ኢትዮጵያ የበርካታ ታሪክና ቅርስ ባለቤት ናት። እነዚህ ቅርሶች እና የተለያዩ ታሪኮች ተቀንብበው ከሚገኙበት የአገራችን ክፍል ውስጥ የትግራይ ክልል አንዱ ነው። ክልሉ በርካታ የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ ቅርሶች ባለቤት ሲሆን በተለይ የአክሱም ሀውልት እና አልነጃሺ የቅርሶቹ ሁሉ አውራ ተደርገው ይወሰዳሉ። በክልሉ ያሉ የቱሪዝም ሀብቶች በምን መልኩ ተይዘዋል? ኢኮኖሚያዊ ፋይዳቸውን የበለጠ በማሳደግ ገቢ ለማግኘት ምን ዓይነት ስራዎች እየተከናወኑ ነው በሚሉና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ከክልሉ የባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ብርክቲ ገብረመድህን ጋር ያደረግነውን ቃለ ምልልስ እንደሚከተለው አቅርበነዋል።
አዲስ ዘመን:- በአጠቃላይ በትግራይ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ለምን ያህል ቦታዎች ተደራሽ ናችሁ፤ ምን እንቅስቃሴስ እያደረጋችሁስ ነው?
ወ/ሮ ብርክቲ፡- እንደሚታወቀው ትግራይ ብዙ የቱሪዝም ሀብቶችና መዳረሻዎች፤ ብዙ የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ ቅርሶችና ታሪኮች ባለቤት ናት። በክልሉ ባሕልና ቱሪዝም እንደ ኤጀንሲ በተለያዩ ተቋሞች ውስጥ የተለያየ አደረጃጃት ነበረው። ክልሉ ብዙ ታሪካዊ ቅርሶች፤ የትውልድ ሀብቶች ያለው በመሆኑ ከ2008ዓ.ም መጨረሻ 2009 ዓ.ም መጀመሪያ ራሱን ችሎ በቢሮ ደረጃ ተቋቁሟል።
አዲስ ዘመን፡- በክልሉ ምን ያህል ወረዳዎች ፅህፈት ቤት ከፍታችኋል?
ወ/ሮ ብርክቲ፡- በአጠቃላይ 52 ወረዳዎች አሉ። ከእነዚህ ውስጥ በ23 ወረዳዎች የባህልና ቱሪዝም ቢሮዎች በወረዳዎች ስር ጽ/ቤቶች ተከፍተዋል።በክልል በቢሮ ደረጃ በወረዳም በጽ/ ቤት ደረጃ የተቋቋመው ብዙ ሀብቶችና ብዙ ታሪካዊ ቅርሶች ስላሉን ነው። ለእነዚህ የሚመጥን አደረጃጃት መኖር አለበት ተብሎ ነው የተሰራው። አሰራሩን አደረጃጀቱን ቀርቦ የሚከታተል ባለሙያና አመራር ስላለ ብዙ መሻሻሎች አሳይቷል።
አዲስ ዘመን፡- በክልሉ ብዙ ታሪካዊ የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ ቅርሶች አሉ። የቱሪዝም አቅሙ ምን ያህል ነው? የቱሪዝም ፍሰቱስ እንዴት ይገለፃል?
ወ/ሮ ብርክቲ፡- ባሕልና ቱሪዝም በክልል ደረጃ ትልቅ የኢኮኖሚ ለውጥ ሊያመጣ የሚችል ዘርፍ ነው። ብዙ ታሪካዊ ቦታዎች አሉ። እንደ እነአክሱም ሀውልቶችና ነባር ሕንጻዎች በአለም ደረጃ የተመዘገቡ ቅርሶች አሉ። እንደነ አልነጃሽ መስጊድ ሙስሊሞችና ክርስቲያኖች ሃይማኖታቸው ሳይለያቸው የአብሮነት መንፈስ የመዋሀድና የመዋደድ መንፈስ ያሳዩበት ታሪካዊ ቅርስ አለ። ክርስቲያኖች ሙስሊሞችን በፍቅር የተቀበሉበት ሁኔታ ትልቅ ማሳያ ሆኖ ለአለም የሚያስተምር ነው አልነጃሺ መስጊድ። ትልቅ የቱሪስት መዳረሻ ነው። በገራአልታ አካባቢዎች የመልክአ ምድሩ አቀማመጥ በጣም ሳቢና ውብ የሆነ ለቱሪስት መስህብ የሆኑ የተለያዩ ተራራዎች አሉ። በገራአልታ ብቻ ሳይሆን በክልሉ ከ120 በላይ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት የሚገኙበት ክልል ነው። ሌላም የተለያዩ አኗኗር ባህል አለባበስ አመጋገብ ያለበትም ክልል ነው። በቱሪስት ዙሪያ ስናይ በክልሉ ብዙ የስራ እድል ሊፈጥር የሚችል እምቅ አቅም ያለው ዘርፍ ነው። ብዙዎችን ደምረን ስናይ ክልሉ ከፍተኛ የሆነ በቱሪዝም ገቢ ሊያመጣ የሚችል ነው። ለዚህም ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት መሰራት አለበት በሚል በሙሉ አቅም ወደስራ የተገባው። አምና ብቻ በ2010 ወደ 51 ሺህ የውጭ ቱሪስቶች ክልሉን ጎብኝተዋል። በ9 ወራት ውስጥ ብቻ። በ2011 የዘጠኝ ወር አፈጻጸሙን ስናይ ቁጥሩ ጨምሮ ወደ 72 ሺህ የውጭ ቱሪስት በትግራይ ክልል የሚገኙ ታሪካዊ ቦታዎችንና ታሪካዊ ቅርሶችን ጎብኝቷል።
አዲስ ዘመን፡- በአብዛኛው ቱሪስቱ ትኩረት የሚያደርግበት ቦታ የት የት ነው ?
ወ/ሮ ብርክቲ፡- አክሱም ነው። በአለም ደረጃ የሚታወቅ ቅርስ ስለሆነ። ብዙ ታሪክ ያለበት ክርስትና ሃይማኖት የገባበት፤ የአለም ስልጣኔ መጀመሪያ የነበረበት የጥንታዊቷ ኢትዮጵያ ትልቅ ስልጣኔ ጫፍ ላይ ደርሶ የነበረበት የአክሱም ስልጣኔ እንደመሆኑ ብዙዎችም አለም አቀፍ ቱሪስቶች ያውቁታልና አሁንም ግዙፍ የቱሪስት መዳረሻ ነው። በብዛት ይመጣሉ። ከአክሱም ቀጥሎ የቱሪስቶች መዳረሻና ትኩረት የገረአልታ ተራሮች ናቸው።ድሮ ብዙ አይታወቅም ነበር የገረአልታ ተራራ። ዛሬ ላይ በደምብ እየተጎበኘ ነው።እዛ ቦታ እነ አቡነ የማታ የሚባሉ ከድንጋይ የተፈለፈሉ አብያተ ክርስትያናት አሉ። በዚያው ስፍራ ላይ ሌሎችም ብዙዎች አሉ። 120ዎቹ ፍልፍል አብያተ ክርስቲያናት በክልሉ ያሉ ሆኖ በገረአልታ ፤በአጽቢ ፤በሳእሲ ጻእዳ አምባ፤በውቅሮ በሌሎችም ቦታዎች የሚገኙ ናቸው። በገራአልታ አቡነ የማታ ከዘጠኙ ቅዱሳን ከሚባሉት ተሰአቱ ቅዱሳን ጋር ይገኛሉ ማለት ነው። በዚያ አካባቢ ጥሩ ግልጋሎት የሚሰጡ ሁለት ሎጆች አሉን። አንዱ ገራአልታ ሎጅ የሚባል ነው። የእኛ አላለቀም እንጂ ትልቅ በመገንባት ላይ ያለ ሎጅ አለ።
አዲስ ዘመን፡- ሎጆቹን የገነባቸው ማነው ?
ወ/ሮ ብርክቲ፡- የውጭ ባለሀብት ነው። ሁለቱን ሎጆች ነው ጥሩ የቱሪስት መዳረሻ ያልናቸው። ሌሎችም አሉን ብዙ። አክሱም ሎጅ አለ። ብዙ የግል ሆቴሎችም አሉ።
አዲስ ዘመን፡- በክልሉ የቱሪስት መዳረሻ ተብለው የተመዘገቡትን የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ ቅርሶች ያሉዋቸውንም አብረው ቢገልጹልን ?
ወ/ሮ ብርክቲ፡- የመዘገብናቸው ተንቀሳቃሽና የማይንቀሳቀሱ ቅርሶች በሚል ነው። ተንቀሳቃሽ ቅርሶች ከ3000 በላይ ይዘናል።
አዲስ ዘመን፡- ተንቀሳቃሽ ቅርስ ከቦታ ቦታ የሚዘዋወር ነው ?
ወ/ሮ ብርክቲ፡- የድሮ የብራና መጻህፍት፤ ንዋየ ቅዱሳን፤መስቀሎች፤ እጀጥበብ ስራዎች ወዘተ አሉ። እነዚህ ተንቀሳቃሽ ናቸው። የማይንቀሳቀሱት ደግሞ በቦታው ተተክለው የኖሩ ያሉ ታሪካዊ ቅርሶች፤ ከአለት ድንጋይ የተፈለፈሉ አብያተ ቤተክርስቲያናት ናቸው። ራሱ አልነጃሺ መስጊድ ሕንጻው አርክቴክቸሩ የሚዳሰስ ቅርስ ነው። አክሱምና ገረአልታ በብዛት አሉ። ሌሎቹም ባሕላዊ ቅርሶች የሚዳሰሱትም የማይዳሰሱትም በክልሉ የተለያዩ ቦታዎች ይገኛሉ።
አዲስ ዘመን፡- የታሪክና የቅርስ ጥናት ተመራማሪዎች ከእናንተ ቢሮ ጋር ይሰራሉ?
ወ/ሮ ብርክቲ፡- በትግራይ ክልል አራት ዩኒቨርሲቲዎች አሉ። እነዚህ አራት ዩኒቨርሲቲዎች የተለያዩ ዲፓርትመንቶች ከፍተዋል። በባህልና በቱሪዝም ዙሪያ የሚሰሩ። በዚህ ዙሪያ የሚያጠኑ ተመራማሪዎችና ዲፓርትመንቶች አሏቸው። እነሱ ጥናትና ምርምር ያደርጋሉ። በወረዳ ደረጃ ያሉ የእኛ ባለሙያዎችም አሉን። አመራርም አሉን። በእዛ ዙሪያ በየአካባቢው ምን አይነት ባህልና ቅርስ ነው ያለው የሚለው በየአመቱም ይመዘገባል። እንዳይጠፋም ይቆጠራል ። ራሱ ጥንት የነበረው ባህል እንዳይጠፋ እንዲያሳድጉ በደንብ ክትትል ይደረግበታል።
አዲስ ዘመን፡- በአክሱም ዘመን የነበሩት ለመጀመሪያ ጊዜ ኢትዮጵያ የተጠቀመችበት የጥንት ሳንቲሞች በቁፋሮ ተገኝተዋል። ጠፍቶ የነበረና የተገኘ ከተማ አለ። የት ነው የተገኙት ?
ወ/ሮ ብርክቲ፡- ማይሹም የሚባል ቦታ በሽሬ አካባቢ ነው። ከአክሱም በፊት የነበረ ከተማ ነው። አርኪዮሎጂካል ሳይት ነው። ብዙ የቁፋሮ ቦታዎችም አሉን። መዝግበነዋል። ብሮሸርም አለው። የእኛም አርኪዮሎጂስቶች አሉ በቢሮአችን። የሚያጠኑት የውጭ ባለሙያዎች ናቸው። አብረው ይሰራሉ።
አዲስ ዘመን፡- በክልሉ የተዘጋጀ የቱሪዝም ፕላን አለ ?
ወ/ሮ ብርክቲ፡- ይሄ የታተመው በግለሰብ ደረጃ ነው። እንደ መንግስትም የእኛ ቢሮ አሳትሞ ነበር። የሚሻሻል ነገር ሊኖረው ይችላል። ‹ጋይድ ቡኩም› (መጠቆሚያ መጽሀፉም) አለን። ቱሪስት ፕላን አለን። ቴክኖሎጂ የምንጠቀምበት ፌስ ቡክ አካውንትና በድረ ገጽ የምንጠቀምበትም አለን። ይሄን በየጊዜው በሚገኙ አዳዲስ መረጃዎች እናሻሽላለን። ከጥቂት ቀናት በፊትም በግለሰብ ተሰርቶ የተመረቀ አለ። ተጋግዘን ነው የሰራነው። ሰርቶም እዩልኝ ብሎ ወደ እኛ ቢሮ ነው ያመጣው። ቱሪስት ቦታዎች ተካተዋል አልተካተቱም የሚል የእኛ ባለሙያዎች ምክርና ድጋፍ ሰጥተውታል። እንዲያወጣው እኛም ደግፈነዋል።
አዲስ ዘመን፡- እስከአሁን ያወራነው ከውጭ አገር በሚመጡ ቱሪስቶች ዙሪያ ነው። የእኛ ሕዝብ የራሱን ታሪክና ቅርስ ይጎበኛል፤ የቱሪስት ፍሰቱ አድጎአል? ቢሮአችሁ ይሄን ለማሳደግ ምን እየሰራ ነው?
ወ/ሮ ብርክቲ፡- በዘንድሮ አፈጻጸማችንም ሆነ ከዚህ በፊት የምናየውም ቢሆን ያለን መሰረታዊ ችግር በዚህ ዙሪያ ነው። የሀገር ውስጥ ቱሪዝም አላደገም።ያሉን ባህልና አስተሳሰብ ገና ብዙ አልተለወጠም። የራሳችንን ነገር አድንቀን ባህላችንን ታሪካችንን ማንነታችንን ለማወቅ እንደ ውጭው ጎብኚ አይደለንም። ክፍተት አለብን። ለምሳሌ መቀሌ ላይ ሆኖ የራሱ የሆነውን ታሪካዊ ቦታ ወይም የቱሪስት መስህቦችን ሄዶ ለመጎብኘት፤ ለማየት ያለው ጥረት በጣም የቀነሰ ነው። ይህ ሁሉም ኢትዮጵያውያን ላይ ያለ ችግር ነው። የራሳችንን ለማየት ለማድነቅ ለመጎብኘት ብዙ ተነሳሽነት የለንም።
አዲስ ዘመን፡- ችግሩን ለመቅረፍ ምን ሰራችሁ ምንስ አቅዳችኋል ?
ወ/ሮ ብርክቲ፡- እኛ ችግሩን ፈትሸነዋል። ለምንድ ነው የእኛ ሰው ባህሉን ታሪኩን ቅርሱን ለማወቅ ጥረት የማያደርገው? ተተኪው ትውልድም ይሄንን ካላወቀ እንዲያውቅ ካልተደረገ ጥሩ ደረጃ አንደርስም። ከውጭ ሀገር መጥቶ ያለንን ባህል ታሪክ ቅርስ ሲያይ ሲመለከት ሲያጠና እኛ የራሳችንን ለምን አናይም የሚል የቅስቀሳ ስራ በስፋት በህዝቡ ውስጥ እንሰራለን። በሚዲያ፤ በትምህርት ቤቶች የሚዲያ ክለቦችና በሀገርህን እወቅ ፕሮግራም በሌሎች ዘዴዎችም እንሰራለን። በደንብ የተጠናከረ አይደለም። ድክመቱ የሁላችንም ነው ብለን እንወስዳለን። ባለሀብቱም ትኩረት አይሰጥም። እዚሁ እየኖረ አቅም እያለው አክሱምን ገረአልታን ወይም ሌሎች ታሪካዊ ቦታዎችን የማያውቅ ብዙ ነው። ስለዚህም በስፋት መስራት ያለብን የሰዎችን አስተሳሰብና አመለካከት በመለወጥ ደረጃ መሆኑን አምነንበት ውጤት ለማስገኘት እየተንቀሳቀስን ነው። ባህላችንም እየተመረዘ እየተበከለ ነው። ይሄን ሁሉ ወደ ነበረበት ለመመለስ በእኛነታችን እንድንኮራ ተተኪው ትውልድም በራሱ ባህል ቅርስ ታሪክ የሚኮራ እንዲሆን ግንባር ቀደም ሆነን መስራት ከሁላችንም ይጠበቃል።
አዲስ ዘመን፡- ለሰጡን ማብራሪያ እናመሰ ግናለን።
ወ/ሮ ብርክቲ፡- እኔም አመሰግናለሁ።
አዲስ ዘመን ግንቦት 1/2011
በወንድወሰን መኮንን