዲካሄድ እያደረግን ነው ሲሉ ያብራራሉ። በሚቀጥሉት ጊዜያትም ከዚህም በተሻለ መንገድ የሚሰራበት ሁኔታ መኖሩን ይጠቁማሉ።

በእንዲዚህ አይነት የንግድ ትርኢቶች ላይ የሚሳተፈው የንግዱ ማኅበረሰብ ትስስሩ ጠንክሮ እንዲቀጥል ፍላጎት እንዳለው በየጊዜው ከሚሰጠው ግብረ መልስ ምክር ቤቱ እንደሚረዳ የሚናገሩት አቶ ውቤ፤ የንግዱ ማኅበረሰብ ዓለም አቀፍ ገበያ ውስጥ መግባት የሚችልበት ትስስር እንዲሰፋና ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥረት እንደሚደረግ ተናግረዋል። አሁን እየተከፈተ ያለውን የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጠና ገበያ መጠቀም የምንችልበት ሰፊ እድል እንዲፈጠርና እንዲመቻች የሚሉ ሀሳቦች ከንግዱ ማኅበረሰብ እንደሚነሳም ይገልጻሉ። ምክር ቤቱም ይህንን መሠረት አድርጎ እየሰራ እንደሆነ ጠቅሰዋል።

አቶ ውቤ እንዳሉት፤ እንደ ምክር ቤት ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች በንግድ ትርኢቱ ላይ ተሳታፊ እንዲሆኑ በምክር ቤቱ በኩል በስፋት እየተሰራ ነው፤ በየዓመቱ በውጭ ሀገሮች የሚገኙ የኢትዮጵያ ዲፕሎማቶች ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ የግሉን ዘርፍ እንዲያዳምጡ ይደረጋል፤ ሁሉም በቢዝነስ ዲፕሎማሲው ላይ እንዲሰሩ ለማድረግ የሚያስችሉ ሁነቶች ይዘጋጃሉ፤ የንግድ እንቅስቃሴው ያለበትን ሁኔታ የሚያሳይና ወደፊት የተሻለ እንዲሆን ለማድረግ የግሉ ዘርፍ የሚፈልገውን መግለጽ የሚችልበት ውይይት እንዲካሄድ በማድረግ ዲፕሎማቶቹ እገዛ እንዲያደርጉ የሚያስችል ሥራ ይሰራል።

በዚህም አምባሳደሮች የንግዱን ማኅበረሰብ ሊያገዙ የሚችሉ ሥራዎችን በመሥራት ረገድ የበኩላቸውን እገዛ እያደረጉ መሆናቸውን አቶ ውቤ ጠቅሰው፤ ከዚህ ባሻገር ኤምባሲዎችን በማነጋገር አብሮ መስራት የሚያስችሉ ሁኔታዎች እየተመቻቹ መሆናቸውን ያስረዳሉ።

ከዚህ በተጨማሪም የንግዱን ማህበረሰብ ወደ ውጭ ሀገራት ይዞ በመሄድ ልምድ እንዲያገኝ የማድረግ ሥራ እየተሠራ መሆኑንም ጠቅሰው፤ የንግዱ ማኅበረሰብ በሀገር ውስጥ ከሚያገኘው ልምድ በተጨማሪ ወደ አሜሪካ፣ አውሮፖ፣ ኤሽያና የተለያዩ አፍሪካ ሀገራት ይዞ በመሄድ ልምድ የሚያገኝበትና ትስስር የሚያጠናክርበት ሁኔታ መፍጠር መቻሉን ነው የሚናገሩት። ወደፊት ከዚህ በበለጠ ሁኔታ በተጠናከረ የተሻለ ለማድረግ እየተሠራ መሆኑንም ገልጸዋል።

‹‹የኢትዮጵያን ይግዙ›› የሚለው መሪ ቃል ለውጭ ሀገር ተሳታፊዎች (ኩባንያዎች) ምን ስሜት መልእክት ያስተላልፋል? በሚል ላቀረብንላቸው ጥያቄ አቶ ውቤ በሰጡት ምላሽ፤ ይህ ‹‹የኢትዮጵያን ይግዙ›› የሚለው መሪ ቃል በራሱ ምን ማለት ነው የሚል ጥያቄ እንደሚያስነሳም ነው እሳቸውም የሚጠቅሱት። የኢትዮጵያን ይግዙ ማለት ሌሎች ግብዓቶችን አንጠቀምም ማለት አይደለም ሲሉም ገልጸው፣ የውጭ ሀገር ተሳታፊዎች ግብዓት እንዲያመጡ እንጂ ሸቀጥ እንዲያራግፉብን አንፈልግም ይላሉ። ይህ መሠረታዊ ጉዳይ መሆኑን ጠቅሰው፣ ‹‹የኢትዮጵያን ይግዙ›› የምንልበት ምክንያት የውጭዎቹ ግብዓት ያምጡልን፤ እኛ ደግሞ አምርተን የኢትዮጵያን መሸጥ እንፈልጋለን የሚል እሳቤ የያዘ መሆኑን ነው አቶ ውቤ የሚያስረዱት።

‹‹ የንግድ ትርኢቱን የውጭ ሀገሮች እቃ መሸጫ ማድረግ አንፈልግም›› ያሉት ዋና ፀሐፊው፣ ‹‹መጀመሪያውንም ይህንን በተለያየ መልኩ በመጠቀም በግልጽ እንዲረዱን ማድረግ ላይ እንሰራለን›› ነው ያሉት።

በንግድ ትርኢቱ በርካታ ተግዳሮቶች እንደሚያጋጥሙ ጠቅሰው፤ ከእነዚህም መካከል የሀገሪቱ ምርቶች በሚፈለገው ደረጃ (ስታንዳርድ) ላይ አለመገኘት፣ የንግዱን ማኅበረሰብ ከውጭ ሀገር ኩባንያዎች ጋር ለማስተሳሰር በሚደረጉ ጥረቶች የሚያጋጥሙ ተግዳሮች እንደሚጠቀሱ ይናገራሉ። የንግዱን ማኅበረሰብ ከተገናኘን በኋላ ግብዓት ወጥ ሆኖ ማቅረብ ላይ ችግሮች ይስተዋላሉ ሲሉ ጠቅሰው፣ አንዳንዶቹ ደግሞ ወደ ውጭ ሀገሮች ሄደው ምርቶቻቸውን ለማስተዋወቅ እንዲሁም አምርተው ወደ ገበያው ለማቅረብ ሲፈልጉ የውጭ ምንዛሪ እጥረት የሚያጋጥምበት ሁኔታም ሌላው ተግዳሮት መሆኑን ይጠቅሳሉ።

የውጭ ምንዛሪ ችግር የመንግሥት ችግር ብቻ እንዳልሆነም ዋና ፀሐፊው ገልጸው፣ የግሉ ዘርፍም አምርቶ የውጭ ምንዛሪ ማምጣት አለበት ይላሉ። ይህንን የሚያደርግበት ምቹ ሁኔታ መፍጠር አለመቻል ሌላው ተግዳሮት እየሆነ መምጣቱን ይጠቁማሉ።

እሳቸው እንዳሉት፤ ምክር ቤቱ ወደፊት በርካታ ሥራዎችን ለመሥራት አቅዶ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል። አሁን ለሦስት ዓመታት የኢኮኖሚ ለውጥ ለማምጣት የሚያስችል እቅድ እየተዘጋጀ ነው። ከዚሁ ጋር በተቀናጀ ሁኔታ የእኛን የዓመቱን እቅድ እንደገና በመመልከት እቅዱን መሠረት በማድረግ ከዲፕሎማቶች ጋር በመነጋገር ችግሮችን ሊፈታ የሚችል የተሻለ እቅድ ማውጣትና በዚያ መንገድ በመሄድ የተሻለ ሥራ ለመሥራት ጥረት ይደረጋል። በሚቀጥለው አመት ሚያዝያ ወር ላይ ለሚካሄደው የንግድ ትርኢት የተሻለ መሥራት የሚያስችላቸው ሥራ ከወዲሁ እየተሠራ ይገኛል።

በዚህ የንግድ ትርኢት ላይ ከንግዱ ማኅበረሰብ የሚጠበቀው የራሱን ምርት አምርቶ የራሱን ምርት የመጠቀም ባህሉን እንዲያጎለብት ነው የሚሉት አቶ ውቤ፤ ለእዚህም ይህንን ‹የኢትዮጵያን ይግዙ› መርህ መከተል አንዱ መሠረታዊ ነገር ሊሆን ይገባል ባይ ናቸው። ‹‹እኛ ቀደም ሲል ጀምሮ ‹የኢትዮጵያን ይግዙ› ብለን እየሠራን እንገኛለን፤ መንግሥትም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በ‹ኢትዮጵያ ታምርት› ንቅናቄ ላይ እየሠራ ነው፤ ሁለቱን በአንድ አቀናጅተን የመንግሥት አካላትና የግሉ ዘርፍ ተናበን የምንሰራበት ሁኔታ ላይ መሠራት አለበት›› ይላሉ።

መንግሥት ለብቻው ‹ኢትዮጵያ ታምርት› በሚል ንቅናቄ፣ የግሉም ዘርፍ እንዲሁ ለብቻው ‹የኢትዮጵያን ይግዙ› በማለት የሚሠሩበት ሁኔታ ሀብትን በተገቢው መንገድ እንዳንጠቀም የሚያደርጉ ናቸው ሲሉ ይገልጻሉ። ይህ አይነቱን አካሄድ ያልተቀናጀና ውጤታማ መሆን የማያስችል ሲሉም ነው የተናገሩት። ይህ እንዳይሆን በመንግሥት በኩል በቅንጅት የሚሠራበት ሁኔታ እንዲኖር ማድረግ እንደሚያስፈልግ ጠቅሰው፣ በግሉ ዘርፍ ራሱ አምራች፤ ራሱ ተጠቃሚ፤ የራሱን ግብዓት የሚፈጥር፤ የራሱን የማምረት ሥርዓት የሚፈጥር የንግድ ማኅበረሰብ እንዲፈጠር ማድረግ እንደሚያስፈልግ አስታውቀዋል። ይህንን በአንድ ላይ አቀናጅቶ ለማስኬድ ትስስርና ትብብር ላይ መሥራትን እንደሚጠይቅ ነው አቶ ውቤ የሚጠቁሙት።

‹የኢትዮጵያን ይግዙ› የግብርና ምርቶቻችን ለመሸጥና ለማስተዋወቅ ትልቅ መንገድ ሆኖ እያገለገለ ነው ብለዋል። አሁን ላይ ‹የኢትዮጵያን ይግዙ› በሚለው መርህ መሠረት የውጭ ሀገር ተሳታፊዎች እየገዙ ትስስርም እየተፈጠረ ነው የሚሉት አቶ ውቤ፤ ‹‹ እኛ ግን በዚያ ልክ ምርቶችን ማቅረብ አልቻልንም፤ አሁንም የምናቀርበው የግብርና ምርት ነው፤ ለዚያውም ምንም እሴት ያልተጨመረበት /ፕሮስስ ያልተደረገ/ ምርት ሲሉ ያመለክታሉ። የውጭ ሀገር ተሳታፊዎችን ግብዓት የምንፈልገው የተለወጠ ምርት አምርተን እንዲገዙን ለማድረግ ነው›› ይላሉ። ይህ ሲባል ደግሞ የእነሱን ግብዓት መጠበቅ ብቻ አይደለም ሲሉ ጠቅሰው፣ እኛም ግብዓት አምርተን ለመጠቀም የምንችልበትን እድል እያመቻቸን የራሳችንን ግብዓት በመጠቀም የራሳችንን ምርት ማምረት ይገባናል ሲሉ ያስገነዝባሉ።

ወርቅነሽ ደምሰው

አዲስ ዘመን   ሐምሌ 12/2015

Recommended For You

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *