አረንጓዴ ዐሻራችን፤ የወል እውነታችን!!

በዓለም ላይ እየበረታና እየተስፋፋ የመጣው የአየር ንብረት ለውጥ የሰው ልጆችን ጨምሮ በምድር ላይ ሕይወት ያላቸውን ፍጥረታት ሁሉ የሕልውና አደጋ ሆኖ ቀጥሏል። ችግሩ ለሰው ልጆች የጤና መቃወስና ለተለያዩ ሕመሞች መዳረግ፤ የድርቅ መፈራረቅና የጎርፍ አደጋ እንዲሁም የግብርና ምርት ለመቀነሱ ዋነኛ ምክንያት መሆን ከጀመረም ዋል አደር ብሏል። በተለይም በማደግ ላይ ያሉ ሀገሮች የችግሮቹ ገፈት ቀማሽ በመሆን የጉዳታቸው መጠን ከዓመት ዓመት እየበረታ ይገኛል።

ይህንን ዓለም አቀፍ ችግር በመከላከልና በመቋቋም ረገድ ኢትዮጵያ የአረንጓዴ ልማት መርሃ- ግብር ነድፋ ተግባራዊ እንቅስቃሴዎችን ከጀመረች ዓመታት ተቆጥረዋል። በእርግጥም ከአንድ ሺ ዓመታት በፊት ጀምሮ የኢትዮጵያ ሕዝብ የዛፍ ችግኞችን የመትከል ልማድ እንዳለውና እንደነበረው የታሪክ መዛግብት ያስረዳሉ። ይሁንና እያደር የዛፎች መቆረጥ በመብዛቱና እነርሱን የመተካት ጥረቱ ዝቅተኛ በመሆኑ ኢትዮጵያ አሁን ላለችበት የደን መራቆት ተዳርጋለች።

ይህንን መራቆት ለማስቀረት በኢትዮጵያ በተለየ መልኩ የአረንጓዴ ዐሻራ ዘመቻ እየተካሄደ ነው። በዚህም ባለፉት አራት ዓመታትም ከ25 ቢሊየን በላይ ችግኞችን መትከል ተችሏል። ኢትዮጵያዊያኖች እንደ አንድ ሆነው እየተሳተፉበት ያለው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሀ ግብር፣ በሀገሪቱ ከተደረጉትና ኅብረተሰቡን በአንድ ወቅት በጋራ በማሳተፍ ከተሰሩ ሥራዎች ሁሉ ግዝፈትን የተላበሰ ነው።

ኢትዮጵያ ባለፉት አራት ዓመታት ያሳየችውን ስኬት ለመድገም “ነገን ዛሬ እንትከል” በሚል መሪ ቃል ሁለተኛ ምዕራፍ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ-ግብርን ከጀመረች ቀናት ተቆጥረዋል። ለዚህም ዘንድሮ 6 ነጥብ 5 ቢሊየን ችግኞችን ለመትከል ዕቅድ ተይዞ እየተሰራ ሲሆን፤ እስካሁንም 3 ነጥብ 4 ቢሊየን ችግኞች መተከላቸውን የግብርና ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል።

የተባበሩት መንግሥታት የአካባቢ ጥበቃ ፕሮግራም እንደሚለው አረንጓዴ ኢኮኖሚ የዜጎችን የኑሮ ሁኔታ የሚያሻሽል፣ ማህበራዊ ፍትህን የሚያመጣ፣ የአካባቢ አደጋዎችንና ሥነ-ምህዳራዊ እጥረቶችን በእጅጉ የሚቀንስ የልማት መንገድ ነው።

በሕገ-መንግስቱ አንቀጽ 44(1) መሠረት ሁሉም ሰዎች ንጹህና ጤናማ በሆነ አካባቢ የመኖር መብት እንዳላቸው ሲደነግግ በአንቀጽ 92(1) መሠረት ደግሞ መንግሥት ሁሉም ኢትዮጵያዊ ንጹህና ጤናማ አካባቢ እንዲኖረው የመጣር ኃላፊነት አለበት። በአንቀጽ 92(4) መሠረትም መንግሥትና ዜጎች አካባቢያቸውን የመንከባከብ ግዴታ አለባቸው።

ዘርፉ ባለሙያዎች እንደሚያስገነዝቡትም፣ የአየር ንብረት ለውጥ ተጽእኖን የመቋቋምና የአረንጓዴ ልማት ሥራዎች ለአንድ አካል የሚተው አይደለም። እንደ ሀገር የሚደረገው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር የሁሉም ኢትዮጵያዊ ጉዳይ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የዘንድሮ ሁለተኛው ምዕራፍ አረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር ባስጀመሩበት ወቅት፤ “በዚህ ጉዳይ ላይ የፖለቲካ ልዩነት፣ የወቅታዊ አጀንዳዎች፣ የእምነት ጉዳይ፣ የጾታ ጉዳይ፣ የሀብት ጉዳይ ሁሉ ትርጉም የለውም። ይሄን የሚሰራ ሰው ለልጆቹ ነው። ለነገ ትውልድ ነው። ለልጁ ለመትከል ዛሬ ስለተጋጨ፣ ዛሬ ስላኮረፈ ልጁን ማስቀየም የለበትም። ሀገራችን ላይ አሁን ላይ ያለውን ነገር በእርቅ፣ በመነጋገር እንፈታዋለን፤ ልጆቻችን ግን የኛን ዳፋ የኛን ችግር አሸጋግረን የምናስቸግራቸው መሆን የለበትም” ብለዋል።

“የምንሰራው ሥራ ለልጆቻችን፣ ለትውልድ እንዲሁም ለሀገራችን ነው። ሀገር ደግሞ የወል እውነት፣ የወል ሃብት ናት። ትውልድም የወል እውነት የወል ሃብት ነው። የወል የሆነ ሃብት ላይ ምንም አይነት ምክንያት አያስፈልግም። ʿችግኝ የማንተክለው አሁን ያለው መንግሥት፣ አሁን ያለው ፖለቲካ ስለማይመቸን ነው የሚሉ አመለካከቶች ትክክል አይደሉም” ማለታቸው ይታወሳል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህ ቅኝት በሐምሌ 10 ቀን 2015 ዓ.ም 500 ሚሊዮን ችግኞችን በአንድ ጀምበር ለመትከል ጥሪ ማስተላለፋቸውን ተከትሎም እንደ ወትሮ ሁሉ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ለማለት በሚያስደፍር መልኩም የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር የወል እውነቱ እንደሆነ ተረድቶ በመርሃ ግብሩ ላይ የራሱን ዐሻራ አሳርፏል።

በአንድ ጀምበር አረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብሩም ሁሉም ኢትዮጵያውያን አረንጓዴ ታሪክ ሠርተዋል፤ አረንጓዴ ታሪክ ጽፈዋል። የራሳችንን ሪከርድ አሻሽለዋል። ታሪክ ሰሪ ትውልድ መሆናቸውን በተግባር ለዓለም አስመስክረዋል። አንድ ከሆነ የማይፈቱት ችግር፣ ከተባበሩ ለድል እንደሚበቁ በተጨባጭ አሳይተዋል። ትላንት እንደ ሀገር የተሰራው ታሪክ ነገም ድህነትን አሸንፈን ለመውጣት በጀመርነው ትግል ሊደገም የሚገባ ነው መደገም ይኖርበታል።

የችግኝ ተከላ የአንድ ወቅት ተግባር ብቻ ሳይሆን ባሕል ሆኖ እንዲቀጥል ማድረግ፤ ተከላውን ማከናወን ብቻ ሳይሆን ተንከባክቦ ለቁም ነገር ማብቃት ከሁላችንም የሚጠበቅ ሀገራዊ ኃላፊነት ነው፤ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብሩም በቀጣይ የክረምት ወራት የሚቀጥል የሁላችንም የቤት ሥራ መሆኑም በአግባቡ በመረዳት መረባረር ተገቢ ነው።

ጉዱ ካሳ ከማንኩሳ

አዲስ ዘመን   ሐምሌ 12/2015

Recommended For You

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *