‹‹አረንጓዴ ዐሻራ እንደ ሀገር የሚያግባባ አጀንዳ የሰጠን መርሃግብር ነው›› ዶክተር ተሻለ ወልደአማኑኤል በደቡብ ክልል የሬድ ፕላስ ፕሮጀክት አስተባባሪ

ዛሬ ኢትዮጵያ በአንድ ጀምበር 500 ሚሊዮን ችግኝ ለመትከል ተፍ ተፍ የምትልበት ዕለት ነው። በዚህ ዕለት ሁሉም ዐሻራውን ሊያኖር ይተጋል። ምክንያቱም የሰው ልጅ የተቸረውን የተፈጥሮ ሀብት በአግባቡ የመጠቀምና የማበልጸግ መብቱ ያለው በገዛ እጁ ነውና ተፈጥሮን ሲንከባከብ ተጠቃሚ ይሆናል፤ ሥርዓቱን ሲያዛባ ደግሞ የገፈቱ የመጀመሪያ ቀማሽ ለመሆን ይገደዳል። ይህ እንዳይሆን በኢትዮጵያ በርካታ ተግባራት በመከናወን ላይ ይገኛሉ። በተለይም ካለፉት አራት ዓመታት ጀምሮ የ‹‹አረንጓዴ ዐሻራ›› በሚል እያንዳንዱ የራሱን ዐሻራ እንዲያኖር የተጀመረው መርሃግብር ውጤታማ ከመሆን አልፎ በሌሎች ሀገራት ጭምር እውቅና እየተሰጠው ያለ ተግባር ሆኗል።

ይህ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃግብር በኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ሐሳብ አመንጪነት ይፋ የተደረገ ነው። መርሃግብሩ ጅማሬውን ያደረገው በ2011 ዓ.ም ሲሆን፣ ከ2011 እስከ 2014 መጨረሻ ድረስ ባሉት አራት አመታት ወደ 25 ቢሊዮን ችግኝ መተከሉ ይታወቃል። ከዚህ ጋር ተያይዞ አዲስ ዘመን የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃግብር ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ፋይዳው ምንድን ነው? የተተከሉ ችግኞችንስ ከመንከባከብ አኳያ ምን መደረግ አለበት? የሚሉትንና ሌሎች ጥያቄዎችን በማካተት በደቡብ ክልል የሬድ ፕላስ ፕሮጀክት አስተባባሪ ከሆኑት ዶክተር ተሻለ ወልደአማኤል ጋር ያደረገውን ቃለ ምልልስ እንደሚከተለው አሰናድቶ አቅርቧል።

 አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያ የዛሬውን ሳይጨምር በመጀመሪያው ዙር ወደ 25 ቢሊዮን ችግኝ ተክላለች፤ ዛሬ ደግሞ በአንድ ጀምበር 500 ሚሊዮን ለመትከል ተሰናድታለችና ይህን እንዴት ያዩታል?

ዶክተር ተሻለ፡- ኢትዮጵያ በተፈጥሮ የታደለች ሀገር እንደመሆኗ በታሪክ እንደምናውቀው የደን ሽፋኗ ከፍ ያለ መሆኑን ነው። ነገር ግን ባለፉት አምስት እና አስር ዓመታት የደን ሽፋኗ በጣም ተመናምኖ ከፍ ያለ ችግር ውስጥ ገብተን እንደነበር አይካድም። ቀደም ሲል ድርቅ ይከሰትና ይጎበኝን የነበረው በየአስር ዓመቱ ነበር። አሁን ግን በየዓመቱ ይከሰት ጀምሯል። ወንዞቻችንን ብንመለከት ቀድሞ የነበራቸውን ሙላት ይዘው ሲቀጥሉ አይስተዋሉም፤ አልፎ ተርፎ እየደረቁ ነው።

ይሁንና ከቅርብ ጊዜ ጀምሮ እየተካሄደ ያለው እንቅስቃሴ የተሻለ ነው። በእርግጥ አሁን ኢትዮጵያ የተያያዘችው የችግኝ ተከላ መርሃግብር በተለያዩ አካላት በተለያየ ጊዜ ተሞክሯል። ነገር ግን የአሁኑን ለየት የሚያደርገው ሀገራዊ አጀንዳ ሆኖ በሀገር መሪ ደረጃ ሃሳቡ መጥቶ መተግበር መጀመሩ ነው። ይህ ደግሞ ሁሉንም የማኅበረሰብ ክፍል ማሳተፍ የቻለ በመሆኑ ከቀደሙት ሁሉ ይለየዋል።

ቀደም ሲል ይህን መሰል ሥራ ይሠራ የነበረው በአዋጅ በተቋቋመ በአንድ ሴክተር ደረጃ ነበር። ምክንያቱም በኢትዮጵያ ያሉ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች እያንዳንዳቸው የቆሞሉት ዓላማና በአዋጅ የተሰጣቸው ሥልጣንና ተግባር አለ፤ በዚህ መሠረት ሲሠሩ ቆይተዋል። ይህ የተፈጥሮ ሀብት ሥራ ግን በሀገር አቀፍ ደረጃ በአንድ ሀገር መሪ መጀመሩና በንቅናቄ መሠራቱ አንደኛ የተሰጠውን ትልቅ ትኩረት የሚያሳይ እንደመሆኑ ትልቅ ነገር ነው። ከዚህም የተነሳ የአሁኑን ልዩ ያደርገዋል። በመሆኑም ለዚህ ሥራ ያልተንቀሳቀሰ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤትም ሆነ ተቋም የለም። ጉዳዩ የዜጎች ሆኗል።

በቁጥርም ብዙ ችግኞች ተተክለዋል። ይህ ከብዛቱና ከንቅናቄው አኳያ ሲታይ በጣም የተለየ ያደርገዋል። ምክንያቱም እስከ ዛሬ ድረስ እኛ እንደ ባለሙያ አጥተነው የነበረ ነገር ቢኖር የተፈጥሮ ሀብት ሥራን የሁሉም የማድረግ ጉዳይን ነበር። ምክንያቱም ሥራው የአንድ መሥሪያ ቤት ሥራ ብቻ ሊሆን አይችልም፤ በአንድ መሥሪያ ቤት ሊተባበር ይችላል። ነገር ግን ዜጎች ካልተንከባከቡ እና ለሥራው ተቆርቋሪ ካልሆኑ ብዙ ርቀት መሄድ አይቻልም። ስለዚህም አሁን እየተተገበረ ያለው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃግብር የአንድ ሀገር ዜጎችን በጥምረት ያንቀሳቀሰ ነው ማለት ይቻላል።

አዲስ ዘመን፡- በአረንጓዴ ዐሻራ መርሃግብር ዛሬ የሚተከለውን 500 ሚሊዮን ችግኝ ሳይጨምር ባለፉት አራት አመታት 25 ቢሊዮን ችግኝ ተተክሏል፤ ይህ ከማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳው አኳያ እንዴት ይገለጻል?

ዶክተር ተሻለ፡- ከማኅበራዊ አኳያ ያለውን ፋይዳ ላስቀድም፤ የሰው ልጅ ከተፈጥሮ ጋር ጥልቅ የሆነ ቁርኝት አለው። ይህን ጥልቅ ቁርኝት ያገኘው ከራሱ ከተፈጥሮ ቢሆንም የተገባውን ያህል እንክብካቤ አላደረገለትም። ይልቁኑ ተፈጥሮን ከሚባለው በላይ ሲጎዳው ተስተውሏል። የሰው ልጅ ከተፈጥሮ በርካታ ነገሮችን ይማራል፤ በተለይም ምርምሩም ግኝቱም በተፈጥሮ ላይ ያጠነጠኑ ናቸው። የፈጠራ ሥራውንም ቢሆን በተፈጥሮ በተቸረው መሠረት ያገኘው ነው። ሌላው ቀርቶ የሰው ልጅ ለተለያዩ የፈጠራ ሥራዎቹ የሚያወጣው ዲዛይን ሁሉ ተፈጥሮን መሠረት ያደረገ ነው። በመሆኑም ተፈጥሮ ለብዙ ነገሩ ምንጭ ነው። ሆኖም በትክክል አልተጠቀመበትም።

በእኛ ሀገር በሰው ልጅ እና በተፈጥሮ መካከል ያለው መስተጋብር እየላላ የሄደ ስለሆነ ይህ የተጀመረው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃግብር ያንን የጠፋውን የተፈጥሮ መስተጋብር መልሶ ለማምጣት ትልቅ ድልድይ ነው የሚል እምነት አለኝ።

ይህ ካልሆነ ግን ሰዎች አካባቢያቸው እየተራቆተ ስለሆነ ባህላቸውን፣ ሃማኖታቸውንና እሴታቸውን ባዳበሩበት ቦታ መኖር አይችሉም፤ አካባቢያቸውን ጥለው ወደ ሌላ ቦታ ይሰደዳሉ። ይኖሩበት የነበረበት አካባቢ ከአካባቢው መራቆትና መሰል ምክንያቶች መኖር ስላልቻሉ የተሻለ ነው ብለው ወደሚያስቡበት ይሰደዳሉ።

ለምሳሌ ዘንድሮ በቦረና የተከሰተውን ድርቅ በምንወስድበት ጊዜ ተፈጥሮው በመዛባቱ የተከሰተ ነው። ስለዚህ የአረንጓዴ ዐሻራ ላይ የምንሠራው ሥራ የተፈጥሮን ሚዛን ያስተካክላል። ይህን በማድረጉ ደግሞ ማኅበራዊ፣ ባህላዊና ሌሎች መስተጋብሮች የተስተካከሉ ይሆናሉ። ከዚህ አኳያ ስደትን መቀነስ ይቻላል። ንብረት በተፈጥሮ አደጋ እንዳይጎዳ ያግዛል። አካባቢን ጥሎ መሰደድ አይኖርም። በመሆኑም ማኅበራዊ ግንኙነትም ሆነ ባህል አይስተጓጎልም። በዚህ በአረንጓዴ ዐሻራ ጤናማ የሚሆነው የሰው ልጅ የሚኖርበት አካባቢ ብቻ ሳይሆን የእንስሳቱ፣ የእጽዋቱና የአዕዋፉም ጭምር ነው።

ከኢኮኖሚው አኳያ ደግሞ ፋይዳው ሁለት ዋና ዋና ነገሮችን የያዘ ነው። አንደኛ በአረንጓዴ ዐሻራ ላይ ከምንሠራው ሥራ የምናገኘው ጥቅም ቀጥተኛ የሆነ ሲሆን፣ ሁለተኛው ጥቅም ደግሞ በተዘዋዋሪ የሚገኝ ነው።

ችግኞች ሲተከሉ የደን ሽፋን ከመጨመራቸው በተጨማሪ ለተለያዩ አገልግሎቶች ይውላሉ። ለምሳሌ ከተተከሉትም ሆነ ከሚተከሉት የችግኝ ዓይነቶች መካከል ለጣውላ እንዲሁም ለፍራፍሬ ዛፍነት የሚያገለገሉ ይሆናሉ። እንዲያ ሲሆን ከምርታቸው ላቅ ያለ ጥቅም ማግኘት ይቻላል።

ለምሳሌ ኢትዮጵያ በአብዛኛው ጣውላ የምታስገባው ከውጭ ሀገር ነው። ስለዚህ የችግኝ በስፋት መተከል ከውጭ ሀገር በውጭ ምንዛሬ የሚገባውን ጣውላ ያስቀርልናል። በተጨማሪም ለሀገር ውስጥ የኮንስትራክሽን ሥራ የዛፍ ውጤቶችን በስፋት ስለምንጠቀም ለዚያ ግብዓት ይውላል።

በአሁኑ ወቅት አንዲት አጣና የምትሸጠው ከመቶ ብር በላይ ነው። ሌሎችም ለተለያየ ግብዓት የምንፈልጋቸው የእንጨት ዓይነቶች በብዙ መቶ ብር የሚሸጡ ናቸው። ስለዚህም በዚህ ረገድ ችግኞችን በስፋት መትከልና ውጤታማ መሆን ቀጥታ የሆነ ጥቅም እንድናገኝ ይረዳናል ማለት ነው።

ሁለተኛውና ትልቁ ጉዳይ ደግሞ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃግብር በአግባቡ እንዲሳለጥ ማድረግ በተዘዋዋሪ መንገድ ለኢኮኖሚው ያለው ፋይዳ ከፍ ያለ እንዲሆን ያደርጋል። በአረንጓዴ ዐሻራ አካባቢያችንን ደን ስናለብስ የተፈጥሮ ሥነ ምህዳሩ ይስተካከላል። ብዝሃነትንም ይጨምራል። ዛፉ፣ ሳሩ፣ ወፉና ነፍሳቱ ሁሉ በተስተካከለ ሥነ ምህዳር መኖር ይጀምራሉ። የተረጋጋ ሥነ ምህዳር ሲኖር ደግሞ ሁሉም በስፍራው መኖር ይጀምራል። የእነርሱ መኖር አካባቢውን የተረጋጋ እንዲሆን ያደርገዋል። እነርሱ ኖሩ ማለት ምርታማነት ይጨምራል ማለት ነው።

ምርታማነት የሚጨምረው እንዴት ነው? ከተባለ ደግሞ እኛ ብዙ ጊዜ የምናስበው ምርታማነት የሚጨምረው ምርጥ ዘርና የአፈር ማዳበሪያ ስናቀርብ ብቻ ነው የሚል አተያይ አለን። ነገር ግን ይህ አንዱ ምክንያት ብቻ ነው። ይህ ብቻውን ግን ምርታማነትን አይጨምርም። በተለይም ወደ እርሻው ዘርፍ ስንወስደው የዘራናቸውና የተከልናቸው አብበው የአበባው ዱቄት ዘር (Pollen) ይሆናል። ይህ ደግሞ ወደ ፍሬ ይቀየራል። እኛ የምናየው ደግሞ ፍሬውን ነው እንጂ እንዴት መጣ የሚለውን አይደለም።

‹‹ፖሊኔሽን››ን በተመለከተ በዓለም ላይ ያሉ ጥናቶች የሚያሳዩን፤ በዓለም ላይ ካሉ የአዝዕርት ዓይነቶች ውስጥ 85 ከመቶ በላይ የሚሆኑት ‹‹ፖሊኔሽን›› የሚያካሂዱት በነፍሳትና በአዕዋፍ ነው። እኔን ጨምሮ ብዙዎቻችን የሚመስለን በንፋስ ነው፤ ነገር ግን አይደለም። ግን ይህን አንድም ቀን እንደ ባለሙያም እንደ ፖሊሲ አዘጋጅም አስበን አናውቅም።

እኔ ግቢ ውስጥ የፍራፍሬ ዓይነቶች አሉ። በሚገርም ሁኔታ ዛፉን እስከሚሸፍኑ ድረስ ያብባሉ። ነገር ግን ከእነዚያ ውስጥ ወደ ፍራፍሬ የሚቀየረው ጥቂቱ ብቻ ነው። ይህ የሆነው በብዙ ምክንያት ነው። አንደኛው ደን ስለወደመና የተፈጥሮ ሚዛኑ ስለተዛባ የተለያዩ ዓይነት ነፍሳት አሁን የሉም። ነፍሳቱ ኖረው 85 ከመቶ የሚሆነው የዕፀዋት ዝርያን ‹‹ፖሊኔት›› እንዲያደርጉ የተረጋጋ የተፈጥሮ አካባቢ ያስፈልጋል። እነርሱ ግን አሁን እንደ ልብ የሉም። ስለዚህ ‹‹ፖሊኔሽን›› ከሌለ ማዳበሪያም ሆነ ምርጥ ዘር ብናቀርብ ምንም ትርጉም የለውም። ምክንያቱም ተፈጥሯዊ ሥርዓቱ ተዛብቷል። ምርታማነት እየቀነሰ ያለው የተፈጥሮ አካባቢና ሥነ ምህዳሩ ስለተጎዳ ነው። ብዝሃነት ያለው አካባቢ ጠንካራ፣ የተረጋጋ፣ ምርታማና ቀጣይነት ያለው ነው።

ስለዚህ አሁን የሚከናወነው የአረንጓዴ ዐሻራ ብዝሃነትን ይጨምራል። የእንስሳትና የዕፅዋት ብዝሃነት ይኖራል። ስለዚህ ብዝሃነት ያለው አካባቢ እንዳልኩሽ ጠንካራ፣ የተረጋጋ፣ ምርታማና የተፈጥሮ አደጋን መቋቋም የሚችል ይሆናል። ከዚህ የተነሳ በተዘዋዋሪም ሆነ በቀጥታ ከተተከሉ ዛፎች ጥቅም እናገኛለን።

በአሁኑ ወቅት በአረንጓዴ ዐሻራ የፍራፍሬ ችግኝ በስፋት ይተከላል። በሌላ በኩል ደግሞ እኛ ሀገር ሦስት ወይም አራት ፍሬ ብቻ የሚይዘው አንድ ኪሎ ማንጎ የምንገዛው በጣም ውድ በሆነ ተመን ነው። በሌላ መልኩ ደግሞ ‹‹ጁስ›› ከግብጽ እናመጣለን። ነገር ግን ኢትዮጵያ ከሞቃታማው ዳሉል እስከ ቀዝቃዛማው ዳሽን ያለው ተፈጥሮዋ የትኛውንም የፍራፍር ዓይነት ማብቀል የሚያስችላት ናት። የአየር ንብረቱም ሆነ የመልካምድር አቀማመጡ ምቹ ነው።

ኢትዮጵያ አንዱ የታደለችበት ነገር ቢኖር የተለያየ የአየር ጸባይና የመልካምድር አቀማመጥ ያላት መሆኑ ነው። በየተወሰነ ርቀት ቆላውን፣ ደጋውን፣ ወይና ደጋውን፣ ውርጩን፣ ሞቀቱን ሁሉ የምናገኝባት ሀገር ናት። የዳሎልም የዳሽንም ባለቤት መሆኗ በራሱ ትልቅ ሀብት ነው። በእርግጥም ኢትዮጵያ ማለት ለእኔ የዓለም መልካምድርና የዓለም የአየር ንብረት በሙሉ ያለባት ሀገር ናት።

ይሁንና በቀላሉ ማምረት የምንችላቸውን የፍራፍሬ ዓይነቶች ሁሉ የምናስገባው ከውጭ ሀገር መሆኑ ደግሞ የሚያስቆጭ ነው። ብናመርት እንኳ በገበያ ላይ የሚታየው ለአንድና ለሁለት ወር ያውም ዋጋው በጣም ውድ ሆኖ ነው። ጭራሽ ብርቱካን የመድኃኒት ያህል ተፈላጊ ቢሆንም ከዋጋው የተነሳ የሚቀመስ ሊሆን አልቻለም። ማንጎውም ሙዙም እንዲሁ ነው። ከዚህ የተነሳ ፍራፍሬ ለማስገባት በምናወጣው የውጭ ምንዛሬ ኢኮኖሚያችንን እየተናጋ ነው።

አሁን ግን እየተሠራ ያለው ሥራ ይህንን ችግር እንድንሻገር የሚያደርገን ነው። አረንጓዴ ዐሻራው ብዝሃነቱን ይመለሳል። ይህ ማለት ብዝሃነት ካለ የተረጋጋ ሥነ ምህዳር ይኖራል ማት ነው። የተረጋጋ ሥነ ምህዳር ምርታማነት አለው። ዘላቂም ነው፤ አደጋም ቢመጣ እንኳ መሻገር የሚችል ነው። ስለዚህ ምርታማነት እንዲያድግ ከተፈለገ የተረጋጋ ሥነ ምህዳር ያለው አካባቢ መፍጠር ይኖርብናል። ያንን ማድረግ የምንችለው በአረንጓዴ ዐሻራው ነው።

አዲስ ዘመን፡- ብዙዎቹ ባለፉት አራት ዓመታት በአረንጓዴ ዐሻራ መርሃግብር የተከናወነው ተግባር የኢትዮጵያን ስም በዓለም መድረክ እንዲጠቀስ አድርጓል ይላሉ፤ ይህን እንዴት ያዩታል?

ዶክተር ተሻለ፡- አረንጓዴ ዐሻራው በጣም ትልቅ ፖለቲካዊ ፋይዳ አለው። እንደ አንድ አጀንዳ ሲታይ ትልቅ ነገር ነው። ምናልባት እስከዛሬ በነበረው ሁነት ኢትዮጵያውያንን በሰፊው ሲያገናኝ የነበረው በአትሌቲክስ ዘርፉ የሚገኝ ድል ነው። በአትሌቲክስ ውጤት ሲመጣ ከዳር እስከ ዳር አንድ እንሆናለን። የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃግብር ንቅናቄ ኢትዮጵያውያንን አንድ የሚያደርግ አጀንዳ ነው። የአረንጓዴ ዐሻራ ጉዳይ የዜጎች ነው። ስለሆነም ፖለቲካዊ ፋይዳው ትልቅ ነው፤ ሰፊ ትርጉምም አለው። የፖለቲካ ሰዎች ደግሞ በፖለቲካ ጽንስ ሀሳብ (theory) የራሳቸው የሚሉት ይኖራቸዋል። የእኔ ምልከታ ግን ይህ ነው።

በአንድ አጀንዳ ተሰባሰብን ማለት በሚቀጥለው ጊዜ ደግሞ ሌሎች የሚያጋጩንን ነገሮች ወደ ጋራ አጀንዳነት በማምጣት ለመፍታት እንችላለን ማለት ነው። ይህንን አሳካን ማለት ሌላም ለሀገር የሚጠቅም በጋራ ለመሥራት መደላድል ይፈጥራል። የአረንጓዴ ዐሻራ ንቅናቄው ለሌሎች የጋራ አጀንዳዎቻችን እንደ አንድ ማስፈንጠሪያ መሣሪያ ነው።

ሆኖም የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራ የአንድ መሥሪያ ቤት ሥራ ብቻ አይደለም። የተፈጥሮ ሀብት የወል ሥልጣንና ኃላፊነት ነው። ሁሉንም ሰው የሚመለከት ነው። ስለዚህ የተፈጥሮ ሀብትን ከመጠበቅ አኳያ በሕገ መንግሥቱ የተቀመጠውን ኃላፊነት በአንድም በሌላ መንገድ እያሳካን ነው። የአረንጓዴ ዐሻራ እንደ ሀገር የሚያግባባ አጀንዳ የሰጠን መርሃግብር ነው።

ይህ ከተሳካ ደግሞ ኢኮኖሚውንም ሆነ አካባቢን ያረጋጋል። የደን መጨፍጨፍና መመናመንን፣ የአፈር መሸርሸርን ወዘተ ችግሮችን ያስቀራል። በመሆኑም ፖለቲካዊ ቀውስ አያስከትልም። ምክንያቱም የፖለቲካ ችግር የሚከሰተው ሰዎች ከአካባቢ መራቆት የተነሳ ቀዬያቸውን ለቀው ከተሰደዱና የሚያርፉበት ሲያጡ ነው። ለምንድ ነው? ከተባለ ሰዎች ካልተረጋጉ ይሰደዳሉ። ሲሰደዱ ተፈጥሮ ሀብት (resource) ከሌለበት ወደ አለበት ይሰደዳሉ። ሲሰደዱ ደግሞ ተሰድደው የሄዱባቸው አካባቢዎች ለጊዜው ቢቀበሏቸውም እንኳ እያደር ግን መከፋታቸው አይቀሬ ነውና ወንድም ከወንድሙ ጋር መጋጨት ይጀምራል።

ስለዚህ ጥሩ የተፈጥሮ ሥነ-ምህዳር ካለ ሰዎች በቀያቸው ተረጋግተው ይቀመጣሉ። ተረጋግተው ከተቀመጡ ደግሞ ምርትና ምርታማነታቸው ይጨምራል። ያመረቱትን ለገበያ አቅርበው ይሸጣሉ፤ ይለዋወጣሉ። ይህ ኢኮኖሚውን ያረጋጋል። ስለዚህ ምጣኔ ሀብቱን የማረጋጋት ትልቅ አቅም ይኖረዋል። በተመሳሳይ ደግሞ ፖለቲካውን የተረጋጋና ሰላም የሰፈነበት ያደርገዋል።

ከዚህ ባሻገር የአረንጓዴ ዐሻራ ተግባር በዓለም አቀፍ ዘንድ ፖለቲካውንም፣ ዲፕሎማሲውንም የሚያቀና ሰናይ ተግባር ነው። በደንብ ተሳክቶልን ጥቅም ካገኘን በፊት የምናስገባቸውን የደን ምርት ኤክስፖርት እናደርጋለን። ኤክስፖርት ስናደርግ የመደራደር አቅማችንን ያሳድጋል። በዲፕሎማሲው ዘርፍ ጥሩ ስዕል ይፈጥራል። ከዚህም የተነሳ ፖለቲካ ፋይዳው ብዙ ነው። ፖለቲካችንንም ያስተካክላል።

አዲስ ዘመን:- ወደ 25 ቢሊዮን ችግኝ እስካሁን ተተክሏል። ዛሬ ደግሞ 500 ሚሊዮን ችግኝ ይተከላል። ይህ መሆኑ የሀገሪቱን የደን ሽፋን በምን ያህል ያሳድገዋል ተብሎ ይገመታል?

ዶክተር ተሻለ :- ይህ በእርግጥም ጉዳዩ መሬት ላይ የሚወርድ ከሆነ የሀገሪቱን የደን ሽፋን ከፍ ያደርገዋል። ቀደም ሲል የሀገሪቱ የደን ሽፋን ሦስት በመቶ ይባል ነበር። አሁን ወደ 15 እና 16 ገደማ ደርሷል የሚል መረጃ አለ። አሁን እየተተከለ ያለው ውጤት ካመጣ ይበልጥ የደን ሽፋኑን የሚያሳድግ ነው። በዘንድሮው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃግብር ከስድስት ቢሊዮን ችግኝ በላይ ለመትከል ታቅዷል። ይሄ በብዙ ሺ ሄክታሮች የደን ሽፋንን ይጨምራል። ስለዚህ በአንድ ጀንበር የሚተከለውን 500 ሚሊዮን ችግኝ ወይም በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ለመትከል የታሰበውን ወደ ስድስት ቢሊዮን ችግኝ በአንድ ወይም በሁለት ሜትር ርቀት በማስላት ምን ያህል ሄክታር መሬት በደን እንደሚሸፈን ማወቅ ይቻላል። በአጠቃላይ ትርጉም ባለው መልኩ የደን ሽፋኑን እንደሚቀይረው ምንም ጥርጥር የለውም።

አዲስ ዘመን፡- የተተከሉ ችግኞችን ብቻ ከቁጥር አንፃር ብቻ መግለፅ ሳይሆን መንከባከብም ግድ ነው የሚሉ አሉ፤ ከመንከባከብ አኳያ ምን ያዩት ክፍተት አለ? ምንስ መታረም አለበት ይላሉ?

ዶክተር ተሻለ፡- በመንከባከብ ረገድ ክፍተቶች በጣም ይኖራሉ። ትልቁ ክፍተት ኢትዮጵያ ውስጥ በደን ልማትም በተፈጥሮ ሀብትም ላይ ያለው ክፍተት ከመሬት ፖሊሲያችን ጋር ያለ ክፍተት ነው። ይህንን ያልኩበት ምክንያት በግል ማሳ ላይ የተተከሉ ዛፎች መቶ በመቶ ይፃድቃሉ። ችግኞች ተተከሉ ማለት ዛፍ ሆነ ማለት ነው። ነገር ግን በወል ማለትም በጋራ መሬት ላይ የተተከሉ ችግኞች ግን እንደ ግል ማሳ ላይ መቶ በመቶ የመጽደቅ ዕድል የላቸውም። ይህ ከመሬት ፖሊሲያችን ጋር ተያይዞ የመጣ ነው። ምክንያቱም አስቀድሜ ለመጥቀስ እንደሞከርኩት የመሬት አጠቃቀም ፖሊሲ የለንም። በተጨማሪ ደግሞ መርሃግብሩ ዘመቻም እየሆነ ስለሆነ ራሱን የቻለ መዋቅር ኖሮት መሠራት አለበት።

የደን ልማት ሥራ በጣም ወጪን ይጠይቃል። ለ13 ወር ዓመቱን ሙሉ የሚሠራ ነው። ለምሳሌ ሀገር በቀል ዛፎችን ችግኝ ለማፍላት ከነሐሴ እስከ ነሐሴ መሠራት አለበት። ያለበለዚያ አይደርስም። አንድ ነርሰሪ (የችግኝ ጣቢያ) በትንሹ አምስት መቶ ሺ ብር ይጠይቃል። ስለዚህ መመደብ ያለበት በጀት በጣም ብዙ ነው። ከእንክብካቤ አኳያ ሲታይ ለተከላ የተደረገውን ትኩረት ያህል ለእንክብካቤ አይደረግም። ይህንን በእርግጠኝነት መናገር እችላለሁ። ሰዎች የተከሉትን ችግኝ ዞር ብለው ሊያዩ ይገባል። ይህ ሲሆን ነው የምንፈልገውን ውጤት ማምጣት የምንችለው።

አዲስ ዘመን፡- ስለዚህ እንክብካቤ ላይ ያለው ክፍተት መታረም ያለበት እንዴት ነው?

ዶክተር ተሻለ፡– እኛ ሀገር የተለመደው ነገር ችግኝ በጋ ላይ ከተተከለ ይደርቃል የሚል ነው። ነገር ግን ክረምት ላይም ይደርቃል። ለምን እንደሚደርቅ ልግለጽልሽ፤ ችግኙን በደንብ ሳንተክል ስንቀር ነው። ማለትም ምንም እንኳ የክረምት ወቅት ውሃ በቂ እርጥበት ቢኖረውም አፈሩ በደንብ ሳይጠቀጠቅ እና ጉድጓዱ ሳይሞላ ሲቀር በዝናቡ ምክንያት የመጣው ጎርፍ ጉድጓዱ ውስጥ ለሁለት ሳምንት እና ለአንድ ወር ተዘፍዝፎ ይቆያል። በዚህ ጊዜ ችግኙ ይበሰብሳል፤ በሳምንቱ ሊደርቅ ይችላል። ከዚህ በተጨማሪ የችግኝ አተካከል ስልታችንም ሳይንሱን የተከተለ ስለማይሆን የመጸደቅ ዕድሉ የተመናመነ ይሆናል። አንዳንዱ ከነላስቲኩ፤ አንዳንዱ ደግሞ ዘቅዝቆ ይተክላል።

ነገር ግን አንድ ችግኝ ሲተከል በመጀመሪያ ከላስቲኩ መውጣት አለበት፤ ከተተከለ በኋላ ደግሞ በተገቢው መንገድ ጉድጓዱን በአፈር መሙላት ተገቢ ነው። ጉድጓዱን በአፈር ካልሞሉት ይደርቃል። በውሃ ማጠርም ሆነ መብዛትም ይደርቃል። ከዚህ አኳያ የእያንዳንዳችንን ተከታታይ እንክብካቤ የሚሻ ነው።

አዲስ ዘመን፡- ካርበን ሽያጭን በተመለከተ ችግኞች እየተተከሉ ወደ ደን እያደጉ ነው። በእናንተ በኩል ምን እየተሠራ ነው? በተለይ የካርበን ሽያጩን ከሀገር ተጠቃሚነት አንፃር ቢያብራሩልኝ?

ዶክተር ተሻለ፡- የካርበን ሽያጭ ዓለም አቀፍ ጉዳይ ነው። ኢትዮጵያ በዚህ ጥሩ ልምድ አላት። በሶዶ እና ሁምቦ የካርበን ፕሮጀክቶች አሉ። በፊት ደን የነበራቸው በኋላ ላይ ግን ደን ሙሉ ለሙሉ ወድሞባቸው የተራቆቱ ቦታዎችን መልሰው እንዲያገግሙ የማድረግ ሥራ እየተሠራ ነው።

በቅርብ ጊዜ ኦሮሚያ ፎረስት ኤንድ ላንድ ስኬፕ ፕሮግራም በሚባለው በቅርብ ጊዜ እስከ 40 ሚሊዮን ዶላር የሽያጭ ስምምነት ተፈርሟል። ይህ በጣም ትልቅ ለውጥ ነው። በሌሎችም ክልሎችም እየተሠራ ነው። በኖርዌይ መንግሥት አማካይነት በሦስት ምዕራፍ እየተሠራ ያለ ሥራ አለ። መጀመሪያ የዝግጅት ምዕራፍ ቀጥሎ የኢንቨስትመንት ምዕራፍ በሚል ተከፋፍሎ እየተሠራ ያለ ሥራ አለ።

የኢንቨስትመንት ምዕራፍ ማለት ያሉ ደኖችን በመንከባከብ አርሶ አደሩን በማኅበር አደራጅቶ እንዲጠብቅ እና የሳሱ ቦታዎችን ተጨማሪ ደን እንዲተክል በማድረግ የደኑ ሽፋን እንዲጨምር ማድረግ ነው። የደኑ ሽፋን መጨመሩ ከተረጋገጠ ደግሞ ኦሮሚያ ፎረስት ኤንድ ላንድ ስኬፕ ፕሮግራም ላይ የካርበን ክፍያ ይኖራል ማለት ነው።

አሁን ሁለተኛውን ምዕራፍ ጨርሰን ሦስተኛውን ምዕራፍ ለመጀመር እየተዘጋጀን ነው። አሁን ገንዘብ የሚገኝበት ምዕራፍ ላይ ነን ማለት ነው። ይህም ለሀገሪቷ ትልቅ ድጋፍ ይሆናል። ነገር ግን የካርበን ክፍያው ማጣፈጫ ነው። ከላይ እንዳልኩት ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊ፣ አካባቢያዊ እንዲሁም ኢኮኖሚያዊ ጥቅሙ ዋናው ጉዳይ ነው። ደንን በመሸጥ ለጣውላም ሆነ ለተለያየ ጉዳይ ማዋል ብሎም ሥነምህዳርን በማስተካከል ብዝሃነትን በመጨመር የሚያመጣው ትርፋማነት ከፍ ያለ ነው። ይህም ከካርበን ክፍያው በብዙ እጥፍ ይበልጣል።

አዲስ ዘመን፡- እስከ አሁን የተተከለ ችግኝ አለ። ዛሬ ደግሞ በአንድ ጀምበር 500 ሚሊዮን ችግኝ ይተከላል። ከተከታታይነቱም ሆነ ከቁጥሩም ከፍተኛነት የተነሳ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ መድረክ እንዴት ትታያለች ይላሉ?

ዶክተር ተሻለ፡- ይህ ለኢትዮጵያ ትልቅ ምስል የሚፈጥር ነው። አንደኛ መትከል ማለት ትልቅ አቅም ነው። መትከል ቀላል ሥራ አይደለም። ከባድ ሥራ ነው። 500 ሚሊዮን ችግኝ በየትኛውም ሀገር ቢሆን በቀላሉ የሚሳካ ሥራ አይደለም። ሁለተኛ ደግሞ ይህ የሀገራችንን ስም እና የመፈጸም አቅም በዓለም ላይ ከፍ ያደርገዋል። ይህ ትልቅ ዝናንና ክብርን የሚያስገኝ ስለሆነ ጥቅሙ የጎላ ነው። በአረንጓዴ ዐሻራ በዓለም አቀፍ መድረክ ጎልተን እንድንወጣ የሚያደርገን ነው። ማንም መበለጥን አይፈልግም። ነገር ግን ዕውቅና ሰጡም አልሰጡ ለእኛ ትልቅ አቅም ይፈጥርልናል። አንዳንዴ እነርሱ የሚዘግቡት የሚፈልጉትን ነገር ነው። ለኢትዮጵያ ግን በጣም ትልቅ ነገር ነው።

አዲስ ዘመን፡- ለሰጡን ሰፋ ያለ ማብራሪያ በጣም አመሰግናለሁ።

ዶክተር ተሻለ፡- እኔም አመሰግናለሁ።

 አስቴር ኤልያስ

አዲስ ዘመን   ሐምሌ 10/2015

Recommended For You

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *