
በሰዎች የእለት ተእለት ሕይወት መውድቅና መነሳት የተለመደ ነው። አንዱ ሲወድቅ ሌላው ይነሳል። ይህኛው ሲነሳ ያኛው ይወድቃል። ብዙዎች ግን አንዴ ከወደቁ ቅስማቸው ተሰብሮ ዳግም ለመነሳት ይቸገራሉ። ጥቂቶች ደግሞ ተስፋ ሳይቆርጡ ከውድቀታቸው ተምረው እንደገና ያንሰራራሉ። ሌሎችም አርዓያ ይሆናሉ።
ለብዙዎች መውደቅ የመጨረሻ እጣ ፈንታ ሆኖ ነው የሚታየው። መውደቅ የመጨረሻ የሕይወት ፍፃሜ ይመስል አንዳንዶች በውድቀታቸው ምክንያት በብርቱ ራሳቸውን ሲጎዱ ይታያል። መውደቅን እንደመሸነፍ የሚቆጥሩም ጥቂት አይደሉም። ከውድቀታቸው የሚማሩ ግን ውድቀታቸውን እንደመልካም አጋጣሚ ቆጥረው እንደ አዲስ ሕይወትን ሲያሳኩ ይስተዋላል።
በዓለም ላይ ተፅእኖ ፈጣሪ የሚባሉ ሰዎች የዛሬ ስኬት ላይ ሊደርሱ የቻሉት እየወደቁና እየተነሱ ነው። የዓለማችን ዝነኛ ቱጃሮች በርካታ ሀብትና ገንዘብ ማትረፍ የቻሉት እንዲሁ ሳይሆን ወድቀው በመነሳት ነው። ሌሎችም በዓለም ላይ ያሉ በልዩ ልዩ ዘርፎች ስኬታማ የሆኑ ሰዎች አንዴ ወድቀው ሌላ ጊዜ ደግሞ ተነስተው ነው ዛሬ ያሉበት ደረጃ ላይ የደረሱት።
ስለዚህ ብዙ ሰዎች ወድቀው ሳይነሱ የሚቀሩት ውድቀት ካለ መነሳትም እንዳለ ሳይረዱ በመቅረታቸው ነው። ከወደቁ መውደቅ እንጂ ዳግም መነሳት እንደሌለ አይምሯቸው ስላመነ ነው። የወደቁትን ያህል ዳግም ለመነሳት የሚያደርጉት ትግል ብርቱ መሆኑን በመፍራትም ጭምር ነው እንደወደቁ እዛው የሚቀሩት። ለውድቀት እጅ በመስጠታቸው ነው የሚወድቁትና መነሳትን የማያዩት።
ሰዎች በባህሪያቸው ከፍ ከፍ ማለትን እንጂ ውድቀትን አይፈልጉም። ይህም የሁሉም ሰው ተፈጥሯ ባህሪ ነው። እንዲህ ሲባል ግን ውድቀት ጥሩ ነገር ነው ለማለት አይደለም። ብዙዎች ግን ውድቀትን እንደ ኪሳራና የመጨረሻ እጣ ፈንታ ነው የሚቆጥሩት። ከውድቀታቸው አይማሩም። ውድቀትን እንደ መልካም የሕይወት መሸጋገሪያ አጋጣሚ አይቆጥሩም። በጣት የሚቆጠሩት ብቻ ናቸው ውድቀትን እንደመማሪያ የሚቆጥሩት።
እኛ ሰዎች ባንፈራ፣ ባንጨነቅ፣ ባንሳሳት፣ ባንወድቅና ባንጎዳ ደስ ይለናል። ሆኖም ሕይወት ለጥ ያለ ሜዳ አይደለችም። ዳገት አላት። ፍርሃት ለከበበን፣ ጭንቀት ለያዘን፣ የጠበቅናቸው ነገሮች በምንፈልገው ልክ አልሄድ ላለን ምንድን ነው ማድረግ ያለብን? መጪውን ጊዜስ ለሥራችን፣ ለትምህርታችን፣ ለፍቅር ግንኙነታችንና ለትዳራችን እንዴት ነው የተሻለ የምናደርገው? ብንወድቅ እንኳን መልሰን የምንነሳው እንዴት ነው? ይህ በጣም ከባድ ጥያቄ ነው። ነገር ግን ሕይወታችን ላይ ለውጥ የሚፈጥሩና ነብስ የሚዘሩ የሚገርሙ ሃሳቦች አሉ።
ከነዚህ ሃሳቦች ውስጥ የመጀመሪያው ወይ ትምህርት ነው ወይ በረከት ነው። አንድ በጣም የምትፈልጉት ነገር ከተሳካ በረከት ነው፤ በጣም ደስ ይላል። ካልተሳካ ደግሞ ትምህርት ነው። ይህ የሰውን ሕይወት ከፍም ዝቅም የሚያደርግ አመለካከት ነው። አሁን መራመድ የቻላችሁት እኮ ያኔ ልጅ እያላችሁ ብዙ ጊዜ ስትወድቁ መልሳችሁ ስለተነሳችሁ ነው። የትኛው ልጅ ነው እስቲ አሁን ‹‹እኔ አሁንስ መረረኝ፣ መውደቅ ሰለቸኝ፣ ባልራመድስ፣ ቢቀርስ ብሎ መራመዱን ያቆመው?
አያችሁ! መውደቅና መነሳት ተፈጥሯዊ ነው። ይህን ደግሞ ማመን አለባችሁ። እንደውም ከትልቁ ስተታችሁ ነው ትልቁን ትምህርት የምትማሩት። ስህተቶቻችሁን ወይም ውድቀቶቻችሁን አትርሷቸው። ግን ወደኋላ እንዲጎትቷችሁ አትፍቀዱላቸው። ከሁሉ በላይ ግን አንድ ነገር አትርሱ። በሕይወታችሁ ምንም ነገር ከገጠማችሁ ወይ ለበረከት ነው ወይ ለትምህርት ነውና ስህተትን አትፍሩ።
ሁለተኛው ሃሳብ ካልጠነከራችሁ ማንም አይፈልጋችሁም። የሆነ ነገር እየሞከራችሁ ሰዎች ከሳቁባችሁ፣ ከተቿችሁ፣ ከሰደቧችሁ፣ ዝቅ አድርገው ካዯችሁ የእነርሱን ትኩረት መሳብ የሚችል ለውጥ ውስጥ ናችሁ ማለት ነው። አያችሁ! ስትሞክሩ ዓይን ውስጥ ትገባላችሁ። ሰዎች አርፎ የተቀመጠን፣ ምንም የማያደርግን ሰው ዞር ብለው አያዩም። ስለዚህ እናንተም እየሞከራችሁ ስለሆነ ነው የተሳሳታችሁት። የተተቻችሁት የሆነ ነገር ለማሳካት እየጣራችሁ ስለሆነ ነው።
ታዋቂው የስነ ልቦና ባለሞያ ዴል ካርኒጌ የሞተን ውሻ ምንም እንደማይደበድብ እወቅ ይላል። ፍቅረኛህ ትልቅ ቦታ የምትሰጥህ እርሷ ብትኖርም ባትኖርም በራስህ መቆም እንደምትችል ካሳየሃት ነው። አየሽ! በዙሪያሽ ያሉ ሰዎች የእነርሱ ጥገኛ ከሆንሽ አያከብሩሽም። ቦታ አይሰጡሽም። ያለእነርሱ መቆም እንደምትችይ፣ በራስ መተማመን እንዳለሽ ካሳየሻቸው ግን ያከብሩሻል።
አንተም ቢሆን ሥራ ቦታ ላይ የትም ብትቀጠር መሥራት እንደምትችል ካሳየሃቸው ሰዎች ትልቅ ቦታ ይሰጡሃል። በዚህ ሂደት ውስጥ ግን ትሳሳት ይሆናል። ትወድቅ ይሆናል። ነገሮች ባልጠበካቸው መንገድ ሊበላሹ ይችሉ ይሆናል። እንደዛም ቢሆን ግን ብቻህን መቆም አትፍራ። መታገል አትፍራ። እንደዛ ከሆነ ሺ ጊዜ ብትወድቅ እንኳን መልሰህ ትነሳለህ። አትርሳ ወዳጄ! ካልጠነከርክ ማንም አይፈልግህም።
ሶስተኛው ሃሳብ ራስ ላይ ማተኮር ነው። ወድቃችሁ መነሳት የምትችሉት ራሳችሁ ላይ ካተኮራችሁ ነው። ብዙ ሰዎች ደስተኛ መሆን ያቃታቸው ትኩረታቸው ሌላ ሰው ላይ ወይም ሌላ ነገር ላይ ስለሆነ ነው። ሰውዬው ቁልፍ ጠፍቶበት ቦግ ያለ የመንገድ መብራት ስር አጎምብሶ ይፈልጋል። ከዛ አንድ መንገደኛ መጥቶ አብሮት ያፋልገው ጀመር። ትንሽ ቆይቶ መንገደኛው ‹‹እኔ የምልህ ቁልፉን ግን እዚህ አካባቢ ነው የጣልከው?›› ሲለው ሰውዬው ‹‹አይ አይደለም፤ ቁልፉ የጠፋብኝ እዛ ጨለማ ውስጥ ነው። ግን ለመፈለግ የሚመቸው እዚህ ብርሃን ጋር ስለሆነ ነው›› አለው። ምስኪን! ቁልፉን መቼም አያገኘውም።
አንተም በሕይወትህ ውስጥ ያልጠበከው ነገር ሲፈጠር መፍትሄውን ከሌሎች ሰዎች አገኛለሁ ብለህ እየጣርክ ከሆነ ከዚህ ቁልፍ ፈላጊ ሰውዬ በምንም አትለይም። መፍትሄው ያለው አንተ ጋር ነው። የትም አትሂድ። የገጠመህን ነገር ለመርሳት ከውጫዊ ነገሮች ጋር መባከኑን አቁም። ቁጭ በልና ከራስህ ጋር ተነጋገር። እንዲህ ተፈጥሯል፤ እንዲህ ሆኗል፤ እንዲህ ማድረግ አለብኝ በል። ሰዎችን፣ ሁኔታዎችን መቀየር አልችልም በልና ተቀበል። መቀየር የምችለው ራሴን ነው በልና ራስህ ላይ አተኩር።
ይህን ጥፋት እንዳልደግመው ምንድን ነው ማድረግ ያለብኝ በልና ቁጭ ብለህ ራስህን ገምግም። ለምሳሌ ቢዝነስ ከሆነ የተበላሸብህ በስሜት ገብቼ፣ በትንሽ መረጃ ተነሳስቼ ይሆናል ቢዝነሴን የጀመርኩት በልና ራስህን ፈትሽ። ትምህርትም ከሆነ ያጠናን ስልትህ ይሆናል። የፍቅር ግንኙነት፣ ከሰዎች ጋር ተጋጭተህ ከሆነ ያንተ የመግባባት ክፍተት፣ አቀራረብህም ሊሆን ይችላል። አየህ! ራስህ ላይ የምታተኩረው አብዛኛው ችግር የሚፈጠረው በአንተ ምክንያት ስለሆነ አይደለም። ግን መቀየር የምትችለው ራስህን ብቻ ስለሆነ ነው። ያለህ አማራጭ እሱ ነው። ስለዚህ ራስህ ላይ አተኩር።
አራተኛው ሃሳብ ደግሞ በከንቱ አትጨነቁ ይላል። ከምናስባቸው ብዙ ክፉና መጥፎ ሃሳቦች መካከል አብዛኛዎቹ እውነት አይሆኑም። እውነት ቢሆኑማ እንዲህ ቁጭ ብለን እንኳን አናወራም ነበር። በከንቱ ነው የምንጨነቀው። እንደውም አንድ ፈላስፋ እንዲህ ብሎ ይጠይቃል፡-
‹‹ችግር አለብህ›› ይልሃል
‹‹አይ የለብኝም›› ካልከው
‹‹አትጨነቃ!›› ይልሃል
‹‹አዎ! ችግር አለብኝ›› ካልከው ደግሞ
‹‹ያንን ችግር ማስተካከል ትችላለህ?›› ይልሃል
‹‹አዎ! ማስተካከል እችላለሁ›› ካልከው
‹‹አትጨነቃ! ማስተካከል ከቻልክ›› ይልሃል
‹‹አይ ማስተካከል አልችልም›› ካልከው
‹‹አሁንም አትጨነቅ ማስተካከል የማትችለውን ነገር አምነህ ተቀበል›› ይለናል ፈላስፋው። ስለዚህ የምትቀይረውን ሳትጨነቅ ቀይር። የማትቀይረውን ደግሞ ሳትጨነቅ ተቀበል። በከንቱ መጨነቅና መብሰልሰል አቁም ወዳጄ!
አምስተኛውና የመጨረሻው ሃሳብ በእምነታችሁ ጠንክሩ የሚል ነው። እምነቱ ላይ ጠንካራ የሆነ ሰው አይፈተንም፣ አይወድቅም አይሳሳትም ማለት አይደለም። ግን ቢወድቅ እንኳን እንደ አዲስ መልሶ መነሳት ይችላል። ጫናዎችን መቋቋም ይችላል። አንዳንዴ ከራስህ አሳልፈህ የምትሰጣቸው ጉዳዮች መኖር አለባቸው።
ለምሳሌ የጓደኛህ ቤት ሄደህ ልትገባ ስትል ሃይለኛ ውሻ እየጮኸ ቢያጨንቅህ፤ አለስገባም ቢልህ ምንድን ነው የምታደርገው? ስልክህን አውጥተህ ትደውልለትና ለጓደኛህ በርህ ላይ ቆሚያለሁ ውሻህ እያስቸገረኝ ነው ውጣና አስገባኝ ትለዋለህ። ጓደኛህም መጥቶ ሽፋን ሰጥቶህ ውሻውን ዝም አሰኝቶ ወደ ቤቱ ያስገባሃል። የውሻው ጩኽት የዚህ ዓለም ችግር፣ የዚህ ዓለም ሃሳብ፣ የዚህ ዓለም ፈተና ነው። ፀጥ የሚያደርግልህ ደግሞ ፈጣሪህ ነው። ለጓደኛህ ደውለህ እንደነገርከው ለፈጣሪህ ንገረው። ለፈጣሪህ አሳልፈህ ስጠው። እሱ ዝም የማያሰኛቸው ችግሮች የሉም።
አንዳንዴ አንተ መቀየር የማትችለው፣ ልትሸከመውና ልትቋቋመው የማትችለውን ነገር ለፈጣሪህ ማስረከብ መቻል አለብህ። ብዙ ሰው ሃይማኖት አለው። እምነት ግን የለውም። ስለዚህ በማይቀይረው ነገር አብዝቶ ይጨነቃል። ሰዎች ሲጨነቁ ደግሞ መሥራት የሚችሉትን ነገር እንኳን አይሰሩም። ይጋረድባቸዋል። የሆነ ነገር መጥቶ አስርስር ያደርጋቸዋል።
ማመን ማለት እኮ በቃ! አሳልፈህ መስጠት፤ መልቀቅ፣ ዝም በልህ መተው ማለት ነው። ለምሳሌ መሬትን ስትረግጣት ‹‹እንደው ታሰምጠኝ ይሆን? ትውጠኝ ይሆን?›› ብለህ እየተጠራጠርክ አትረግጣትም። መሬትን አምነሃት በሙሉ ልብህ ነው የምትረግጣት። አንዳንድ ችግሮችህን ከራስህ አሳልፈህ ለፈጣሪህ መስጠት መለማመድ አለብህ። በቃ! እርሱ ፀፅ ያደርጋቸዋል። እርሱ ያስተነፍሳቸዋል። ከራስህ አሳልፈህ ስጥ። እምነትህ ላይ ጠንክር ወዳጄ! ወድቆ የሚነሳ ሰው እምነቱ መጠንከር አለበት።
ከላይ የተነሱት አምስቱ ሀሳቦች በሕይወታችን ትርጉም ያለው ለውጥ ለማምጣት የሚያስችሉና በተለይ በተለያዩ የሕይወት እንቅስቃሴዎች ውስጥ ለሚያጋጥሙን ውድቀቶች ዳግም መነሻ መድኃኒት ናቸው። እነዚህን የሃሳብ መድኃኒቶች ብንውጣቸው ተፈውሰን ከውድቀት ወደ መነሳት እንሸጋገራለን። ስለዚህ በዚህ ወድቆ መነሳት በበዛበት ዓለም ውስጥ እንደዚህ አይነት ነቃ የሚያደርጉ ሃሳቦች መልካም ናቸውና ሃሳቦቹን ወደ ተግባር መቀየሩ አይከፋም።
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 8/2015