በአንድ ጀምበር 500 ሚሊዮን ችግኝ መትከል የኢትዮጵያ ጉዳይ ነው !

 የዓለማችንም ሆነ የሰው ልጅ ዐበይት ስጋቶች የዓለም ሙቀት መጨመር፣ የኒውክሌር ጦር መሳሪያና ሽብርተኝነት ናቸው ቢባልም። ከጊዜ ወደ ጊዜ የሰውን ልጅ ያለ ልዩነት እያስጨነቀ ያለው በዓለም ሙቀት መጨመር የተነሳ እየተከሰተ ያለው የአየር ንብረት ለውጥ ነው። የዓለም ሙቀት መጨመር ወይም “global warming ” በረጅም ጊዜ ሒደት እየተስተዋለ የመጣ የከባቢ አየር ሙቀት መጨመር ነው። ለከባቢ አየር ሙቀት መጨመር ደግሞ የሰው ልጅ ግንባር ቀደም ተጠያቂ ነው። ወደ ከባቢ አየር የግሪንሀውስ ጋዝ ማለትም ካርበን ዳይኦክሳይድና ሚቴን በብዛት በመልቀቅ ሙቀት እንዲጨምር አድርጓል። ይህ ደግሞ የአየር ንብረት መዛባትን እያስከተለ ነው።

ሰሞኑን በአውሮፓ ተሰምቶም ሆነ ታይቶ የማያውቀው ከፍተኛ ሙቀት በመከሰቱ ዜጎች እርቃናቸው በዛፍ ጥላዎች፣ በባሕር ዳርቻዎችና በከተማ ፋውንቴኖች እንዲኮለኮሉ ሲያደርግ፤ በኒውዮርክና ኒው ደልሒ ደግሞ በጣለው በታሪክ ከፍተኛ ዝናብ የጎርፍ መጥለቅለቅ ተከስቷል። በደቡብ አፍሪካ ጆሀንስበርግ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ በአውሮፓና በአሜሪካ ክረምት እንደምናስተውለው ከፍተኛ በረዶ ጥሏል። ሰሞነኛዎቹን የአየር ንብረት መዛባት አነሳሁ እንጂ ሀገራችንን ጨምሮ አኅጉራችን ያደጉት ሀገራት ሲለቁት በኖሩ ካርበን ዳይኦክሳይድና ሚቴን ጋዝ ፍዳችንን መክፈል ከጀመርን አስርት ዓመታት ተቆጠሩ።

በርሀማነት እየተስፋፋ፣ ግግር በረዶ እየቀለጠ፣ የባሕርና የውቅያኖስ ከፍታ እየጨመረ፣ የአፈር ምርታማነት እየቀነሰ፣ ዝናብ እየጠፋ በአጠቃላይ የአየር ንብረቱና ስነ ምህዳሩ እየተቀየር እናት ተፈጥሮ ለፍጥረት ሁሉ ጀርባ እየሰጠች ነው። በሰው ልጅ ህልውና ላይ አደጋ እየተደቀነ ይገኛል። ፎሲል ፊውል ወይም ነዳጅ፣ ጋዝና ድንጋይ ከሰል በስፋት ጥቅም ላይ እየዋሉ መሆናቸው፤ የደኖች መመናመን፣ የሕዝብ ቁጥር መጨመር፣ የኢንዱስትሪዎች መስፋፋትና ለአካባቢ ጥበቃ ግድ የሌለው ግብርና ካርበን ዳይኦክሳይድና ሚቴን በከፍተኛ መጠን ወደ ከባቢ አየር መለቀቁ የአለማችንን ሙቀት ጨምሯል።

የዓለም ሙቀትን ለመቀነስ የተቀናጀ አለማቀፍ ጥረትንና ርብርብን ይጠይቃል። የግሪንሀውስ ልቀትን መቀነስ፣ ታዳሽ ኃይልን ማስፋፋት፣ የመሬት አጠቃቀምን ማሻሻል፣ የሕዝብ ቁጥርን መቀነስ፣ የደን ጭፍጨፋን ማስቆምና በስፋት ችግኝ መትከል ግድ ይላል። ሀገራችን በተለይ ባለፉት አምስት ዓመታት አርዓያነት ያለው ተግባር እያከናወነች ነው። ታዳሽ ኃይልን እያስፋፋች፤ ወደ ከባቢ አየር የምትለቀውን ግሪንሀውስ እየቀነሰች፤ በየዓመቱ በቢሊየኖች የሚቆጠሩ ችግኝ እየተከለች ነው። ሆኖም ዓለም አርዓያነቷን ሊከተልና ሊደግፋት ይገባል። በአንድ ሀገር ጥረት ብቻ የዓለም ሙቀት መጨመርን መቀነስና መከላከል አይቻልምና።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የፊታችን ሐምሌ 10 ቀን 2015 ዓ.ም ኢትዮጵያውያን በአንድ ጀምበር 500 ሚሊየን ችግኝ በመትከል ታሪክ እንዲሰሩ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ መርሀ ግብሩን፣ አስመልክተው ባስተላለፉት መልዕክት፤ አረንጓዴ ዐሻራ ለእኛ ብዙ ነገራችን ነው፤ የግብርና ምርታችንን ከፍ የሚያደርግና በምግብ ራሳችን እንድንችል የሚያበቃን ነው ብለዋል፡፡ ከዚህ ባለፈም “ኢትዮጵያ ለምለሟ” ብለን ያዜምንላትን ዜማ፣ እውነት እንዲሆን የሚያደርግ ነው። ድርቅና ረሃብ የሚባለውን ታሪክ ለማድረግ የሚያስችል ዐቅም ነው ሲሉም ገልጸዋል፡፡

ሐምሌ 10 ቀን 2015 ዓ.ም በአንድ ጀምበር 500 ሚሊዮን ችግኝ እንተክላለን፤ ዳግም ታሪክ እንስራ፣ በዚህ ቀን ኢትዮጵያውያን የራሳችንን ሪከርድ እንሰብራለን፤ ከዚህ በፊት ከ350 ሚሊዮን በላይ ዛፎች በአንድ ጀምበር ተክለን ዓለምን ጉድ አስብለናል። ዘንድሮም 6 ነጥብ 5 ቢሊዮን ችግኝ ለመትከል በየክልሉ፣ በየዞኑና በየወረዳው ክረምቱን ከምንሠራቸው ሥራዎች አንዱ አረንጓዴ ዐሻራችንን ማኖር ብለን እየሰራን ነው። ባለፉት አምስት ዓመታት 25 ቢሊዮን ችግኞችን ተክለናል።

ሐምሌ 10 ቀን 2015 ዓ/ም ጀምበር ወጥታ እስክትገባ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ቤቱ አይውልም፤ በዕቅፍ ካለ ሕጻን፣ በድካም ካለ አረጋዊ፣ በአልጋ ከሚገኝ ታማሚ በስተቀር ቤቱ ማንም አይውልም። ምክንያቱም ይህ የፖለቲካ ጉዳይ አይደለም፤ የፓርቲ ፕሮግራምም አይደለም፤ የመንግሥት ጉዳይም አይደለም። ይህ የኢትዮጵያ ጉዳይ ነው።

አረንጓዴ ዐሻራ አሁን ያለው ትውልድ የትናንት ዕዳውን ይከፍልበታል፤ በደን ተሸፍና የኖረች ሀገር ዛሬ ራቁቷን እንድትሆን ያደረግናት እኛ ነን፣ ከተከልነው የቆረጥነው በልጧል፣ የትናንቱ ደን በታሪክ መዛግብት ላይ ብቻ የሚገኝ ሆኗል፡፡ ዐረንጓዴ ዐሻራ ይሄንን የቀደምቶቻችን ዕዳ እንድንከፍል ያደርጋል። ለነገ ትውልድ ወረት ነው፡፡ የምናስረክባት ሀገር በሁለንተናዋ ሉዓላዊነቷ የተጠበቀ መሆን አለበት። የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ፣ የዲፕሎማሲ፣ የማኅበራዊ ኑሮ፣ የተፈጥሮ ሉዓላዊነቶቿ ተሟልተው መከበር አለባቸው።

ስድስት በር ያለው ቤት አንዱን ከፍቶ እስከዋለ ድረስ የሌሎቹ በሮች መዘጋት ደኅንነቱን አያስጠብቅለትም። የሀገር ሉዓላዊነትም በሁለንተናዊ መስኮች እስካልተጠበቀ ድረስ በተከፈተው በር የሚገባው ብዙ ነው፣ ታዳሽ ኃይልን የኢነርጂ ዋና ምንጭ ለማድረግ ቆርጠን ለተነሣን ሕዝቦች፤ አረንጓዴ ዐሻራ እንደ ዐድዋ ዘመቻ የሉዓላዊነታችን ማስጠበቂያችን ነው።

የእምነትና የባህል፣ የፖለቲካ ፓርቲና አስተሳሰብ፣ እድሜና ጾታ፣ የትምህርትና የኑሮ ደረጃ ሳይለየን ሐምሌ 10 ቀን ከጀምበር ቀድመን እንውጣ፤ ከጀምበር በኋላ እንመለሳለን፤ ኢትዮጵያን አረንጓዴ እናለብሳለን፡፡ በኢትዮጵያ የምትኖሩ የውጭ ሀገር ዜጎች፣ ኤምባሲዎች፣ የዓለም አቀፍ ድርጅቶች ሠራተኞች፣ በኢትዮጵያ በኩል የምታልፉ መንገደኞች፣ ለተለያየ ጉዳይ በአጋጣሚ ወደ ኢትዮጵያ የመጣችሁ የውጭ ሀገር ሰዎች ሐምሌ 10 ቀን አረንጓዴ ዐሻራችሁን አኑሩ፣ ዓለምን በኢትዮጵያ በኩል አልብሱ፤ ኢትዮጵያ ታሪክ ስትሰራ የታሪኩ አካል ሁኑ፣ ኢትዮጵያ ዓመቱን ሙሉ አረንጓዴ እስክትለብስ ድረስ መትከላችንን እንቀጥላለን ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥሪ አድርገዋል።

ሀገራችን በታሪኳ ከፈጸመቻቸው እየፈጸመቻቸው ካሉ ግዙፋን ፕሮጀክቶች ታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ጨምሮ አንድ ላይ ቢደመሩ የ” አረንጓዴ አሻራ “ን ያህል ክብደት አልሰጣቸውም፡፡ የህዳሴውም ሆነ የሌሎች ታላላቅ ግድቦች ህልውና የሚወሰነው ዛሬ በትጋት በምንከውነው የአካባቢ ጥበቃ ስራ ነውና፡፡ ችግኝ ተከላ የአየር ንብረት ለውጥን፣ የዓለም ሙቀት መጨመርንና የአካባቢ ጥበቃ

 ቁምላቸው አበበ በአማራ ባህል፣ ቱሪዝምና ማስታወቂያ ቢሮ፤ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት፤ በደቡብ መገናኛ ብዙኀን፤ በጋዜጠኝነትና በታሪክ ባለሙያነት ያገለገሉ ሲሆን፤ የደቡብ ኤፍ ኤምን ከባልደረቦቻቸው ጋር በመሆንም አቋቁመዋል። በፌዴራል ውሃ ስራዎች ኮንስትራክሽን ድርጅትና በአለ በጅምላ በኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተርነት አገልግለዋል። ከአአዩ በቋንቋና ታሪክ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን የሰሩ ሲሆን፤ በዚሁ ዩኒቨርሲቲ በጋዜጠኝነትና ኮሙዩኒኬሽን ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በማጠናቀቅ ላይ እያሉ ባጋጠማቸው ድንገተኛ ህመም ተስተጓጉሏል። ጥልቅ ሀሳብ ያዘሉ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ የሚያተኩሩ ፁሑፎችን በማህበራዊ ሚዲያና በተለያዩ ጋዜጦች በማውጣት ይታወቃሉ።

ችግሮቻችንም ሆነ ድህነትን፣ የምግብ ዋስትና ጎድለትን፣ የምርታማነት ተግዳሮትን፣ ድርቅን፣ ርሀብን፣ የዝናብ መቆራረጥንና መቅረት፣ የውሀ እጥረትን፣ የኑሮ ውድነትን፣ በፈጣን የሕዝብ ቁጥር እድገትና በምርት አቅርቦት መካከል ያለውን ክፍተት፣ ስራ አጥነት፣ ከገጠር ወደ ከተማ የሚደረግ ፍልሰትን፣ የጸጥታና የደህንነት ችግርን፣ ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ የሚደረገውን ሽግግር በማሳለጥ እና ሁለንተናዊ ብልፅግናን ለማለም መስፈንጠሪያ በመሆን ያገለግላል። ለዚህ ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ችግኝ ተከላን ሁሉ ነገራችን ያሉት። እኔም የችግሮቻችን ሁሉ መፍቻ ማስተር ኪይ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡

ከጥቂት ዓመታት በፊት ደጋ የነበሩ ወይና ደጋ፣ ወይና ደጋ የነበሩ ቆላ፣ ቆላ የነበሩ በርሀ፣ በርሃ የነበሩ አካባቢዎች እንደ ሳህራ እጅግ በርሃማ እየሆኑ ነው፡፡ ዓመት እስካመት ይገማሸሩ የነበሩ ወንዞች፣ በየገመገሙ፣ በየጋራና በየሸንተረሩ ይንፎለፎሉ የነበሩ ምንጮች ደርቀዋል፡፡ ወደ 60 በመቶና ከዚያ በላይ የነበረው የደን ሽፋን እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ከሶስት በመቶ የማይበልጥ ነበር፡፡ አሁን በተደረገ ርብርብ የደን ሽፋኑን ወደ 17 በመቶ ከፍ ብሏል ቢባልም አኃዙን ተከትሎ የመጣው የአየር ንብረት ለውጥ ጥራት ለሙግት ክፍት ነው፡፡ በአየር ንብረት ለውጡ የተነሳ በየአስር ዓመቱ ይከሰት የነበረው ድርቅ በየዓመቱ ከመመላለሱ ባሻገር በበልግና በመኸረም መከሰት ጀምሯል፡፡ ከዓመት ዓመት ይከሰት በነበረ የዝናብ እጥረት የተነሳ የከርሰና የገፅ ምድር ውሃ እጥረት ተከስቷል፡፡

እየተቆራረጠና እየተዛባ የሚጥለውን ዝናብ ቢሆንም ደኖች በመራቆታቸው የተነሳ አፈሩ ውሃ መያዝ ባለመቻሉ ጠብ ባለቁጥር ስለሚሸረሸር የአፈር መከላትን እያባባሰ ግብርናውን አደጋ ላይ ጥሎታል፡፡ በዚህ የተነሳ ከሕዝብ ብዛቷ አንጻር ተመጣጣኝ ምርት ማምረት አልቻለችም፡፡ የግብርና ቴክኖሎጂ ምርጥ ዘር፣ ማዳበሪያ፣ ፀረ አረምና ተባይ ኬሚካል በመጠቀም ምርትን ለማሳደግ የተደረገው ጥረት አይደለም አግሮ ኢንዱስትሪውን ዜጋውን መመገብ እንደተሳነው ከመንገድ ቀርቷል፡፡ በቅርብ የወጡ ጥናቶች 47 በመቶ የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን የከፋ የምግብ እጥረት እንዳለባቸው ያትታሉ፡፡

የዓለም ሙቀት መጨመርን ተከትሎ የመጣው የአየር ንብረት ለውጥ ለሀገራችንም ሆነ ለአፍሪካ ጥሩ ዜና የለውም፡፡ እየታረሰ የነበረው መሬት ለምነቱን በማጣቱና በመራቆቱ የተነሳ እየቀነስና እየተራቆተ ይገኛል፡፡ ግብርና ለሀገሪቱ ጥቅል ብሔራዊ ምርት ድርሻው 47 በመቶ ቢሆንም፤ መታረስ ካለበት መሬት 17 በመቶ ብቻ ነው እየታረሰ ያለው፡፡ ይህ በሌላ በኩል እርስ በርሱ የሚቃረን ይመስላል፡፡ የከፋ የምግብ እህል እጥረት፣ ድህነትና የበዛ ስራ አጥ ባለበት ሀገር መታረስ የሚገባው 83 በመቶ መሬት ጦም ያድራል፡፡ አበው የወለፈንዲ ስልቻ ጤፍ ይቋጥራል፣ ባቄላ ያፈሳል እንዲሉ፡፡ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ሀገራችንን ጨምሮ በዓለማችን እያየናቸው ያሉ የደን ቃጠሎዎች፣ ድርቅ፣ ጎርፍ፣ ውሽንፍር፣ የበርሀ መስፋፋት፣ የወቅቶች መዛነፍ፣ ወዘተረፈ የዓለም ሙቀት መጨመር እነ ትራምፕ እንደ ሚሊቱ የደባ ኀልዮት ሳይሆን የእለት ተእለት የህይወት ገጠመኝ ከሆነ ውሎ አድሯል፡፡

የበለጸጉ ሀገራት ዛሬ ድሀ ሀገራትን ዋጋ እያስከፈለ ባለው የኢንዱስትሪ አብዮት ባካበቱት ሀብት እየተቋቋሙት ሲሆን እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ሀገራት ግን በዓለም ሙቀት መጨመር ያለእዳቸው ውድ ዋጋ እየከፈሉ ነው፡፡ በግብርናችን ያለ መዋቅራዊና ተቋማዊ ችግር የራሱ ድርሻ ቢኖረውም የዓለም ሙቀት መጨመር የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በሚደረገው እንቅስቃሴ ላይ ጋሬጣ እየሆነ ይገኛል፡፡ ግብርናችን ዛሬም ከበሬ ጫንቃ ያልወረደ፣ በተበጣጠሰ መሬት ላይ የተመሰረተ፣ የግብርና ቴክኖሎጂውም በተለይ የማዳበሪያና የምርጥ ዘሩ አቅርቦቱ የየአካባቢውን ስነ ምህዳርን ከግምት ያላስገባ ስለነበር ከሞላ ጎደል የገጠር ልማት ፖሊሲው የታለመለትን ያህል ውጤታማ ሊሆን ባለመቻሉ ዛሬም ከተመፅዋችነት ሊያወጣን አልቻለም፡፡

ዛሬም በቀን ሶስት ጊዜ መመገብ አልቻልንም፡፡ ይሁንና በተለይ ካለፉት ዓመታት ወዲህ የኩታ ገጠም ግብርናን፣ በተወሰነ ደረጃ ስነ ምህዳርን ታሳቢ ያደረገ የቴክኖሎጂ እገዛ፣ የከርሰና የገጸ ውሃን አሟጦ የመጠቀም፣ ፍራፍሬና አትክልት ላይ ለመስራት፣ በተለይ አምና የከተማ ግብርና ትኩረት ማግኘቱ፤ በአርብቶ አደሩ የሚገኙ ጦም ያደሩ ሰፋፊ መሬቶችን በመስኖ ለማልማት አበረታች ጥረትና ርብርብ መደረጉ እና ከውጭ የሚገባውን ስንዴ ከማስቀረት አልፈን ወደ ውጭ መላክ መጀመራችን ተስፋ ያስቆረጠን ግን ደግሞ ብቸኛ ሊባል በሚችለው ግብርና ከምግብ ዋስትና ባሻገር ተስፋችንን እንድናድስ አድርጎናል፡፡ ለዚህ ተስፋ ሰጭ ጅምር በልኩ እውቅና መስጠት ያሻል፡፡ ሆኖም ከዘመቻና ከንቅናቄ ባሻገር ባህላችን ልናደርገው ይገባል። ተቋማዊና መዋቅራዊ አድርገን ለትውልድ ልናስተላልፈው አደራ አለብን።

አረንጓዴ አሻራ ለትውልዶች የሚተላለፍ አረንጓዴ ችቦ ነው። ትውልዶች ተቀባብለው ካላስቀጠሉት ውጤታማ ሊሆን አይችልም። ትውልዶች አሻራውን እንዲያስቀጥሉ በስርዓተ ትምህርቱ የተካተተ ዕውቀትን እንዲገበዩ ሊመቻችላቸው ይገባል። ከ1ኛ ደረጃ እስከ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የአረንጓዴ አሻራ ክበባት ሊበረታቱና ሊቋቋሙ ግድ ይላል። ብዙኃን መገናኛዎችም ከአካባቢ ጥበቃና ከአረንጓዴ አሻራ ጋር ተያይዞ አርዓያነት ያላቸውን ግለሰቦችና ተቋማትም ማስተዋወቅ ይጠበቅባቸዋል።

ዓለማቀፉ የሰላም፣ የእርቅ፣ የሽምግልናና የግልግል ረቡኒ/ መምህር / ፕሮፌሰር ሕዝቅያስ አሰፋ ዘላቂ ሰላም እውን እንዲሆን ሰው በመጀመሪያ ከፈጣሪ ጋር ከዚያ ከራሱ ጋር በማስከተል ከተፈጥሮ ጋር ሰላም፣ እርቅ ማውረድ አለበት ይላሉ፡፡ ከተፈጥሮ ጋር ሰላም ለመፍጠር የሰው ልጅ ተፈጥሮን እንዳይኑ ብሌን መንከባከብ ይጠበቅበታል፡፡ ከዚህ ጎን ለጎን የሰውን ልጅ ከተፈጥሮ ጋር የሚያሸማግሉ፣ የሚያስታርቁ የኖቤል የሰላም ተሸላሚ የሆኑትን የአካባቢ ጥበቃ ተሟጋች ኬኒያዊቷን ዋንጋሪ ማታይ፣ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትርን ማንሳት ይቻላል፡፡

በሀገራችን ከረፈደ ቢሆንም እየተሰሩ ያሉ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሰራዎች ይበል የሚያሰኙ ናቸው፡፡ በሀገራችን የተፈጥሮ ጥበቃ ታሪክ የመጀመሪያ የሆነውና በክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ፊት አውራሪነት የተመራው የ” አረንጓዴ አሻራ “ ሀገራዊ ንቅናቄ ይሄን ዓመት ጨምሮ ወደ 32 ቢሊዮን የሚጠጉ ሀገር በቀል ችግኞችን ይተክላል፡፡ ይህ ለነገው ትውልድ ጭምር ለምለም፣ ነፋሻ፣ ምንጮች የሚንፎለፎሉባት፣ ወንዞች የሚገማሸሩባት፣ ወዘተ . ሀገር ለማቆየት ያስችላል፡፡ አይደለም የዛሬ ብላቴናዎችና ወጣቶች እኔ እንኳን ዝግባ፣ ቀረሮን፣ ኮሶን በቅጡ ለይቼ አላውቃቸውም፡፡ ደደብ ስለሆንሁ አይደለም፡፡ ያ የቀደመኝ ትውልድ ጠብቆና ተንከባክቦ ስላላቆየኝ እንጂ። ይሄ ትውልድ ግን ከመሰል ተወቃሽነትና ተከሳሽነት ለመዳን ኃላፊነቱን በመወጣት ላይ ይገኛል፡፡

ሀገራት የካርቦን ልቀትን ለመቀነስ ካልሰሩ ከኢንዱስትሪ አብዮት ወዲህ የከባቢ አየር ሙቀት በ1 ነጥብ 5 ዲግሪ ሴንትግሬድ ይጨምር ይሆናል ሲል ስጋቱን ያጋራው የTIME ዘገባ እስከ አውሮፓውያኑ 2030 ዓ.ም 350 ሚሊዮን ሕዝብ ለድርቅ፣ 120 ሚሊዮን ሕዝብ ለከፋ ድህነት ሊጋለጥ ይችላል ሲል አበክሮ ያስጠነቅቃል፡፡ የዓለም ሙቀት በሽርፍራፊ ሴንትግሬዶች በጨመረ ቁጥር የአየር ንብረት ለውጡ እየተባባሰ ይሄዳል፡፡ ይህ ፍርሀትን ለማንገስ ሳይሆን በሳይንቲስቶች የተረጋገጠ ጥሬ ሀቅ ነው፡፡ የአካባቢ ጥበቃ ተሟጋቾች፣ የዘርፉ ተመራማሪዎች ላለፉት አስርት ዓመታት ፖለቲከኞች ለአሳሳቢው የአየር ንብረት መዛባት ትኩረት እንዲሰጡት ነጋ ጠባ ቢወተውቱም ሰሚ ሳያገኙ ቆይተዋል፡፡

ሻሎም !

አሜን ።

 በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን)

አዲስ ዘመን   ሐምሌ 6/2015

Recommended For You

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *