አረንጓዴ ዐሻራ – ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚና ዘላቂ ልማት

መንደርደሪያ

ለእኛ ለኢትዮጵያውያን እንደ ባህልና ወጋችን፣ እንደኖረው የጥንት እሴታችን፣ በትውልድ ቅብብሎሽ እንደተሻገረው ተግባራችን የተፈጥሮን ሚዛን ጠባቂነት፤ የዛፎችን ሕይወትነት በእጅጉ እንረዳለን። ዛፎች (በጥቅሉም እጸዋት) ለእኛ ኢትዮጵያውያን የአካባቢን ሚዛን ጠባቂዎች፣ ሥነምህዳርን አስተካካዮች ብቻ አይደሉም። ይልቁንም ዛፎች/እጸዋት ለእኛ የፈውስ ምንጭ መድኃኒት ናቸው፤ የዕለት ጉርስ ምግብ ናቸው፤ የሰላም አምባና የመሸማገያ እልፍኝ ናቸው።

በጥቅሉ እጸዋት የከባቢን ሥነ ምህዳር መጠበቂያችን፤ የሕመም ፈውሶቻችን፤ የምግብ ዋስትናዎቻችን፤ የድካም ማረፊያ ጥላዎቻችን፤ የመማጸኛና የእርቅ ማውረጃ እልፍኞቻችን፣ … ሆነው ዘመናትን አብረውን የኖሩ ሀብቶቻችን ናቸው። ለዚህም ነው በኢትዮጵያውያን ዘንድ የዛፍ ችግኝን እንደ ልጅ ተንከባክቦ የማሳደግ የኖረ እሴት ከትናንት አልፎ ዛሬ ድረስ እየተገለጠ ያለው።

ዛፍ መትከል እና መንከባከብ በኢትዮጵያውያን ዘንድ የእገሌ ተብሎ የሚተው አይደለም፤ ከመሪ እስከ ተርታው ሕዝብ፤ ቀለም የቆጠረውም፣ ቀለም ያልቆጠረውም፣ ገበሬውም፣ እረኛውም፣ የቢሮ ሠራተኛውም፣ ሴቱም፣ ወንዱም፣ ሕፃናቱም፣ አዛውንቱም፣ ንጉሡም፣ ንግሥቷም፣… ሁሉም ከሊቅ እስከ ደቂቅ የራስ የቤት ሥራ ተደርጎ የሚወሰድ ነው። ትናንት በነገሥታቱ፤ ኋላም በፕሬዚዳንቱ፤ ዛሬም በጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚታየው ዛፍን የመትከል ትልቅ ተግባርም የዚሁ ውጤት ነው።

ይሁን እንጂ «የእናት ሆድ ዥንጉርጉር» እንዲሉ፤ ጊዜ በተጓዘና ዓለም ሰለጠንኩ ባለች ቁጥር የኖረ ባህል መዘንጋቱ፣ የትውልድ ምግባር መሸርሸሩ አይቀርም። ከዚህ የተነሳም ኢትዮጵያችን በአንድ በኩል ተፈጥሮ ያለበሳት፤ በሌላም በኩል በሕዝቦቿ ይሁንታ የተለገሳት ደን በእኛው በኢትዮጵያውያን መጨፍጨፍና መመናመን ጀመረ።

በዚህም ለምለሚቷ የተባለችው ኢትዮጵያ ልምላሜዋን አጥታ ተራቆተች፤ የደን ካባዋን ተገፍፋ ለፀሐይና ሐሩር ተጋለጠች፤ የውሃ ማማ የሆኑ ተራሮቿ እጸዋቶቻቸውን ተነጥቀው ለምንጮቻቸው ጥላ አጥተው ተራቆቱ። ምድረ ገነቷ ኢትዮጵያ ወደ ምድረ በዳነት እየተቀየረ መጣች። በጎርፍ አፈሯ መጠረግ፤ በአውሎ ንፋስ አቧራ መልበስ፤ በኤሊኒኖ መመታትና ሌላም የአየር ንብረት ለውጥ ሰለባነቷን የሚያረጋግጡ ሁኔታዎች የዘወትር መገለጫዋ ሆነ።

ለምለሚቷ እና ምድረ ገነት የተባለችው ሀገር አስርት ዓመታትን እየቆጠረ በሚከሰት እንደ 1977ቱ ዓይነት ድርቅ እየተመታች በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎቿን ለረሃብ፤ በሺዎች የሚቆጠሩትንም ለሞት እና ለስደት መዳረግ ግብሯ ሆነ። በኋላም የአስር ዓመቱን የምልሰት ምጣኔ ወደ አምስት፣ ሁለትና አንድ ዓመት እየቀነሰ ድርቅ የሚጎበኛት፤ ዜጎቿን ለሰብዓዊ ድጋፍ የሚዳርግባት፣ ስደትና መፈናቀል እንዳያባራ ያደረገባት፣ በጥቅሉ የአየር ንብረት ለውጥ በእጅጉ ፈተና ውስጥ የከተታት ሀገር ሆነች።

“Green Legacy Initiative” በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኢኮኖሚ እና ማኅበራዊ ጉዳይ ዘላቂ ልማትን የሚመራው ዲፓርትመንት (United Na­tions Department of Economic and Social Affairs Sustainable Development) ድረ ገጽ ላይ የወጣ መረጃ እንደሚያመለክተው፤ የ120 ሚሊዮን ሕዝብ መኖሪያ የሆነችው ኢትዮጵያ፣ በተደጋጋሚ በድርቅ ከሚጠቁ ሀገራት መካከል አንዷ ናት።

መረጃው እንደሚያመለክተው፣ በሀገሪቱ በተፈጠረው የደን መመናመንና የአካባቢ መራቆት ምክንያት ከፍ ያለ የአየር ንብረት ለውጥ ተጠቂ ሆናለች። የአየር ንብረት ለውጥ መዛባት እንደ ዓለም እያሳደረ ካለው ተጽዕኖ አኳያም፣ ኢትዮጵያ ጎርፍ፣ ድርቅና ሌሎች የተፈጥሮ አደጋዎች ሰለባነቷ ከጊዜ ወደጊዜ እየጨመረ መጥቷል። በዚህም በተለይ በዝናብ ላይ ጥገኛ ሆኖ የዘለቀው ግብርናዋ በእጅጉ ተፈትኖ ቆይቷል።

ይሁን እንጂ ሀገር በዚህ ችግር ውስጥ፤ ሕዝብም በዚህ ፈተና ውስጥ መኖር ስለማይገባው፤ ይሄን ችግር ተቋቁሞ ከማለፍ አንጻር ብቻ ሳይሆን፤ በዘላቂነት ከመከላከል አኳያ ኢትዮጵያ በዓለምአቀፍ ደረጃ ለአካባቢ ጥበቃ ትኩረት እንዲሰጥ ስምምነት ከተደረሰ (የዩ. ኤን.ኤፍ.ሲ.ሲ.ሲ እኤአ በ1994 ከፀደቀበት) ጊዜ ጀምሮ በፖሊሲ ታግዛ ለአየር ንብረት ለውጥ እየሰጠች ያለችው ምላሽ እያደገ መጥቷል።

በተለይ ባለፉት አራት ዓመታት የተከናወነው የአረንጓዴ ዐሻራ ኢኒሼቲቭ/መርሃ ግብር ችግሩን አሸንፎ በዘላቂነት ከመፍታት አኳያ ትርጉም ያለው ሥራ እየተከናወነበት ያለ ነው። ይሄ ደግሞ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የ2030 /እኤአ/ የዘላቂ ልማት ግብን ከማሳካትም ሆነ የአፍሪካ ኅብረትን አጀንዳ 2063ን /እኤአ/ እውን ከማድረግ አኳያ ትልቅ አቅም የሚሆን አስተማሪ ተግባር ነው።

የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብርም ይሄን በማሳካት ሂደት ደግሞ ሦስት መሠረታዊ ዓላማዎችን አስቀምጧል። የመጀመሪያው የተጎዳውን ሥነምህዳር እንዲያገግም ማስቻል፤ ሁለተኛው፣ በሚተከሉት በቢሊዮን የሚቆጠሩ ችግኞች የኢትዮጵያን የደን ሽፋን ማሳደግ፤ በዚህ ሁሉ ተግባር የአየር ንብረት ለውጥ የሚያሳድረውን ተጽዕኖ መቀነስ የሚለው ደግሞ ሦስተኛው ዓላማና ግቡ ነው።

እነዚህን ሦስት ዓላማዎች በማሳካት ሁነትና ሂደት ውስጥ እንዲገለጥ ሆኖም ነው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር ከሃያ ሚሊዮን በላቁ ኢትዮጵያውያን ቀና ተግባር በመጀመሪያው ምዕራፍ ሃያ አምስት ቢሊዮን ችግኞችን መትከል ኢትዮጵያን የማልበስ ጉዞው በውጤት ታጅቦ የተጓዘው፤ እናም ይሄንኑ ስኬቱን በሁለተኛው ምዕራፍ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር ለመድገም እየተተጋ ያለ የጋራ ፕሮጀክት ተደርጎ የተያዘው።

አረንጓዴ ዐሻራ ሲታወስ

በአራት ዓመታት ውስጥ 20 ቢሊዮን ችግኞችን የመትከል ግብ አስቀምጦ በ2011 ዓ.ም ክረምት ላይ የተጀመረው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር፤ እንደ ቀደሙት የአካባቢ ጥበቃ ተግባራት በአንድ ሰሞን ዘመቻ ችግኝ ተክሎ የሚኬድበት አልነበረም። ምክንያቱም በነገሥታቱ ዘመን በአፄ ምኒልክም ሆነ በአፄ ኃይለሥላሴ ዘመን መሪዎች ችግኝ ተክለዋል፤ በደርግ ዘመንም ፕሬዚዳንት መንግሥቱ ኃይለማርያም ዛፍ አልምተው ደን ፈጥረዋል፤ በዘመነ ኢህአዴግም የቀድሞዎቹ ጠቅላይ ሚኒስትሮች አቶ መለስ ዜናዊም ሆኑ አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ የየራሳቸው አበርክቶ ነበራቸው።

ይሁን እንጂ እነዚህ ሁሉ ሂደቶች (በተለይ በዘመነ ኢህአዴግ) ችግኝ የመትከል መርሃ ግብርን በዘመቻ ከመከወን የዘለለ ዘላቂነት ያለው ተግባርን የሚያመጡ ሕዝባዊ መሠረት ያልያዙ፤ ዛፍ የመትከል ባህልን ያላሰረጹ፤ መርሃ ግብርን ከማሟላት የዘለለ ዓላማ መር ያልነበሩ ናቸው ማለት ይቻላል። ምክንያቱም ዓላማ ቢቀመጥላቸው ከግብ ይደርሱ ነበር። ሕዝብ የእኔ ብሎ ቢቀበላቸውና ችግኝ መትከልን ባህሉ እንዲያደርግ ቢሠራባቸው ኖሮ ሳይቆራረጡ ይዘልቁ ነበር።

የ2011ዱ/ዓ.ም/ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር ግን ከእነዚህ የተለየ ነበር። ምክንያቱም የኢኒሼቲቩ ባለቤት የሆኑት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሥራውን በባለቤትነት መርተውታል። ያለመታከት ተክለው ለሕዝቡ አርዓያ ሆነው ሕዝቡን ባለቤት አድርገውታል። ከምንም በላይ ግን መርሃ ግብሩ ለእቅድ ማሟያ ያህል የሚከወን ሳይሆን፣ ለዓላማ እየተከናወነ ያለ ስለመሆኑም በውጤት የታጀበ የአራት ዓመታት ጉዞውን መግለጥና መመልከት ይቻላል።

ለምሳሌ፣ ባለፉት አራት ዓመታት (በመጀመሪያው ምዕራፍ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር ወቅት) 20 ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከል ነበር ግብ የተቀመጠው። ይሁን እንጂ ሥራው በጥብቅ ዲስፕሊን የተመራ፤ በመሪው ያልተቆራረጠ ሠርቶ የማሠራት መንገድ፤ በሕዝቡም ቀና አስተሳሰብና ተሳትፎ ታግዞ ለአራቱ ዓመታት የተያዘው እቅድ ከግቡ አልፎ 25 ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከት አስችሏል።

የየአካባቢውን የአየር ጠባይ እና ሌሎች ጉዳዮችን ታሳቢ አድርገው ሲተከሉ የነበሩት እነዚህ ችግኞች ታዲያ ተተክለው ዝም የተባሉም አልነበሩም። በዚህም የአራት ዓመታቱ ሥራ በአማካይ የ85 በመቶ የጽድቀት ምጣኔ የታየበትም ነበር። ይሄ የሆነው ደግሞ የዛፍ ችግኞቹ በተከሏቸው አካላት ብቻ ሳይሆን፤ በየአካባቢው ማኅበረሰብ የእኔ ሀብት ናቸው የሚል የባለቤትነት እሳቤን በመፍጠራቸው ነው። ይሄ የሕዝብ ተቀባይነት የማግኘት ሂደት ደግሞ በመጀመሪያው ምዕራፍ በአንድ ጀንበር ከ20 ሚሊዮን ሕዝብ በላይ የተሳተፈበት 350 ሚሊዮን ችግኝ እስከመትከል ያደረሰ አዲስ ታሪክ የታየበትም ሆኗል።

እነዚህ አራት ዓመታት ከእቅድ በላይ ማሳካት ያስቻሉ ብቻ አልነበሩም። ይልቁንም የሚተከሉት ችግኞች ከአካባቢ ጥበቃ ሚናቸው ከፍ ያለ አበርክቶ እንዲኖራቸው ታስቦ የተከናወነ እንጂ። በዚህም በአመዛኙ የሚተከሉት ችግኞች ሀገር በቀል እንዲሆኑ ተደርጓል። ከሚተከሉት ውስጥም ከሃምሳ በመቶ በላይ የሚሆኑት ለምግብነት የሚውሉ የዛፍ ዝርያዎች ተለይተው ነው የተተከሉት። ከዚህ ባሻገር ለመድኃኒትነት፣ ለእንስሳት መኖነት፣ ለአካባቢ ውበት እና ሌሎችም ዘርፈ ብዙ ግልጋሎት የሚውሉ ችግኞች ነበሩ በትኩረት እንዲተከሉ የተደረገው።

ከአካባቢ ጥበቃና የካርበን ገበያ አኳያ

አንድ ምዕተ ዓመት ከሚጠጋ ጊዜ በፊት እስከ 40 በመቶ የደን ሽፋን እንደነበራት የሚነገርላት ኢትዮጵያ፤ ከሕዝብ ቁጥር መጨመር ጋር ተያይዞ ዜጎች ለቤት መሥሪያ፣ ለማገዶ፣ ለጣውላና ለሌሎች የእንጨት ውጤቶች፣ ለእርሻና መሰል ፍላጎቶቻቸው መሟላት ሲሉ በደን ላይ በሚያደርሱት ጉዳት ምክንያት የደን ሀብቷ ተመናምኖ እስከ ሦስት በመቶ አሽቆልቁሎ እንደነበር መረጃዎችን በመጥቀስ የሚናገሩ አሉ። በዚህም የዓለም የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖ እንደ ሀገር ከተፈጠረው የደን ሀብት መመናመን ጋር ተዳምሮ ኢትዮጵያ እንደ ሀገር ከፍ ላለ ችግር መዳረጓ በተለያዩ ሁነቶች ተገልጿል። ይሄንኑ በተለያዩ አጋጣሚዎች ከሚመለከታቸው አካላት መስማት ተችሏል።

ይሄን የደን መመናመንም ሆነ እሱን ተከትሎ እንደ ሀገር እየተከሰቱ ያሉ አደጋዎች የተገነዘቡ ኢትዮጵያውያን፤ ይሄንን የተራቆተ አካባቢ እንዲያገግም ማድረግ እንደሚገባ አምነው፤ በአንድ በኩል ከጉዳት የተረፉ ደኖችን የመንከባከብ፤ በሌላ በኩል የተራቆቱ አካባቢዎችን መልሰው እንዲያገግሙ ለማስቻል የችግኝ ተከላ ተግባራትን ወደ ማከናወን ገብተዋል።

በዚህ ተግባራቸውም በግለሰብ፣ በቤተሰብ፣ በአካባቢ፣ በቤተ እምነቶች ብሎም በሀገር ደረጃ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ዘርግተው መተግበር ጀመሩ። የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር ደግሞ የዚህ ተግባራቸው ቀዳሚው ማሳያ ሲሆን፤ በእንደዚህ መልኩ እያከናወኑ ባሉት ተግባርም ተመናምኖ እስከ ሦስት በመቶ ደርሶ የነበረውን የደን ሽፋን ከ15 ነጥብ አምስት በመቶ በላይ (አንዳንድ መረጃዎች ከ17 በመቶ በላይ ይላሉ) ማድረስ ችለዋል።

በዚህ መልኩ የተከናወኑ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብሮች ታዲያ የደን ሽፋንን ከማሳደግ ባሻገር የሚገለጽ አያሌ ፋይዳ እንዳላቸው በተግባር ታይቷል። ለአብነት፣ የደን ሽፋን ለማሳደግ በተሠራው ሥራ የአካባቢ ጥበቃ ትልቅ ትኩረት ተሰጥቶት ነበር። በዚህ ደግሞ ደኖች እንዲለሙ ብቻ ሳይሆን፤ የደረቁ ምንጮች እንዲመለሱ፤ የተሸረሸሩ መሬቶች እንዲያገግሙ፤ በድርቅና ጎርፍ የሚጠቁ አካባቢዎችም የተከሰተባቸው የአየር መዛባት እንዲስተካከል ማድረግ አስችሏል። በመሆኑም ተግባሩ የደን ሽፋንን ለማሳደግም፤ ሥነ ምህዳርን ለመጠበቅም ትልቅ አቅም የፈጠረ ነበር።

የተራቆቱ አካባቢዎች መልሰው እንዲያገግሙ ከማድረግ እና ሥነምህዳርን ከመጠበቅ ባሻገር፤ በሂደቱ በተፈጠሩ ደኖችም ሆነ ቀደም ብለው ባሉ ጥብቅ ደኖች አማካኝነት ታምቆ በሚቀር የካርቦን ጋዝ አማካኝነት ገቢ ማግኘት የተቻለበትንም ዕድል የፈጠረ ነው። በዚህ መልኩ የሚገኝን የካርቦን ሽያጭ ገቢም በአንድ በኩል ለተጨማሪ የአካባቢ ጥበቃ ተግባር እንዲውል ማስቻል፤ በሌላ በኩል ደግሞ በደን ልማቱ ቀጥተኛ ሚና ያለውን የየአካባቢው ማኅበረሰብ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥም ጅምር ውጤቶች እንዲገኙ አስችሏል።

ለምሳሌ፣ በ2013 ዓ.ም የወጣ መረጃ እንደሚያመለክተው፣ በባሌና ምዕራብ አርሲ ጥብቅ ደኖች ሲተገበር በቆየው የበካይ ጋዞች ቅነሳና የደን ጭፍጨፋን የመቀነስ ፕሮጀክት (ሬድ ፕላስ) አማካይነት 12 ሺህ 500 ሔክታር የሚሸፍን የደን ሀብትን በመጠበቅ 5 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን የካርቦን ጋዝ ልቀትን ማስቀረት ከመቻሉም በላይ ከ149 ሚሊዮን ብር በላይ ከካርቦን ሽያጭ ገቢ ማግኘት ተችሏል።

በተመሳሳይ መልኩ በወላይታ ዞን በሁምቦ ወረዳ የአካባቢው አርሶአደሮች በተከሏቸውና ጠብቀው ባቆዩዋቸው ዛፎች ምክንያት ከሚገኝ የካርቦን ሽያጭ ተጠቃሚ መሆን ችለዋል። በሌሎች አካባቢዎችም ተመሳሳይ ሥራዎች እየተሠሩ ውጤት እየመጣ ስለመሆኑም ነው የተለያዩ መረጃዎች የሚያሳዩት። በመሆኑም በዚህ መልኩ የደን ሽፋንን በማሳደግ ሥራ ውስጥ የአካባቢን ሥነምህዳር መጠበቅም ሆነ ለዓለም ፈተና የሆነውን የበካይ ጋዝ ልቀት በመከላከል ረገድ የራሳችንን ሚና እያበረከትን ተጠቃሚነታችንንም በዚያው ልክ ማሳደግ የሚያስችለንን ይሄንን ተግባር አጠናክረን መቀጠል ይኖርብናል።

ከሥራ ዕድል ፈጠራና የምግብ ዋስትና አኳያ

የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር ትግበራ ሂደት አንዱ ልዩ የሚያደርገው የሕዝብን ባለቤትነትና ተጠቃሚነት ማዕከል አድርጎ መከናወኑ ነው። ምክንያቱም ከችግኝ ዝግጅት ጀምሮ በችግኝ ተከላም ሆነ ችግኞቹ የሚያስገኙት ዘርፈ ብዙ ጥቅም የሕዝቡን ተሳትፎም ሆነ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ላይ ያተኮሩ ናቸው።

ለምሳሌ፣ ችግኝ ለመትከል መጀመሪያ ችግኞቹ መዘጋጀት፤ በኋላም የመትከያ ጉድጓዶች ተቆፍረው ዝግጁ መሆን አለባቸው። እናም ይሄን የሚያደርጉ ወጣቶች፣ ሴቶች እና የየአካባቢው ነዋሪዎች አሉ። እነዚህ ነዋሪዎች ደግሞ ችግኝ በማዘጋጀትም ሆነ የችግኝ መትከያ ጉድጓድ ቆፍሮ ዝግጁ በማድረግ ሂደት በመሳተፋቸው የሥራ ዕድልም፣ የገቢ ምንጭም ማግኘት ችለዋል።

በዚህ ረገድ መረጃዎች እንደሚያሳዩት፤ ባለፉት አራት ዓመታት ለአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር ችግኝ ዝግጅት በርካታ ወጣቶች በተለይም ሴቶችና እናቶች የሥራ ዕድል ተፈጥሮላቸዋል፤ የገቢ ምንጭም ሆኖላቸዋል። ለአብነትም 767 ሺህ ለሚሆኑ ሴቶችና ወጣቶች የሥራ ዕድል ባለቤት እንዲሆኑም፤ የገቢ ምንጭ እንዲኖራቸውም አስችሏል።

መርሃ ግብሩ በዚህ መልኩ የሥራ ዕድል እና የገቢ ምንጭ ከመሆን ባለፈ፤ የዜጎችን የምግብ ዋስትና በማረጋገጥ ረገድ ከፍ ያለ አበርክቶ ያለው ነው። ምክንያቱም ለተከላ የተዘጋጁት ችግኞች ለምግብነት የሚውሉ ዛፎችን ያካተቱ በመሆናቸው ነው። መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፣ በአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር ከሚተከሉ ችግኞች መካከል እስከ 60 በመቶ የሚሆኑት ፍሬያቸው ለምግብነት የሚውሉ ዛፎች ሲሆኑ፤ በዋናነት አቮካዶ፣ ፓፓያ፣ አፕል፣ ማንጎና መሰል የፍራፍሬ ዛፎች ተጠቃሽ ናቸው።

እንደ ችግኝ ዝግጅቱ ሁሉ፤ ተተክለው ለፍሬ ከበቁ ዛፎችም ዜጎች ተጠቃሚ መሆን የቻሉ ሲሆን፤ ለዚህ አንዱ ማረጋገጫ ደግሞ በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) «በፍራፍሬ ልማት ከፍተኛ ለውጥ እየመጣ ነው፤ በዚህ ደግሞ አርሶ አደሩ ብቻ ሳይሆን አርብቶ አደሩ አካባቢም አስደናቂ ውጤት እያስገኘ መሆኑን መመልከት ችለናል፤ ሰሞኑን በደቡብ ኦሞ ዞን ኝአንጋቶም ነበርኩ፤ አካባቢው በአርብቶ አደር የሚታወቅ ነው፤ ጥቂት አርሶ አደሮች አምና ከተተከሉ ፓፓያ በአንድ ወቅት ብቻ ከ100 ሺህ ብር በላይ ትርፍ እንዳገኙ ነግረውኛል፤» ሲሉ የተናገሩት ነው።

በመሆኑም የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብሩ ለዜጎች የሥራ ዕድል የፈጠረ፤ የገቢ ምንጭ መሆን የቻለ እና ምግብ ዋስትና ሥራው አጋዥ ሆኖ የተገለጠ ስለመሆኑ መገንዘብ የተገባ ነው። ከዚህም በላይ ሀገራዊ እሴቶች እንዲጎለብቱና ተጠብቀው እንዲቀጥሉ፤ በዚህ እሳቤ የተቃኙ ትውልዶች እንዲፈጠሩ፤ እንደ ሕዝቦች ሕዳሴው ግድብ ሁሉ ዜጎች የጋራ የሆነ ብሔራዊ ፕሮጀክት እንዲኖራቸው፤ አልፎ ተርፎም ቀጣናዊ ትስስርና ትብብርን በማጎልበት ከፍ ያለ ዲፕሎማሲያዊ ፋይዳ ኖሮት እየተተገበረ ያለ መርሃ ግብር ስለመሆኑ በልኩ መገንዘብም፤ በዚሁ ልክ ተሳትፎን በማረጋገጥ ማስቀጠልም ይጠይቃል።

ከዘላቂ ልማትና ኢኮኖሚ ግንባታ አኳያ

የአካባቢ ጥበቃ ሥራን ማጠናከር፣ የአየር ንብረት ለውጥን ተቋቁሞ መሻገር፣ የደን ሽፋንን ማሳደግ፣ ግብርናውን ከዝናብ ጥገኝነት ማላለቅና መሰል የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር ቱሩፋቶች ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚያዊ እድገት እና ዘላቂ ልማትን ማረጋገጥ የሚኖራቸው ፋይዳ ከፍ ያለ ነው። ምክንያቱም የኢትዮጵያ ልማት እና እድገት በእነዚህ ሁኔታዎች ላይ የተመሠረተ በመሆኑ ነው።

ይሄን ስል ያለምክንያት አይደለም። ለአብነት በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሁለተኛው ምዕራፍ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር አዲስ ታሪክ መጻፍ የሚያስችለንን በአንድ ጀምበር 500 ሚሊዮን ችግኝ የመትከል እቅድን ይፋ ባደረጉበትና ለሕዝቡም መልዕክት ባስተላለፉበት ወቅት እንደገለጹት፤ አረንጓዴ ዐሻራ የዛሬን ሕይወት ማስተካከያ ብቻ ሳይሆን ለነገ ትውልድ ወረት ነው።

አረንጓዴ ዐሻራ ለእኛ ብዙ ነገራችን ነው። የግብርና ምርታችንን ከፍ የሚያደርግና በምግብ ራሳችን እንድንችል የሚያበቃን ነው። ሁለት ሦስት ጊዜ አምርተን የምግብ ምርት በርካሽ እንዲገኝ የሚያስችል ነው። ወንዞች እስከ ወሰናቸው እንዲሞሉ አድርጎ የመስኖና የመጠጥ ውኃ እንዳይቋረጥ የሚያደርግ ነው። የደን ሽፋን አሳድጎ የአየር ንብረቱን የሚያስተካክል ነው። የሕዳሴ ግድባችንን ጤንነት የሚያስጠብቅ ነው።

ሌላው ቀርቶ፣ ኢትዮጵያ ታምርት ብለን ለጀመርነው ሀገራዊ የኢንዱስትሪ አብዮታችን የጀርባ አጥንት ሆኖ የሚያገለግል፤ ለኢንዱስትሪዎቻችን የጥሬ ዕቃ ግብዓት ለማቅረብ አቅም የሚፈጥር ነው። ምክንያቱም፣ ኢንዱስትሪዎቻችን የእንጨት ውጤቶችን ለማምረት ዛፍ ይፈልጋሉ። ዛፍ ከተከልን ደግሞ ለእነዚህ ግብዓት የሚሆን ጣውላን ከውጭ ከማስገባት ታቅበን በውስጥ አቅም መሸፈን ያስችለናል።

ይሄ ሲሆን ደግሞ የውጭ ምንዛሬ ከማውጣት ይልቅ የውጭ ምንዛሬ ወደማግኘት እንሸጋገራለን። ምክንያቱም ከውጭ የሚገቡ የእንጨት ውጤቶችን በሀገር ውስጥ በመተካት የውጭ ምንዛሬን ማስቀረት፤ እንዲሁም የእንጨት ምርቶችን ወደ ውጭ በመላክ የውጭ ምንዛሬን ወደ ማስገኘት መሸጋገር ያስችላል።

በተመሳሳይ፣ የአግሮ ፕሮሰሲንግ ኢንዱስትሪዎቻችን የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር ውጤት ከሆኑት አቮካዶ፣ ፓፓያ፣ ማንጎ፣ አፕልና ሌሎችም የፍራፍሬና መሰል ዛፎች የሚፈልጉትን ግብዓት ማግኘት ይችላሉ። ይሄ ሲሆን ከውጭ ማስገባት ቀርቶ ወደ ውጭ መላክ የሚቻልበትን አቅም ይፈጥራሉ። በዚህ ረገድ ለምሳሌ በአቮካዶ (በጥሬውም፣ በዘይቱም) ከወዲሁ የታዩ ጅምሮች አሉ።

ከዚህ በተጓዳኝ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር የሌማት ትሩፋት አጋዥ አቅምነቱም ከፍ ያለ ነው። ምክንያቱም ከባቢያዊ ሥነምህዳርን በመጠበቅ የአፈር መሸርሸርን በመከላከል፣ የተስተካከለ የዝናብ ዑደትን በማስፈን ብሎም የውሃ ሀብትን በመጨመር ለግብርና ሥራ የሚያበረክተው አስተዋጽዖ የጎላ ስለሆነ። የዛፎች አበባ ከመልካም መዓዛነትና መድኃኒትነት ባሻገር ለንብ ማነብ ሥራ እጅጉን ምቹና ተስማሚ ሁኔታን በመፍጠር በማር ልማት ላይ የተያዘውን አቅጣጫ ለውጤት የሚያበቃ ይሆናል።

በመሆኑም መርሃ ግብሩ በዚህ መልኩ ከፍ ያለ ሀገራዊ ኢኮኖሚን የመገንባት እና እድገቱንም ዘላቂ በማድረግ ሂደት ውስጥ ጉልህ ሚና ያለው፤ በተለይም ሀገራዊ እሴቶች እንዲጎለብቱና ተጠብቀው እንዲቀጥሉ፤ በዚህ እሳቤ የተቃኙ ትውልዶች እንዲፈጠሩ፤ ለዜጎች የጋራ የሆነ ብሔራዊ ፕሮጀክት እንዲኖራቸው፤ አልፎ ተርፎም ቀጣናዊ ትስስርና ትብብርን በማጎልበት ረገድ ለዲፕሎማሲው የሚጫወተው አበርክቶም እጅጉን የጎላ ነው።

የኢትዮጵያ የኢኮኖሚክ አሶሴሽን (Ethiopian Economics Association) አረንጓዴ ዐሻራ ለዘላቂ የኢኮኖሚ እድገት በኢትዮጵያ (Green Legacy Initia­tive for Sustainable Economic Development in Ethiopia) በሚል ርዕስ፣ እአአ ፌብሯሪ 2023 ባወጣው ጥናት እንዳመለከተው፤ መርሃ ግብሩ በኢትዮጵያ የደን ሽፋንን ከማሳደግ፣ የአካባቢን ሥነምህዳር ከመጠበቅና የአየር ንብረት ለውጥን ከመቋቋም ባለፈ፤ የሚተከሉት ችግኞች ለምግብ ዋስትና፣ ለኢንዱስትሪ ግብዓት ጥሬ ዕቃነት፣ ለጣውላና ሌሎችም የእንጨት ውጤቶችን ለሚፈልጉ ተግባራት ከፍ ያለ አበርክቶ አለው። በጥቅሉ በሀገሪቱ የግብርናም ሆነ የኢንዱስትሪ ልማት ሥራዎች ስኬታማነት የማይተካ ሚና ይጫወታል።

ሰነዱ አያይዞ እንደሚያስረዳው፣ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብርን ዘርፈ ብዙ የኢኮኖሚና ዘላቂ ልማት ፋይዳ ኅብረተሰቡ ግንዛቤ ያለው ሲሆን፤ ሰፊ ቁጥር ያለው ሕዝብ በመርሃ ግብሩ ተሳታፊ ማድረግም፣ መሆንም የቻለው ከዚሁ ግንዛቤው እና የጥቅሙ ተቋዳሽነቱን የሚያረጋግጡ ጅምር ውጤቶች በማየቱ ነው። ይሄ እንደተጠበቀ ሆኖ ግን ሥራውን የበለጠ ማላቅ፤ ተሳትፎና ተጠቃሚነቱንም ማጉላት፤ የሕዝብ ባለቤትነቱን ከዘላቂ ተጠቃሚነቱ ጋር ማቆራኘት በእጅጉ ወሳኝ ብቻ ሳይሆን፤ መርሃ ግብሩ በሀገሪቱ ዘላቂ ልማትና እድገት ውስጥ ሊወጣ የሚገባውን ሚና በአግባቡ እንዲወጣ ያስችለዋል።

እንደ መውጫ

አረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር በዚህ መልኩ ዘርፈ ብዙ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳዎቹን ይዞ ከዓመት ዓመት እምርታን እያሳየ በስኬት ቀጥሏል። በዛሬው ዕለት (ሐምሌ 10 ቀን 2015 ዓ.ም) በአንድ ጀምበር 500 ሚሊዮን ችግኞችን ተክሎ ታሪክ የመጻፍን እቅድ ያቀፈው ሁለተኛው ምዕራፍም ቢሆን ከጅምሩ መልካም ደረጃ ላይ ይገኛል። በመሆኑም በሁለቱ ምዕራፎች ኢትዮጵያን አረንጓዴ ማልበስ የሚያስችል የ50 ቢሊዮን ችግኝ ተከላ ግስጋሴ ግለቱን ጠብቆ ሊጓዝ ይገባዋል።

በዚህ ረገድ በመርሃ ግብሩ ቀጣይነት ላይ ስጋት እንዳላቸው የሚያነሱ አካላት አይጠፉም። እነዚህ አካላት ያለፉት አራት ዓመታት ውጤታማ ጉዞ አላሳመናቸውም፤ ወይም አምነው ሊቀበሉት አልፈለጉም። ይልቁንም በሳይንቲስቶች ቡድን ተካሂዶ በ‘ሮያል ሶሳይቲ ጆርናል’ ላይ ታተመ በሚሉት አንድ ጥናት ማጣቀሻነት በእስያ ውስጥ ደን ለማልማት የተካሄደ ፕሮጀክት ከአምስት ዓመታት በኋላ መቀጠል ሳይችል ቀርቷል፤ የኢትዮጵያ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብርም መሰል ችግር ሊገጥመው ይችላል የሚል ቅዠታቸውን ሊያሰርጹ ይሞክራሉ።

ሆኖም እነሱ ይሄንን ሲሉ ያልተገነዘቡት አንድ ጉዳይ አለ። ይሄም በእስያም ሆነ በየትኛውም አካባቢ የሚከናወን የችግኝ ተከላ ተግባር ባለቤት ኖሮት ወይስ በጅምላ ጉዞ የሚከወን ስለመሆኑ አላጤኑም። ቀደም ብዬ ለጽሑፌ መንደርደሪያ ይሆነኝ ዘንድ በመግቢያዬ እንዳነሳሁት፤ በኢትዮጵያም መሰል ተጀምረው ያልተቋጩ፤ ተወጥነው ያልተጠናቀቁ፤ ጉዞ ጀምረው ከግባቸው ያልደረሱ በርካታ የየዘመን ማሳያዎች አሉ።

የአሁኑ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር ግን ባለቤት አለው፤ መሪ አለው፤ ሕዝባዊ መሠረትና ቅቡልነት አለው፤ ስለ ሀገሩ አረንጓዴ መልበስ እንቅልፍ የሚነሳው ትውልድ አለው። በጥቅሉ ሥራው በእሳቤው ባለቤት ያውም በጠቅላይ ሚኒስትሩ ፊት አውራሪነት ያለመታከት የሚከወን ነው፤ ጉዞው በሕዝብ ቀና ልብ ታትሞ ላይቆራረጥ በወል የተያዘ ነው፤ ትግበራው ቁጭት በወለደው የማሸነፍ ኃይል በውጤት ታጅቦ እየተጓዘ ያለ ነው።

የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር የትናንቱን ማንነት የመመለስ፤ የዛፍ ጥላነትን፣ የደን ሥነምህዳር ጠባቂነትን፣ የእጸዋት ምግብነትና መድኃኒትነትን፣ የዛፎችን የእርቅና ሽምግልና ብሎም መማጸኛ እልፍኝነትን የመመለስ ቁጭት ወለድ ትልም ወደ ተግባር የተለወጠበት ነው።

የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር እንደ ቀደመው ዓለምአቀፍ ተልዕኮን ለመፈጸም እና ድጋፍ ለማግኘት ሲባል የሚከወን ሳይሆን፤ እንደ ሀገር የተጋረጡ የድርቅ፣ የረሃብ፣ የመፈናቀል፣ በጥቅሉ በደኖች መመናመን ምክንያት በተፈጠረ የአየር ንብረት ለውጥ የተጣባውን የሰው እጅ የመጠበቅ በሽታ ለማከም ሲባል የሚደረግ ራስን የመቻል የሞት ሽረት ተጋድሎ ነው።

ለዚህም ነው፣ መርሃ ግብሩ በተጀመረበት ያውም በመጀመሪያው ዓመት ሐምሌ 22 ቀን 2011 ዓ.ም በተካሄደው የአረንጓዴ ዐሻራ ቀን በአንድ ጀንበር 200 ሚሊዮን ችግኝ ለመትከል ታቅዶ 353 ነጥብ 6 ሚሊዮን ችግኝ መትከል የተቻለው። ከጅምሩ ሕዝባዊ መሠረት እንዲኖረው በመሠራቱም ነው ከ23 ሚሊዮን ሕዝብ በላይ በዚህ መርሃ ግብር መሳተፍ የቻለው።

ጉዞው የአየር ንብረት ተጽዕኖን የመቋቋም፤ የተራቆቱ አካባቢዎችን እንዲያገግሙ በማድረግ የደን ሽፋንን የማሳደግና ሥነምህዳርን የመጠበቅ፤ የምግብ ዋስትናን የማረጋገጥና ከተረጂነት የመላቀቅ፤ የሥራ ዕድል የመፍጠር፤ የገቢ አቅምን የማሳደግ፤ በሀገር በቀል ዛፎች የሚገኝ የመድኃኒት፣ የመዓዛና ሌሎችም ከፍ ያሉ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳዎቻቸውን የመመለስ ነው።

በየኔነው ስሻው

አዲስ ዘመን   ሐምሌ 10/2015

Recommended For You

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *