ግብርናው እንዲሰጥ የሚጠይቀው ሁሉ ይሰጠው!

ኢትዮጵያ ምጣኔ ሀብቷ በግብርና ላይ የተመሰረተ ሆኖ ቆይቷል።ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የአገልግሎትና የኢንዱስትሪ ዘርፎች የግብርናውን ሸክም መቀነስ ጀምረው እንጂ ላለፉት ዘመናት ግብርና የሀገሪቱ ኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት ሆኖ ነው የኖረው።ባለፈው አንድ አስርት አመት ግብርናውን ትራንስፎርም ለማድረግና በምጣኔ ሀብቱ ውስጥ ያለውን የአንበሳ ድርሻ በኢንዱስትሪው ለመተካት ታቅዶ ቢሰራም፣ እንደታሰበውም እንደታቀደውም አልሆነም፤ ግብ ርናው አሁንም የሀገሪቱ የምጣኔ ሀብት የደም ስር ሆኖ ቀጥሏል።

እንደተጠቀሰው ባለፉት አመታት የግብርናውን ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ ብዙ ጥረቶች ተደርገዋል። በቴክኖሎጂና በምርምር ለመደገፍ ብዙ ጥረት ተደርጓል። በማዳበሪያና በምርጥ ዘር አቅርቦት ላይ በስፋት የተከናወነውን ተግባር ለእዚህ በአብነት መጥቀስ ይቻላል።

ከቅርብ አመታት ወዲህ ደግሞ ሀገሪቱ በመስኖ ስንዴ ልማት በሰፊው በመሥራት ተጠቃሽ ስንዴ አምራች ለመሆን በቅታለች። ከሶስት አመት በፊት በቆላማው የሀገሪቱ ክፍል በተጀመረ የስንዴ መስኖ ልማት ሶስት ነጥብ ስድስት ሚሊየን ኩንታል ስንዴ ማግኘት ተችሏል። ይህ አሀዝ የስንዴ ልማቱን በወይና ደጋ እና በደጋ አካባቢ ጭምር በማስፋፋት በቀጣዩ አመት 24 ነጥብ አምስት፣ ባለፈው የምርት ዘመን ደግሞ 53 ሚሊየን ኩንታል ለማድረስ ተሰርቷል።

የእርሻ ሥራውን ከበሬ ጫንቃ ለማውረድና ግብርናውን ከእጅ ወደ ግብርና ለማላቀቅ በሜካና ይዜሽን ለመደገፍም ብዙ ተሰርቷል፤ ብዙ ርቀትም መጓዝ እየተቻለ ነው። አርሶ አደሩ የሜካናይዜሽን ማሽነሪዎችን እንዲያገኝ የተለያዩ አማራጮች ቀርበዋል።

የአርሶ አደሩ የቅርብ አጋር የሆኑት የአርሶ አደሮች የህብረት ሥራ ማህበራትና ዩኒየኖቻቸው አስቀድሞም በሜካናይዜሽን ላይ በትኩረት ሲሰሩ መቆየታቸው ይታወቃል። እነዚህ ማህበራት ዛሬ በገጠር እየተስፋፋ ለመጣው ሜካናይዜሽን እርሾ በመሆን አገልግለዋል ማለትም ይቻላል። ሀገሪቱ አሁን በእጅጉ እየሰራችባቸው በምትገኘው አግሮ ኢንዱስትሪዎች ላይ ማህበራትና ዮኒየኖቻቸው አስቀድመው ገብተውበታል። አግሮ ኢንዱስትሪዎችን ጭምር በማቋቋም አሁን በተፈጠረው ምቹ ሁኔታ ይህን ሥራ አጠናክረው ቀጥለዋል።

አርሶ አደሮች የማሸነሪዎች ባለቤት እንዲሆኑ መንግስት የተለያዩ መንገዶችን አመቻችቷል፤ አርሶ አደሮች ማሽነሪዎችን በብድር ማግኘት የሚችሉበት የማሸነሪ ሊዝ አገልግሎት ተፈጥሯል።በዚህም አርሶ አደሮቹ ማሽነሪዎቹን በእጃቸው እያስገቡ ይገኛሉ። በዚህ ላይ ማሸነሪዎችን መግዛት ለማይችሉት አርሶ አደሮች አገልግሎቱን በኪራይ ማግኘት የሚችሉባቸው የሜካናይዜሽን አገልግሎት የሚሰጡ ማህበራት ተፈጥረዋል።

ሀገሪቱ ግብርናዋን የማዘመን ሥራዋን አሁንም አጠናክራ ቀጥላለች። ለእዚህም በቅድሚያ ለሜካናይዜሽን ግብርና መስፋፋት አንድ አስተዋጽኦ በሚያደርገው ኩታ ገጠም እርሻ ማስፋፋት ላይ በትኩረት እየተሰራ ነው።በእዚህም የኩታ ገጠም እርሻን ባለፉት አምስት አመታት ከስድስት ሚሊየን ሄክታር በላይ ማድረስ ተችሏል፤ ይህን ሥራ እንዲሰራ የተቋቋመው የቀድሞው የግብርና ትራንስፎርሜሽን ኤጀንሲ የአሁኑ የግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ከለውጡ በፊት ከአንድ ሚሊየን ሄክታር በላይ ያላደረሰውን የኩታ ገጠም እርሻ ማስፋፋት ሥራ ባለፉት አምስት አመታት ነው ከስድስት ሚሊየን ሄክታር በላይ ማድረስ የተቻለው።ይህን አሃዝ በዚህ የምርት ዘመን ወደ ስምንት ነጥብ አምስት ሄክታር ለማሳደግ ታቅዶ እየተሰራ ነው።

መንግስት በተለያየ መልኩ ለግብርናው ዘርፍ ከሚያደርገው የፋይናንስ ድጋፍ በተጨማሪ ለአርሶ አደሩ የአፈር ማዳበሪያ አቅርቦት የሚያደርገውን ድጎማ ቀጥሎበታል።ለአፈር ማዳበሪያ ባለፈው የምርት ዘመን 15 ቢሊየን ብር ድጎማ የሰጠው መንግስት፣ ይህን ድጎማውን በ2015/16 የምርት ዘመን ደግሞ 21 ቢሊየን ብር አድርሶታል። ይህ ደግሞ ለዘርፉ በተለያዩ መልኮች ከሚመድበው በጀት በተጨማሪ የተደረገ ነው።

በዚህ ብቻ ሳያበቃ የሀገሪቱ የፋይናንስ ተቋማት ለግብርናው ዘርፍ ብድር እንዲያቀርቡ ሲያሳስብ ቆይቷል፤ ይህን ተከትሎም በተወሰኑ መልኩም ቢሆን የፋይናንስ ተቋማት ለግብርናው ዘርፍ የብድር አቅርቦት ማደረግ ጀምረዋል።

እነዚህ ሁሉ ርብርቦች የግብርናው ዘርፍ ምርትና ምርታማነት እንዲጨምር አስተዋጽኦ እያበረከቱ ይገኛሉ። በ2014/15 የምርት ዘመን በመኸር እርሻ በሰብል ልማት በአነስተኛ ማሳ ያላቸው አርሶ አደሮች 480 ሚሊዮን ኩንታል (100+%) ምርት ተገኝቷል። ይህ ምርታማነት የታየው 13ነጥብ ስምንት ሚሊየን ሄክታር መሬት በማልማት 472 ሚሊየን ኩንታል ለማምረት ታቅዶ በተከናወነው ተግባር ነው።ይህ የምርታማነት መጠንን የሚያመለክት አሀዝ ከእቅድ በላይ የተገኘ መሆኑንም መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

በ2015/ 16 የምርት ዘመን ከመኸር ወቅት ብቻ ከ508 ሚሊየን ኩንታል በላይ ለማምረት መታቀዱን የግብርና ሚኒስቴር መረጃዎች ያመለክታሉ።ምርቱ የሚገኘው በክላስተርና በመደበኛ ግብርና ከሚሸፈነው 16 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ይሆናል።

ስንዴን ብቻ ብንመለከት ደግሞ ባለፈው የምርት ዘመን በመኽር ወቅት ብቻ 110 ሚሊየን ኩንታል ስንዴ ማግኘት ተችሏል።ይህን አሀዝ 400 ሚሊየን ኩንታል ለማድረስ እየሰራ መሆኑን ነው የግብርና ሚኒስቴር መረጃ የሚጠቁመው።በዚህ ላይ በበልግ ወቅትና በመስኖ ከሚለማው ስንዴ ሊገኝ የሚችለው ምርት ሲታከል የሀገሪቱ የስንዴ ምርት መጠን ምን ያህል ከፍ ሊል እንደሚችል መገመት አይከብድም፡፡

ሀገሪቱ በስንዴ ልማት ላይ ያደረገችው መጠነ ሰፊ ጥረት የስንዴ ፍላጎቷን በራሷ መሸፈን ከማስቻሉም በላይ ለጎረቤት ሀገሮች መሸጥ የምትችልበትን ሁኔታ ፈጥሮላታል።ይህ ሁኔታ ከውጭ ስንዴ ለማስገባት የምታወጣውን የውጭ ምንዛሬ ከማስቀረት በተጨማሪ የተወሰነም ቢሆን የውጭ ምንዛሬ እንድታገኝ የሚያስችልም ነው።

የሀገሪቱ የስንዴ ምርት በመስኖ በመኸር ወቅት መጨመር ሀገሪቱ ከፍተኛ መጠን ባለው የውጭ ምንዛሬ ከውጭ የምታስመጣውን ስንዴ ብቻ አይደለም ያስቀረው።ስንዴ በማስመጣት ሂደት ሊፈጠር ይችል የነበረውን ቀውስም ነው ያስቀረው።ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በቅርቡ ህዝብ ተዋካዮች ምክር ቤት አባላት ለቀረቡ ጥያቄዎች ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት በሩሲያና ዩክሬን መካከል በተቀሰቀሰው ጦርነት ሳቢያ ማዳበሪያና ስንዴ ከዩክሬን የሚገዙ ሀገሮች ለችግር ታደርገው እንደነበር ጠቁመዋል፤ ኢትዮጵም ማዳበሪያ ለመግዛት ይህ ፈተና ገጥሟታል፤ ኢትዮጵያም ስንዴ ከውጭ የምታስገባ ቢሆን ሊደርስባት ይችል የነበረው ፈተና ሲታሰብ የስንዴ ልማቱ ፋይዳ በእጅጉ ከፍተኛ እንደሆነ መረዳት ይቻላል።

በሄክታር የሚገኘው የምርት መጠን እንዲጨምር እየተሰራ ሲሆን፣ በዚህም ለውጦች እየተመዘገቡ ናቸው፤፡ ይሁንና ግን በተለያዩ ምክንያቶች የሚጠበቀውን ያህል ምርታማነቱ አላደገም።ለእዚህ ምክንያት ከሆኑት መካከል የአፈር አሲዳማነት መስፋፋት ይጠቀሳል።ሀገሪቱ ለእርሻ ስራ ካዋለችው መሬት ወደ ሰባት ሚሊየን ከሚጠጋው /ወደ 43 በመቶው/ በአሲዳማነት ክፉኛ እንደተጠቃ የግብርና ሚኒስቴር መረጃዎች ያመለክታሉ።ይህ አሲዳማነት በሄክታር የሚገኘውን የምርት መጠን ከመቀነስ በተጨማሪ ሀገራዊ አማካይ ምርታማነት ላይም አሉታዊ ተጽእኖ እያሳደረ እንደሚገኝ እየተገለጸ ነው።

ሚኒስቴሩ ይህን ችግር ለመፍታት ሰሞኑን በተጀመረው የ2016 በጀት አመት የአፈር ለምነት ንቅናቄ እንደሚያደርግ አስታውቋል።በዚህም ምርትና ምርታማነቱን ማሳደግ እንደሚቻል ታምኖበታል።በአሲዳማነት በተጠቃ በሰባት ሚሊየን ሄክታር መሬት ላይ ይህን ማድረግ ቢቻል ምርትና ምርታማነትን በሃምሳ በመቶ መጨመር እንደሚቻል ተጠቁሟል።ምርትና ምርታማነትን ከ10 ኩንታል በሄክታር ወደ 40 እና 50 ኩንታል ማሳደግ እንደሚቻልም ተመልክቷል። ይህን በማድረግ እንደ ሀገር ያለውን አማካይ ምርታማነት ማሳደግ ይቻላል ተብሏል። ይህ ህክምና ኖራን ብቻ በመጠቀም የሚካሄድ ነው፡፡

በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን ምርታማነት ለማሳደግ መሬት የማስፋፋት አስፈላጊነትን ጠቁመዋል።አሁን ያለው 15 ሚሊየን ሄክታር የሚታረስ መሬት በቂ እንዳልሆነም ጠቅሰው፣ በአሲድ የተጠቃውን መሬት በኖራ በማከም የእርሻ መሬቱን 20 ሚሊየን ሄክታር ማስጠጋት እንደሚቻልም ነው ያመለከቱት።

ለእዚህም የግብርና ሚኒስቴር በአፈር ለምነት ላይ ሊያካሂድ ያቀደውን የአፈር ለምነት ንቃናቄ በተጠናከረ መልኩ ማካሄድ ይኖርበታል።ይህን የምርታማነት ጸር ለማስወገድ የሚያስችለው ግብዓት በሀገር ውስጥ በስፋት የሚገኝ ኖራ ነው።ለእዚህ የሚያስፈልጉት ለኖራ ምርት የሚያስፈልገውን ግብዓት የሚፈጩ ፋብሪካዎች ብቻ ናቸው።ቅርብ ጊዜ የወጡ መረጃዎች እንዳመለከቱት ደግሞ ወደ አምስት የሚጠጉ ዝቅተኛ አቅም ያላቸው ኖራ የሚፈጩ ፋብሪካዎች ተተክለዋል፤ ይህ ሊበረታታ የሚገባው ቢሆንም፣ ከችግሩ ስፋት አኳያ በዚህ ላይ በስፋት መስራት ያስፈልጋል።ይህን ለማድረግ የሚሰሰት ምንም አይነት ሀብት ሊኖር አይገባም።ሙሉ አቅምን አስተባብሮ በዚህ የምርታማነት ጸር ላይ መዝመት የግድ ነው።

ሀገሪቱ በእርሻ መሬት መስፋፋት ላይም መስራት ይኖርበታል።እንደሚታወቀው ሀገሪቱ ለእርሻ ሊውል የሚችል ሰፊ፣ ለምና ድንግል መሬት ባለጸጋ ናት። በተለይ በቆላማዎቹ የሀገሪቱ አካባቢዎች ለእርሻ ከእርሻም ለመስኖና ለሰፋፊ እርሻ ሊውል የሚችል መሬት በስፋት ይገኛል።በጋምቤላ፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ በአፋርና በሶማሌ ክልል በመስኖም ሆነ ከመስኖ ውጭ በሆነ መንገድ ለእርሻ ሊውል የሚችል ሰፊ ለም መሬት መኖሩ ይታወቃል።

ከዚህ መሬት የተወሰነውን ወደ እርሻ ሥራው ማስገባት ቢቻል የዘርፉን ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ እየተከናወነ ያለውን ተግባር ጨምሮ ባለሀብቶች በአካባቢዎቹ በስፋት ሊሰማሩ የሚችሉበት ሁኔታ ቢፈጠር በዘርፉ ሊመጣ የሚችለውን የምርትና ምርታማነት ለውጥ መገመት አይከብድም።ይህን መሬት ሥራ ላይ ሳያውሉ ሀገሪቱ ሰፊ ለምና ድንግል መሬት ባለጸጋ ናት ማለቱ ትርጉም አይኖረውም።ይህን እምቅ ሀብት ለኢንቨስትመንት ለማዋል የየአካባቢዎቹን አርሶና አርብቶ አደር ሕዝቦች፣ የየክልሎቹን መንግስታት ይዞ ለመስራት ከወዲሁ መዘጋጀት ያስፈልጋል።

እንደሚታቀው ግብርናው የሀገሪቱ የምግብ ዋስትና ማረጋገጫ ወሳኙ መሣሪያ ነው።ለሀገሪቱ ለተለያዩ ምጣኔ ሀብታዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ተግባሮች የሚውል የውጭ ምንዛሬ ከሚገኝባቸው ዘርፎች አንዱም ይሄው ግብርና ነው። የግብርናውን ዘርፍ ትራንስፎርም ለማድረግና ኢንዱስትሪ በቦታው እንዲተካ ማድረግ ሲታሰብም ግብርና ትልቅ አቅም ያለበት ቦታ መሆኑ ታይቶና በዚያ ላይ በስፋት መሥራት የኢንዱስትሪውን ዘርፍ በማሳደግ በግብርናው እግር ለመተካት ታስቦ ነው። ይህ ሁሉ ግብርናው ላይ በስፋት መሥራትን በእጅጉ ይጠይቃል።

በቴክኖሎጂ /በማዳበሪያና ምርጥ ዘር፣ በሜካናይዜሽን፣ወዘተ/፣ ለሜካናይዜሽን ምቹ ሁኔታን በሚፈጥረው ኩታ ገጠም እርሻ ማስፋፋት፣ በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት፣ ወዘተ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ እየተከናወኑ ያሉ ተግባሮች አበረታችና ይበልጥ ተጠናክረው ሊቀጥሉ የሚገባቸው ናቸው፤ በአሲዳማነት የተጠቃን መሬት ለማከም የተጀመሩ ጥረቶችም እንዲሁ በላቀ ደረጃ ሊሰራባቸው የሚገቡ ናቸው። በአሲዳማነት ሳቢያ በሄክታር የሚገኘው ምርት በእጅጉ የቀነሰ ነው፤ ይህን መሬት በኖራ በማከም ብቻ በምርታማነት ላይ ለውጥ ማምጣት እንደሚቻል እየተገለጸ ነው፤ ኖራው ደግሞ በእጅ ያለ ሀብት ነው።በአፈር ለምነት ላይ የታሰበውን ንቅናቄ ተግባራዊ በማድረግ በአሲዳማነት ሳቢያ አደጋ ውስጥ ያለውን ምርታማነት መታደግ ፈጣን ሥራን ይጠይቃል።

በግብርናው ዘርፍ ይህን ሁሉ ማከናወን የሚያስፈልገው ከግብርናው የሚፈለገው እጅግ ብዙ በመሆኑ ነው። የግብርናውን ዘርፍ ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ ሥራ ላይ ውለው ውጤታማ ያደረጉትንም ሥራ ላይ ቢውሉ የበለጠ ውጤታማ ሊያደርጉ የሚችሉትንም መተግበር ያስፈልጋል። ግብርናው ስትሰጠው ይሰጣል ይባላል።እንዲሰጥ የሚጠይቀው ሁሉ ይሰጠው።

ኃይሉ ሣህለድንግል

አዲስ ዘመን   ሐምሌ 8/2015

Recommended For You

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *