በዓለም ላይ የሰው ሠራሽ አስተውሎት (አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ) ቴክኖሎጂ ችሎታ እና ብቃት እያደገ መምጣቱ ይነገራል። ከዚህም ጋር ተያይዞ ሰው ሠራሽ አስተውሎት ሕግና ማዕቀፍ ተዘጋጅቶለት በአግባቡ ካልተመራ በሰው ልጆች ሕይወት እና አኗኗር ላይ ስጋት ሊያስከትል እንደሚችል የዘርፉ ባለሙያዎች በየጊዜው የሚያነሱት ጉዳይ ነው። ኢትዮጵያም ቴክኖሎጂውን ቀደም ብለው ከጀመሩ የዓለም ሀገራት ተሞክሮ በመውሰድ ሰው ሠራሽ አስተውሎት (አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ) ኢንስቲትዩት በ2012 ዓ.ም እንዲቋቋም አድርጋለች። የኢንስቲትዩቱን መቋቋም ተከትሎ ዘርፉ የሚመራበት ፖሊሲ በማዘጋጀት ሲሰራም ቆይቷል።
በቅርቡም ይህንን ሰው ሰራሽ አስተውሎት በሕግና በሥርዓት ለመምራት እንዲቻል እየተዘጋጀ ባለው ረቂቅ ፖሊሲ ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ምክክር በማድረግ የግብዓት ማሰባሰቢያ መድረክ ተዘጋጅቶ ነበር። በመድረኩ ተገኝተው የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ሁሪያ አሊ እንደሚሉት፤ የሰው ሠራሽ አስተውሎት (አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ) ቴክኖሎጂ ከኮምፒዩተር ሳይንስ የትምህርት መስክ አንዱ ነው። ዘርፉ ማሽን በማስተማር የሰውን ልጅ እውቀት፣ ክህሎት፣ ቋንቋና ችግሮችን በመፍታት መፍትሔ የሚያበጅ ነው። ይህም ድካምን ይቀንሳል፤ ጥራትና ፍጥነትን በመጨመር ምርትና ምርታማነት እንዲጨምር ያደርጋል።
የሰው ሠራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂ ባደጉ ሀገራት በኢንዱስትሪዎች እና አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ምርታማነት ላይ ጥራትና ቅልጥፍናን መጨመሩን የሚናገሩት ሚኒስትር ዴኤታዋ፤ ዘርፉን ማሳደግ የሀገር ሁለንተናዊ ተጠቃሚነትን ለማሳደግና የደህንነት ስጋትን ለመቀነስ እንደሚረዳም ጠቁመዋል። በመሆኑም የሰው ሰራሽ አስተውሎት የአሠራር ሥርዓቶችን ለመዘርጋት የሚያግዝ ረቂቅ ፖሊሲ ማዘጋጀት ማስፈለጉን አስታውቀዋል። የሰው ሠራሽ አስተውሎት ለሀገር ሁለንተናዊ እድገት አስፈላጊ መሆኑን ጠቅሰው፤ የደህንነት ስጋትን ለመቀነስ በፖሊሲ የተደገፈ የሕግ ማዕቀፍ ሥርዓት ማበጀት ወሳኝ መሆኑንም ነው ሚኒስትር ዴኤታዋ የሚገልጹት።
እሳቸው እንደሚሉት፤ በረቂቅ ፖሊሲው በዘርፉ ሀገሪቱ ያለችበትን ነባራዊ ሁኔታና የወደፊት የልማት እድገት አቅጣጫዎቿን የሚያመላክቱ ጉዳዮች ተካተዋል። ረቂቅ ፖሊሲው የባለድርሻ አካላት አስተያየት ተካትቶበት ሲጸድቅ በሰው ሠራሽ አስተውሎት ዙሪያ የሚያጋጥሙ ችግሮችን ለመለየትና የመፍትሔ ሀሳብ ለማስገኘት ያስችላል ብለዋል። በቀጣይ በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት አማካይነት በሀገራችን ከሚዘጋጀው የዳታ ማጋሪያ፣ መመሪያ ስታንዳርድና የሥነ ምግባር መመሪያዎችን ለማርቀቅና ለመተግበር እንዲሁም ከሚመለከታቸው ተቋማት ጋር በቅንጅት ለመሥራት የሚያስችል አሰራር እንዲኖር ጥልቅ ምልክታ ሊሰጥ የሚችል ረቂቅ ፖሊሲ መሆኑን ያብራራሉ።
የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ታዬ ግርማ በበኩላቸው፤ የሰው ሠራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂ ወደ ኢትዮጵያ የገባው በቅርቡ መሆኑን ጠቁመው፤ እስካሁን በግለሰቦችና በተለያዩ ቡደኖች ሲሰራ መቆየቱን ይገልጻሉ። በኢትዮጵያ የሰው ሠራሽ አስተውሎት (የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ) ቴክኖሎጂ ሀገራዊ ሚና እንዲኖረው እና ሀገራችንም በቴክኖሎጂው ተጠቃሚ እንድትሆን የሚያደርግ ሕግ ሲኖር ነው ይላሉ።
ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ በዘርፉ ሁሉን አቀፍ ሥራ ለመስራት ፖሊሲ እንደሚያስፈልግ ጠቅሰው፤ ለዚህም ብሔራዊ የአርቲፊሻል አንተለጀንስ ፖሊሲ ማዘጋጀት እንዳስፈለገ ይናገራሉ። የመሠረተ ልማት ግንባታ፣ የሥርዓት ግንባታ፣ ምቹ ምሕዳር መፍጠር ረቂቅ ፖሊሲው ትኩረት ያደረገባቸው ጉዳዮች መሆናቸውን የጠቀሱት ዶክተር ታዬ፤ ረቂቅ ፖሊሲው ኢትዮጵያ በሰው ሠራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂ ከአፍሪካ ግንባር ቀደም የልህቀት ማዕከል እንድትሆን ራዕይ በሰነቀ መልኩ እየተዘጋጀ ያለ እንደሆነም ተናግረዋል።
እሳቸው እንደሚሉት፤ ረቂቅ ፖሊሲውን የማዘጋጀቱ ሥራ ከአንድ ዓመት በላይ ጊዜ ወስዷል። የፖሊሲ ዝግጅት ኮሚቴው ከተለያዩ አካላት ጋር ቃለምልልስ አድርጓል፤ መረጃ ሰብሰቧል። ከዚህ በፊት የተዘጋጁ ሰነዶችን መርምሯል፤ ልዩ ልዩ ሰነዶችን ግብዓት መሠረት በማድረግም ነው ወደ ሥራው የተገባው። በቴክኖሎጂ ከፍተኛ ሚና ያላቸው ባለድርሻ አካላት ግብዓት እንዲሰጡ እና ሌሎች አማራጮች ማየት እንዲቻሉ እየተደረገ ነው። የግብዓት ማሰባሰቢያ መድረኩ ረቂቅ ፖሊሲው ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ቀርቦ ከመጽደቁ በፊት የመጨረሻ ሂደት አካል ነው።
የረቂቅ ፖሊሲው የቴክኒክ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዶክተር በአካል ግዛቸው በበኩላቸው እንደሚሉት፤ ፖሊሲውን መቅረጽ ያስፈለገበት ዋንኛ ምክንያት የሰው ሰራሽ አስተውሎት የራሱ የሆነ ልዩ ባሕሪይ ስላለው ነው። የሰው ሠራሽ አስተውሎት ብዙ ሀገራትን ተጠቃሚ ያደረገ፣ በርካታ ሥራዎች የሚከወኑበት ነው። በግብርናው፣ በጤናውና በሁሉም ዘርፎች ምርታማነትን በከፍተኛ ሁኔታ የሚጨምር እና ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ በመሆኑ ነው ብለዋል።
ዶክተር በአካል እንደሚሉት በዓለም አቀፍ ደረጃ ግዙፍ ኢኮኖሚ የሚያንቀሳቅሱ ሀገራት ከዲጅታል ቴክኖሎጂ ጋር ተያይዞ እንደ ፌስቡክ፣ ቲክ ቶክ እና ቲውተር ያሉ ፕላትፎርሞችን እያንቀሳቀሱ መሆናቸውን ጠቅሰው፤ በሀገራችን ግን አስፈላጊ የሆኑ ጥናታዊ ጽሑፎች በዩኒቨርሲቲዎች በሁለተኛ እና በሶስተኛ ዲግሪ/ ፒኤችዲ/ ፕሮግራሞች ላይ ሲሰሩ ቢታዩም መሬት ላይ ወርደው ተግባራዊ ሆነው በተጨባጭ ችግሮችን ሲፈቱ፤ ሁኔታዎች ሲቀይሩ እንደማይታዩ ይናገራሉ። ከዚህ የተበጣጠሰ ጥናታዊ ውጤት የተነሳ አስፈላጊውን ጥቅም ማግኘት አለመቻሉ አንድ ክፍተት መሆኑን ነው ዶክተር በአካል የሚገልጹት።
በሰው ሠራሽ አስተውሎት ተጨባጭ ለውጥ ለማምጣት ምን መሥራት አለብን ተብሎ ሲታሰብ መጀመሪያ ያለውን ክፍተት መረዳት ያስፈልጋል የሚሉት ዶክተር በአካል፣ ክፍተቱ ከተለየ በኋላ ዳታውን መሬት ላይ ለማውረድ ውስንነት እንዳለም ይጠቁማሉ። ከዚህም የግሉ ዘርፍ ተጠቃሚነትና ወሳኝ ሚና መጫወቱን የማይፈቅድ ሥርዓት ስለመኖሩ ተረድተናል ይላሉ። እነዚህን ክፍተቶች ለመሙላት ከፍ ባሉ የፖሊሲ ማዕቀፎች በሀገር ደረጃ የመንግሥት ጣልቃ ገብነት አስፈላጊ መሆኑን ጠቅሰው፣ ረቂቅ ፖሊሲ ወደ ማዘጋጀት የተገባውም ይህ ታይቶ መሆኑን ተናግረዋል።
እሳቸው እንደሚሉት፤ ረቂቅ ፖሊሲው ሰባት ቁልፍ ጉዳዮች የያዘ ነው። ቁልፍ ጉዳዮቹም የመረጃ አስተዳደር፣ የሰው ሃብት ልማት፣ ምርምርና ልማት፣ ድጋፍና ማበረታቻ፣ መሠረተ ልማት፣ የሕግ ማዕቀፍና ሥነ ምግባር መርሆች እና ዓለም አቀፍና አህጉር አቀፍ ትብብርና ትስስር የሚሉት ናቸው። እነዚህን ቁልፍ ጉዳዮች በመያዝ የዳታ አስተዳደርና ልማት በማልማት የሰው ሰራሽ አስተውሎትን መጠቀም፣ መሥራትና ማምረት የሚችል እና ሥነ ምህዳሩን መደገፍ የሚችል የሰው ኃይል ማፍራት ያስፈልጋል።
የረቂቅ ፖሊሲው ዝግጅት አሁን የደረሰበት ደረጃ ላይ እንዲገኝ ብዙ ሂደቶች እያለፈ መምጣቱን የሚናገሩት ዶክተር በአካል፤ ከ36 በላይ የሆኑ ከሰው ሠራሽ አስተውሎት ጋር ግንኙነት ያላቸው የመንግሥትና የግል ተቋማትና ባለድርሻዎች ግብዓት መሰብሰቡን ይገልጸሉ። ይህ የግብዓት ማሰባሰቢያ ውይይት በረቂቅ ፖሊሲው ላይ የሚደረግ ግብዓት ማሰባሰብ ሂደት የመጨረሻ መሆኑንም ይናገራሉ። ቀጣዩ ሂደት ሰነዱ በተገኘው ግብዓት ከዳበረ በኋላ በፕላንና ልማት ሚኒስቴር ተገምግሞ እንዲጸድቅና ተግባራዊ እንዲሆን እንደሚደረግ ያስረዳሉ።
ዶክተር በአካል እንደሚሉት፤ ፖሊሲ ጸድቆ ወደ ሥራ ሲገባ ተጠቃሚነት ይመጣል። ተጠቃሚነት ማረጋገጥ የሚለው ደግሞ ቴክኖሎጂውን ለሚጠቀመውም ሆነ ከቴክኖሎጂ የራቀውን ሰው ጭምር ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው። ለምሳሌ ያህል በግብርናው ዘርፍ “አፈሩ ጥሩ ነው ወይስ አይደለም፤ ዝናብ ይጥላል ወይስ አይጥልም፤ በዚህኛው ዓመት ምን ብዘራ ያዋጣኛል” የሚሉትን እና የመሳሰሉትን ለማወቅ የሰው ሠራሽ አስተውሎት የማሰብን ውሳኔ ሰው ሠራሽ በሆነ መልኩ ለማሽን(ለኮምፒዩተር) ያስተምራል። መልኩ ካስተማርነው ማሽኑ የሰለጠነ ነውና ገበሬንና ሌሎችንም የሚያማክርና አገልግሎት ሲያስፈልግም የሚሰጥ ይሆናል።
አንዱ የፖሊሲ ጉዳይ የሕግ ማዕቀፍ አስተዳደርና ሥነ ምግባር እንዲኖር ማድረግ እንደሆነ ነው ዶክተር በአካል ይናገራሉ። አሁን ላይ በዓለም አቀፍ ደረጃ በሰው ሠራሽ አስተውሎት ላይ ከተጋረጡበት ችግሮች ውስጥ የሚነገረው ነገር እውነተኛ አይደለም፤ ሰው ሠራሽ አስተውሎቱ ራሱን ቀይሮ ሌላ ነገር ሊሆን ይችላል፤ የሚጠቀመው ዳታ በሆነ አቅጣጫ የተዛባ ሆኖ ውሳኔዎችን ሊያዘባ ይችላል የሚሉ ስጋቶችም እንደሚነሱ ይጠቁማል፤ እኛ ገና ጀማሪዎች ብንሆንም በረቂቅ ፖሊሲው እነዚህን ጉዳዩች ታሳቢ መደረጋቸውን ይገልጻሉ።
በተመሳሳይም የሰው ሠራሽ አስተውሎት ከደቀነው ስጋት አንዱ የሥራ እድል ይቀንሳል የሚል እሳቤ መሆኑን የሚናገሩት ዶክተሩ በአካል፤ ለዚህም መፍትሄ ሊሆን የሚችለው ምርታማነትን መጨመርና ከፍተኛ የኢኮኖሚ አቅምን መገንባት ከተቻለ ሕዝቡን የሚጠቅም ነገር ማድረግ እንችላለን ማለት ነው ይላሉ። ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የሰው ጉልበት ዋጋ በጣም ዝቅተኛ መሆኑን ጠቅስው፤ ምናልባት ምርትና ምርታማነት በመጨመር በምናገኘው የኢኮኖሚ አቅም የነዚህን ሰዎች ገቢ በአገር ደረጃ መጨመር የሚያስችለን ሀሳብ ይኖረው ይሆናል ሲሉ ይናገራሉ። እነዚህ ችግሮች በተፈቱ ቁጥር የሀገር ኢኮኖሚ አቅም አብሮ እንደሚገነባ ገልጸው፣ የሰው ሠራሽ አስተውሎት እንደ ምርጫ የሚታይ ሳይሆን ግዴታ መሆን እንዳለበት ያብራራሉ።
ዶክተር በአካል እንደሚሉት፤ እስካሁን ፖሊሲ ባለመኖሩ በርካታ ጥናቶች መደርደሪያ ላይ ቀርተዋል። በትክክለኛ መረጃ ላይ መሠረት ያደረጉ ውሳኔዎችን መወሰን እየቻልን እንዳንወሰን አድርጓል። መረጃዎች ሌሎችን ለማጋራት የጠራ ካለመሆኑ አንጻር ብዙ ውሳኔዎች ላይ መድረስ ያለባቸው ሀሳቦች ጠፍተዋል፤ በተለያዩ ዘርፎች ብዙ ነገሮች መሥራት እየተቻለ እንዳይሰራ እንቅፋት ሆኗል። ዞሮ ዘሮ ረቂቅ ፖሊሲው በሰው ሠራሽ አስተውሎቱ ላይ የሚታየው አደጋ ሳይጠቅስና ለዚያም ደግሞ መታሰብ ያለባቸው ስትራቴጂዎች ሳያስቀምጥ አያልፍም።
የዓለም ሀገራት የሰው ሠራሽ አስተውሎትን መጠቀም ከጀመሩ ቆይተዋል። በዚህም ብዙ ርቀት ተጉዘዋል፤ እኛስ እንደ ሀገር እንዴት ነው ከኋላቸው ተነስተን ልንደርስበት የምንችለው ብለን ላቀረብንላቸው ጥያቄ ዶክተሩ በሰጠት ምላሽ እንዳሉት፤ አሁን እንደ ሀገር በሰው ሠራሽ አስተውሎት ዘርፍ እየተሰራ ያለው ዓለም ላይ ለመድረስ ነው። እነዚህም ከመሠረተ ልማት፣ ከዳታና ከሚስራባቸው ሲስተሞች አንጻር እያንዳንዳቸውን በማስልጠን፣ በመገንባት እና ቴክኖሎጂን በማሸጋገር የምናመጣቸው ናቸው ይላሉ።
እነዚህም መንግሥት ጣልቃ ገብቶ የገንዘብ ድጋፍ/ፈንድ/ በማድረግ፣ አሠራሮችን በመዘርጋት የሚስተካከሉ ይሆናል ሲሉ ጠቅሰው፣ አሁን ያለንበት ሁኔታ በደንብ ከሰራን ዓለም ላይ እንደርሳለን ብለዋል፤ ይህ ብቻም ሳይሆን ዓለምን አልፈን መሄድም የምንችልበት አቅም እንዳለን ያሳያል የሚሉት ዶክተሩ፤ አሁን በኛ አቅም መድረስ የምንችልበትን ቦታ፣ መድረስ የምንችልበት አቅም ካረጋገጥን ይበቃል ብለዋል።
የረቂቅ ፖሊሲው ዝግጅት የቴክኒክ የኮሚቴ አባል የሆኑት ዶክተር ጫላ መርጋ በበኩላቸው የሰው ሠራሽ አስተውሎት በጥንቃቄ መያዝ ያለበት ቴክኖሎጂ መሆኑን ይናገራሉ። ከደህንነት አንጻር ያለው ተፅእኖ ሰፊ መሆኑን የአደጉትን ሀገራት ተሞክሮ አስገንዝበው፣ ፖሊሲው መዘጋጀቱ በእጅጉ አስፈላጊ እንደሆነ ያመለከታሉ፤ በረቂቅ ፖሊሲው ላይ የቀረቡትን አስተያየቶችና ጥያቄዎችን በግብዓትነት በመውስድ እንደገና በማየት የሚካተቱበትን ሁኔታ ማመቻቸት እንደሚያስፈልግ ዶክተር ጫላ አመልክተዋል።
በቅርቡ የወጣ ዓለም አቀፍ መረጃ እንደሚያሳየው፤ የሰው ሰራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂ 30ሺ ሰዎች በ10 ዓመት ውስጥ የማይሰሩትን በጥቂት ደቂቃዎች መሥራት የሚያስችል፣ ትልቅ የቋንቋ ሞዴልን፣ ጥናታዊ ጽሁፎችን ሳይቀር የሚያዘጋጅና ከዚያም ያለፉ ብዙ ነገሮችን ማድረግ የሚችል እንደሆነ ያሳያል የሚሉት ዶክተር ጫላ፤ ይህ ደግሞ ከዚህ በፊት የነበረውን ነገር በማፋረስ ማሽኑ መማር ከቻለ ሰው ለምን ይማራል የሚለውን እሳቤ እንዳያመጣ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚያስፈልግም ጠቁመዋል።
የሰው ሠራሽ አስተውሎትን ተከትሎ የሚመጣ ቴክኖሎጂ ለሰው ልጅ ብዙ ነገሮች ሊያቀል የሚችል ብቻ እንዳልሆነ ተናግረው፣ የጎንዮሽ ጉዳት እንዳለውና ለዚህ ሁሉ ችግር መፍትሔ ለመስጠት ፖሊሲ ሊኖር እንደሚገባ ጠቁመዋል። ፖሊሲው ቴክኖሎጂ ያለውን በጎ ነገር በመጠቀም ሊያስከትል የሚችለውን ጉዳት ደግሞ ለመቀነስ የሚረዳ ነው ብለዋል። በአጠቃላይ በመድረኩ ባለድርሻ አካላት በረቂቅ ፖሊሲው ሰነድ ላይ የተለያዩ ጥያቄዎችና አስተያየቶችን አንስተዋል። ከመድረኩም ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽ በመስጠት የተነሱትን አስተያየቶች በግብዓትነት እንደሚወሰዱም ተመላክቷል።
ወርቅነሽ ደምሰው
አዲስ ዘመን ማክሰኞ ሐምሌ 11 ቀን 2015 ዓ.ም