ሁለተኛ ዙር የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ወርልድ ቴኳንዶ ፌዴሬሽን የ2015 ዓ.ም የክለቦች ቻምፒዮና ትናንት ተጠናቋል። ቻምፒዮናው ከሐምሌ 1/2015 ዓ.ም ጀምሮ በአራት ኪሎ ስፖርትና ትምህርት ስልጠና ማዕከል ለስድስት ተከታታይ ቀናት ሲካሄድ ቆይቷል።
የቻምፒዮናው ዓላማ በአዲስ አበባ ከተማ በተለያዩ ክለቦች ስልጠና እየወሰዱ ያሉ የቴኳንዶ ስፖርተኞች ብቃታቸውን በውድድር እንዲለኩ ማድረግ ሲሆን፤ ይህ ቻምፒዮና ደግሞ ትልቁ መድረክ ነው፡፡
በከተማው ከ90 በላይ የወርልድ ቴኳንዶ ስፖርት ክለቦች የሚገኙ ሲሆን፤ በዘንድሮ የክለቦች ቻምፒዮና ከአርባ በላይ የሚሆኑት ተሳትፈዋል። በውድድሩ በክለቦችና ተወዳዳሪዎች መካከል ጠንካራና እልህ አስጨራሽ ፍልሚያዎች የተደረጉ ሲሆን፤ የተመልካችን ቀልብ መግዛትም ችለዋል፡፡
በውድድሩ በሴቶች አጠቃላይ አሸናፊ ወሰን ወርልድ ቴኳንዶ ክለብ ሲሆን 280 ነጥቦችን መሰብሰብ ችሏል። አዳኒ ማርካን ወርልድ ቴኳንዶ ክለብ ደግሞ በ257 ነጥቦች ሁለተኛ በመሆን ውድድሩን ጨርሷል። ኪሩቤል ቤስት ወርልድ ቴኳንዶ ክለብ በ242 ነጥብ ሦስተኛ መሆን ችሏል።
በተመሳሳይ በወንዶችም የውድድሩ አጠቃላይ አሸናፊ ወሰን ወርልድ ቴካንዶ ክለብ ሲሆን፤ ኑር አልኑር ሁለተኛና ማሙያ ካሚል ሦስተኛ በመሆን ውድድራቸውን ጨርሰዋል። ክለቦቹ እንደየደረጃቸው የዋንጫና የምስክር ወረቀት ተበርክቶላቸዋል። ለተወዳዳሪዎችም እንደየደረጃቸው የሜዳሊያና የገንዘብ ሽልማት ተበርክቷል። በዚህም መሰረት
1ኛ የወጣው ተወዳዳሪ የ8 ሺ ብርና የሜዳሊያ ተሸላሚ ሲሆን፤ ሁለተኛ የወጣው ደግሞ የ6ሺ ብርና የሜዳሊያ ሽልማት ተበርክቶለታል። ሦስተኛ ሆኖ ያጠናቀቀው ደግሞ የሦስት ሺ ብር ተሸላሚ መሆን ችላል፡፡
ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከሰት በኋላ ፌዴሬሽኑ ወደ ውድድር ለመመለስ ጠንካራ ሥራ በመስራቱ የተሻለና
ጥሩ ቻምፒዮና ማዘጋጀት ችሏል። በውድድሩ የተሳተፉት ተወዳዳሪዎች በጥቁር ቀበቶ ደረጃ የሚገኙ ሲሆን፤ በወንድና ሴት በየካታጎሪው ስድስት ስድስት በአጠቃላይ አስራ ሁለት ተወዳዳሪዎች ተሳትፈዋል።
ክለቦቹ በውድድሩ ለመሳተፍ የአዲስ አበባ ወርልድ ቴኳንዶ ፌዴሬሽን የሚፈቅደውን ህግና ደንብ ማሟላት
እና አሰልጣኞች ደግሞ የሦስተኛ ዲግሪ ጥቁር ቀበቶ መያዝ እንዲሁም የአሰልጣኝነት ስልጠና የወሰዱ መሆን ይጠበቅባቸዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ ወርልድ ቴኳንዶ ፌዴሬሽን ውድድርና ሥነ ሥርዓት ኮሚቴ ኢንተርናሽናል ማስተር ደሳለኝ ተክሉ፣ የከተማ አስተዳደሩ ወርልድ ቴኳንዶ ፌዴሬሽን ከከተማው አልፎ በሀገር አቀፍና ዓለም አቀፍ ውድድሮች የሚሳተፉትን ተወዳዳሪዎች የሚያበቃበት መድረክ መሆኑን ጠቅሰዋል። በከተማው ውስጥ 90 የሚደርሱ ክለቦች ውድድሮችን ቢያንስ በዓመት ሁለት ጊዜ እንደሚያካሂዱ የጠቆሙት ማስተር ደሳለኝ፤ እነዚህ ውድድሮች ሁሌም ሲካሄዱ እንደ ሀገር አቀፍ፣ መላ ኢትዮጵያ ቻምፒዮና ሌሎች ውድድሮች የተዘጋጁና ብቃታቸው የተፈተሸ አትሌቶች እንዲኖሩ የሚደረግ መሆኑን ተናግረዋል። ስፖርቱ አዕምሮን አካልንና ሥነምግባርን አንድ ላይ አቅፎ የያዘ በመሆኑ ብቁ ዜጋን ለማፍራት ትልቅ የሆነ ሥራ የሚሰራበት ነው። ለዚህም የፌዴሬሽኑ የውድድርና ሥነ ሥርዓት ከሌሎች ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመተባበር ውድድሩ ባማረና በደመቀ መልኩ እንዲካሄድ አድርጓል፡፡
በቻምፒዮናው ያሸነፉ ክለቦችንና ተወዳዳሪዎችን ለማበረታታት የሰርተፊኬት፣ የሜዳሊያና ዋንጫ ሽልማት ተበርክቷል። የሽልማቱና የማበረታቸው ሥራ የተሻለ ሲሆን፤ ወደፊት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የፌዴሬሽኑ ውድድርና ሥነ ሥርዓት ኮሚቴ ገልጿል። ለተማሪዎች ለአሰልጣኙና ለሌሎች የሚያስፈልገውን ነገር በሂደት ለማሟላት እንደሚሰራም ጠቁሟል። ፌዴሬሽኑ ውድድሩን በክፍለ ከተማ ደረጃ ድረስ በማውረድ ትልቅ የውድድር ዕድሎችን መፍጠር እንደቻለም ጠቅሷል።
ዓለማየሁ ግዛው
አዲስ ዘመን ሐምሌ 7/2015