አፍሪካን በ2024ቱ የፓሪስ ኦሊምፒክ በሴቶች እግር ኳስ ከሚወክሉት ሁለት ሀገራት መካከል አንዱ ለመሆን እየተካሄደ በሚገኘው የማጣሪያ ውድድር፤ ወደ ሁለተኛ ዙር የሚያልፉ ቡድኖች እየተለዩ ይገኛሉ። ነገ በሚኖረው የጨዋታ መርሐ ግብርም ኢትዮጵያ እና ተጋጣሚዋ ቻድን ጨምሮ የተወሰኑ ሀገራት ቀጣይ የሚኖራቸውን ዕጣ ፋንታ የሚያውቁ ይሆናል። በመጀመሪያው ዙር የመጀመሪያ ጨዋታ ግማሽ ደርዘን ግብ ያስቆጠረው የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን (ሉሲዎቹ) ነገ ከቻድ ጋር የመልስ ጨዋታቸውን ያከናውናሉ።
ከትናንት በስቲያ በክረምቱ ከባድ ዝናብ ምክንያት ከተያዘው የጨዋታ ሰዓት ዘግይቶ የተጀመረው ጨዋታ በሉሲዎቹ የበላይነት መጠናቀቁ የሚታወስ ነው። በአሰልጣኝ ፍሬው ኃይለገብርኤል የሚመሩት ሉሲዎቹ በኦሊምፒኩ ለመሳተፍ አራት ዙሮችን ማለፍ በሚጠይቀው ማጣሪያ ለመሰለፍ ሳምንታትን ሲዘጋጁ ቆይተዋል። አበበ ቢቂላ ስታድየም ላይ በነበረው ጨዋታም ፍጹም የበላይነቱን በመውሰድ የቻድ አቻቸውን በግማሽ ደርዘን ግብ መርታት ችለዋል።
ሉሲዎቹ ሦስት የሚሆኑትን ግቦች ከእረፍት በፊት ያስቆጠሩ ሲሆን፤ መሳይ ተመስገን በ13ኛው ደቂቃ የቻድን የግብ መስመር በመድፈር ቀዳሚዋ ተጫዋች ሆናለች። አረጋሽ ካልሳ እና ናርዶስ ጌትነት በ24ኛው እና 26ኛ ደቂቃ ላይ በተከታታይ ግብ በማስቆጠር ሉሲዎቹ በበርካታ ግብ እንዲመሩ አስችለዋቸዋል። ከእረፍት መልስም አረጋሽ ካልሳ 63ኛው ደቂቃ ላይ ለቡድኑ አራተኛውን፤ በስሟ ደግሞ ሁለተኛውን ግብ በማስቆጠር በከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነት ልትመራ ችላለች። ረድኤት አስረሳኸኝ እና ንቦኝ የን በበኩላቸው 78ኛው እና 82ኛው ደቂቃ ላይ ተጨማሪዎቹን ግቦች በማስቆጠር ቡድኑ 6ለ ምንም እንዲያሸንፍ ምክንያት ሆነዋል።
በሴቶች እግር ኳስ እምብዛም የማይታወቀው የቻድ ብሔራዊ ቡድን ካለው እጅግ ውስን የውድድር ተሳትፎ አንጻር የዓለምን እግር ኳስ በሚመራው ፊፋ በሚሰጠው ወርሐዊ ደረጃ መካተት አልቻለም። በአንጻሩ በሰፊ የግብ ልዩነት የመጀመሪያው ጨዋታ ያጠናቀቁት ሉሲዎቹ ከዓለም የሴት ቡድኖች 125ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል። ነገ በሚኖረው የመልስ ጨዋታ ላይም ወደ ሁለተኛው ዙር የሚያልፈው ቡድን የሚለይ ይሆናል።
ከሁለቱ ቡድኖች አላፊ የሚሆነው ደግሞ ከጠንካራው የናይጄሪያ ብሔራዊ ቡድን ጋር የሚጋጠም መሆኑን የተያዘው መርሐ ግብር ያመላክታል። በዓለም የሴቶች እግር ኳስ ደረጃ 42ኛ ላይ የተቀመጠው ቡድኑ በአፍሪካ ቀዳሚ ከሆኑ ቡድኖች መካከል አንዱ ሲሆን፤ ዓለም ዋንጫን ጨምሮ በበርካታ ዓለም አቀፍ ውድድሮች ላይ ተሳታፊ ነው። በኦሊምፒክ መድረክም አህጉሪቱን በመወከል በተከታታይ ለሦስት ጊዜያት ተሳታፊ ሊሆን ችሏል። የመጀመሪያ ተሳትፎው እአአ በ2000 የሲድኒ ኦሊምፒክ ሲሆን፤ እአአ በ2004 የአቴንስ እንዲሁም 2008 የቤጂንግ ኦሊምፒኮች ናቸው።
የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን(ካፍ) እያካሄደ ከሚገኘው የሴቶች ኦሊምፒክ ማጣሪያ ውድድር ጎን ለጎን የወንዶች ዓለም ዋንጫ ማጣሪያ የዕጣ ማውጣት ሥነሥርዓትም አካሂዷል። በኮትዲቯሯ አቢጃን በተካሄደው ሥነሥርዓት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በመጀመሪያው ምድብ ከተካተቱ 6 ሀገራት ጋር ተደልድሏል። በምድቡም ዋሊያዎቹን ጨምሮ ግብፅ፣ ቡርኪና ፋሶ፣ ጊኒ ቢሳው፣ ሴራሊዮን እና ጅቡቲ ይገኛሉ።
ካፍ 45ኛ ጠቅላላ ጉባኤውን ባደረገበት መድረክ የፊፋው ፕሬዚዳንት ጂያኒ ኢንፋንቲኖ፣ የካፍ ፕሬዚዳንት ዶክተር ባትሪስ ሞሴፔን ጨምሮ አህጉሪቷ ያፈራቻቸው የቀድሞ የእግር ኳስ ከዋክብትም ተገኝተዋል። በዕጣ ማውጣት ሥነሥርዓቱም የኮንፌዴሬሽኑ አባል ሀገራት በ9 ምድብ ሊደለደሉ ችለዋል። በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ 48 ሀገራት በሚሳተፉበት በዚህ የዓለም ዋንጫ አፍሪካ በ10 ሀገራት የምትወክል ሲሆን፤ የማጣሪያ ጨዋታውም በመጪው ዓመት ኅዳር ወር/2016 ዓ.ም ይጀመራል።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 8/2015