ሀገሪቱ ለጀመረችው ልማት ስኬት የሚያስፈልጋትን የውጭ ምንዛሬ ለማግኘት ሸቀጦችን በጥራትና በብዛት ለዓለም ገበያ በማቅረብ ተወዳዳሪ መሆን ይጠበቅባታል። ይህንን ማድረግ አጠቃላይ ሀገራዊ ኢኮኖሚውን ከማነቃቃት ባለፈ፤ ትርጉም ያለው ዕድገት ለማስመዝገብም ዋነኛ አቅም ነው፡፡
ከዚህ የተነሳም መንግስት ሀገራዊ የውጪ ምንዛሪ ግኝቶችን ማሳደግ የሚያስችሉ የተለያዩ ስትራቴጂክ ተግባራትን ሲያከናው ቢቆይም፤ በዚህ ዓመት በተለያዩ ሀገራዊና ዓለምአቀፋዊ ምክንያቶች በወጪ ንግድ ላይ የታቀደውን ያህል ውጤታማ መሆን አልተቻለም። ክፍተቱ ሀገሪቱ ካሏት የውጪ ምንዛሪ ግኝቶችን ማሳደግ የሚያስችሉ ብዙ አማራጮች አንጻር ለዘርፉ ትኩረት ሰጥቶ መስራት ከተቻለ በመጪዎቹ ዓመታት ሊለወጥ እንደሚችል ይታመናል።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከትናንት በስቲያ ባካሄደው 28ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ የ2015 በጀት ዓመት አፈጻጻምን አስመልክቶ ከምክር ቤቱ አባላት ለቀሩቡላቸው ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽና ማብራሪያ የኤክስፖርት ገቢን በተመለከተ እንዳስታወቁት፤ ባለፉት ሁለት ዓመታት ከወጪ ንግድ የሚገኘው ገቢ መሻሻሎች ቢያሳይም፤ በዚህ ዓመት ግን ከአምናው በ11 በመቶ ቀንሷል፡፡
በአንጻሩ ደግሞ የአግልገሎት ዘርፉ 14 በመቶ፣ ሬሚታንስ በአራት ነጥብ ስድስት በመቶ፣ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ደግሞ በአስር ነጥብ አራት በመቶ ማደጉን፤ ሁሉም ሲደመሩ የውጭ ምንዛሬ ግኝቱ ከአምናው ያነሰ እንዳልሆነም ጠቁመዋል፡፡ በእቅዱ በሸቀጦች ኤክስፖርት የተቀመጠው ተሳክቶ ቢሆን ኖሮ በከፍተኛ ደረጃ ለውጥ ሊመጣ ይችል እንደነበርም ተናግረዋል፡፡
በሸቀጥ ኤክስፖርት ላይ ለታየው ቅናሽ የወርቅ ህገወጥ ግብይት፣ የኮንትሮባንድ መስፋፋት፣ የቡና የዓለም ገበያ ዋጋ መቀነስ በምክንያትነት ተጠቁሟል፡፡ እነዚህ ተግዳሮቶች በርግጥም ችግሮች መሆናቸውን መንግስት ቀደም ሲልም ሲገልጽ ቆይቷል፡፡ ችግሮቹን ለመፍታት ሰፋፊ ጥረቶች ቢደረጉም፣ የወጪ ንግዱ ግን ቅናሽ የታየበት ሆኗል፡፡
በርግጥ መንግስት በወርቅ ላይ እየተፈጸመ ያለውን ህገወጥ ተግባር ለመከላከልና ለመቆጣጠር ግብረ ኃይል አቋቁሞ እየሰራ ነው፡፡ ግብረ ኃይሉ እያከናወነ ባለው ተግባር በተለይ በቤኒሻንጉል ጉሙዝና ጋምቤላ ክልሎች በህገወጥ የወርቅ ዝውውር ላይ የተሰማሩ በርካታ የውጭ ሀገር ዜጎችና ተባባሪ ኢትዮጵያውያን በቁጥጥር ስር እየዋሉ ናቸው፡፡
በተመሳሳይ መልኩ መንግስት የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴን ለመቆጣጠር እየወሰደ ያለው እርምጃ ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡ የሀገር መከላከያ፣ የፌዴራል ፖሊስ በዚህ በኩል ሰፊ ተልዕኮ ተሰጥቷቸው እየሠሩ ይገኛሉ፡፡ ይህም እንደ ወርቅ ያሉት ማዕድናት በህገወጥ መንገድ እንዳይመረቱና ከሀገር አንዳይወጡ ከማድረጉ በተጨማሪ፣ ወጪ ኮንትሮባንድ ሸቀጥን ለመቆጣጠር ከፍተኛ ሚና ይጫወታል፡፡ በዚህም ሀገሪቱ ከቁም እንስሳቷ፣ ከጫትና ከሌሎችም ምርቶች ማግኘት ያለባትን የውጭ ምንዛሬ እንድታገኝ ከፍተኛ ሚና ይጫወታል፡፡
ሌላው የሀገሪቱ የውጭ ምንዛሪ ግኝት ምሰሶ ቡና መሆኑ ይታወቃል፡፡ ባለፈው በጀት ዓመት ለውጭ ገበያ ከቀረበ ቡና ከአንድ ነጥብ አራት ቢሊየን ዶላር በላይ ተገኝቷል፤ ይህም በቡና የወጪ ንግድ ታሪክ የመጀመሪያው ነበር፡፡ በዚህ ላይ በመመስረት ከዚህ የሚልቅ የውጭ ምንዛሬ ከቡና ለማግኘት ቢታቀድም በዓለም አቀፍ ደረጃ የቡና ዋጋ መቀነስ ሳቢያ እቅዱን ማሳካት አልተቻለም፡፡
የቡና ግብይቱን የሚመራው የቡናና ሻይ ባለስልጣን ለተከሰተው የዋጋ መቀነስና ይህን ተከትሎ ለተፈጠረው የውጭ ምንዛሬ ቅናሽ መፍትሄ እያፈላለገ ይገኛል፡፡ ከባለስልጣኑ የተገኘ መረጃ እንዳመለከተው፤ ተጨማሪ የቡና ምርት መዳረሻ ሀገሮችን ለማፍራት እየተሰራ ነው፡፡ የመዳረሻ ሀገሮችን ለማስፋት እያተካሄደ ያለው እንቅስቃሴ ችግር ለመፍቻ ብቻ ሳይሆን ለወደፊቱም የሚሆን ተጨማሪ ገበያ ማግኘት የሚያስችል እንደሆነ ይታመናል፡፡
ሌሎች ለሀገሪቱ የውጭ ምንዛሬ በማስገኘት በሚታወቁት እንደ አበባ፣ ስጋና የስጋ ውጤቶች፣ የቁም ከብት፣ አትክልትና ፍራፍሬ በመሳሰሉት የሚገኘውን የውጭ ምንዛሬ ለማሳደግ የሚደረጉ ሀገራዊ ጥረቶች ተጠናክረው ከቀጠሉ፤ በዘርፉ ተጨማሪ አቅም መገንባት የሚያስችል አስቻይ ሁኔታ በስፋት ስለመኖሩ ብዙም ለጥያቄ የሚቀርብ አይሆንም፡፡
ከውጪ ንግዱ የሚገኘው የውጭ ምንዛሬ ትልቅ የልማት አቅም ከመሆኑ አንጻር፤ ለውጪ ገበያ የሚቀርቡ ሸቀጦችን በጥራትና በብዛት ማምረት፤ ለተመረቱ ሸቀጦች የተሻለ የገበያ መዳረሻ ማፈላለግ፤ እነዚህ ምርቶች ለኮንትሮባንድ ገበያ ተጋላጭ እንዳይሆኑ በጠንካራ ዲሲፕሊን የሚመራ የቁጥጥር ስርአት መፍጠር ወሳኝ ነው፡፡ የገበያ ደንቃራዎችን እና በምርታማነት ላይ ያሉ ፈተናዎችን አሸንፎ መውጣት የሚያስችል ዝግጁነት መፍጠርም ያስፈልጋል፡፡ ለዚህ ደግሞ መንግስትና ሁሉም የወጪ ንግዱ ተዋንያን ለዘርፉ ልዩ ትኩረት ሰጥተው መስራት ይጠበቅባቸዋል!።
አዲስ ዘመን ሐምሌ 1/2015