ከ120 ሚሊዮን በላይ የሚገመት ህዝብ ያላት ኢትዮጵያ፣ ተገቢውን (ከፍተኛውን) ደረጃ ያሟሉት ትምህርት ቤቶቿ ስድስት ብቻ መሆናቸውን የኢፌዴሪ ትምህርት ሚኒስቴር ይፋ አድርጓል:: ስድስት ብቻ! ይህ ቁጥር አንገት የሚያስደፋና የሚያስደነግጥ መራራ እውነት እንጂ ቀልድ ወይም ውሸት አይደለም።
ከ86 በመቶ በላይ የሚሆኑት የሀገሪቱ የአንደኛና የመካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በዝቅተኛ የጥራት ደረጃ ላይ (ከደረጃ በታች ሆነው) የሚገኙ ናቸው:: ከ71 በመቶ በላይ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችም ለመማር ማስተማር የሚያስፈልጉ መሠረተ ልማቶች አልተሟሉላቸውም፤ ይህ ሀገራዊ ደረቅ እውነታ ነው::
ትምህርት በማንኛውም ማህበረሰብ ውስጥ ድህነትን ለማጥፋትና ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እድገትን ለማምጣት ምትክ የሌለው ሚና የሚጫወት መሣሪያ ከመሆናቸው አንጻር ፤ ትምህርት ቤቶች በዚህ የጥራት ደረጃ ላይ መገኘታቸው እጅግ በጣም አስደንጋጭ ነው::
ትምህርት ለሁሉም ዘርፎች እድገት ቁልፍ ነውና፣ የትምህርት ቤቶች ጥራት መጓደል በሁሉም ዘርፎች ለሚከሰቱ ውድቀቶች አንዱ ምክንያት ይሆናል:: በዚህ ረገድ በኢትዮጵያ የሚስተዋለው የትምህርት ቤቶች ጥራት ጉድለት ሀገሪቱ በሁሉም ዘርፎች ላጋጠሟት ችግሮች አስተዋፅዖ ማድረጉ ሊዘነጋ አይገባም::
ጥራት በሌለው ትምህርት ቤት ‹‹የተማረ›› ተማሪ የሀገር እዳና ሸክም እንጂ የሀገርና የወገን መመኪያ የመሆን እድሉ እጅግ ጠባብ ነው:: ከደረጃ በታች የሆኑ ትምህርት ቤቶች ሀገሪቱ የምትፈልገውን ብቁና በቂ የሰው ኃይል ማፍራት አይችሉም:: ጥራት የሌላቸው ትምህርት ቤቶች ሥራ ፈላጊ እንጂ ስራ ፈጣሪ ትውልድ አይፈጥሩም። የምርምርና የቴክኖሎጂ ሥራው ጎልብቶ ኢኮኖሚውን በሚፈልገው መጠን እንዲያግዝ አያስችሉም።
ይህ የትምህርት ቤቶች ጥራት ዝቅተኛ መሆን በተማሪዎች ውጤት ላይ እጅግ አስከፊና አስደንጋጭ ተፅዕኖ ለማሳደሩ የ2014 ዓ.ም የከፍተኛ ትምህርት ተቋም መግቢያ ፈተና ውጤት ዓይነተኛ ምስክር ነው:: የትምህርት ሚኒስቴር ይፋ ባደረገው የፈተናው ውጤት መረጃ መሠረት፣ ፈተናውን ከወሰዱ 899ሺ 520 ተማሪዎች መካከል ከግማሽ በላይ ውጤት (ከ350 በላይ) ማስመዝገብ የቻሉት 29ሺ 909 (3.3%) ብቻ መሆናቸው ይታወሳል::
ውጤቱ ይፋ ከተደረገ በኋላ ብዙ ዓይነት አስተያየቶች ሲሰነዘሩ ነበር:: ከአስተያየቶቹ መካከል አንዱ ከግማሽ በላይ ውጤት ያስመዘገቡት ተማሪዎች ቁጥር እጅግ ዝቅተኛ መሆኑ የትምህርት ጥራት አለመኖሩን የሚያመለክት እንደሆነ የሚገልፀው ሃሳብ ነበር:: ለትምህርት ጥራት መጓደሉም መንስዔዎች ናቸው የተባሉ ብዙ ምክንያቶችም ተጠቅሰዋል::
የሆነው ሆኖ፣ የፈተናው ውጤት አስደንጋጭና አስገራሚ መሆኑ የሚያጠያይቅ አይደለም:: ከአጠቃላይ ተፈታኞች መካከል አራት በመቶ ያህሉ እንኳ ከግማሽ በላይ ውጤት አለማስመዝገባቸው ‹‹ሀገር ተረካቢ ነው›› ስለሚባለው ትውልድ በእጅጉ እንድንጨነቅ ያስገድደናል::
የፈተናው ውጤት በምን ዓይነት የትምህርት ሁኔታ ውስጥ እያለፍን እንደምንገኝ በግልፅ አሳይቷል:: አራት ከመቶ ተፈታኞች እንኳ ከግማሽ በላይ ውጤት አለማስመዝገባቸው ትምህርትን እንዴት እየቀለድንበት እንደሆነ ጥሩ ማሳያ ነው:: ይህ ደግሞ የሀገር ግንባታ ዋነኛ መሠረት የሆነው አምድና የሀገሪቱ ህልውና እጅግ አስደንጋጭ አደጋ ውስጥ እንደገባ ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ነው:: ታዲያ ይህ የሆነው በእርግማን ወይም በክፉ ምኞት ሳይሆን በትምህርት ቤቶች ጥራት ጉድለት ምክንያት ነው:: ጥራት በጎደለው ትምህርት ቤት ውስጥ ‹‹የተማረ›› ተማሪ ከፍተኛ ውጤት ሊያስመዘግብ አይችልም::
በመሆኑም ከዚህ አስደንጋጭ ችግር ለመውጣት የሚያስችሉ የመፍትሄ አማራጮችን በፍጥነት መመልከትና መተግበር ያስፈልጋል:: የትምህርት ሚኒስቴርም ትምህርት ቤቶችን የማሻሻል ሥራ የመንግሥት ወይም የአንድ ወገን ብቻ ኃላፊነት እንዳልሆነና የትምህርት ቤቶችን ችግር መፍታት የሚቻለው ማህበረሰቡን በዘላቂነት ማሳተፍ ሲቻል ነው በሚል እምነት፣ ‹‹ትምህርት ለትውልድ›› የትምህርት ቤቶች መሠረተ ልማት ማሻሻያ ሀገራዊ ንቅናቄን ሰኔ 25 ቀን 2015 ዓ.ም በይፋ አስጀምሯል:: የህዝባዊ ሀገራዊ ንቅናቄው ማስጀመሪያ መርሃ ግብሮች በክልሎችም እየተካሄዱ ይገኛሉ::
ንቅናቄው የቀድሞ ተማሪዎች፣ ታዋቂ ግለሰቦች፣ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን፣ ባለሀብቶች፣ የግልና የመንግሥት ተቋማት እንዲሁም የልማት አጋሮች እንዲሁም ሌሎች የኅብረተሰብ ክፍሎች በትውልድ ቦታቸው፣ በተማሩባቸው ቦታዎች እና በሚሠሩባቸው አካባቢዎች የትምህርት ቤቶችን መሠረተ ልማት ለማሟላት አስተዋጽኦ የሚያደርጉበት እንደሆነ ተገልጿል::
ስለሆነም ይህን በመላው ኢትዮጵያ ከሚገኙ ትምህርት ቤቶች መካከል ተገቢውን (ከፍተኛውን) ደረጃ ያሟሉት ትምህርት ቤቶች ስድስት ብቻ የመሆናቸውን አስደንጋጭ እውነት አውቆ እጅን አጣጥፎ መቀመጥ ከሀገር ክህደት ያላነሰ ወንጀልና ነውር ነውና ሁሉም ዜጋ ያለውን ሀብት (ጊዜ፣ እውቀት፣ ገንዘብና ጉልበት) አስተባብሮ ሊረባረብ ይገባል::
የኢትዮጵያ የትምህርትና ሥልጠና ሥርዓት ለትምህርት ዘርፍ መሻሻልና የተማረ የሰው ኃይል ለማፍራት አዎንታዊ አስተዋፅዖዎችን እንዳበረከተ ባይካድም፣ ዓይነተ ብዙና ውስብስብ ችግሮችም አሉበት:: ከእነዚህ ችግሮቹ መካከል አንዱ የትምህርት ቤቶች ጥራት ጉድለት ነው:: የትምህርት ቤቶች ጥራት ጉድለት የትምህርትና ሥልጠና ሥርዓቱ ከተግባር ክህሎትና ፈጠራ ይልቅ በንድፈ ሃሳብ ላይ ከማተኮሩ እንዲሁም የምዘና ሥርዓቱም ለተግባራዊ እውቀት ትኩረት ካለመስጠቱ ጋር ተደምሮ የትምህርት ዘርፉ ጉዞ አሳሳቢ እንዲሆን አድርጎታል::
የአንድ ሀገር የትምህርት ሥርዓት መበላሸት የሀገሪቱ ህልውና አደጋ ውስጥ እንደገባ ሁነኛ ማሳያ ተደርጎ ይወሰዳል:: ሰላም የሰፈነባት፣ ማህበራዊ መረጋጋት ያለባት፣ ምጣኔ ሀብቷ ያደገና ፖለቲካዋ የሰከነ ሀገር እውን ማድረግ የሚቻለው ጥራት ባለው የትምህርት ሥርዓት የተገነባ ትውልድ ማፍራት ሲቻል ነው:: ጥራት በሌለውና በወደቀ የትምህርት ሥርዓት ውስጥ ያለፈ ትውልድ ለሀገር ህልውና ትልቅ አደጋ ይሆናል:: ለዚህም ነው ‹‹አንድን ሀገር ለማፍረስ ጦር ማዝመት ሳያስፈልግ፣ የሀገሪቱን የትምህርት ሥርዓት ማበላሸት በቂ ነው›› የሚባለውን ሃሳብ በተደጋጋሚ የምንሰማው::
በራሳቸው የሚተማመኑ፣ በምክንያታዊ ትንተና የሚያምኑ፣ በሙያቸው ብቃት ያላቸው፣ ሥራ ፈጣሪዎች፣ አዳዲስ ግኝቶችን አፍላቂዎች፣ ጠንካራ የሥነ ምግባርና ግብረገባዊ እሴቶችን የተላበሱ፣ ለሕግ ዘብ የቆሙ፣ በዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪና ብቁ ዜጋ ሆነው አጠቃላይ ሰብእናቸው የተገነባ ዜጎችን ማፍራት የሚቻለው ጥራት ባለው የትምህርት ሥርዓት ነው። አንዲት ሀገር ሁለንተናዊ እድገትን በማምጣት የሕዝቦቿን ኑሮ ማሳደግ የምትችለው በሚኖራት የሰው ኃይል እምቅ አቅም ነው:: የሰው ኃይል መገንቢያው ዋነኛው መሣሪያ ደግሞ ትምህርት ነው::
አስተማማኝና ብቁ የሰው ኃይል ለማፍራት ብቸኛው መንገድ ጥራት ያለው የትምህርት ሥርዓትን መዘርጋት ነው:: ጥራት ያለው የትምህርት ሥርዓት ለመዘርጋት ከሚያስፈልጉ ግብዓቶች መካከል አንዱና ዋነኛው ደግሞ የመማር ማስተማር ሂደቱን ውጤታማ የሚያደርጉ ደረጃቸውን የጠበቁ ትምህርት ቤቶችን በሚፈለገው ብዛትና ጥራት ማቅረብ (መገንባት) ነው:: የትምህርት ጥራትን በተጨባጭ ዕውን ለማድረግ ትምህርት ቤቶች መሰረት በመሆናቸው ጥራታቸውንና አሰራራቸውን ማሻሻል አማራጭ የሌለው ተግባር መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል።
እስኪ ጉዳዩ ትኩረት ቢያገኝ፣ ያን አስደንጋጭ እውነት ልድገመውና ጉዳዬን ልቋጭ … በመላው ኢትዮጵያ ከሚገኙ ትምህርት ቤቶች መካከል ተገቢውን (ከፍተኛውን) ደረጃ ያሟሉት ትምህርት ቤቶች ስድስት ብቻ ናቸው:: ስድስት ብቻ! ከ86 በመቶ በላይ የሚሆኑት የሀገሪቱ ትምህርት ቤቶች በዝቅተኛ የጥራት ደረጃ ላይ (ከደረጃ በታች ሆነው) የሚገኙ ናቸው!
ፒያንኪ ዘኢትዮጵያ
አዲስ ዘመን ረቡዕ ሐምሌ 5 ቀን 2015 ዓ.ም