ችግኞችን ከመትከል ባሻገር

ክረምት መሬት ርሳና ረስርሳ የተዘራባትን አብቅላ ለበጋው የሚሆነን ስንቅ ስለምታቀብለን እናስበዋለን፤ እንወደዋለንም። ይህ እንዳለ ሆኖ ደግሞ ካለፉት አምስት አመታት ወዲህ በሰፊውና በተጠናከረ ህጻን አዋቂው፣ የተማረው ያልተማረው፣ የመንግሥት የግል ሠራተኛው፣ የቤት እመቤቷ አዛውንት፣ አባወራና እማወራዋ ሁሉን ባሳተፈ መልኩ የተራቆተውን ምድራችንን በአረንጓዴ ልማት አሻራችን የማልበስ ጉዞ ላይ በመሆናችንም ጭምር ነው።

ዛሬ ላይ ቆመን ያለፉትን አመታት ስራዎቻችንን ብናስብ እንኳን በርካታ ስነ ምህዳራዊ ለውጦች ለማምጣታችን እማኝ መጥቀስ ላያሻን ይችላል። ምክንያቱ ደግሞ የአየር ንብረታችን ተሻሽሎ ወቅቶች ጊዜያቸውን ጠብቀው እንዲለዋወጡ አስችሎ … በትንሽ ዝናብ ያልፈን የነበረው ክረምት ሳይቀር ወቅቱን ጠብቆ ገብቶ እየወጣ ብዙ ለውጦች እየመጡ ስለመሆኑ የምናየው ሃቅ ነው።

‹‹ነገን ዛሬ እንትከል›› ለሚለው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር መሪ ቃል “ነጋችን እንዲያምር ዛሬ ላይ ተግተን ዋጋ ከፍለን እንስራ” የሚል ትርጓሜ ሰጥቼዋለሁ፡፡ በዚህ መሪ ቃል እየተገበርነው ያለው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብራችን ባሳለፍናቸው ዓመታት በተሰራው ስራ የመጣው ለውጥ ከእኛ አልፎ ለጎረቤት ሀገሮች፣ ከዚያም በላይ ለመላው ዓለም በተለይም በአየር ንብረት ለውጥ ችግር ውስጥ ላሉ ሁሉ ትልቅ መልዕክት የሚሆን ስለመሆኑ የሚያጠያይቅ አይደለም።

ታዲያ በዘንድሮ ዓመትም መንግሥት ያስቀመጠውን በአንድ ጀምበር 500 ሚሊዮን ችግኞችን እንተክላለን የሚለውን እቅድ ከግብ እንዲደርስ ሁሉም ባለበትና በተሰማራበት መስክ የበኩሉን መወጣት እንዳለበት ትንሽ ለማለት ፈለኩ።

ከመነሻዬም እንዳልኩት ምንጊዜም ቢሆን ለውጥና እድገት ሲታሰብ መነሻው ጥረት፣ አብሮ መስራት፣ መግባባት ከዚያም ባለፈ ደግሞ በረከት የምትሰጠንን ምድር አብዝቶ መንከባከብ ከሁሉም የሚቀድም ሊሆን ይገባል። እኔ እንደማስበው ምድራችንን እያራቆትን ነገን ሳይሆን ዛሬን ብቻ ለመኖር የምንጥር ከሆነ፣ ቀጣይነታችን እጅግ አደጋ ውስጥ የወደቀ ሊሆን እንደሚችል መገመቱ መቼም ለቀባሪው እንደማርዳት ዓይነት ነው።

ታዲያ እኛ ኢትዮጵያውያን ወትሮም ቢሆን ተባብረን ብዙ ነገሮችን የመለወጥ ኃይል ያለን ከመሆኑ አንጻር አሁንም በጀመርነው ፍጥነትና መጠን መጓዝ ከቻልን እስካአሁን ካስገረምነው በላይ ዓለምን የማናስገርምበት፣ ምድራችንን አረንጓዴ አልብሰን መጠሪያችን (መለያችን) የሆነውን ድህነትና ረሃብ ታሪክ የማናደርግበት ምክንያት አይኖርም።

ይህ ግን የሚሳካው ቁጭ ብለን ስለተመኘን አልያም እናደርገዋለን ብለን ስለዛትን ብቻ አይደለም፤ ይልቁንም እናደርገዋለን ብለን ከልባችን በመነሳት ከዛም ወደተግባራዊ እርምጃው በሙሉ ልብና ቁርጠኝነት በመግባት እንጂ። በመሆኑም መላው ኢትዮጵያዊ የነገ ዓለሙን የልጆቹን ሀገር ውብና ለኑሮ የተስማማች፣ ፍሬያማና ከድህነት ረሀብና ችግር የወጣች ለማድረግ ዛሬ ላይ ሳይታክት መስራት፤ በተቀመጠው

 የጊዜ ሰሌዳና በወጣው ፕሮግራም መሰረት አረንጓዴ አሻራውን ባለበት ባመቸው ቦታ ሁሉ ማሳረፍ የውዴታ ግዴታው መሆኑንም መገንዘብ ያሻል።

ይህንን ስናደርግ ምኞታችን ከምኞትነት ተሻግሮ ውጤት ያመጣል፡፡ ሃሳባችን ሃሳብ ሆኖ እንዳይቀር መሬት ወርዶ በሥራ እንዲተረጎም ይሆናል። ከለውጡ ወዲህ በተለይም አረንጓዴ አሻራን በማሳረፉ በኩል በተሰራው ሥራ ከፍተኛ ለውጥ እንዳስመዘገበ አይተናል።

ከላይ ስነሳ እንደገለጽኩትም ምድራችን የምንፈልገውን ያህል ባይሆንም ዛሬ ላይ ከነበረችበት የመራቆት አደጋ ወደ አረንጓዴነት ተመልሳለች፤ ይህ ደግሞ የአየር ንብረቱ እንዲስተካከል የበኩሉን ሚና ተወጥቷል።

የአየር ንብረቱ በዚህ መልክ መስተካከሉ ደግሞ የዘራነው ሁሉ እንዲያፈራ አስችሏል። ታዲያ ይህንን ጅምር በብዙ ሥራ ብንደግፈው የት እንደርስ ይሆን? መልሱን ለየራሳችሁ እተወዋለሁ።

ይህ የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብራችን ዘንድሮም በተጠናከረ ሁኔታ የሚቀጥል ሲሆን፤ በርካታ ስራዎች እየተከናወኑ፣ ቅድመ ዝግጅቶችም በሀገር አቀፍ ደረጃ እየተደረገ ነው።

ሐምሌ 10 ቀን 2015ዓ.ም ደግሞ በመላው ሀገሪቱ እጅ ለእጅ ተያይዘን ቀኑን ሙሉ በምናደርገው አረንጓዴ አሻራን የማሳረፍ ስራ 500 ሚሊዮን ችግኞችን እንተክላለን። እኔ ግን ከዚያም የበለጠ እንተክላለን ብዬ አስባለሁ። ይህንን ያልኩበት ዋናው ምክንያት ደግሞ እስከ አሁን በተከልናቸው ዛፎች የመጣውን ለውጥ ያየ ሁሉ እጁን አጣጥፎ ስለማይቀመጥ ከታቀደው በላይ ብዙ እንደምንሄድ እርግጠኛ ስለሆንኩ ነው።

በሌላ በኩል ከዚህ በፊት ብዙ ችግኞችን በተለያዩ ቦታዎች በመትከል ከፍ ባለ ሁኔታ አረንጓዴ አሻራችንን አኑረናል። ይህ በጣም ጥሩና ደስ የሚል ነገር ነው።

ነገር ግን እነዚህ ችግኞች ከመትከል ባለፈ ምን ያህል ተንከባክበናቸዋል? የሚለው ጥያቄ አስፈላጊና ትኩረት የሚሻ ነው። እኔ ባለኝ መረጃ አንዳንድ የመንግሥትና የግል ተቋማት የተከሏቸውን ችግኞች ጠባቂና ተንከባካቢ በመቅጠር አስፈላጊውን የእድገት ክትልል እንደሚያደርጉ አውቃለሁ። በጣም ደስ የሚል ነገር ነው፤ ሌሎችስ የተከላችኋቸውን ችግኞች በምን ያህል መጠን እየተንከባከባችኋቸው ነው? መልሱን ለራሳችሁ።

አሁን ደግሞ 500 ሚሊዮን ችግኝን ልንተከል ስለሆነ የእንክብካቤውን ጉዳይ እንዴት ልንከታተለው አስበናል? ይህ አንገብጋቢ ጥያቄ አረንጓዴ አሻራን ለማሳረፍ በሚዘጋጁ ዘንድ ሁሉ ሊታሰብበትና ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ መሰረታዊ ጥያቄ ነው።

ስራችን ፍሬ የሚያፈራውና ውጤት የሚያመጣው እንዲሁም የአረንጓዴ ልማት ስራችን አሁን በጀመረው መልኩ ለዓለም ማሳያ ሊሆን የሚችለው ስለተተከለ ብቻ ሳይሆን አድጎና አብቦ የሚፈለግበትን ውጤት ሲያመጣ ጭምር ነውና ችግኝ በመትከልም ሆነ በማስተከል ሂደቱ ላይ የምንሳተፍ ሁላችንም ይህንን ልናስብበት ይገባል እላለሁ።

ችግኞችን ከመትከል ባሻገር ተገቢውን እንክብካቤ ማድረግ ላይ ትኩረት በማድረግ ሁላችንም ለተከላው የምናደርገውን ርብርብ ችግኞቹን በመንከባከቡ ላይም በመድገም የሚጠበቀውን ውጤት ለማስመዝገብ እንሥራ!

በእምነት

አዲስ ዘመን ሐምሌ 7/2015

Recommended For You

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *