የአንድ ሀገር ፖለቲካ ጤናማነት መሳያ ከሆኑት ጉዳዮች አንዱ የተለያዩ አስተሳሰቦችን የተሸከሙ የፖለቲካ ፓርቲዎች መኖር ፤ አስተሳሰባቸውን በነፃነት የሚያስተናገዱበት ሀገራዊ ዐውድ መፍጠር፤ በዚህም ሀገርና ሕዝብን ተጠቃሚ ማድረግ እንደሆነ ይታመናል።
በተለይም ለረጅም ዘመናት አምባገነናዊ በሆኑ አገዛዞች ስር ወድቀው፤ ያልተገቡ ዋጋዎችን በመክፈል ትልልቅ ጠባሳዎችን የተሸከሙ፤ ትናንቶቻቸው በብዙ የቁዘማ ትርክቶች የተሞሉ ሕዝቦች የፖለቲካ አስተሳሰብ ብዝኃነትን ተላብሰውና ከትናንቶች ቁዘማ ወጥተው ነገዎቻቸውን ብሩህ ማድረግ ትልቁ ዓላማቸው ነው።
ይህንን አቅም በአግባቡ በመጠቀም ሂደት ውስጥ፤ በአንድም ይሁን በሌላ የፖለቲካ ስብዕና ተላብሰው የሚንቀሳቀሱ ግለሰቦችና ቡድኖች ኃላፊነት ከፍ ያለ ነው። ከቀደሙ አስተሳሰቦች ወጥመድ ወጥተው፤ ራሳቸውንም የሀሳብ የበላይነት ለሚጠይቀው አዲሱ የፖለቲካ አስተሳሰብ ማስገዛት ይጠበቅባቸዋል ።
ከተራ አሉባልታ እና አሉባልታው ከሚፈጥራቸው ትርክቶች በመውጣት፤ ተጨባጭ መረጃዎችን መሠረት ባደረጉ ሀገራዊ እውነታዎች ላይ በመመርኮዝ፤ ለሕዝብና ለሀገር ነገዎች የሚጠቅሙ ሀሳቦችን ማፍለቅና ለሀሳቦቹ ተግባራዊነት ቁርጠኛ ሆኖ መገኘት ይኖርባቸዋል።
ሀገራዊ የፖለቲካ ሥርዓቱ በሀሳብ የበላይነት ላይ መመሥረቱ፤ ለሀገር ዕድገትና ለሕዝቦች ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ከሚኖረው ፋይዳ የሚነሳ ነው፤ ይህንን በአግባቡ ተረድቶ ጭፍን ተቃውሞ ሊፈጥራቸው ከሚችላቸው ያልተገቡ ተግባራት መታቀብ ከሁሉም በላይ የፖለቲካ ስብዕና አለን ከሚሉ ግለሰቦችና ቡድኖች የሚጠበቅ ነው ።
በሀገራችን በብዙ መልኩ ተንሰራፍቶ የቆየውን አምባገነናዊ የፖለቲካ ሥርዓት፤ በሀሳብ ልዕልና በሚመራ ፖለቲካ ሥርዓት ለመለወጥ ከለውጡ ማግስት ጀምሮ ሰፋፊ ሥራዎች ተሠርተዋል፤ ዛሬም እየተሠሩ ነው። ሥራዎቹ በተለያዩ ውስጣዊና ውጭያዊ ተግዳሮቶች የተጠበቀውን ያህል ውጤታማ መሆን ባይችሉም ጅማሮው ግን አሁንም በብዙ ተሰፋዎች የታጠረ ስለመሆኑ መናገር አይከብድም።
በተለይም በአስተሳሰብ ልዕልና ላይ ለተመሠረተው የፖለቲካ አስተሳሰብ እንግዳ ከመሆናችን ጋር በተያያዘ፤ የፖለቲካ መድረኮቻችን ዛሬን ጨምሮ ሰፊው የለውጥ ጊዜ በሀገራዊ አጀንዳዎች ላይ ተደማምጦ ለሀገር ዕድገትና ለሕዝባችን ተጠቃሚነት ከመሥራት ይልቅ ጥላቻን እና አሉባልታን መሠረት ባደረጉ ትርክቶች ተሸፍነው ታይተዋል።
ይህ የተሳሳተ የፖለቲካ ጉዞ አሁን አሁን ፍጹም ባልተገባ ቅኝት ከተገራ እንደ ሀገር በዓለም አቀፍ ደረጃ ያስመዘገብናቸውንና እያስመዘገብናቸው ያሉትን ስኬቶች ትርጉም አልባ በማድረግ፤ የታሰበውን ሀገራዊ ለውጥ መፈታተኑ አይቀሬ ነው።
በርግጥ ሀገራችን ከለውጡ ማግስት ጀምሮ በብዙ ፈተናዎች ውስጥ ማለፏን ሁሉም ዜጋ በእለት ተእለት ሕይወቱ ያስተዋለው ነው፤ ችግሮቹ ጥለውት ካለፉት ጠባሳ አንጻርም ለሕዝብ ስለ ችግሮቹ ክብደት ማውራት “ለቀባሪ አረዱት” የሚያስብል ነው።
ለውጡን ገና ከጅምሮ ለማኮላሸት መላ ሀገሪቱን በሁከትና ብጥብጥ ለማመስ በተቀናጀ መንገድ ሰፊ የጥፋት ሥራዎች ታቅደው ተተግብረዋል፤ በሀገርና በመንግሥትም ላይ ግልጽ ጦርነት ታውጆም ሀገርን እንደሀገር የሕልውና ስጋት ውስጥ የሚከቱ ክስተቶች ተፈጥረው አልፈዋል።
“በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ” እንደሚባለው ኮቪድ በዜጎች ሕይወት ላይ ሆነ በሀገር ኢኮኖሚ ላይ የፈጠረው ከስጋት ያለፈ አደጋ፤ ባዶ ካዝና ለተረከበው መንግሥት የቱንም ያህል ፈተና ሊሆን እንደሚችል ለማሰብ ከቀና አዕምሮና ከንጹሕ ልብ ባለፈ የተለየ ዕውቀት የሚጠይቅ አይደለም። እነዚህን ተግዳሮቶች አልፎ ሀገርን እንደሀገር ማጽናት ተችሏል።
ዓለም በፋይናንስ ቀውስ ውስጥ በሆነችበት፤ የየሀገራት ገንዘቦች የመግዛት አቅም እየተዳከመ፤ የኑሮ ውድነት በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍ ብሎ እየተሰማ ባለበት ሁኔታ፤ በሀገሪቱ የተከሰተው የኑሮ ውድነት ሊያስከትል የሚችለውን ሀገራዊ አደጋ ለመከላከል በመንግሥት በኩል ሰፊ ርምጃዎች ተወስደዋል። በዚህም አደጋውን ትርጉም ባለው መንገድ መቀነስ ተችሏል።
ለነዚህ ሀገራዊ እውነታዎች ጆሮ ነፍጎ ችግሮችን ማጯጯህ ለጀመርነው አዲስ የፖለቲካ ሥርዓት ግንባታ ስኬት ተግዳሮት ከመሆን ባለፈ ለማንም የሚያስገኘው ዘላቂ ተጠቃሚነት ሊኖር አይችልም። ይኖራል ብሎ ማሰብም በሕዝባችን የለውጥ ተስፋ ላይ ከመሳለቅ የሚያልፍ አይሆንም።
አሁን ላይ እንደሀገር ለጀመርነው በሀሳብ ልዕልና ላይ የተመሠረተ የፖለቲካ ሥርዓት ግንባታ ስኬት ከሁሉም በላይ የሚጠቅመን ከአሮጌው የቆየ አስተሳሰብ አንጎበር መውጣት፤ ከተራ አሉባልታ እና አሉባልታዎች ከሚፈጥራቸው ትርክቶች ራሳችንን አርቀን፤ በተጨባጭ መረጃዎች እና ገንቢ አስተሳሰቦች ላይ የተመሠረተ የፖለቲካ ባሕል ነው!
አዲስ ዘመን ሰኔ 30/2015