ሐምሌ 10 ቀን 2015 ዓ.ም፦ አዲስ ታሪክና ገድል መጻፊያ ቀን!

የአካባቢ አየር መዛባት ባለፉት ስድስት አስርት ዓመታት እያስከፈለን ያለውን ከፍ ያለ ዋጋ ለመቀልበስ፤ የአረንጓዴ አሻራ /ሀገርን አረንጓዴ የማልበስ ዘመቻ/ በስኬት እንዲጠናቀቅ የእያንዳንዱ ዜጋ ንቁ ተሳትፎ ወሳኝ ነው። ችግሩ ዓለም አቀፋዊ ስጋት ከመሆኑ ጋር በተያያዘም የዓለም አቀፉን ማኅበረሰብ ጠንካራ ድጋፍ የሚሻ ነው።

በዓለም አቀፍ ደረጃ እየተስተዋለ ባለው አየር ንብረት ለውጥ እንደ ሀገር በተደጋጋሚ የድርቅ አደጋዎች ተጋላጭ ሆነናል። በየአስር ዓመቱ በሚከሰት ድርቅ ለረሀብ የሚጋለጡ፤ የሰው እጅ ለማየት ከዚያም ባለፈ አካባቢያቸውን ለቀው ለመሰደድ የሚገደዱ ዜጎች ቁጥር በየጊዜው እየጨመረ ነው። ይህ ተመጽዋችነትን በመፍጠር የብሔራዊ ክብራችን ተግዳሮት ከሆነ ዓመታት ተቆጥረዋል።

ቀደም ባሉት ዓመታት ለእርሻም ሆነ ለኑሮ የተሻሉ የሚባሉ የተፈጥሮ አካባቢዎች፤ አሁን አሁን ለእርሻም ሆነ ለኑሮ የማይመቹበት ሁኔታ እየተከሰተ ነው። ከዓመት ዓመት የሚፈሱ ወንዞችና ምንጮች እየደረቁ የየአካባቢውን ነዋሪ ሕይወት ሁለንተናዊ በሆነ መልኩ እየተፈታተኑት ነው። እንደ ሀገርም ነገዎቻችንን ብሩህ ለማድረግ ለምናደርገው እልህ አስጨራሽ ትግል ፈተናም ከሆኑ ውለው አድረዋል።

ለተፈጥሮና አካባቢያችንን ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ ባለመቻላችን/ባልተገባ መልኩ በደን ሀብታችን ላይ ባደረስነው ውድመት/የተከሰተው ይህ ሀገራዊ ችግር አሁን ላይ መፍትሄ ካላፈላለግንለት፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ካለው የአካባቢ አየር ብክለት ጋር ተዳምሮ እኛን ብቻ ሳይሆን መጪዎችን ትውልድ ብዙ ዋጋ ሊያስከፍል ይችላል።

ከሁሉም በላይ የተፈጥሮ አካባቢ መራቆትን ተከትሎ የሚፈጠረው የድርቅ አደጋ በምግብ እህል እራሳችን ለመቻል የምናደርገውን ጥረት ትርጉም አልባ ከማድረግ አልፎ፣ እንደሀገር ልንወጣው ወደማንችለው ሁለንተናዊ አዘቅት ውስጥ ሊጨምረን እንደሚችል ይታመናል። ዛሬ ላይ ብዙ ዋጋ እየከፈልን የምንገነባቸውን ሜጋ ፕሮጀክቶችንም ፋይዳ አልባ ሊያደርጋቸው ይችላል።

ይህንን ሀገራዊ ፈተና ለመሻገር ከሁሉም በላይ የዛሬ አራት ዓመት የጀመርነውንና፣ በብዙ ርብርብና ሀገራዊና ህዝባዊ ቁርጠኝነት ስኬታማ እየሆነ ያለውን የአረንጓዴ አሻራ በተጠናከረ መንገድ ከማስቀጠል ያለፈ አማራጭ የለንም። ይህ ፕሮግራም ዘመን ተሻግሮ የመጪዎቹን ትውልድ እጣ ፈንታ መወሰን የሚያስችል ትልቁ ሀገራዊ አቅማችን ነው።

ዛሬ ላይ እንደ ዜጋ እያንዳንዱ ሰው የሚተክለው ችግኝ ነገ ላይ ትውልዶችን ትናንት እንደ ሀገርና ህዝብ ብዙ ዋጋ ካስከፈለን ድርቅ መታደግ፣ የተሻለ የመኖሪያ አካባቢና የኢኮኖሚ አቅም በመፍጠር በሀገራቸው የተረጋጋ ሕይወት እንዲኖሩ የሚያስችል፣ ሀገራዊ መሰረት የመጣል ያህል ትልቅ ትርጉምና ፋይዳ ያለው ደማቅ ሀገራዊ ታሪክ የመጻፍ ልዩ ተልዕኮ አካል ነው።

ባለፉት አምስት ዓመታት 20 ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከል አቅደን 25 ቢሊዮን ተክለናል:: መትከል ብቻ ሳይሆን መንከባከብ በመቻላችን አካባቢያችን በሚታይ መልኩ እየተቀየረ ነው፤ የአፈር መሸርሸር እየቀነሰ ነው፤ አዕዋፍና አራዊት ወደተፈጥሮ አካባቢያቸው እየተመለሱ ነው፤ የዝናብ ሁኔታ እየተስተካከለ ነው፤ የወንዞቻችን እና የምንጮቻችን የውሀ መጠን እየጨመረ ነው፤ ከተሞች አረንጓዴ እየለበሱና እየተዋቡ ነው፤ የፍራፍሬ ዛፎችን ተክሎ የኢኮኖሚ አቅምን ማሳደግም እየተቻለ ነው::

ዘንድሮም 6.5 ቢሊዮን ችግኞችን በመትከል ለራሳችንም ሆነ ለመላው ዓለም ሀገራችንን አረንጓዴ ለማልበስ ያለንን ቁርጠኝነት ለማጽናት እየሰራን ነው:: ከዚህ በፊት ከ350 ሚሊዮን በላይ ዛፎች በአንድ ጀምበር ተክለን አስደናቂ ተግባር እንደፈጸምነው ሁሉ፤ ዘንድሮም 500 ሚሊዮን ችግኞችን በአንድ ጀምበር በመትከል የራሳችንን ሪከርድ ለማሻሻል መትጋት ይኖርብናል።

በዚህ ዕለት እንደሀገር ልንሰራ ያቀድነው ታሪክ አካል አለመሆን፤ ከአንድ ትልቅ እና ደማቅ ትውልድ ተሻጋሪ ታሪክ መጉደል ነው፤ የቀደሙት አባቶቻችን ለታሪክ ካላቸው ከፍ ያለ ከበሬታ አንፃርም፤ ያባቶቻችን ልጆች እንደመሆናችን መጠን ለዚህች ታሪካዊ ቀን /ለሀምሌ 10/2015 ዓ/ም/ ራሳችንን በሁለንተናዊ መንገድ ማዘጋጀት እና የታሪኩ አካል መሆን ይጠበቅብናል!

አዲስ ዘመን   ሐምሌ 6/2015

Recommended For You

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *