በክብረ ወሰን የታጀበ ታሪክ ጽፈን ለትውልድ የሚተርፍ ገድል ፈጽመናል!

 ኢትዮጵያውያን የቱባ ባሕል ብቻ ሳይሆን በዘመናት ጅረት ውስጥ ሲታወስ የሚኖር የማይደበዝዝ ታሪክ ባለቤቶች ናቸው። እነዚህ የየዘመናት ታሪኮቻቸው ደግሞ ለየዘመኑ ትውልዶች መታወሻ ብቻ ሳይሆኑ፣ ለተተኪ ልጆቻቸው የኩራት ምንጭና የሌላ ታሪክ መሥሪያ አቅም ሲሆኑ ማየት የተለመደ ነው።

በዓድዋ የተፈጸመው የአያት ቅድመ አያቶች ታሪክ፣ ዛሬም ድረስ ኢትዮጵያውያን ታሪክን ከመዘከር በላይ በክብርና ሉዓላዊነታቸው እንዳይደራደሩ አድርጓቸዋል። ዳግማዊ ዓድዋ የተባለው የዓባይ ግድብም ኢትዮጵያውያን ሉዓላዊነታቸውን ምሉዕ የሚያደርጉበትን የኢኮኖሚው መስክ አቅም ብቻ አይደለም። ይልቁንም የዘመናት ቁጭትን መልስ የሰጡበት፤ እንደ ቀደምቶቻቸው ሁሉ በዘመናቸው አዳዲስ ታሪክ መጻፍ እንደሚችሉ ያረጋገጡበት ታላቅ ብሔራዊ ፕሮጀክታቸው እንጂ።

እነዚህ ድንቅ ኢትዮጵያውያን ታዲያ ዛሬ ደግሞ የዓለም ራስ ምታት ሆኖ ምድራችንን እየናጣት ላለው ሌላ ሕመም ፈውስ ይዘው ቀርበዋል። በአየር ንብረት ለውጥ ጥቁር ጥላ ላይ ብርሃንን ፈንጥቀው ጽልመቱን ሊገፍፉ ታላቅ ተጋድሎን ጀምረዋል። ባለፉት አራት ዓመታት 25 ቢሊዮን ችግኝ በመትከል ኢትዮጵያን አረንጓዴ አልብሰው የችግሩን ጠርዝ መናድ፤ የችግር ትብታቡንም ክር መተርተር ጀመሩ። ታዲያ እነዚህ ዓመታት 25 ቢሊዮን ችግኞች የተተከሉባቸው ብቻ አይደሉም፤ በአንድ ጀንበር 350 ሚሊዮን ችግኞችን በመትከል አዲስ ታሪክ የጻፉባቸውና ዓለምአቀፍ ክብረወሰን በእጃቸው ያስገቡበትም ነበር።

ኢትዮጵያውያን የማይቋጩትን አይወጥኑምና ዘንድሮም ምዕራፍ ሁለትን አሐዱ ብለው ጀምረዋል። በቀጣይ አራት ዓመታት 25 ቢሊዮን ችግኝን ለመትከል ውጥን በተያዘበት በዚህ ምዕራፍ፤ በዘንድሮው ዓመት ብቻ ስድስት ነጥብ ሦስት ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከል ነው እየተሠራ ያለው።

ከዚህ ባሻገር እንደ መጀመሪያው ምዕራፍ ሁሉ በአረንጓዴ አሻራው ጉዞም ሌላ አዲስ ታሪክ የመጻፍ ውጥን ተቀመጠ። ይሄም በራስ የተያዘን ሪከርድ የመስበር እና በአንድ ጀንበር 500 ሚሊዮን ችግኞችን የመትከል ነበር። ይሄንኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ይፋ ባደረጉበት ወቅት፤ ይሄንን መፈጸም ትልቅ ሀገራዊ ታሪክም፣ ኃላፊነትም ስለመሆኑ አስረግጠው ተናገሩ። በዕለቱም (ሐምሌ 10 ቀን 2015 ዓ.ም) መላው ኢትዮጵያውያን ለዚሁ ተግባር ማልደው ወደ ችግኝ ተከላ እንዲሰማሩ አሳሰቡ።

ቀድሞውንም የዛፍን ፋይዳ የሚረዳው እና የመሪዎቹን ቀና ዓላማ የሚገነዘበው ኢትዮጵያዊም ታሪክ መጻፍ ልማዱ ነውና ለዚህ አዲስ ታሪክ ራሱን አዘጋጀ። ዕለቱም ደረሰና ማልዶ ዝናብና ብርድ ሳይበግረው በሙሉ ልብና ተነሳሽነት ወደ ችግኝ መትከያ ስፍራዎች ተመመ። ከልቡ ተነስቶ፣ በሙሉ ፍላጎቱ ተሰማርቶ፣ ስለ ሀገርና ክብሩ ሠርቶ ከመሪው ጎን ሆኖ በአረንጓዴ አሻራው ጉዞው ሌላ የሚነገርና የሚተረክለት አዲስ ታሪክ ጻፈ።

ኢትዮጵያውያን ከዓድዋ ተራሮች የድል ውሎ የወረሱት ለአገር ሉዓላዊነትና ለማንነት ክብር ያለመደራደር ጉዞ ሳይደበዝዝ፤ በዓባይ ግድብ የጀመሩት ሌላ የነጻነት መንገድ እጅን በአፍ እንዳስጫነ፤ ዛሬ ደግሞ ዓለም የተፈተነበትን ሕመም ለመፈወስ በአረንጓዴው መንገድ አረንጓዴ ምድርን ለመፍጠር ባደረጉት ተጋድሎ ዓለምን አስደምመዋል። ከራሳቸው ጋር ተወዳድረው አሸናፊ ሆነዋል፤ ችግሮችን ድል ነስተው ኃያልነታቸውን ገልጠዋል።

በዚህም ይሄንን ሐቅ ዓለም ባይፈልግም እንዲመለከታቸው፤ ቢመርረውም እንዲያዳምጣቸው፤ ቢጎረብጠውም እንዲያስተውላቸው አስገድደውታል። ተግባራቸው ከራስ ያለፈ ለዓለም ፈውስን፤ መንገዳቸው ከቤት ያለፈ ለጎረቤት ምቾትን፤ ተግባራቸው ከውስጥ ለውጪው ዓለም አርዓያነት አጎናጻፊነትን እያረጋገጡ መገስገሳቸውን ቀጠሉ።

ምክንያቱም የአረንጓዴ አሻራ ጉዞው የአየር ንብረት ተፅዕኖን አደብ የሚያስይዝ ብቻ ሳይሆን፤ ለምግብ ዋስትና፣ ለሥራ ዕድል ፈጠራ፣ ለግብርናና ኢንዱስትሪያቸውም ስኬታማነት ዋስትና ሆኖ የሚያገለግል መሆኑን ካለፉት አራት ዓመታት ጉዟቸው አረጋግጠዋል።

አሁንም በአራት ዓመት 25 ቢሊዮን ችግኝ ለመትከል መነሳታቸውም ሆነ በአንድ ጀንበር 500 ሚሊዮን ችግኝ ተክለው ማስደመማቸው ከዚሁ ሁሉን አቀፍ ፋይዳ የመነጨ ጭምር ነው። ይሄ ደግሞ ኢትዮጵያ ብቻዋን በሯን ዘግታ የምትጠቀምበት አይደለም። ምክንያቱም የአየር ንብረት ለውጡ ፈተናው የዓለም እንደመሆኑ መፍትሔውም የጋራ ነው።

ኢትዮጵያውያን ይሄን በሚገባ ስለምንገነዘብ ከችግሮቻችን ልቀን ለመገኘት አቅም በሚሆነን በአረንጓዴ አሻራ ጉዟችን የራሳችንን ሪከርድ ሰብረን አዲስ ታሪክ ጽፈናል፤ የምንወዳትን ሀገራችንን በአንድ ጀንበር በ500 ሚሊዮን ችግኞች አረንጓዴ አልብሰናታል። በክብረ ወሰን የታጀበ ታሪክ ጽፈንም ዘመን ተሻጋሪ ገድል ፈጽመናል!

አዲስ ዘመን ማክሰኞ ሐምሌ 11 ቀን 2015 ዓ.ም

Recommended For You

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *