ኢትዮጵያ ባለፉት 4 ዓመታት ባካሄደችው የመጀመሪያው ምዕራፍ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ- ግብር 25 ቢሊዮን ችግኞችን በመትከል በስኬት አጠናቅቃለች። ዘንድሮም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሁለተኛውን ምዕራፍ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ-ግብር ሰኔ 1 ቀን 2015 ዓ.ም «ነገን ዛሬ እንትከል» በሚል መሪ ሀሳብ በአፋር ክልል ማስጀመራቸው ይታወሳል። በዚህም 6 ነጥብ 5 ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከል ዕቅድ ተይዞ ከ7 ቢሊዮን በላይ ችግኞች ዝግጁ ሆነው የመተከያ ቀናቸውን እየጠበቁ ነው። እስካሁንም 3 ነጥብ 4 ቢሊዮን ችግኞች ተተክለዋል። በአንድ ጀምበር 500 ሚሊዮን ችግኝ የመትከል ጉዞም በመንገድ ላይ ይገኛል።
«ነገን ዛሬ እንትከል» የተባለው በምክንያት ነው። ኢትዮጵያ ለዓለም ምሳሌ የሆነ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ባህሏ እያደረገች ነው። የነገውም ትውልድ ይህን ይዞ እንዲቀጥል ዛሬ የምንተክለው ችግኝ ብቻ ሳይሆን ነገ የሚዳብር ባህልን ጭምር ነው።
ዓለምን እየፈተነ ያለውን የአየር ንብረት ለውጥ ለመቋቋምና ዘላቂ መፍትሄ ለማበጀት ችግኝ መትከል አማራጭ የሌለው መፍትሔ ነው። ዕጽዋት በልምላሜያቸው ለምድር ጌጥ ብቻ ሳይሆኑ ለጤናማ ሕይወት ዋስትና ናቸው። ለተፈጥሮ ሚዛን መጠበቅ ዘብም ናቸው። በዘመናት ሂደት የሰው ልጅ ብዝኃ-ሕይወትን እያመናመነ፣ አካባቢውን እያዛባ፣ ምድርን እያጎሳቆለ… የዓለምን የምቹነት ዋስትና በራሱ እጅ እየተነጠቀ መምጣቱ እሙን ነው። ይህም ቀጣይነት ያለው ጤናማ የሕይወት ዋስትና እንዳይኖረው በገዛ አንገቱ ላይ ሸምቀቆ እንዲያጠብቅ አድርጎታል።
ከትውልድ-ትውልድ የዕጽዋት መመናመን፣ የደን ሽፋን መራቆት፣ የአካባቢ መበከል ተዳምሮ የዓለምን ጉስቁልና እያባባሰው መጥቷል። የዓለምን ሕዝብ መልከ-ብዙ ለሆነ ቀውስም ዳርጓል። ይህን ሁሉን አቀፍ የአየር ንብረት ለውጥ ለመቀልበስ በጊዜ መላ ካልተበጀለት ቀውሱ እየተባባሰ፣ የወደፊት ትውልድም ይበልጥ ገፈት ቀማሽ ሆኖ ይቀጥላል። በተለይም ከምግብ ዋስትና ችግር አሁንም ድረስ ላልተላቀቀችው አፍሪካ ይበልጥ ስጋት ነው።
የምድርን ጤናማነት ጠብቆ ለነገው ትውልድ ማስረከብ የዚህኛው ትውልድ ኃላፊነትም ግዴታም ጭምር ነው። ቀጣዩ ትውልድ ባላጠፋው ነገር የተፈጥሮ የቅጣት ጅራፍ ሊያርፍበት አይገባም። የተራቆተች ሳይሆን ለምለም የሆነች ኢትዮጵያን ለትውልድ ማስረከብ ያለብንም ለዚሁ ነው።
በአረንጓዴ ዐሻራ ጤናማና ዘላቂ ከባቢ በመገንባት፣ ለነገ ትውልድ የተሻለ ዓለም ለማውረስ የአንገብጋቢው ጥያቄ ትክክለኛ መልስ ነው። ይህን አጠናክሮ መቀጠል የመንግሥት ሳይሆን የዚህ ትውልድ የቤት ሥራ ነው። በመላ ሀገሪቱ ከሊቅ እስከ ደቂቅ ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍሎች እያሳተፈ የሚገኘውም በዚሁ ምክንያት ነው።
ኢትዮጵያን በአፍሪካና በዓለም አቀፍ መድረክ የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ተምሳሌት ያደረገው ይህ ተሞክሮ፣ ከመንግሥት ቅስቀሳና ከግለሰቦች ጥረት ባለፈ ሀገራዊ ቅርፅ እየያዘ መምጣቱን ባለፉት አራት ዓመታት የተካሄደው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ-ግብር ትልቅ ማሳያ ነው።
ዛፍ እንደ ቅርስ፣ እንደ ሐውልት ታሪክ ማስተላለፊያ ነውና በየዘመኑ ትጉ ሰዎች ለትውልድ ቅርስ ትተው እንዳለፉት ይህም ትውልድ አረንጓዴ ዐሻራውን በማሳረፍ ለቀጣዩ ውለታ ማኖር ይገባዋል። ለልጅ ልጆቹ ዕዳ ሳይሆን ልማትን የሚያሸጋግርበት ዋነኛ መንገዱ አረንጓዴ ዐሻራ ነው። በዚህም ዛሬ ያለው ትውልድ የተሻለች ኢትዮጵያን የማሸጋገር ታሪካዊ ኃላፊነት አለበት።
ያለ ልዩነት ለነገው ትውልድ የተሻለች ሀገርን ለማስረከብ በአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ-ግብር ስኬት መረባረብ የሁሉም ዜጋ ኃላፊነት ነው። የአረንጓዴ ዐሻራ መነሳሳት የሀገራችንን የነገ ዕጣ ፈንታ የሚወስን፣ ጊዜውን የሚዋጅ ተግባር ነው። ኢትዮጵያ በተፈጥሮ የተቸረችው አየር ንብረትና መልክዓ- ምድር ለዚህ የሚጋብዝ ነው። ደን ልማት ዘላቂ ሥራ መሆን አለበት። ባለቤትነት እንዲጨምርም በወል መሬት ብቻ ሳይሆን በግል ይዞታም አረንጓዴ ዐሻራ መተግበር አለበት።
በአጠቃላይ የደን ልማት አካል የሆነው አረንጓዴ ዐሻራ ሀገራዊ ፋይዳው ሁለንተናዊ ነው። ከሀገራዊ ፋይዳው ባለፈ ቀጣናዊና ዓለም አቀፋዊ በረከቶችንም ተሸክሟል። የደን ልማት የቅንጦት ሳይሆን የሕልውና ጉዳይ ነው። በመሪ ቃሉ እንደተመላከተውም አረንጓዴ ዐሻራ የመጪው ትውልድ ቅርስና ውርስ ነውና፤ ሁሉም ዐሻራውን ሊያሳርፍና ለተተኪው ትውልድ ምቹና ደህንነቷ የተጠበቀ ሀገር እንዲያወርስ ይጠበቃል!
አዲስ ዘመን ሐምሌ 10/2015