ታሪክ ድንገት እና በአጋጣሚ የሚሆን ክስተት አይደለም። ከሁሉም በላይ ነገን አሻግሮ ማየትን፤ ለዚያ የሚሆን ቁርጠኝነት ፤ ለጊዜና ጊዜ ለሚፈጥረው መልካም አጋጣሚ ራስን ማስገዛትና መዋጀትን የሚጠይቅ፤ ከአሁን ላይ ተነስቶ ነገን ሊያሻግር የሚችል ትልቅ ማኅበራዊ ክስተት ነው ።
በዚህ ውስጥ ታሪክ መሆን የሚያስችል ሀሳብ፤ ሀሳቡን የሚሸከም ማኅበረሰብ/ሰው/፣ ሀሳቡን ተጨባጭ ማድረግ የሚያስችል የዓላማ ልዕልና /ቁርጠኝነት/፤ ለዚህ ደግሞ ከዛሬ ተግዳሮቶች/ፈተናዎች ላይ የሚነሳ ነገዎችን ተስፋ አድርጎ የሚያልም /ተሻጋሪ/ አዕምሮ ያስፈልጋል ።
እኛ ኢትዮጵያውያን የታሪክ ሠሪ አባቶቻችን ልጆች ከመሆናችን አንጻር፤ ለታሪክና ታሪክ ለሚፈጥረው ሞገስና ልዕልና እንግዳ አይደለንም። የቀደሙት አባቶቻችን በብዙ መስዋዕትነት የደመቁ ታሪኮችን ሠርተው፤ ለኛ ለልጆቻቸው በማውረስ ከመቃብር በላይ የሆነ ገድል ፈጽመው አልፈዋልና፡፡
ዛሬ ላይ እንደ አንድ ትልቅ ሕዝብ በዕለት ተዕለት ሕይወታችንም ሆነ በዓለም አቀፍ መድረኮች አንገታችንን አቅንተን፤ ከፍ ባለ ብሔራዊ ኩራት መንቀሳቀስ የቻልነው ትናንት ላይ በተከናወኑ፤ አባቶቻችን ብዙ ዋጋ ባስከፈሉ ደማቅ ታሪኮቻችን አማካኝነት ነው።
ማኅበረሰብ የትውልዶች ቅብብሎሽ ከመሆኑ አንጻር፤ እያንዳንዱ ትውልድ የዘመኑ ባላደራ ነው። ከዚህ አንጻርም የቀደሙ ትውልዶችን ታሪክ ከመተረክ ባለፈ ለመጪዎቹ ትውልዶች ለትርክት የሚበቃ የራስን ታሪክ ሠርቶ ማለፍ ይጠበቃል።
ይህ በአንድ በኩል የቀደሙት የታሪክ ትርክቶች ሞገሳቸውን እንዳያጡ ማድረግ የሚያስችል፤ ከዚህም ባለፈ እያንዳንዱ ትውልድ የሚኖርበትን ዘመን የሚዋጅ ታሪክ በመሥራት ሕዝባዊ ታሪክ ሠሪነትን ማስቀጠል የሚያስችል አቅምና ቁርጠኝነትን በየትውልዱ ማደስ የሚያስችል ነው።
ከዚህ አንጻርም ላለፉት ስድስት አስርተ ዓመታት የነበሩ ትውልዶች በሀገሪቱ ታሪክ ውስጥ ክፍተት ሆኖ አንገት ሲያስደፋን የነበረውን ድህነት እና ኋላቀርነትን ታሪክ ማድረግ የሚያስችሉ የተለያዩ መነቃቃቶችን በመፍጠር፤ ሀገራዊ እውነታውን የሚቀለብስ ታሪክ ለመሥራት ረጅም ርቀት ተጉዘዋል።
መነቃቃታቸው የታሰበውን ሀገራዊ ለውጥ ማምጣት ባይችልም፤ በየትውልዱ ውስጥ ቁጭት በመፍጠር አሁን ያለው ትውልድ ድህነትን ታሪክ አደርጋለሁ በሚል መነቃቃት ተነሳስቶ፤ የራሱን ታሪክ በመሥራት ጉዞ ውስጥ እንዲገኝ የመንገድ ስንቅ ሆኖታል።
በርግጥ ጉዞው ቀላል አልሆነም፣ እንደቀደሙት ትውልዶች በብዙ ፈተናዎች እና ውጣ ውረድ የተሞላ፤ ሀገርን እንደሀገር የሕልውና አደጋ ውስጥ እስከመክተት የደረሰ፤ የሕዝባችንን ዘመን ተሻጋሪ ማኅበራዊና እና መንፈሳዊ እሴቶች አደጋ ውስጥ የከተተ ሆኗል።
ሕዝባችን ብሩህ ነገዎችን በብዙ ተስፋ እየጠበቀ ዘመናትን ከተሻገረበትን ተስፋው የሚያፋታ፤ ድህነትን ታሪክ አደርጋለሁ ብሎ የጀመረውን አዲስ የታሪክ ጉዞ የሚያሰናክል፤ ቋንቋውን የሚደበላልቁ፤ የፊት ገጽታን የሚያጨፈግግ ብዙ ፈተናዎችን አስከትሎ መጥቶበታል ።
በዚህ እልህ አስጨራሽ የታሪክ ምዕራፍ ውስጥ ትውልዱ የራሱን ሕያው ታሪክ ለመሥራት እያደረገ ያለው ጥረትና ጥረቱ እያስገኘለት ያለው ፍሬ፤ በርግጥም ከታሪክ ባለቤትነት በስተጀርባ ያለውን ታሪክን የማዋለድ ምጥ የቱን ያህል አቅምና ቁርጠኝነት እንደሚጠይቅ መታዘብ ያስችላል ።
ከዚህም አንዱ ዛሬ ላይ እንደሀገር መጪው ጊዜያችንም ላይ ሆነ በመጭው ትውልድ ትልቅ ታሪክ ሆኖ ሊዘከር የሚችለውን ሀገርን አረንጓዴ የማልበስ ንቅናቄ /አረንጓዴ አሻራ/ በሁለንተናዊ መንገድ ስኬታማ እንዲሆን እያደረግነው ያለው ርብርብ ፤ የብሩህ ቀናት ተምሳሌት ልትሆን የምትችለውን አረንጓዴ ሀገር አምጦ የመውለድ ያህል ነው።
ምጡ በመጪዎቹ ትውልዶች ላይ እንደ ሀገር የይቻላል መንፈስን በብዙ አቅም መዝራት የሚያስችል፤ ትውልዶቹ በተሻለ የመኖሪያ አካባቢና የተመቻቸ ሁኔታ ለራሳቸውና ከራሳቸውም አልፈው እነሱን ለሚተካው ትውልድ በአዲስ ታሪክ የደመቀች ሀገር ማስረከብ የሚያስችል እርሾ ነው።
የትውልዶች የተንሰላሰለ ታሪክ ፈጣሪነት የሚያጸና፤ ሀገራዊና አዎንታዊ የታሪክ ትርክቶችን በማስፋት፤ የተበላሹ የታሪክ ገጾችን የሚያድስ፤ ትውልዶች ከትናንት ዛሬ፤ ከዛሬ ነገ አንገታቸውን አቅንተው፤ በልበ ሙሉነት የሚራመዱበትን አዲስ የታሪክ ገጽ መጻፍና ማስነበብ የሚያስችል ነው
አዲስ ዘመን ሐምሌ 8/2015