በአንድ ጀምበር ታሪክ የሚሰሩ እጆች

ጀምበር ወጥታ እስክትገባ..

ለሀገር ክብር መባ

ነገ ሳልል አሁን

ዛፍ ልትከል፣ ሰው ልሁን።

የዛሬ ነጻ ሃ ሳቤን በስንኝ ጀምሬአለሁ።

ታሪክ ያለው ታሪክ ሊሰራ በተሰናዳ አእምሮና ልብ ውስጥ ነው። ኢትዮጵያውያን በአንድነት ከተነሱ የሚያቆማቸው እንደሌለ በተለያየ ጊዜ አይተናል። ከነዚህም ውስጥ አንዱ በየአመቱ የክረምት መግባትን ተከትሎ የሚከወነው የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር አንዱ ነው። ሌላው እና አዲስ ታሪክ ልንሰራበት የተዘጋጀነው በአንድ ጀምበር 500 ሚሊዮን ችግኞችን ለመትከል የተነሳንበት ህዝባዊ ንቅናቄ ነው።

ሐምሌ 10/2015 ዓ.ም በአረንጓዴ አሻራ ዳግማዊ ድል የምንቀዳጅበት ቀን ነው። ጀምበር ወጥታ እስክትገባ ለሀገር ክብር አሻራችንን የምናሳርፍበት የብሄራዊ ኩራት ቀን ነው። ይሄን ቀንና ይሄን ህዝባዊ ተሳትፎ አስመልክተው ጠቅላይ ሚኒስተር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ መልዕክት አስተላልፈዋል። ‹አረንጓዴ አሻራ ለእኛ ብዙ ነገራችን ነው። የግብርና ምርታችንን የምናሳድግበት እና በምግብ ራሳችንን የምንችልበት፣ ሁለት ሶስት ጊዜ አምርተን የምግብ ምርቶችን በርካሽ እንድናገኝ የሚያደርግ፣ የደን ሽፋንን ጠብቆ የአየር ንብረትን የሚያስተካክል› ላቅ ያለ ፋይዳ ያለው እንደሆነ ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ሰፊውን ድርሻ የሚይዘው ‹ኢትዮጵያ ለምለሟ› የሚለው ታሪክ ነው። በብዙ ሀገረኛ ዜማዎቻችን ውስጥ ይሄ እውነት በኩራት እና በሞገስ ተጠቅሷል። አሁን ላይ ይሄ ስም ተረት ከመሆን ባለፈ በእውን የሚታይ አይደለም። ምክንያቱም የደን ሽፋናችን ከጊዜ ወደጊዜ በሰው ሰራሽ እና በተፈጥሮ አደጋዎች በመመናመኑ ነው። ያለፈ ታሪካችንን ለመመለስ እና አዲሷን ኢትዮጵያ ለመፍጠር የአረንጓዴ አሻራ ንቅናቄ የአንበሳውን ድርሻ ይወስዳል።

‹ኢትዮጵያ ለምለሟ› ብለን ዳግም የምንጠራትን እና ዳግም የምናዜምላትን ሀገር መፍጠር የዚህ ትውልድ የቤት ሥራ ነው። ንቅናቄአችን ለውጥ እያመጣ እንደሆነ ያለፈውን ጊዜ ማየቱ በቂ ነው። ከራሳችን አልፈን ለአፍሪካና ለዓለም ምልክት የሆንበት የአረንጓዴ አሻራ ትግበራ ነበር። የአሁኑ ደግሞ ለየት ባለ እና ሌላ አግራሞትን በሚጭር መንፈስ በአንድ ቀን 500 ሚሊዮን ችግኞችን ልንተክል አካፋ ይዘናል።

እንዲህ አይነቱ ህዝባዊ ንቅናቄ ችግኝ ከመትከል ባለፈ ሌላም ላቅ ያለ ትርጉም ያለው ነው። የእንችላለን መንፈስን ከመፍጠር ባለፈ ኢትዮጵያውያን በአንድነት ከተነሳን የሚያቆመን ኃይል እንደሌለ የሚያሳይ ነው።

የሰው ልጅ ጊዜውን እና እውቀቱን በአግባቡ መጠቀም ከቻለ ሁሌም ታሪክ መስራት ይችላል። የታሪክ አብራኮች የአንድነት ጽንሶች ናቸው። ታሪክ ለመስራት ተያይዘንና ተቃቅፈን ወደፊት ከመሄድ ባለፈ ሌላ ምርጫ የለንም። በአንድ ጀምበር 500 ሚሊዮን ችግኞችን መትከል አንድነት የሚለው ስም ካልሆነ ምንም አይገልጸውም። በአንድ ጀምበር ባለታሪክ መሆን የአንድነት ውጤት ካልሆነ የምንም ሊሆን አይችልም።

በአንድነት ከቆምን ታሪክ የሚሰሩ እጆች አሉን። በአረንጓዴ አሻራ በኩል ከራሳችን አልፈን ለአፍሪካ ብሎም ለዓለም ምልክት የሆነው በአንድና ሁለት ማንነቶች አይደለም በኢትዮጵያዊነት ነው። እጆቻችን የእኛን አንድ መሆን የሚጠብቁ ናቸው። አእምሯችን ታሪክ ሊሰራ የእኛን ወንድማማችነት በመጠበቅ ላይ ነው። እንደአረንጓዴ አሻራ ያሉ ዓለምን ያስደነቅንባቸው ተራማጅ አስተሳሰቦቻችን በድህነት እና በኋላቀርነታችን ላይ ቢደገሙ በአጭር ጊዜ ውስጥ የለውጥ ባለቤቶች እንሆን ነበር የሚለው በዚህ ምዕራፍ የገባኝ ትልቁ መረዳቴ ነው።

አንዳንድ ቀኖች አሉ…ታሪክ ጽፈው ባለታሪክ የሚያደርጉን። ባለፉት አመታት ውስጥ በአረንጓዴ ንቅናቄ በድል ላይ ድልን እያስመዘገብን የለውጥ እና የተሀድሶ መንፈስ ውስጥ ነበርን። በአንድ ቀን ከ350 ሚሊዮን በላይ ችግኞችን ተክለን ዓለም ጉድ ሲለን ነበር። ዘንድሮ ደግሞ በላቀ እና ከፍ ባለ የመንፈስ ልዕልና ተሽለን መጣን። በአንድነት ስንቆም እንዲህ ነን…ለዓለም መደነቂያ ነው የምንሆነው።

የተናቅነው እና ዝቅ ያልነው አንድነት ስላጣን ነው። ታሪክ በአንድነት እጆች የሚጻፍ የህብረብሄራዊነት እሳቤ ነው። በአረንጓዴ አሻራ ዓለም አቀፍ ውዳሴንና መደነቅን ያመጣንው በጋራ ስላሰብን ነው። በጋራ ማሰብ በጋራ ማደግ፣ በጋራ መልማት ነው። ሀገራችንን የምናገለግለው እንዲህ ባለው ሀገራዊ ንቅናቄ ላይ ተሳትፎ ስናደርግ ነው። እንዲህ አይነቱ አጋጣሚ ሀገሬን በምን ላግዛት ብሎ ለሚጠይቅ ጥሩ አጋጣሚ ነው።

ሐምሌ አስር የኢትዮጵያ ቀን ነው። ጸዐዳ የምትለብስበት፣ ራቁቷን የምንሸፍንበት ቀን። ጀምበር ወጥታ እስክትገባ እጆቻችን ከታሪክ እውነት ጋር ይተሳሰራሉ። ስለኢትዮጵያ እንደክማለን፣ ስለትውልዱ እንሰራለን። ስማችንን በዓለም አደባባይ በወርቅ ቀለም እንጽፋለን። ለሀገር መድከም ለራስ መድከም እንደሆነ፣ ለትውልድ መልፋት ለራስ መልፋት እንደሆነ ላልገባቸው እንናገራለን።

ህይወት የሚገኘው ከአረንጓዴ ቀለም ውስጥ ነው። አረንጓዴ ምድር የህይወት መብቀያ፣ የህላዊ ማፍሪያ ማህጸን ነው። ምድር ህይወትን አምጣ የምትወልደው እንዲህ ባለው የተፈጥሮ ዝምድና ነው። ከዚህ እውነት በመነሳት አረንጓዴ አሻራ የመኖር እና ያለመኖር ጉልህ ጥያቄ እንደሆነ መረዳት እንችላለን። ምድርን በአረንጓዴ መሸፈን ህይወትን ማስቀጠል ሲሆን በተቃራኒው ማራቆት ህይወትን መግታት ነው።

በአረንጓዴ አስተሳሰብ ከዓለም ፊተኛ ነን። ዓለም ፊቷን አዙራ እኛን እያየች እና እያደመጠች ትገኛለች። አምናና ካቻምና ያስመዘገብናቸው ድሎች ዛሬም በእኛ እጅ ውስጥ ናቸው። ዘንድሮም አዲስ ታሪክ ልናስመዘግብ በተጠንቀቅ ቆመናል። በእርግጠኝነት ይሄንንም የሚሽር አዲስ ሪከርድ በሚመጣው አመት እንጠብቃለን። እስካሁን ድረስ በአረንጓዴ አሻራ በኩል የሚገዳደረን ጠፍቶ የራሳችንን ሪከርድ ራሳችን እየሰበርን ያለበት ሁኔታ ነው ያለው።

የአረንጓዴ አሻራ ፕሮግራም ችግኝ ተክለን የምናልፈው ብቻ አይደለም። ልዕልናው እና አሳታፊነቱ፣ አንድነቱና ህብረቱ ከሀገራችን ወቅታዊ ጉዳዮች ጋርም በበጎ ቢነሳ ባይ ነኝ። ከችግኝ ተከላ ባለፈ ችግሮቻችንን በጋራ እጆች እንዴት መርታት እንዳለብን ጥቁምታ የሚሰጥ ነው። መቶ ሃያ ሚሊዮን እጆች ኢትዮጵያን በዓለም አደባባይ ባለክብር እና ባለማዕረግ ማድረግ ከቻሉ ችግሮቻቸው ላይም መዝመት የማይችሉበት ምንም ምክንያት የለም።

ዓለም ሞክሮ ያልቻለው ግን ደግሞ በእኛ የተቻሉ ብዙ ነገሮች አሉ። እኚህ እውነታዎች በአንድነት ከተጓዝን የማንደርስበት እንደሌለ የሚጠቁሙን ናቸው። እናም የሚያዋጣንን እንምረጥ። የሚያዋጣን እንደአረንጓዴ አሻራ በአንድነት ተሰልፈን የአንድነት ታሪክ መጻፍ ነው። አብዛኞቹ ታሪኮቻችን በአንድነት እጆች የደመቁ ናቸው።

የዚህ ዓለም ትልቁ ጉዳይ የአየር ንብረት ለውጥ ጉዳይ ነው። ከትናንት እስከዛሬ የሰው ልጅ በዚህ ጉዳይ ላይ ብዙ መክሮ እና ዘክሮ ያውቃል። ስልጣኔና ዘመናዊነቱ ግን ህይወቱን ወደሞት ከመውሰድ ባለፈ የፈየደለት የለም። አረንጓዴ አሻራ ደግሞ ለዚህ ስጋትና ተግዳሮት ትልቅ መፍትሄ ሆኖ ከፊት የሚሰለፍ የመፍትሄ አካል ነው።

የአየር ንብረት ለውጥ ስጋቱም ሆነ በረከቱ የማይደርስበት የምድር ክፍል የለም። እድገት እና ስልጣኔ፣ ድህነት እና ኋላ ቀርነት ከዚህ እውነት ጋር በእጅጉ የተቆራኙ ናቸው። ሌሎች መሰረታዊ መነሻዎች እንዳሉ ሆነው ለአፍሪካ በተለይም ደግሞ ለምስራቅ አፍሪካ ድህነት እና ተረጂነት መስፋፋት የአየር ንብረት ለውጥ የአንበሳውን ድርሻ ይወስዳል።

የአካባቢ ጥበቃ እንደሀገር ለተጋረጡብን ችግሮች፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ እየተስፋፋ ለመጣው የኑሮ መወደድ የአየር ንብረት ለውጥ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ አለበት። አሁን ላለብንም ሆነ ነገ ለሚፈጠሩ የመኖር እና ያለመኖር መሰረታዊ የህልውና ጥያቄዎች መልስ የሚሰጠን አረንጓዴ አሻራ ብቻ ነው። ዓለም በጥበቧ የዚህ ስጋት መድኃኒት አልፈጠረችም።

መፍትሄው በእውቀት እና በሳይንሳዊ ዘዴ የተመራ የአካባቢ ጥበቃ ንቅናቄ ነው። በአረንጓዴ አስተሳሰብ አረንጓዴ ምድር እስካልፈጠርን ድረስ ከችግሩ የምናመልጥበት ሌላ አቋራጭ መንገድ የለንም። ችግሩ ዓለም አቀፍ ነው። በተለየ መንገድ አፍሪካን የሚያጠቃ፣ ከአፍሪካም ምስራቅ አፍሪካን በተለይም ከሰሀራ በታች ያሉ ሀገራትን የሚያጠቃ መሆኑ ባለፉት አመታት በግልጽ የታየ ነው።

እንዲህ አይነቱ ስጋት በአረንጓዴ አስተሳሰብ የሚሽር፣ በአረንጓዴ ምድር የሚያገግም ሲሆን፤ ሀገራችን ኢትዮጵያ ደግሞ በዚህ ረገድ ህዝባዊ በሆነ ተሳትፎ በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና ያገኘችበትን እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ ናት። ባለፉት አመታት ውስጥ የተከልናቸው ችግኞች ለውጥ እያመጡ እንደሆነ በተለያየ ጊዜ ካየነው እና ከሰማነው እውነት መረዳት ችለናል።

የአረንጓዴ አሻራ ትግበራ የአየር ንብረት ለውጥ ላይ ብቻ የሚቆም ሳይሆን ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያለው እንደሆነ የሚያጠያይቅ አይደለም። የስጋቱን ያክል ብዙ በረከትም አለው። የአየር ንብረትን በማስተካከል ተስማሚና ምቹ ከባቢ እንዲኖር ማድረግ አንዱና ዋነናው በረከቱ ሲሆን፤ ከዚህ ጋር ተያይዘው የሚመጡ ሌሎች ብዙ ጸጋዎችም አሉ።

በርሃማነትን መከላከል ምርታማነትን ይጨ ምራል። ወቅቱን በጠበቀ ዝናብ ዘርተን እንድናበቅል፣ አጭደን እንድንበላ እድል ይሰጠናል። በተስተካከለና በተገባ የአየር ንብረት ከባቢ ራሳችንን በምግብ እንድንችል በማድረግ ድህነትን እንድንረታ ያደርጋል። ከዚህ ሁሉ በላይ ደግሞ በህይወት እንድንኖር ዋስትና ይሰጠናል።

የቱሪዝም ኢንዱስትሪው እንኳን ይሄን እውነት ተከትሎ የሚነቃቃ ነው። ቱሪዝም መነሻው አካባቢ ነው። አካባቢ ስንል ዘርፈ ብዙ ቢሆንም ዋናው እና ትልቁ ግን ሳቢና ማራኪ ስነምህዳር የሚለው ነው። የአረንጓዴ አሻራ በረከት ወንዝ ዳር እንዳለች ጽጌሬዳ አበባ ነው። ወንዝ ዳር የበቀለች ጽጌሬዳ አበባ ምን እንደምትመስል ማስረዳቱ ለቀባሪ ማርዳት ነው።

አረንጓዴ ቀለም የሀገር ቬሎ ነው። ነጭ በነጭ ለብሰን ሀይሎጋ እንደሚባልልን የደስታ ቀናችን የኢትዮጵያ ሰርጓም አረንጓዴ ቀለም ነው። ሚዜዎቿ ደግሞ እኛ ልጆቿ ነን። በአረንጓዴ እሳቤ፣ በአረንጓዴ ቬሎ ሀገር እየዳርን አረንጓዴ ትውልድ እንፈጥራለን። እጆቻችን ታሪክ እንዲሰሩ ጀምበር ወጥታ እስክትገባ ለኢትዮጵያ ትንሳኤ የበኩላችንን እናዋጣለን።

ለሀገር መድከም ፖለቲካዊ እሳቤ አይደለም። አንዳንዶች ሁሉን ነገር ከፖለቲካ ጋር አስተቃቅፈው ለምንም ነገር አስተዋጽኦ ሲጠየቁ ፖለቲካ ይመስላቸዋል። ፖለቲካና ሀገርን ማገልገል የተለያዩ አስተሳሰቦች ናቸው። ሀገርን ማገልገል የዜግነት ግዴታ ከመሆኑም በተጨማሪ የሁላችንም የጋራ ኃላፊነት ነው። አረንጓዴ አሻራ በምንም አይነት መልኩ ፖለቲካዊ እሳቤ ሊሆን አይችልም፤ ሀገር የመፍጠር፣ ትውልድ የማዳን የጋራ እውነት እንጂ።

እንደ አረንጓዴ አሻራ የመሰሉ ንቅናቄዎች የማንም ሳይሆኑ የኢትዮጵያ ሆነው ወደህይወታችን የሚመጡበት አጋጣሚ ብዙ ነው። ኢትዮጵያ የምትደምቅበት፣ ትውልዱ የሚከብርበት ሀገራዊ ንቅናቄ ፖለቲካዊ እሳቤ ሊሆን አይችልም። አረንጓዴ አሻራ የፖለቲካ ጉዳይ ሳይሆን የኢትዮጵያ ጉዳይ ነው። ሀገርን በማገልገል ውስጥ የእኔ የአንተ የሚባል የለም። ሀገር ማለት እኔ አንተ እና ለሌላው ሰው ነው ካልን በማገልገላችን ውስጥ የምንገለገለው ራሳችን ነን።

በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)

አዲስ ዘመን ሐምሌ 7/2015

Recommended For You

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *