ቃልን በተግባር

ሐምሌ 10 ቀን 2015 ዓ.ም እለተ ሰኞ ኢትዮጵያውያን በጋራ ታሪክ የሠሩበት፤ ቃል ተግባር ሆኖ በዓለም ታሪክ 500 ሚሊዮን ችግኞችን በአንድ ጀንበር በመትከል የቀደመውን የይቻላል መንፈስ የአደሱበት፤ አረንጓዴ አሻራ ሀገራዊ ግለት ከፍ ያለ ደረጃ ላይ የደረሰበት ቀን ሆኖ በታሪክ ውስጥ ልዩ ስፍራ አግኝቶ አልፏል።

መላው ሕዝብ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን (ዶ/ር) ጥሪ ተከትሎ ጀምበር ወጥታ እስክትገባ 500 ሚሊዮን ችግኞችን ለመትከል የተያዘው እቅድ በአንድነት ከቆሙ ታሪክ መሥራት በለመዱ እጆች እውን አድርጓል። እንደ ሀገር ካለፈው ጊዜ በልጠንና ከፍ ብለን በዓለም አደባባይ መሰማት ችለናል ።

ቃል ወደተግባር ተቀይሮ እንዳለፈው ጊዜ ዘንድሮም፤ የተጨማሪ ታሪክ ባለቤት ሆነናል። ሀገርን ባስቀደመ፣ ትውልድን ታሳቢ ባደረገ፤ የኢትዮጵያን መጻኢ እድል ባንጸባረቀ መንገድ ሕዝቡ በነቂስ ወጥቶ በአረንጓዴ ልማት ንቅናቄ ላይ ብሔራዊ አሻራውን አሳርፏል።

በእለቱ ‹ነገን ዛሬ እንትከል› በሚል ተራማጅ እሳቤ ሁሉንም የማኅበረሰብ ክፍል ባሳተፈና የያገባኛል ስሜትን ባሰረጸ መልኩ በጎ እንቅስቃሴ ተደርጓል። ኢትዮጵያዊነትን ባስቀደመ፣ ከፖለቲካና ከእኔነት በፀዳ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያውያንን ከፍ ያደረግንበት ንቅናቄ ነበር። ቃላችንን ወደተግባር ቀይረን በንቃት እና በብቃት እንደምንችል ያሳየንበት ሌላው ደማቅ ታሪካችን ሆኖ አልፏል።

በመጀመሪያ ዙር በአረንጓዴ እሳቤ የተቃኙት ያለፉት አራት ዓመታት በኢትዮጵያ የሥነምሕዳር ታሪክ ውስጥ ከፊት የሚሰለፉ ናቸው። የሀገራችንን የወደፊት ዕጣ ፈንታ ይወስናሉ የተባሉት ችግኞች አድገው የሚፈለገውን ጥቅምና ግልጋሎት እየሰጡ እንደሆነ በተለያየ ጊዜ ምስክርነት ተሰጥቷል። ከአካባቢ ጥበቃ ጎን ለጎን የማኅበረሰቡ የምግብ ዋስትና በመሆን ጉልህ ድርሻ በማበርከት ይሁንታን ተችሯቸዋል።

ባለፉት አራት ዓመታት ውስጥ ሀገራችን ኢትዮጵያ ለታሪክ በተሰናዱ እጆች 25 ቢሊዮን ችግኞችን በመትከል በድል አጠናቃለች። በዚህ ሂደት ውስጥ ከአካባቢ ጋር ተያይዞ ብዙ ለውጦች መጥተዋል፤ በቀጣይ በሥነምሕዳር እና በአካባቢ ልማት የጎላ ድርሻ እንደሚኖራቸው መነሻቸው ጥቁምታ ሰጥቷል።

ሁለተኛው እና ‹ነገን ዛሬ እንትከል› በሚል መሪ ቃል በአፋር ክልል ጅማሮውን ያደረገው 6.5 ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከል እቅድ የተያዘለት በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) መሪነት ሰኔ 1 ቀን 2015 ዓ.ም የተጀመረው የአረንጓዴ ልማት መርሐ ግብር 3.4 ቢሊዮን ችግኞች በመትከል እንቅስቃሴውን ጀምሯል። የዚህ ንቅናቄ አንድ አካል የሆነው የሐምሌ አስሩ የእለተ ሰኞው ሕዝባዊ ተሳትፎ በአንድ ጀምበር 500 ሚሊዮን ችግኞችን በመትከል ታሪካዊ ድልን አስመዝግቧል። እንደምንችል ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያውያን በአንድነት እና በጋራ ከተነሱ የሚያቆማቸው ኃይል እንደሌለ ያየንበት ነበር።

ይሄን እውነታ በማስመልከት ከሰሞኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው መልዕክት አስተላልፈው ነበር። ‹ፉክክራችን ከራሳችን ጋር ነው። እያንዳንዳችን የራሳችንን ሪከርድ መስበር አለብን፣ ችግር የራሱን ሪከርድ እንዲሰብር ልንፈቅድለት አይገባም። ችግር የራሱን ሪከርድ ከሰበረ ተሸንፈናል ማለት ነው› ብለው ነበር።

እንደተባለውም ከራሳችን ጋር ተፎካክረን የራሳችንን ሪከርድ በመስበር አዲስ ሀገራዊ ድልን አስመዝግበናል። በአንድነት ስለቆምን ችግር የራሱን ሪከርድ አልሰበረም። በጋራ ስለተራመድን ሽንፈት ወደቤታችን አልገባም። ለዓለም ቅርብ የሆነ እውነት ቢኖር ድሎች የሚመጡት ከአንድነት ሀሳብና ከሕዝባዊ ተሳትፎ ቀጥሎ ነው የሚለው እውነት ነው።

እንደሀገር በምናስበውም ሆነ በምናልመው ሕልም ውስጥ አንድነት እና ሕዝባዊነት ካለ የታሪክ ባለቤት ከመሆን የሚያግደን አይኖርም። ሕልሞቻችን አንድነትን ከለበሱ እንደዓድዋና እንደህዳሴ ግድብ አሁን ደግሞ እንደአረንጓዴ አሻራ ዓለም አቀፍ መደነቅን ነው የሚፈጥሩልን።

አንድነትን ያለበሰ ሕልምና ምኞት መነሻ እንጂ መድረሻ የለውም። ሕልሞቻችን ውስጥ ሩቅ የሚወስድ ከብሔር የጸዳ፣ ከእኔነት የራቀ የኢትዮጵያዊነት መንፈስ ያስፈልገናል። ድህነት እና ማጣት ሪከርድ ሰብረው በኋላቀርነት ያቆሙን አንድነት የዋጀው የጋራ እውነት ስላጣን ነው። ዛሬ ዛሬ ዘረኝነት እና ራስ ወዳድነት አሸናፊ ሆነው ለዝቅታ የጣሉን ኢትዮጵያዊ ቀለማችንን ስላደበዘዝን ነው። ባለፉት አራት ዓመታት ውስጥ ዓለምን ያስደነቁ የአረንጓዴ አሻራ ንቅናቄዎች ችግሮቻችን ላይ ቢደገሙ እንደ አረንጓዴ አሻራ ዓለም በክብር ስማችንን ለመጥራት በቻለ ነበር።

እንደሀገር የተጋረጡብን ፖለቲካዊም ሆኑ ሌሎች ችግሮች እንደአረንጓዴ አሻራ የአንድነት ሀሳብ ይሻሉ። በዓለም አደባባይ ስማችን በክብር የተነሳባቸው አጋጣሚዎች ሕዝባዊ ቀለም ያላቸው ናቸው። ጽንፍ በወጣ የብሔር እሳቤ እና በእኔነት ተጉዘን የጋራ ታሪክ መሥራት አንችልም። የኢትዮጵያ ከፍታ ያለው፣ የትውልድ እውነት ያለው በጋራ በመቆም ውስጥ ነው። በአረንጓዴ ልማት ከአፍሪካ አልፈን ወንዝ የተሻገርነው ኢትዮጵያን ስላስቀደምን ነው። ላሉብን ዘርፈ ብዙ ችግሮች ትልቁ መፍትሔም ኢትዮጵያ የቀደመችበት የንግግርና የውይይት መድረክ ነው።

በአንድነት ለቆመ ማኅበረሰብ ለውጥ የትም አለ። ታሪክ ስፍራው አንድነት ውስጥ ነው። ይሄን እውነት አስመልክቶ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ያጋሩትን መልዕክት ማስታወስ ያሻል፣ ‹ችግርን የምናሸንፈው መጀመሪያ የራሳችንን፣ ቀጥሎ የአካባቢያችንን ፣በመጨረሻም የዓለምን ሪከርድ ስንሰብር ነው› ።

በአንድነት ተነስተን የራሳችንን ሪከርድ ሰብረን፣ እንደሀገር ደምቀን ዓለም አቀፍ እውቅና አግኝተናል። እነኚህ ሁሉ ደማቅ ስሞች በአንድነት የተማጡ የጋራ መጠሪያዎች ናቸው። አንደ ሀገር ደማቅ ስም ለመጻፍ ኢትዮጵያዊነት የቀደመበት ሀሳብና ተግባር፣ ሙግትና ውይይት ያስፈልገናል። ከአረንጓዴ አሻራ ሀሳብ እና ንቅናቄ ብዙ መማር እንችላለን። እንዴት መጣ? እንዴትስ ዓለም አቀፍ እውቅናና ክብር ተቸረው? ብለን ስንጠይቅ አንድ እውነት ብቻ ነው የምናገኘው። መነሻ ሀሳቡ ኢትዮጵያዊነት ነው መድረሻው ደግሞ እንዳየነው አንድነት ነው።

በአጭር ጊዜ ውስጥ ለዛውም በብዙ ተግዳሮት ውስጥ ሆነን ይሄን ያክል ለውጥ ማምጣት ከቻልን ችግሮቻችንን በቁጥጥራችን ስር የማናደርግበት ምንም ምክንያት እንደሌለ አመላካች ነው። ነውረኛ ታሪኮቻችንን አድሰን በአዲስ ስም ለመቆም ቅድሚያ ለሀገር የሚል አመለካከት ያሻናል። ሀገራችንን ባስቀደምን ቁጥር እርባና ቢስ ጽንፈኛ አስተሳሰቦች ከአሰብንበት እንዳንደርስ አያስቆሙንም ።

በኢትዮጵያ ስም ብዙ ሆነን ብዙ ችግኞችን ተክለናል። በኢትዮጵያ ስም አንድ ሆነን የአንድነት ታሪክ ጽፈናል። በወንድማማችነት ከቆምን ብዙኃነታችን እና ኅብረብሔራዊነታችን የምንፈልጋትን ሀገር ለመፍጠር ከበቂ በላይ ነው። ዕድሎቻችንን የደበቅናቸው ራሳችን ነን። የማደግና የመለወጥ ጸጋችን በእኛ መልካም ፍቃድ ውስጥ ነው።

በአንድነት ከቆምን ብዙ ነን። ተያይዘንና ተደጋግፈን ከተነሳን ሩቅ የሚወስድ ኃይል አለን። ይሄን እውነት ለማረጋገጥ ደግሞ ባለፉት አራት ዓመታት ውስጥ በአንድነት ተክለን በአንድነት ያፀደቅናቸውንና ዓለም አቀፍ አድናቆት ያገኘንባቸውን የአረንጓዴ አሻራ ንቅናቄ ማየቱ በቂ ነው።

በአንድ ጀምበር 500 ሚሊዮን ችግኝ መትከል አንድነት ከመሆን ሌላ ስም የለውም። እስኪ ይሄን ክብርና ሞገስ በመለያየት ውስጥ ቆማችሁ አስቡት..ምንም ነው ፤ አይደል? እውነት ነው ምንም ነው። ክብር የሰጠን አንድነታችን ነው። ፊተኝነትን ያጎናጸፈን አብሮነታችን ነው። የአረንጓዴ እሳቤ አዲሲቷን ኢትዮጵያ ለመፍጠር ጥሩ መነሻ ጥሩ ንቃት ነው። ራሳችንን አድሰን የታደሰች ሀገር ለመፍጠር ከመነሻነት አልፎ እንደመድረሻ ሊያገለግለን የሚችል ጽንሰ ሀሳብ ነው። ጀምረን በውብ ፍጻሜ ጨርሰናል። አስበን በውብ ንቅናቄ ቋጭተናል። ቃላችን ወደተግባር ያልተቀየረበት አጋጣሚ አልነበረም..ለምን ካልን አንድ ነበርን ።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ብሔራዊ ኩራታችን እየሆኑ ከመጡ ንቅናቄዎች ውስጥ አንዱ የአረንጓዴ አሻራ ፕሮግራም እንደሆነ ይታወቃል። ባለፉት ዓመታት ውስጥ በአየር ንብረት ለውጥ ላይ እያሳየነው ባለው ሕዝባዊ ንቅናቄ ለብዙዎች መነሻና መደነቂያ መሆናችን ይታወሳል። ከዓለም ቀዳሚ ከመሆን ባለፈ ስምና ክብር፣ ሙገሳና አድናቆት ያገኘንበት ክስተት ነበር።

ካለፈውና ዘንድሮ ከተገበርነው ሕዝባዊ እውነታ በመነሳት ሀገራችን ምን እንደሚበጃት መረዳት አይከብደንም። የሚበጀን በአንድ ጀምበር እልፍ ችግኞችን እንዲተከሉ እጆች በጋራ መቆም ነው። የሚበጀን ኢትዮጵያን የጉዳያችን አንደኛ አድርገን ወደፊት መራመድ ነው። እንደ ሀገር ብዙ ፀጋና በረከት አለን። ተፈጥሮ ለእኛ አድልታ በብዙ ባርካናለች። ይሄ ዕድል ዋጋ አውጥቶ እድገት እና ብልጽግናን የሚሰጠን ኢትዮጵያ በሚል የብዙኃን ስም ሲታጀብ ነው።

በጎ በሆነ፣ ከራሳችን አልፎ ለሌሎች በሚተርፍ ሀሳብ እና ንቅናቄ ከትላንት ወደዛሬ መጥተን ብዙ ለውጦችን እያየን ነው። ዓለም መልስ ላጣለት የአየር ንብረት ለውጥ የበኩላችንን በማድረግ ጽናታችንን አሳይተናል። ልክ እንደዛሬው ሁሉ መጪውም ጊዜ ይሄን በመሰለው ሕዝባዊ ንቅናቄ በድል ላይ ድል እንደሚሆን ካየነው እውነታ መረዳት ይቻላል።

ሀገራችን የሚያስፈልጋት ለውጥና አድናቆት እያገኘንበት እንዳለው የአረንጓዴ አሻራ ንቅናቄ አንድነት የታከለበት ኢትዮጵያዊነት ነው። በአንድነት ቆመን ዓለምን አስደንቀናል። በአንድነት ተነስተን ለብዙዎች መደነቂያ ሆነናል። ልክ እንደዚህ እንደሀገር የተፈጠሩብንን ችግሮችም በአንድነት በመቆም መመከት ልንማረው የሚገባ ትልቁ ቁም ነገር ነው።

አረንጓዴ አሻራ ከችግኝ መትከል ባለፈ ብዙ እውነታዎችን የገለጠልን ክስተት ነው። ታሪክ የሠራንባቸውን ዘመኖች መለስ ብለን ብናይ በአንድነት የቆምንባቸው ሆነው እናገኛቸዋለን። በተቃራኒው ያለው እውነታም ተቃራኒውን የሚመስል ነው። በየትኛውም መመዘኛ ቢታይ አረንጓዴ አሻራ አንድ ትርጓሜ ነው ያለው፣ እርሱም ኢትዮጵያን የመጠበቅ፣ የማክበር እና የማበልጸግ ጉዳይ ነው። በጋራ የተነሳነውም ይሄ እውነት ስለገባን ነው። ሌሎች አንድነት ያጣንባቸው እንዲገቡን የሚያስፈልጉ እውነታዎችም አሉ።

በአንድነት ቆመን ይሄን ያክል የድል እና የክብር ስምን ከተቀዳጀን በመለያየት ያባከናቸው ጊዜያቶች ሊቆጩን ይገባል። በአንድነት እጅ ጀምበር ወጥታ እስክትገባ ዓለምን ማስደነቅ ከቻልን ጀምበር ወጥታ እስክትገባ መከራ ያሳዩንን ችግሮቻችንንም በቁጥጥራችን ስር ማድረግ እንደምንችል ምልክት የሰጠን ንቅናቄ ነው።

የአረንጓዴ አሻራ እሳቤ በኢትዮጵያዊነት ጀምሮ በኢትዮጵያዊነት የሚያበቃ ነው። መነሻውና መድረሻው ሀገርና ሕዝብ ትውልድም ነው። ከዚህ ውጪ ምንም ሊሆን የማይችል ነው። የኢትዮጵያ ጉዳይ በሆነው በዚህ ብሔራዊ ንቅናቄ ላይ እንዳለፈው ጊዜ ድል ቀንቶን በድል ተመልሰናል። የሚቀረን ድህነት ነው። የሚቀረን በጋራ ችግሮቻችን ላይ መዝመት ነው። አረንጓዴ አሻራ የሀገር ቡልኮ ነው። ገላችን እንዳይበርደው የላመ እና የጣመ እንደምንበላውና የወፈረ እንደምንለብሰው ሀገርም እንዳይበርዳት አረንጓዴ አስተሳሰብ ያሻታል። አረንጓዴ አሻራ የሀገር ልብስ ነው። ደስታና የአዕምሮ ሰላም መነሻቸው ከሀገር አረንጓዴ ልብስ ውስጥ ነው።

በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)

አዲስ ዘመን ማክሰኞ ሐምሌ 11 ቀን 2015 ዓ.ም

Recommended For You

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *