የባለፈው ዓመት የፈተና አሰጣጥ ሥርዓት ተዓምራዊ ክስተት አስተናግዷል። በዚህ ክስተት ስንዴ ከእንክርዳዱ የተለየ ይመስላል። በበርካታ ሺዎች የሚቆጠሩ ተማሪዎች የከፍተኛ ትምህርት ተቋም መግቢያ ነጥብ ሳያመጡ ቀርተዋል። ምንም ያላሳለፉ ትምህርት ቤቶች እንደነበሩም ተሰምቷል። በዚህም ውጤት መምህራን፣ የወላጅ ቤተሰቦችና በትምህርቱ ዘርፍ የሚሠሩ አካላት አንገታቸውን ደፍተዋል። ሀገርም ቅስሟ ተሰብሯል። ታዲያ ስብራቱን የሚጠግነው ምንድን ነው? ከተባለ ጥሩ የፈተና ዝግጅት ማድረግ እንደሆነ በዘርፉ ያሉ ባለሞያዎች ይጠቁማሉ።
ነጥብ ማምጣት የተሳናቸው ተማሪዎች የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን ደጃፍ እንዲረግጡ ሁሉም የበኩሉን አስተዋፅኦ እንዲያበረክት ይጠበቃል። ሥራዎችን በተግባር ማሳየትም ያስፈልጋል። ከዚህ አንጻር ታዲያ ራሳቸው ተማሪዎችና ትምህርትቤቶች ምን ዓይነት ዝግጅት እያደረጉ ነው ሲል አዲስ ዘመን ጠይቋል።
በእርግጥ የዘንድሮው የከፍተኛ ትምህርት ተቋም መግቢያ ፈተና ሁለት ዓይነት ተፈታኞችን ያስተናግዳል። የመጀመሪያዎቹ አምና ተፈትነው በየዩኒቨርሲቲው ውስጥ የማሻሻያ /Remedial/ ፈተና ለመውሰድ የሚሰናዱ ሲሆኑ ሁለተኞቹ ደግሞ በዘንድሮው በጀት አመት ትምህርታቸውን ሲከታተሉ የቆዩ ተማሪዎች ናቸው።
አዲስ ዘመን ትኩረት ያደረገው በዘንድሮው በጀት አመት ትምህርታቸውን ሲከታተሉ የቆዩ ተማሪዎች ላይ ሲሆን ተማሪዎቹ አምና ከነበሩት ተማሪዎች ውድቀት ተምረው ዘንድሮ የተሻለ ነገር ለማሳየት ምን ዓይነት ዝግጅት እያደረጉ እንደሆነ ለመፈተሽ ሞክሯል።
ተማሪ ኬና አፈወርቅ የደጅአዝማች ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የ12ኛ ክፍል ተማሪ ናት። በምትችለው አቅም ሁሉ ለዘንድሮው ፈተና እየተዘጋጀች ነው። ከአምናው ክስተትም በርካታ ነገሮችን ተምራለች። አምና ተማሪዎች ብዙ አዳዲስ ነገሮች እንደገጠማቸው፤ ከዚህ ውስጥ አንዱ የፈተና አካባቢያቸውን መልቀቃቸው፤ ሌላው ደግሞ ከፈታኞቻቸው መካከል አንዱንም አለማወቃቸው እንደነበር ታስታውሳለች። በዚህም የሥነልቦና ጫና ውስጥ ገብተው እንደነበር ትገልፃለች። ይህ ደግሞ ተማሪዎች የጠበቁትን ውጤት እንዳያመጡ ማድረጉን ትጠቁማለች።
‹‹እኛም በእነርሱ ቦታ ብንሆን ይህ አይገጥመንም ብሎ ማሰብ አይቻልም›› የምትለው ተማሪ ኬና፤ ሆኖም መንግሥት ያመቻቸው ነገር ስላለ በብዙ መንገድ ችግሮቻችን ይፈታሉ የሚል እምነት እንዳላት ትገልፃለች። የዘንድሮ ተፈታኞች በብዙ ነገር ዕድለኛ እንደሆኑም አንስታ፤ ከአምናው የተማሪዎች ችግር እርሷና ጓደኞቿ ተምረው ለተሻለ ውጤት መዘጋጀት መቻላቸው አንዱ መሆኑን ትጠቅሳለች። ጥሩ ተሞክሮ ሆነውኛል ከምትላቸው መካከልም የአጠናን ዘዴ ቅድሚያ ትኩረት የምትሰጠው መሆኑን ትጠቁማለች። ከአስረኛ ክፍል ጀምሮ ያለውን ትምህርት ማንበብና ጥሩ ዝግጅት ማድረግ እንዳለባትም መረዳቷን ትገልፃለች።
በሌላው በኩል ዩኒቨርሲቲ ውስጥ መፈተን ምን እንደሚመስል እንደተማረችና ጎበዝ ለሆነና በራሱ ለሚተማመን ተማሪ ውጤታማ የመሆኛ ቦታ እንደሆነ ማወቋን ተማሪ ኬና ትናገራለች። ለዚህም ዩኒቨርሲቲዎች ተረጋግቶ ለመሥራት ምቹ ሁኔታን እንደሚፈጥሩ በምክንያትነት ታነሳለች። ‹‹እዚህ ቦታ ላይ አንድ ነገር ብቻ ማድረግን ይጠይቃል። ይህም በሥነልቦና መዘጋጀትን። እናም ተማሪዎች የራሴን እሠራለሁ፤ አቅሜን እፈትናለሁ ብለው ከሄዱ የሚገጥማቸው ነገር የለም›› ትላለች ተማሪ ኬና ከሰማችው አንጻር በመነሳት።
ከአምና ተፈታኞች ከወሰደቻቸው ልምዶች በተጨማሪ ትምህርት ቤታቸው ከሥነ-ልቦና አንጻር እንዲዘጋጁ የሚያደርጉላቸው እንክብካቤ ይበልጥ እንድትረጋጋ እንዳደረጋት የምትገልጸው ተማሪ ኬና፤ ተማሪዎች ከባለፈው የአፈታተን ሥርዓት ብዙ ልምድ ይወስዳሉ ስትል ሃሳቧን ታጋራለች። ከጉዳቱ ይልቅ ጥቅሙ እንደሚያይልም ማመን አለባቸው ትላለች። በተለይ ደግሞ ጎበዝ ተማሪዎች ምንም ዓይነት ችግር ሳይገጥማቸውና የሚያዋክባቸው ነገር ውስጥ ሳይገቡ በተረጋጋ መንፈስ ፈተናውን መሥራት መቻላቸው በምክንያትነት የሚጠቀስ መሆኑን ትናገራለች። በራስ አቅም መሥራት ምን ያህል ውጤታማ እንደሚያደርግ ያዩበታልና ተጠቀሙበት ስትል ትመክራለች።
የፈተና አወጣጡን መረዳት፣ የገባው ላልገባው ማስረዳትና እስከመጨረሻው የፈተና ጊዜ ድረስ በቡድን ማጥናት እንደሚያስፈልግም ትጠቁማለች። በትምህርት ቤት ቤተመጻሕፍት ውስጥ ማጥናት ያልተመቻቸው ተማሪዎች እንደ አብርሆት ባሉ ቤተመጻሕፍቶች ውስጥ መጠቀም እንደሚችሉም ትጠቅሳለች። እርሷም ይህንኑ እያደረገች መሆኑን ትናገራለች። ከዚህ በተጓዳኝ ወርክሺቶችን ከመጻሕፍቶች ጋር በማገናኘት፣ ሞዴል ፈተናዎችን ደጋግማ በማንበብና በመሥራት ዝግጅቷን እያካሄደች መሆኑን ትገልፃለች።
የተማሪ ኬናን ሀሳብ የሚጋራውና በዩኒቨርሲቲ መፈተን ብዙ ጥቅም እንዳለው የሚገልጸው ደግሞ ተማሪ ካሌብ ወንደሰን ነው። ተማሪ ካሌብ እንደሚለው በትምህርት ቤት መፈተን በጥንቃቄ ደረጃ ብዙ ክፍተቶች ይታዩበታል። ከዚህ ውስጥ አንዱ ‹‹የእኔ አሸናፊ ነው›› ለማለት የሚደረግ ግብግብ ሲሆን ይህም ለፈተና መሠረቅና ተማሪዎች እንዲኮራረጁ ዕድል መስጠትን ያሰፋል። በዚህም የሚገባው ቀርቶ የማይገባው ተማሪ ጭምር ዩኒቨርሲቲ ይገባል። ይህ ደግሞ ለተማሪው ብቻ ሳይሆን ለሀገርም ውድቀት ነው።
‹‹አሁን መንግሥት የወሰደው እርምጃ እጅግ ጠቃሚ ነው። ጎበዝ ተማሪዎችን ጥሏል የሚል እምነትም የለኝም። ምክንያቱም ጎበዞቹ የወደቁት አዳዲስ ነገሮች ስለገጠሟቸው ፍራቻ ውስጥ ገብተው ነው›› ይላል ተማሪ ካሌብ። የተማሩትን አልሠሩም። ይህ ደግሞ በማሻሻያ ፈተና እንደሚፈታ ያለውን እምነት ይገልፃል። ተማሪዎች እየተረጋጉ ስለመጡ አቅማቸውን እንደሚያሳዩም ይጠቁማል።
በአምናው ውጤት በጣም ፈርቶ እንደነበር የሚናገረው ተማሪ ካሌብ፤ በተለይ ውጤት ያመጣው ተማሪ ቁጥር ዝቅተኛ መሆኑን ሲሰማ በፈተናው እንዳይወድቅ ስጋት ገብቶት እንደነበር ያስታውሳል። አሁን ግን ከጓደኞቹ ልምድ ወስዶ ለፈተናው ራሱን አዘጋጅቷል።
ተማሪ ካሌብ እንደ ተማሪ ኬና ሁሉ የ12ኛ ክፍል ተፈታኝ በመሆኑ፤ ለፈተና በብዙ መልኩ እየተዘጋጀ እንደሆነ ይናገራል። በተለይም ዩኒቨርሲቲ ገብቶ ሲፈተን ምንም ዓይነት የሥነልቦና ጫና ውስጥ ላለመግባት ጥረት እያደረገ እንደሚገኝ ያስረዳል። ፍራቻ ለጥንቃቄ መልካም ቢሆንም በዚያ ውስጥ መዘፈቅና አለመሥራት ግን የበለጠ ይጥላል ብሎ ስለሚያምን አስቀድሞ ለፈተናው ዝግጅት እያደረገ ስለመሆኑም ይጠቁማል። እርሱና ጓደኞቹ በምን ዓይነት መስመር ውስጥ መጓዝና የተሻለ ውጤት ማምጣት እንዳለባቸው እየተመካከሩም እያጠኑ እንዳሉ ይጠቅሳል።
ካሌብ ‹‹ያጠና ተማሪ አያልፍም፤ ዕድል ነው›› በሚለው ሃሳብ አይስማማም። ይህ የሰነፎች መፈክር እንደሆነም ያምናል። ማንኛውም ተማሪ ራሱን ካረጋጋና በሚገባው ልክ መዘጋጀት ከቻለ ያሰበው ላይ ይደርሳል ባይ ነው። ተማሪ ስህተት ሊፈጽም የሚችለው አንድም ከሚገባው በላይ ጭንቀት ውስጥ ከገባ አለያም ደግሞ በቂ ዝግጅት ካላደረገ እንደሆነ ያስባል። የአምናው ፈተናም ከዚህ አኳያ የተፈጠረ እንደሚሆን ይገምታል።
የዘንድሮ ተፈታኞች በብዙ ነገር ዕድለኞች ነን የሚለው ተማሪ ካሌብ፤ በአዲሱ የአፈታተን ሥርዓት ተማሪዎች ራሳቸውን እንዲፈትሹ ያስችላቸዋል ይላል። በራስ አቅም ሠርቶ የሚመጣን ውጤት እንዲያዩት ዕድል እንደሚያገኙና በራስ መተማመን ማዳበር እንደሚችሉ ይገልፃል። ይህ ሲሆን ዩኒቨርሲቲ መግባት ባይችሉ እንኳን የራሳቸውን ተስፋ የሚያለመልሙበትን ዕድል ለማግኘት እንደሚጥሩ ያስረዳል።
ተማሪ ካሌብ ሶፍትዌር ያበለፅጋል። በዚህ ሥራውም ከትምህርቱ ውጪ ውጤታማ መሆን ችሏል። ትምህርትን ከሙያ ጋር አቀላቅሎ መማር ይበልጥ ውጤታማ እንደሚያደርግም ተረድቷል። በፈተና የተሻለ ውጤት አምጥቶ ኮምፒዩተር ሳይንስን ለመማር አቅዷል። ለዚህም ከአሁኑ ዝግጅት እያደረገ ነው። በሙያና በአቅም መሥራት ፈተናን ማለፍ ብቻ ሳይሆን የነገን ተስፋ ማለምለም እንደሆነም ከወዲሁ አውቋል። ተማሪዎችም ይህንን አውቀው ለፈተናው ብቻ ሳይሆን ለነገው ማንነታቸው ተጨንቀው ራሳቸውን ከወዲሁ ዝግጁ ሊያደርጉ እንደሚገባም ይመክራል።
የደጃዝማች ወንድይራድ ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር ካሱ ኩምሳ እንደሚሉት፤ በአምናው ፈተና 429 ተማሪዎችን ትምህርት ቤቱ አስፈትኗል። ሆኖም ብዙዎቹ ወደ ማሻሻያ ፈተና ገብተዋል። ከፍተኛ ውጤት ያመጡ ተማሪዎች በጣም ጥቂት ናቸው። ይህ የሚያሳየው ደግሞ ብዙ መሥራት እንደሚያስፈልግ ነው። በዚህም ዘንድሮ ሌት ተቀን ሥራዎች እየተሠሩ ይገኛሉ።
በትምህርት ቤቱ 416 ተማሪዎች በቀንና በማታ ለ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ የማጠቃለያ ፈተና እየተዘጋጁ ይገኛሉ። ዘንድሮ ከአምና የተሻለ ውጤት ይጠበቃል። ተማሪዎች በትምህርታዊ ጉዳዮች ኢንተርኔት እና ቤተመጻሕፍት እንዲጠቀሙ፣ ያላለቁ የትምህርት ይዘቶችን እንዲያጠናቅቁ በማድረግ እገዛ እየተደረገላቸው ነው። መምህራንም ሞዴል ፈተናዎችን በማዘጋጀትና ተማሪዎች እንዲለማመዱ፣ በቡድን እንዲተጋገዙ እያደረጉ ይገኛሉ። የተማሪዎችን ችግሮች በቅርበት በመከታተል አስፈላጊ የጋይዳንስ ድጋፎችም ጭምር እየተደረጉ ናቸው።
ርእሰ መምህሩ እንደሚናገሩት የዘንድሮው የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ የማጠቃለያ ፈተና ከሐምሌ 19 እስከ ሐምሌ 30 ቀን 2015 ዓ.ም እንደሚሰጥ ትምህርት ቢሮ አሳውቋል። ከትምህርት ውጪ ተወዳዳሪ ሆኖ መምጣትም መኖርም አዳጋች መሆኑ በዘርፉ የተሻለ ውጤት ለማምጣት ከምንም በላይ መሥራት ያስፈልጋል። ስለዚህ ትምህርት ቤቱ በዚህ መልኩ ዝግጅት እያደረገ ይገኛል።
የነጠረና የነቃ ተማሪ ለማፍራት የተጀመረው የአፈታተን ሥርዓት ጥሩ ነው። የተለየ አቅጣጫ መከተል እንዲቻል ትምህርት ሠጥቷል። ያልተሠሩ ሥራዎችም እንዲሠሩ አድርጓል። ቅዳሜ የትምህርት ቀን አድርጎ መሥራት መቻሉ አንዱ የአምናው ፈተና ተሞክሮ ነው። ይህ የቅዳሜ ትምህርት ደግሞ የሚሰጠው ፈተና ላይ የሚመጣውን ብቻ በመምረጥ ነው። አሁን ባለው ሁኔታ በባለሙያ ጭምር በመታገዝ ተማሪዎችን በሥነልቦና እንዲዘጋጁ የማድረግ ሥራዎችም ተያይዘው እየተሠሩ ይገኛሉ።
በክፍል ውስጥ እንደ አንድ የትምህርት ዓይነት የማይሰጠው አብቲቲውድ ክፍለጊዜ ተመድቦለት ተማሪዎች ቅዳሜ እንዲማሩት እየተደረገ ነው። ይህ ትምህርት ከሰኞ እስከ አርብ ባሉት የትምህርት ጊዜያትም አጠቃላይ የትምህርት ክፍለጊዜው ካለቀ በኋላ ለሳምንት ያህል እንዲሰጥ እየተደረገ ይገኛል።
ርእሰ መምህሩ እንደሚያብራሩት በአብዛኛው ከግንቦት በኋላ የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች የክፍል ትምህርታቸው ስለሚጠናቀቅ በትምህርት ቤት ውስጥ መገኘት አይፈልጉም። የራሳቸውን ዝግጅት ለማድረግ በፈለጋቸው ሰዓት እንጂ በቋሚነት አይመጡም። ዘንድሮ ግን ይህንን የመቀየር ሥራ ተሠርቷል። ይህም መምህራን በተለያየ መልኩ ሊያዘጋጇቸው ፈቃደኛ በመሆናቸው ፍላጎቱ ያላቸው ተማሪዎች በቋሚነት ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ ዕድል ተመቻችቷል። በዚህም ምሽት ጭምር የሚያነቡና የሚተጋገዙ ተማሪዎች ተፈጥረዋል።
ትምህርትቤቱ ሌላም ዕድል ለተማሪዎች አመቻችቷል። ይህም ሃያ አራት ሰዓት እንዲያነቡ ቤተመጻሕፍቱን ክፍት ማድረግ ነው። ለዚህ ደግሞ ወላጆች ኃላፊነቱን ወስደው የትርፍ ሰዓት ክፍያ ይከፍላሉ። ጎበዝ ተማሪዎችና የቤተመጻሕፍት ክበብ አባላትም አገልግሎቱን አቀላጥፈው በመስጠት ያግዛሉ። በተመሳሳይ በትምህርት የላቁ ተማሪዎች ደከም ያሉትን የማገዝ ተግባር እንዲያከናውኑ ምቹ ሁኔታዎች ተፈጥረዋል። ይህ ሥራ ደግሞ እስከ ሐምሌ አምስት ድረስ ቀጥሏል።
ትምህርት ቤቱ ተማሪዎች የራሳቸውን የአጠናን ዘዴ የሚያዳብሩበት መድረክም አመቻቷል። ተማሪዎች በትምህርት ቤት ብቻ ሳይሆን በቤትም እንዲያጠኑ ዕድል ፈጥሯል። ይህም በኦንላይን ትምህርት የመስጠት ስልት ነው። እናም በዚህ ዝግጅታቸው ተማሪዎች በዘንድሮው የከፍተኛ ትምህርት ማለፊያ ፈተና ጥሩ ውጤት ያገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል። ከዚህ ጋር ተያይዞም ለተማሪዎች በተለይ ኩረጃን ተስፋ አድርገው መንቀሳቀስን ከአሁኑ ሊያቆሙ ይገባል። ትምህርት ቤቶች በተቻላቸው ሁሉ እየለፉላቸው በመሆኑ ያንን በመገንዘብ ለውጤታማነታቸው መትጋት ይጠበቅባቸዋል።
ለሁለተኛ ጊዜ በዩኒቨርሲቲዎች የሚካሄደው የዘንድሮው ሀገር አቀፍ የማጠቃለያ ፈተና በትምህርት ይዘት እና በሥነ-ልቦናም ዝግጅት እየተደረገ እንደሆነ የትምህርት ሚኒስቴር መግለፁ የሚታወስ ሲሆን፤ ሀገር አቀፍ የትምህርት ምዘና እና ፈተናዎች ኤጀንሲ በቅድመ ዝግጅት ሥራው እስከአሁን 869 ሺህ 765 የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች ሀገር አቀፍ የማጠቃለያ ፈተናውን ለመውሰድ በበይነመረብ እንደተመዘገቡ አስታውቋል። ከነዚህ ውስጥ 503 ሺህ 812 ተማሪዎች የሶሻል ሳይንስ፤ 365 ሺህ 954 የተፈጥሮ ሳይንስ ተፈታኞች መሆናቸውን ጠቁሟል። ተፈታኝ ተማሪዎች በትምህርት ይዘት እና በሥነልቦና ዝግጁ እንዲሆኑ ለክልሎች መመሪያ መውረዱንም አመልክቷል።
ጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን ሐምሌ 10/2015