ኢትዮጵያ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የአረንጓዴ ኢኮኖሚን ስኬታማ ለማድረግ በትኩረት እየሰራች ትገኛለች። ይህን ዓላማዋን በውጤት የታጀበ ለማድረግ የሚያስችላትንም እንቅስቃሴ ማከናወን ከጀመረች ዓመታትን ያስቆጠረች ሲሆን፣ የመጀመሪያው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብሯም ጅማሬውን ያደረገው በ2011 ዓ.ም ነበር። በወቅቱም መርሃ ግብሩን ይፋ ያደረጉት የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ እንደሆኑም የሚታወቅ ሲሆን፣ ከዚህም አኳያ ሀገሪቱ ባለፉት አራት ዓመታት ሕዝባዊ ንቅናቄን በመፍጠር ከ25 ቢሊዮን በላይ ችግኝ መትከል ችላለች።
ይህ ጉዳይ ቀጣይነት ያለው እንደመሆኑ፣ ዘንድሮ ለአምስተኛ ዓመት የተያዘው እቅድ ከስድስት ቢሊዮን በላይ ችግኝ ለመትከል ሲሆን፣ ትናንት በተካሔደው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ላይ ደግሞ ሕዝባዊ ንቅናቄ በመፍጠር በአንድ ጀምበር 500 ሚሊዮን ችግኞችን መትከል ተችሏል። የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ፣ ‹‹ዓላማችን ሪከርዳችንን መስበር ነው።›› ሲሉም መግለጻቸው ይታወቃል። በእርግጥ እርሳቸው እንዳሉት የአረንጓዴ አሻራ ጉዳይ ኢትዮጵያን የመጠበቅ፣ የማክበርና የማበልጸግ ጉዳይ ነው፤ በመሆኑ ኢትዮጵያውያኑ ለዚህ በጎ ዓላማ ያለማንም ገፋፊነት አሻራቸውን ማኖር ችለዋል።
ኢትዮጵያ በአምስተኛው ዙር የተከለችውን ሳይጨምር በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ባለፉት አራት ዓመታት ማለትም ከ2011 ዓ.ም እስከ 2014 ዓ.ም ድረስ ባካሄደችው መርሃ ግብር የተተከለው የችግኝ ብዛት 25 ቢሊዮን የደረሰ መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ። በትናንትናው ዕለትም ግማሽ ቢሊዮን ችግኝ መተከሉ ብቻ ሳይሆን ሪከርድ ጭምር የተሰበረበት መርሃ ግብር ሆኖ አልፏል። ከዚህ የተነሳ ይህ በትኩረት እየተሰራበት ያለው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ከኢኮኖሚው አኳያ የሚያስገኘው ፋይዳ ምንድን ነው ስንል የዘርፉን ባለሙያዎች አነጋግረናል።
በዓለም አቀፉ የአረንጓዴ እድገት ኢንስቲትዩት ውስጥ የአፍሪካ የደንና የተፈጥሮ ሀብቶች አያያዝ መሪ የሆኑት ዶክተር ገመዶ ዳሌ እንደሚሉት፤ የአረንጓዴ አሻራ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታው በቀጥታም ሆነ ቀጥተኛ ባልሆነ መንገድ የሚገለጽ ነው። ከዚህ አኳያ የመጀመሪያው ጉዳይ ውሃ ማግኛ አንዱ ተግባር ሲሆን፣ ውሃ የሚያመጣቸው በረከቶች ደግሞ በርካታ ናቸው።
ለምሳሌ ተፋሰሶችን በአግባቡ ከያዝን የውሃ ሃብት ይጨምራል። ውሃ ተገኘ ማለት ደግሞ ምግቡም የኤሌክትሪክ ኃይሉም በቀላሉ ይገኛል። እንደሚታወቀው የኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ኃይል ምንጩ ሃይድሮ ኤሌክትሪክ ፓወር ነው። ከውሃ መገኘት የተነሳ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በተያዘለት ሰዓት መሙላት ስለሚቻል የውሃ መገኘት የኤሌክትሪክ ኃይል መገኘት ይሆናል። እሱ ደግሞ በኢኮኖሚያችን ላይ የሚኖረው አስተዋጽኦ ቀጥተኛ ነው። ስለዚህ የኃይል መገኘት የሚመጣው ከውሃ ነውና የችግኞች መተከልና ውጤታማ መሆን ለውሃ መኖር ትልቁ ቁልፍ ጉዳይ ነው፤ ይህ ደግሞ ለሀገሪቱ ኢኮኖሚ ፋይዳ ላቅ ያለ ነው ይላሉ።
እንደ ዶክተር ገመዶ አባባል፤ የሚተከለው ችግኝ ከውጭ በውጭ ምንዛሬ የሚገባውን የእንጨት ምርት በተለይ የጣውላን ምርት በመተካት ረገድ ተስፋ የሚጣልበት ነው። ይህ ብቻ ሳይሆን በአሁኑ ወቅት እየተተከሉ ያሉ ችግኞች አገር በቀል ከመሆናቸው ጋር ተያይዞ ከጥንካሬያቸውና ከውበታቸው ጋር በተያያዘ የተሻሉ ናቸው።
በኮንስትራክሽን እያደግን ያለን አገር እንደመሆናችን የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው በጣም ተስፋፍቷል። የኮንስትራክሽን እንጨቶች የሚፈለጉት በከፍተኛ ደረጃ ነው። ለምሳሌ አንድ ቋሚ ወይም አጣና ለመግዛት የሚወጣው ወጪ ከፍተኛ ነው። ነገር ግን ችግኝ ተክሎ አንድ አጣና ማድረስ የሚያመጣው ገቢ ደግሞ በዚያው ልክ ከፍ ያለ ነው። ከዚህ አኳያ የምንተክላቸው ችግኞች ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ እንዲኖራቸው ታስበው ስለሚተከሉ ውጤታማነታቸው ላቅ ያለ ነው ሲሉ ዶክተር ገመዶ ይናገራሉ።
በደቡብ ክልል የሬድ ፕላስ ፕሮጀክት አስተባባሪ ዶክተር ተሻለ ወልደአማኑኤል በበኩላቸው፤ ልክ እንደ ዶክተር ገመዶ ሁሉ የአረንጓዴ አሻራ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳው ሁለት ዋና ዋና ነገሮች ያሉት ነው ይላሉ። አንደኛ በአረንጓዴ አሻራ ላይ ከምንሰራው ሥራ የምናገኘው ቀጥተኛ ጥቅም ሲሆን፣ ይህም ችግኝ ሲተከል የደን ሽፋን መጨመሩና የተተከለው ደን ደግሞ ምርታማ ሲሆን ፋይዳው ላቅ ያለ እንደሚሆን ያስረዳሉ። ለምሳሌ ከተተከሉት የችግኝ አይነቶች መካከል የጣውላ ዛፍና የፍራፍሬ ዛፍ ተጠቃሾች ሲሆኑ፣ ከእነዚህ ላቅ ያለ ጥቅም እናገኛለን ብለዋል።
እርሳቸው እንደሚናገሩት፤ ኢትዮጵያ ጣውላን ከውጭ ማስገባት ድረስ ደርሳለች። ስለዚህ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብሩ ይህንን ክፍተት ይሞላዋል። ከዚህ በተጨማሪ ለሀገር ውስጥ የኮንስትራክሽን ሥራ የዛፍ ውጤቶችን በስፋት ስለምንጠቀም ለዛ ግብዓት ይሆናል። በአሁኑ ወቅት አንዲት አጣና የምትሸጠው በመቶ ብር ቤት ነው። ሌሎችም ለተለያየ ግብዓት የምንፈልጋቸው እንጨቶች በብዙ መቶ ብር የሚሸጡ ናቸው።
ዶክተር ተሻለ፣ ሁለተኛውና ትልቁ ጉዳይ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብርን ማሳለጥ ለኢኮኖሚው በተዘዋዋሪ መንገድ ያለው ፋይዳ ከፍ ያለ እንደሆነ ይናገራሉ። በአረንጓዴ አሻራ አካባቢያችንን ደን ስናለብስ የተፈጥሮ ሥነ ምህዳሩ ይስተካከላል። ብዝሀነትንም ይጨምራል። ዛፉ፣ ሣሩ፣ ወፉና ነፍሳቱ ሁሉ መኖር ይጀምራሉ። የተረጋጋ ሥነ ምህዳር ሲኖር ሁሉም መኖር ይጀምራል። የእነዚያ መኖር አካባቢው የተረጋጋ እንዲሆን ያደርጋል። እነርሱ ኖሩ ማለት ምርታማነት ጨመረ ማለት ነው ሲሉ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታውን ያስረዳሉ።
እያንዳንዱ የብዝሀ ሕይወት ሀብት ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንዳለው የሚጠቅሱት ደግሞ ዶክተር ገመዶ ሲሆኑ፣ ከመድኃኒት አኳያ ሲታይ ወደ ስድስት ሺ 29 አካባቢ ዝርያዎች በኢትዮጵያ መኖራቸውን አመልክተዋል። ከዚያ ውስጥ 10 ከመቶ የመድኃኒት እጽዋት ናቸው። ከዚህ የተነሳ የመድኃኒት ፋብሪካዎችን እንገንባ ብንል እንኳ በአግባቡ ከለየንና ከተጠቀምንበት አቅማችን ብዙ ሊያስኬደን የሚችል እንደሆነ አመልክተው በዚህም ዘርፍ ኢኖሚያዊ ጠቀሜታው ከፍ ያለ ነው ብለዋል። በተለይ አብዛኛው የማኅበረሰብ ክፍል ዛሬም ቢሆን ለመድኃኒትነት እጽዋትን በመጠቀም ላይ ይገኛል።
ከዚህም የተነሳ የችግኞች በስፋት መተከል ለመድኃኒት መግዣ የሚወጣውን ወጪ መቀነስ የሚያስችል ነው። በመሆኑም ይህ አንዱ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ነው ሲሉ አስረድተዋል። ዶክተር ገመዶ እንደሚናገሩት፤ የችግኝ መተከል ሥርዓተ ምህዳሩ ያስተካክላል፤ ውሃ እንዲገኝ ያደርጋል። የውሃ መኖር ደግሞ ለም አፈር እንዲኖር እድል ይሰጣል። የለም አፈሩ መኖር ደግሞ ለሰው ሰራሽ ማዳበሪያ የሚወጣውን ወጪ በማስቀረት ረገድ ሚናው ላቅ ያለ ነው። ከዚህ አኳያ ሲታይ አረንጓዴ አሻራ ለኢኮኖሚያችን ያለው ፋይዳ ከፍተኛና ነው።
በአረንጓዴ አሻራ መታቀፍ የሚገባቸው የእንጨትነት ባህሪ ያላቸው ዛፎች እንደሆኑ የሚያስረዱት ዶክተር ገመዶ፣ ከዚህ አኳያ በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ላይ የተተከሉ የፍራፍሬ ችግኞች ምንም እንኳ በአጭር ጊዜ መድረስ ባይችሉም ለምግብ ዋስትና መረጋገጥ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አላቸው ብለዋል። ለምሳሌ ማንጎ ወይም አቮካዶን ብንወስድ ለምግብ ዋስትና መረጋገጥ የራሳቸው የሆነ ፋይዳ አላቸው። ይህ አንደኛው ጥቅማቸው ሲሆን፣ ሁለተኛው ጥቅማቸው ደግሞ እነርሱ በሚተከሉበት አካባቢ ያለው ሥርዓተ ምህዳር የተስተካከለ ይሆናል ሲሉ አመልክተዋል።
ችግኞቹ የሚተከሉት በማሳ አካባቢ እንደመሆኑ በዙሪያው ያለው መሬት አፈሩ እርጥበት አዘል እንዲሆን ያደርገዋል። ከዚህም የተነሳ በአካባቢው የሚዘሩ ስንዴም ሆነ የጤፍ ሰብል ምርታማነታቸውም ጤናማነታቸውም እንዲሻሻል ስለሚያደርግ በቀጥታ ለምግብ ዋስትና መረጋገጥ የበኩሉን አስተዋጽኦ ያበረክታል ብለዋል።
ዶክተር ተሻለ በበኩላቸው እንደሚናገሩት፤ አሁን የሚከናወነው የአረንጓዴ አሻራ ብዝሀነትን ይጨምራል። ይህ ሲሆን፣ ደግሞ የእንስሳትና የእጽዋት ብዝሀነት ይኖራል። ስለዚህ ብዝሀነት ያለው አካባቢ ጠንካራ፣ የተረጋጋ፣ ምርታማና የተፈጥሮ አደጋን መቋቋም የሚችል ነው። በተጨማሪም ቀጣይነት ያለው ነው።
የተፈጥሮ ሀብታችንን መጠበቅ የኢኮኖሚያችን መሠረት ነው የሚሉት ዶክተር ገመዶ ደግሞ፣ ላቲን አሜሪካን፣ ቦሊቪያ፣ ፔሩ ሀገራት ደን የኢኮኖሚ መሠረታችን ነው በሚል ከደን ሀብት የሚገኘውን ጥቅማ ጥቅም ከግምት ውስጥ አስገብተው የሚሰሩ ናቸው ሲሉ ተናግረዋል። የተፈጥሮ ሀብታቸውን የኢኮኖሚያው መሠረት ያደረጉ በርካታ ሀገራት እንዳሉም አስታውሰው፤ እኛም በሒደት የምናቀናው ወደዚያው ነው ሲሉ ገልጸዋል።
ለምሳሌ የደን ሽፋን ለሀገር ውስጥ ምርት (ለጂዲፒ) የሚያበረክተው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው። ነገር ግን በአሁኑ ወቅት የአረንጓዴ አሻራ ለሀገር ውስጥ ምርት የሚያበረክተው አስተዋጽኦ በመቶኛ ሲሰላ ዝቅ ያለ ነው፤ ቢሆንም በተያዘው ፍጥነት የሚቀጥል ከሆነ ልክ እንደ ቻይና የመሳሰሉ በኢኮኖሚያቸው የበለጸጉ ሀገራት ተጠቃሚ የምንሆንበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም የሚል ተስፋ አለ ይላሉ።
ልክ ከግብር ይህን ያህል ማግኘት አለብን ብሎ እንደሚታቀደው ሁሉ ከደን ሀብትም በዚህ ልክ ማግኘት ይጠበቅብናል ተብሎ መታቀድ አለበት በማለት ይናገራሉ። ይህ ደግሞ ያለብንን ክፍተት ከወዲሁ ማረም ከቻልን ጠቀሜታው የጎላ ነው ብለዋል። አብዛኛዎቹ ሀገሮች የደን ምርታቸውን ለጂዲፒያቸው የሚጠቀሙበት እስከ 40 በመቶ ድረስ ነው። ከዚህ ሌላ ኢኮኖሚያቸው ሙሉ ለሙሉ በደን ላይ የተመሰረቱ ሀገራት እንዳሉም ተናግረዋል።
ዶክተር ገመዶ፣ አረንጓዴ አሻራ በተዘዋዋሪ መንገድ ለኢኮኖሚ ያለው ፋይዳ ከፍ ያለ ነው ይላሉ፤ አንደኛ ደን ባለበት አካባቢ የማኅብረሰብ ጤንነት የታደሰ ይሆናል። ይህ ቀላል ግምት የሚሰጠው አይደለም። ሌላው ደግሞ የአየር ንብረት ለውጥን በመከላከል ረገድ በጎርፍና በድርቅ የሚከሰተን አደጋ በመቀነስ አኳያ ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው። የደን መኖር ብዝሀ ሕይወት እንዲጠበቅ የሚኖረው ፋይዳ ከፍተኛ ሚና የሚጫወት ነው። ሁለት ሶስተኛው ወይም 66 በመቶ አካባቢ ብዝሀ ሕይወት የሚኖሩት በደን ውስጥ ነው። እነዚህ የደን የተዘዋዋሪ ፋይዳዎች ናቸው።
በአረንጓዴ አሻራ የፍራፍሬ ችግኝ የሚተከል መሆኑን የሚያስታውሱት ዶክተር ተሻለ፣ ይህም በየጊዜው እየናረ የመጣውን የአትክልትና ፍራፍሬ ዋጋ እንደሚያረጋጋው ተናግረዋል። በአሁኑ ወቅት አንድ ኪሎ ማንጎ ውድ በሆነ ዋጋ ለመግዛት እንገደዳለን ብለዋል፤ በሌላ መልኩ ደግሞ ከግብጽ ‹‹ጁስ›› እናመጣለን። ነገር ግን በኢትዮጵያ ውስጥ ሁሉም አይነት የአየር ጸባይ ከመኖሩ የተነሳ ሁሉንም የፍራፍሬ አይነት ማምረት ያስችላል ሲሉም ተናግረዋል። ስለዚህ ምርታማነት እንዲያድግ ከተፈለገ የተረጋጋ ሥነ ምህዳር ያለው አካባቢ መፍጠር አለብን። ያንን ማድረግ የምንችለው በአረንጓዴ አሻራው ነው ብለዋል።
በሌላ በኩል የአረንጓዴ አሻራው ተሳልጦ መሠራት ከካርቦን ሽያጭም ገቢ የሚያመጣ ጉዳይ መሆኑን የሚጠቅሱት ዶክተር ተሻለ ናቸው፤ የካርበን ሽያጭም በአሁኑ ወቅት ዓለም አቀፍ ጉዳይ መሆኑንም ይናገራሉ። እርሳቸው እንደሚናገሩት፤ ኢትዮጵያ በዚህ ጥሩ ልምድ አላት። በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍል በተሠራው ሥራ ከካርቦን ሽያጭ በበርካታ ሚሊዮን ዶላር የሚቆጠር ገንዘብ ተገኝቷል። አሁን ሁለተኛውን ምዕራፍ ጨርሰን ሶስተኛውን ምዕራፍ ለመጀመር እየተዘጋጀን ነው። አሁን ገንዘብ የሚገኝበት ምዕራፍ ላይ ነን ማለት ነው። ይህም ለሀገሪቷ ትልቅ ድጋፍ ይሆናል።
ነገር ግን የካርቦን ክፍያው ማጣፈጫ ነው። ከካርቦን ክፍያው በተሻለ ትልቁን ጥቅም የሚይዘው ሥነ ምህዳርን በማስተካከልና ብዝሀነትን በመጨመር የሚመጣው ትርፋማነት በብዙ እጥፍ ይበልጣል። ከካርቦን ሽያጭ ጋር ተያይዞ በመጀመሪያ ግንዛቤውን ማሳደግ ይገባል የሚሉት ደግሞ ዶክተር ገመዶ ናቸው። ለዚህ ምክንያታቸውን ሲገልጹ እንዳሉት፤ ከካርቦን ሽያጭ ጋር ተያይዞ የራሱ የሆነ ፈተና ስላለው ነው ይላሉ።
እንደ ባለሙያዎቹ ገለጻ፤ አረንጓዴ አሻራ ከፌዴራል እስከ ቀበሌ ድረስ በተሰናሰለ መልክ ሊሰራበት የሚገባ ነው። የደን ምንጣሮ ዛሬም በከፍተኛ ደረጃ ቀጥሏል፤ ይህ መሆን የለበትም። ዛሬም በሕገ ወጥ መንገድ የደን ሀብት እየተዘረፈ ነው። እነዚህን ችግሮች ማስተካከል የግድ ነው። ከደን የሚገኘውን ፋይዳ ብቻ መከተል ሳይሆን በአግባቡ እንዳንጠብቅ ባደረጉን ችግሮች ላይ በትኩረት መሠራት አለበት። በዓለም አቀፍ ደረጃ የተስማማንባቸው ዓለም አቀፍ ግዴታዎችንም የበለጠ ማክበር ይጠበቅብናል። በተለይም ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የአረንጓዴ ኢኮኖሚያችንን ለመገንባት የገባነውን ሀገራዊና ዓለም አቀፋዊ ግዴታዎችን ባገናዘበ መልኩ በአግባቡ በማልማት መጠቀም ያስፈልጋል።
በተለይ ዶክተር ገመዶ እንደገለጹት፤ በእርግጥ አሁን ኢትዮጵያ እየሄደችበት ያለው ሁኔታ በርካታ ነገር ከጠፋ በኋላ ለማስተካከል የሚደረግ ጥረት ነው። የደን ሀብቶቻችንን በከፍተኛ ደረጃ ከመነጠርን በኋላ አልፎ ተርፎ እንዲመናመኑና ወደማሳነት እንዲለወጡ ብሎም ሥርዓተ ምህዳራቸው እንዲቀየሩ ካደረግናቸው በኋላ ነው ያንን ለማስተካከል እየደከምን የምንገኘው። ለምሳሌ እንደ እኛ ያጠፉ በርካታ ሀገራት አሉ። ይሁንና በቁርጠኝነት ለማስተካከል እየሄዱ ያሉ ሀገራትን ብናይ ከአፍሪካ እንደ ኢትዮጵያ በሀገር መሪ ደረጃ የተሄደበት ርቀት የለም። ይህ ይበል የሚያሰኝ ተግባር ሲሆን፣ ኢኮኖሚ ፋይዳውን በአግባቡ ለመጠቀም ግን ዋናው መፍትሔ በዘመቻ መልክ የተጀመረውን ነገር በተቋም ግንባታ ተጠናክሮ እንዲሔድ ማድረግ ወሳኝ ነው።
አስቴር ኤልያስ
አዲስ ዘመን ማክሰኞ ሐምሌ 11 ቀን 2015 ዓ.ም
To learn more about what s been dubbed economy class syndrome and how travelers can protect themselves, we talked with experts about this growing public health problem [url=https://fastpriligy.top/]priligy cost[/url] 1 Potential for Other Drugs to Affect Bupropion Hydrochloride Extended Release Tablets XL