በአረንጓዴ አሻራ የተጨማሪ አዲስ ታሪክ ባለቤት መሆን

የዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ሰሞኑን ትኩረት ሆነው ከሰነበቱት አጀንዳዎች ውስጥ አንዱ ሰኔ 28 ቀን 2015 ዓ.ም በዓለማችን እጅግ ሞቃታማው ቀን ሆኖ መመዝገቡ ነው። የአሜሪካ የአካባቢ ትንበያ ብሔራዊ ማዕከል መረጃ እንዳመላከተው፤ የዓለም አማካይ ሙቀት እንደ ሰኔ 28ቱ ቀን ከፍ ብሎ አያውቅም። በዚሁ ቀን የተመዘገበው አማካይ የዓለም ሙቀት 17 ነጥብ 01 ዲግሪ ሴሊሺየስ (62 ነጥብ 62ዲግሪ ፋራናይት) ነው ።

ከዚህ ቀደም እጅግ ሞቃታማ የዓለማችን ቀን የተባለው በፈረንጆቹ አቆጣጠር 2016 ነሐሴ ወር፤ አማካይ 16 ነጥብ 92 ዲግሪ ሴሊሺየሽ (62 ነጥብ 46 ዲግሪ ፋራናይት) የተመዘገበው ሲሆን፤ ይህም ዘንድሮ ከተመዘገበው የሙቀት መጠን ጋር ሲነጻጻር የከባቢ አየር ሙቀት የመጨመሩ እውነታ የቱን ያህል አሳሳቢ እየሆነ እንደመጣ አመላካች ሆኗል ።

በዚሁ ሙቀት ሳቢያ የአሜሪካ ደቡባዊ ክፍል ነዋሪዎች እየተሰቃዩ መሰንበታቸው፤ ችግሩ በቻይና ከ35 ዲግሪ ሴሊሺየስ በላይ ሆኖ እንደቀጠለ በዚህም ቻይናውያን ለተመሳሳይ ችግር መጋለጣቸውን የተለያዩ ዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙኃን ዘግበውታል። በአፍሪካ ሰሜናዊ ክፍልም እስከ 50 ዲግሪ ሴሊሺየስ የሚደርስ ሙቀት የተመዘገበ ሲሆን፤ በቀዝቃዛማነቱ የሚታወቀው የአንታርክቲካ ክፍል ሳይቀር ሙቀት ማስመዝገቡ ተመልክቷል ።

ዓለም አቀፉ የዓየር ንብረት ለውጥ ተመራማሪ የሆኑት ፍሪዴሪክ ኦቶ በጉዳዩ ዙሪያ እንደተናገሩት “አሁን እየሆነ ያለው አሳዛኝ ነገር ነው። በአየር ንብረት ላይ እየታየ ያለው ለውጥ እጅግ አስደንጋጭ እና በሰው ልጆች እና ሥነ ምሕዳር ላይ የተወሰነ የሞት ፍርድ ውሳኔ ነው” ብለዋል። በተመሳሳይም የዓለም ጤና ድርጅት በዓለማችን ላይ እየተከሰተ ያለው የአየር ንብረት አሳሳቢ ሆኖ መቀጠሉን በመግለጽ፤ ችግሩ እየተባባሰ በመምጣቱ በዓለማችን ላይ ረሃብ፣ ስደት እና የተለያዩ በሽታዎች ስጋት መፈጠሩን አመልክቷል ።

የአፍሪካ ቀንድ አካባቢም ቢሆን በአንድም ይሁን በሌላ ከድርቅ ከችግሩ ጋር በተያያዘ፤ ላለፉት ስድስት አስርተ ዓመታት ለድርቅ አደጋዎች ተጋላጭ ሆነዋል። በየአስር ዓመቱ የሚከሰተው ይኸው የድርቅ አደጋ አሁን አሁን በየዓመቱ እየተከሰተ ከፍ ያለ ሰብዓዊ ቀውስ እያስከተለ ይገኛል ።

መፍትሔው ምንድን ነው ?

ለችግሩ ዘላቂ መፍትሔ የሚሆነው ከሁሉም በላይ የተፈጥሮ አካባቢን ማከም ነው። ለዚህ ደግሞ በዋንኛነት ሊጠቀስ የሚችለው በኢትዮጵያውያን እየተተገበረ ያለው አረንጓዴ አሻራ ነው። ከአምስት ዓመታት በፊት ወደ ሥልጣን በመጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ዶ/ር አነሳሽነት የተጀመረው ይህ ሀገርን አረንጓዴ የማልበስ ንቅናቄ ችግሩን ለመቅረፍ ለሚደረገው ጥረት ከሀገር አልፎ ዓለም አቀፍ ተሞክሮ እንደሚሆን ይታመናል።

በእርግጥ ቀደም ባሉት ዘመናት የነበሩ የኢትዮጵያ መሪዎች ለአካባቢ ጥበቃ ልዩ ትኩረት ሰጥተው ይንቀሳቀሱ እንደነበር የታሪክ ማኅደራት ያስረዳሉ። ከዳግምዊ ምኒሊክ ጀምሮ ያሉ መሪዎች በየዘመናቸው ችግኞችን ተክለዋል፤ ሕዝቡም እንዲተክል አበረታተዋል። የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ዶ/ር አስተዋፅዖ ግን በአይነቱ ለየት ያለውና ግዝፈት ያለውም ጭምርም ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገና ወደ ሥልጣን በመጡ ማግስት፤ በአረንጓዴ አሻራ በኩል በአራት ዓመታት ውስጥ 20 ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከል መታቀዱን አስታውቀው፤ ዜጎችን ተከላው ስኬት ርብርብ እንዲያደርጉ ጥሪ ሲያደርጉ በጉዳዩ ዙሪያ ለመዘባበት የሞከሩ አልጠፉም ነበር። በመጀመሪያ ዓመት ከ4 ቢሊዮን በላይ ችግኞችን፤ እንዲሁም በአንድ ቀን ከ350 ሚሊዮን በላይ ችግኞችን መትከል መቻሉ፤ ሀገርን እንደ ሀገር የትልቅ ዓለም አቀፍ ታሪክ ባለቤት ማድረግ አስችሏል።

ጉዳዩን በቅርብ የተረዱ ወገኖች፣ የአረንጓዴ አሻራ የሀገሪቱን የተፈጥሮ አከባቢ በማከም፤ የሚታይ እና የሚጨበጥ ለውጥ እያስገኘ ስለመሆኑ ምስክርነታቸውን ይሰጣሉ፤ የአረንጓዴ ዕፅዋት ሽፋንን እንዳሳደገ፣ የአየር ንብረት ለውጥን እየተከላከለ እና የሰዎች ሕይወት ላይ ለውጥ እያመጣ እንደሆነም ይናገራሉ።

ሀገሪቱ እያከናወነችው ያለው የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር/አረንጓዴ አሻራ/ ሀገሪቱን በአረንጓዴ ከማልበስ ባሻገር ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸውን የፍራፍሬ ችግኞች በመትከል የዜጎችን ተጠቃሚነት የማሳደግ ስትራቴጂክ ተልዕኮ እንዲይዝም እየተደረገ ነው።

ለዚህ ደግሞ ዘንድሮ ከሚተከሉ ችግኞች ውስጥ የፍራፍሬ ችግኞች /አቮካዶን፣ ፓፓያን ወዘተ/ እንዲካተቱ መደረጉ አንድ ማሳያ ነው። ይህም ከኢኮኖሚ ጠቀሜታው በተጨማሪ በምግብ እራስን ለመቻል ለሚደረገው ሀገራዊ ትኩረት አቅም እንደሚሆን ይታመናል።

እስካሁን ባለው ሁኔታ በመጀመሪያው ዙር የአረንጓዴ አሻራ ለመትከል ከታቀደው 20 ቢሊዮን ችግኝ ከእቅዱ በላይ 25 ቢሊዮን መትከል ተችሏል። ይህ ሀገርን አረንጓዴ የማልበስ ዘመቻው በመንግሥት ሆነ በመላው ሕዝቡ የተሰጠውን ትኩረት አመላካች ነው ይህንኑ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስም በሚቀጥሉት ሁለት የክረምት ወራት 6 ቢሊዮን ችግኞችን በመትከል የተተከሉትን ችግኞች ቁጥር 31 ቢሊዮን ለማድረስ በዕቅድ ተይዟል።

ሰኔ 1 ቀን 2015 የተጀመረው የዘንድሮ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ግለቱን ጠብቆ በመጓዝ ላይ ይገኛል። በትናንቱም እለት በአንድ ጀንበር 566 ሚሊዮን በላይ ችግኞችን በመትከል የቀደመውን የ350 ሚሊዮን ሪከርዳችንን አሻሽለናል። ቀኗ ለኢትዮጵያውያን ልዩ ታሪካዊ ቀን ሆና አልፋለች። ሀገርና ሕዝብንም የአዲስ ታሪክ ባለቤት ማድረግም አስችላለች!።  

እስማኤል ዓረቦ

 ይህ አምድ በተለያዩ ፖለቲካዊ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ዜጎች ነፃ ሀሳባቸውን የሚሰጡበት ነው።በዓምዱ ላይ የሚወጡ ጽሁፎች የዝግጅት ክፍሉን አቋም አያመለክቱም።

አዲስ ዘመን ማክሰኞ ሐምሌ 11 ቀን 2015 ዓ.ም

Recommended For You

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *