በሀገራችን ዘመናዊ ትምህርት ከመጀመሩ ቀደም ብሎ በአብዛኛው የትምህርት ስርአቱ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ጋር የተሳሰረ እንደነበር የታሪክ መዛግብት ያስረዳሉ፡፡ በወቅቱም ቤተክርስቲያኗ ማንበብና መጻፍን ጨምሮ መንፈሳዊ አስተምህሮዎችን ያካተቱ የተለያዩ ትምህርቶችን ስትሰጥ ቆይታለች፡፡
ዘመናዊ ትምህርት ከተጀመረ በኋላ ግን የትምህርት ስርአቱ ሀገራዊ ተልእኮ ተቀርጾለት የተማረ የሰው ኃይል ለማፍራት በስፋት ሲንቀሳቀስ ቆይቷል፡፡ በዚህም ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የተማሩ ዜጎችን በማፍራት ሀገሪቱ አሁን ላለችበት ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማህበራዊ እድገት እንድትደርስ የማይተካ አስተዋፅኦ አበርክቷል ።
በቀደመው ዘመን አብዛኞቹ ዜጎች በበቤተክህነት የትምህርት ስርአት ውስጥ ከማለፋቸው የተነሳ አንድ ልጅ እስከ ዳዊት መድገም የደረሰ ትምህርት ካለው በቂ ተደርጎ ይቆጠራል፤ ይህ ደግሞ በአብዛኛው ማንበብና መጻፍን ታሳቢ ያደረገ እንደነበር ታሪክ ያትታል። በዚህ ውሥጥ ያለፉ ዜጎች ለመንግስት ስራ በቂ ሆነው ይቆጠሩ እንደነበርም እንዲሁ።
በአስራ ዘጠነኛው ክፍለዘመን መግቢያ ጀምሮ በሀገሪቱ ማቆጥቆጥ ከጀመረው ዘመናዊነት /ስልጣን/ አንፃር ትምህርት ከመጣበት ባህላዊ መንገድ ወጥቶ ዘመናዊነት እየተላበሰ ሄዷል። የዳግማዊ ምኒሊክ ትምህርት ቤትም የመጀመሪያው ዘመናዊ ትምህርት ቤት በ መሆን አገልግሎት መስጠት ጀምሯል፡፡
ይህንኑ ተከትሎ በ1925 ዓ.ም በመላው ሀገሪቱ 20 የሚሆኑ ትምህርት ቤቶች በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ተከፍተው ስራ ቢጀምሩም ፤ የተማሪዎች ቁጥር ግን ከስምንት ሺ መብለጥ አልቻለም ነበር፡፡ በአፄ ኃይለስላሴ ዘመን መንግስት ዘመናዊ ትምህርትን በሀገሪቱ ለማስፋፋት የተደረጉ ጥረቶች እውነታውም ቀይረውታል።
ብዛት ያላቸው ዜጎች ወደ ትምህርት ቤቶች በመሄድ የዘመናዊ ትምህርት ተቋዳሽ መሆን ችሏል። በደርግም ሆነ በኢህአዴግ አስተዳደር ዘመን የትምህርት ተደራሽነትን ለማስፋት በርካታ ስራዎች ተከናውነዋል፡፡
ትምህርት ቤቶች የትውልድ መቅረጫ ቦታዎች በመሆናቸው የተሟላ መሰረተ ልማት እንደሚያስፈልጋቸው ለጥያቄ የሚቀርብ አይደለም። ቤተ መፅሀፍት፣ ቤተ ሙከራ እንዲሁም ለመማር ማስተማር የሚረዱ ግብዓቶች ሊሟሉላቸው ይገባል፡፡ ይህ ባልተሟላበት ሁኔታ ስለትምህርት ሆነ ውጤታማነቱ አፍን ሞልቶ መነጋገር አይቻልም ።
በርግጥ በኢትዮጵያም የትምህርት ዘርፍ ውጤታማ እንዲሆን በቀደሙት ጊዜያት በርካታ ስራዎች ተከናውነዋል፡፡ ከነዚህም ውስጥ በየአካባቢው ትምህርት ቤቶችን መገንባት ተጠቃሽ ነው፡፡ ለዚህም በመላው ሀገሪቱ ከ50 ሺ የሚጠጉ ትምህርት ቤቶች ተገንብተው መገኘታቸው ተጨባጭ ማሳያ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል። መንግስትና አጠቃላይ ማህበረሰቡ ለትምህርት የሰጡትን ትኩረትም አመላካች ነው።
እነዚህ ትምህርት ቤቶች ባላቸው አቅም ዜጎች ለራሳቸውና ለሀገራቸው ከዛም አልፈው ለዓለም ትርጉም ያለው አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ አስችለዋል። ሀገርን በዓለም አቀፍ መድረክ ያስጠሩ ስመ ጥሩ ዜጎችን በማፍራትም ባለውለታዎች ሆነዋል።
አሁን አሁን እነዚህ ትምህርት ቤቶች ዘመኑ የሚጠይቀውን የሰለጠነ የሰው ኃይል በማፍራት ሂደት ውስጥ በብዙ ፈተናዎች ውስጥ መሆናቸው የአደባባይ ሚስጥር ከሆነ ውሎ አድሯል። እንዲያውም በቅርቡ ትምህርት ሚኒስቴር ባወጣው መረጃ ከትምህርት ቤቶቹ 99ከመቶ የሚሆኑት ለመማር ማስተማሩ ስራ ውጤታማነት የተሟላ ቁመና የላቸውም።
የትምህርት ሚኒስቴር ጥናት እንደሚያሳየው፤
ለመማር ማስተማር ስራው ብቁ ሆነው የተገኙና በዓለም አቀፍ መስፈርቶች በአራተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት የመንግስት ትምህርት ቤቶች በቁጥር ስድስት ሲሆኑ አሀዙ በመቶኛ ሲሰላ ፤ ከ0 ነጥብ 001 በመቶ በታች ናቸው፡፡
010 በመቶ የሚሆኑት ትምህርት ቤቶች ደግሞ በተቀመጠው መስፈርት መሰረት ሶስተኛ ደረጃ ላይ የሚገኙ ሲሆን ቀሪዎቹ ከ89 በመቶ በላይ የሚሆኑት በአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ላይ የሚገኙ ለመማር ማስተማር ስራ ምቹ ያልሆኑ እንደሆኑ በጥናቱ ተቀምጧል።
አብዛኛው ትምህርት ቤቶች የመሰረተ ልማት በተለይ የንፁህ መጠጥ ውሃ፣ የመብራት፣ የቤተ ሙከራ እንዲሁም የመማሪያ ክፍሎች እጥረቶች አሉባቸው፡፡ እነዚህን ክፍተቶች መንግስት ለብቻው ሊደፍናቸው አይችልም ፤ ልድፈናቸውም ብሎ ቢንቀሳቀስ አራትና አምስት አስርት ዓመታትን የሚጠይቁ ናቸው።
አብዛኛው ህብረተሰብ በመንግስት ትምህርት ቤቶች ውስጥ ልጆቹን የሚያስተምር ቢሆንም ትምህርት ቤቶቹን በባለቤትነት መንፈስ ማስተዳደር አለመቻሉ፤ ለተፈጠረው ችግር በዋነኛነት ተጠቃሽ ነው። ይህ እውነታ በአዲስ አበባ ሳይቀር /የተሻለ ግንዛቤ አለው በሚባለው ማህበረሰብ /በስፋት ተስተውሏል።
ትምህርት ቤቶቹ ከደረጃ በታች መሆናቸው ተማሪዎች ማግኘት ያለባቸውን እውቀት እንዳያገኙ ፈተና ሆኗል። ችግሩ በተለይ በመንግስት ትምህርት ቤቶች ውስጥ በይበልጥ ተስተውሏል፡፡ ይህም በትምህርት ጥራት ላይ መሰረታዊ የሚባል ክፍተት እንዲፈጠር አድርጓል።
ችግሩ አሁን ላይ ሀገራት ተግዳሮት የሆነ ሲሆን፤ ችግሩን ለመሻገርም የነቃ የህብረተሰቡ ተሳትፎ ወሳኝ የሆነበት ታሪካዊ ምእራፍ ውስጥ ገብተናል፡፡ ለዚህም ሰሞኑን በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አመካኝነት ሀገራዊ የትምህርት ቤቶችን ደረጃ የማሻሻል ሀገራዊ ንቅናቄ ተጀምረዋል።
ንቅናቄው የእያንዳንዱን ዜጋ ሁለንተናዊ ተሳትፎ ከሁሉም በላይ የሚጠይቅ፤ በሀገሪቱ የተፈጠረውንና ዋጋ እያስከፈለን ያለውን ትምህርት ጥራት ችግር በመፍታት፤ እንደ ሀገር የጀመርነው የብልጽግና ጉዞ ስኬታማ እንዲሆን የሚኖረው ፋይዳ ከፍያለ ነው።
የትምህርት መሰረተ ልማት ያሟሉ ትምህርት ቤቶች፤ በእውቀት የበለፀገ ትውልድ በመቅረፅ ካላቸው አስተዋጽኦ አንጻር ንቅናቄም ለመጪው ትውልድ ብሩህ ነገዎች መሰረት የመጣል ያህል ተደርጎ የሚወሰድ ነው።
በንቅናቄው ማስጀመሪያ መርሀግብር ላይ፤ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ እንደተናገሩት፤ በየትኛውም የኢትዮጵያ ጫፍ ትምህርታቸውን የተከታሉ ሁሉ ትናንት የተማሩበትን ትምህርት ቤቶች ዛሬ ባስፈላጊው መንገድ መደገፍ አለባቸው።
ድጋፉን በተግባር ለማሳየትም ሁሉም ሰው በሐሳብ፣ በገንዘብ፣ በጉልበት እንዲሁም ያለውን ሁሉ ለትምህርት ቤቶች ማዋል አለበት፡ ፡ ትምህርት ቤቶችን ደረጃ ለማሻሻል በሚደረገው ንቅናቄ ተወዳዳሪ አገር የመገንባት ሂደት በመሆኑ ሁሉም ዜጋ በመገንዘብ የንቅናቄው አካል መሆን ይጠበቅበታል፡፡
ከዚህ አንጻር ንቅናቄ በሙሉ ልብ መደገፍ የሁሉም ዜጋ ኃላፊነት ነው፡፡ በውጭ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ይህን ሀሳብ ተረድተው ግንባር ቀደም ሊሆኑ ይገባል፡፡ ትምህርት ቤቶቹ አሁን ካሉበት የመሰረተ ልማት ክፍተቶች መታደግ ካልተቻለ በእውቀት የዳበረ ትውልድ መፍጠር አይቻልም ፡፡ ይሕ ደግሞ የሀገር ውድቀት ጅማሪ እና ፍጻሜ ነው።
መርድ ክፍሉ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 1/2015