ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ ኢትዮጵያ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብርን በመተግበር በዓለም አቀፉ መድረክ ፊታውራሪ ሆና በቢሊዮን የሚቆጠሩ ችግኞችን በመትከል ለዓለም ምሳሌ በመሆን ላይ ትገኛለች። የመጀመሪያው ዙር ተብሎ በሚታወቀውና አራት አመታትን ባስቆጠረው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር 20 ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከል ዕቅድ ተይዞ 25 ቢሊዮን ችግኞችን በመትከል አዲስ ታሪክ መጻፍ ተችሏል።
የዚሁ መርሃ ግብር አንዱ አካል የሆነውና በአንድ ጀምበር 350 ሚሊዮን ችግኞችን በመትከል በህንድ ተይዞ የነበረውን ሪከርድ በመስበር ኢትዮጵያ አዲስ ታሪክ ጽፋለች። ሰኔ 1 ቀን 2015 ዓ.ም በተጀመረው ሁለተኛው መርሃ ግብር ደግሞ 6ነጥብ 5 ቢሊዮን ችግኝ ለመትከል ታቅዶ ወደ እንቅስቃሴ የተገባ ሲሆን፣ የዚሁ አካል የሆነው በአንድ ጀምበር 500 ሚሊዮን ችግኞችን የመትከል ዕቅድን ኢትዮጵያውያን 567 ሚሊዮን ችግኝ በመትከል አስደማሚ በሆነ መልኩ በማሳካት የራሳቸውን ሪከርድ ማደስ ችለዋል።
ሐምሌ 10 ቀን በተካሄደው የ500 ሚሊዮን የአንድ ጀምበር የችግኝ መትከል መርሃ ግብር ከህጻን እስከ አረጋውያን፤ ከሴት እስከ ወንድ ከተማረው እስካልተማረው በአጠቃላይ ሁሉም ማኅበረሰብ የዜግነት ግዴታውን እንዲወጣ በተደረገው ሀገራዊ ጥሪ መሠረት ሕዝቡ ንቅል ብሎ በመውጣት አዲስ ታሪክ ጽፏል። በዕለቱም ከ34 ሚሊዮን ሕዝብ በላይ በመውጣት 567 ሚሊዮን ችግኝ በመትከል በዓለም መድረክ አዲስ ታሪክ ጽፏል።
በዕለቱ የነበረውም አንድነት፤ ለጋራ ችግር በጋራ የመቆም ጥረት፤ ሀገራዊ ፍቅርና ትብብር ኢትዮጵያውያንን በዓለም መድረክ አሸናፊዎች እንዲሆኑ አስችሏቸዋል። አንድነት፤ ፍቅር፤ ትብብር ካለ ማንኛውንም ችግር በጋራ ማሸነፍ እንደሚቻል ኢትዮጵያውያን በአደባባይ ምሳሌ ሆነዋል።
ካለፉት አራት አመታት ጀምሮ ኢትዮጵያ በአንድ በኩል በልማት ግስጋሴ በሌላ በኩል በግጭትና በጦርነት መካከል ሆና ስትጓዝ ቆይታለች። ባለፉት አራት አመታት ኢትዮጵያውያን የህዳሴ ግድብ ከገባበት አጣብቂኝ በማውጣትና አስተማማኝ በሆነ ከፍታ እንዲጓዝ በማድረግ አዲስ ታሪክ መጻፍ ችለዋል። ከዚሁ ጎን ለጎን በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶክተር) ፊታውራሪነት ኢትዮጵያውያን በአረንጓዴ ዐሻራ ስኬት ማጎናጸፍ ችለዋል።
የሀገሪቱን ገጽታ እና የቱሪስት ፍሰት የሚያሳድጉ ሥራዎችንም በመሥራት ኢትዮጵያ በጎብኚዎች ተመራጭ ሀገር እንድትሆን የተሠራውም ሥራ የብዙዎችንም ቀልብ የገዛ ነው። በገበታ ለሸገር ፕሮጀክት የአንድነት፤ የወንድማማችነትና የእንጦጦ ፓርኮች ከአዲስ አበባ አልፈው የሀገር ኩራት ለመሆን በቅተዋል። በገበታ ለሀገር ደግሞ የኮይሻ፤ የጎርጎራና የወንጪ ፕሮጀክቶች የኢትዮጵያ መለያ ለመሆን በቅተዋል። ባለፉት አራት አመታት በግብርና፤ በኢንዱስትሪና በኤክስፖርት ዘርፎች የታዩት እምርታዎች የኢትዮጵያን ከፍታና የወደፊት ተስፋ የሚያመላክቱ ናቸው።
ከእነዚሁ ስኬቶች ጎን ለጎን ጦርነት፤ ግጭት፤ መፈናቀል፤ ስደት፤ ድርቅ፤ የመሳሰሉት ችግሮች ኢትዮጵያን ፈትነዋታል። አለመተማመን፤ መወነጃጀል፤ ጥላቻና ቂምም የፖለቲካችን አንዱ መለያ ሆኖ አብሮን ቆይቷል። ይህም ሁኔታ በተወሰኑ የሀገሪቱ አካባቢዎች ጦርነት እንዲቀሰቀስ፤ ግጭት እንዲበራከት፤ ሞትና የንብረት ውድመት እንዲከሰት አድርጓል። በዚህም በርካቶች ሕይወታቸውን አጥተዋል፤ ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል፤ ተሰደዋል።
ይህ ታሪክ ግን አንድ ቦታ ማብቃት አለበት። በተለይም ከትላንት በስቲያ የታየው እና ኢትዮጵያውያን በአንድነት ያሸነፉበት በአንድ ጀምበር የ500 ሚሊዮን ችግኝ የመትከል መርሃ ግብር ኢትዮጵያን በፍቅር፤ በአንድነትና በትብብር ከቆሙ ነባር ችግሮቻቸውን ነቅለው ወደ ብልጽግና ጎዳና መጓዝ እንደሚችሉ ማሳያ መሆን የሚችል ነው።
ኢትዮጵያውን በአንድነት ያሳኩት የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር በጋራ ችግኝ ከመትከል ባሻገር ችግሮቻቸውንም በጋራ ነቅለው መጣል እንደሚችሉ ተምሳሌት የሚሆን ነው። የሀገሪቱ ገጽታ ሆነው የቆዩትን ጦርነት፤ ግጭት፤ መፈናቀል፤ ስደት፤ አለመተማመን፤ መወነጃጀል፤ ጥላቻና ቂምን ነቅሎ ለመጣል በአረንጓዴ ዐሻራ የታየውን ስኬት እንደ ትልቅ አቅምና ተሞክሮ ልንጠቀምበት ይገባል።
አዲስ ዘመን ሐምሌ 12/2015