ለመንግሥት ሥራዎች የሚበጀትን ሀብት በአግባቡ ለታለመለት ዓላማ መዋሉን ማረጋጋጥ ፤ ለዚህ የሚሆን ግልጽ የሆነ አሠራር እና የተጠያቂነት ሥርዓት መፍጠር፤ ለአንድ ሀገር እድገት፣ ለዜጎች ፍትሃዊ ተጠቃሚነት እና ለነገዎቻቸው ብሩህነት ወሳኝ እንደሆነ ይታመናል።
በተለይም ከፍተኛ የማደግ መሻት ያላቸው እና ይህንን ፍላጎታውን የሚሸከም ኢኮኖሚያዊ አቅም የሌላቸው ሀገራት፤ ያላቸውን ውስን ሀብት በቁጠባና ውጤታማ በሆነ መልኩ ሥራ ላይ ማዋል እንዲችሉ ጠንካራ የበጀት አጠቃቀም እና የተጠያቂነት ሥርዓት መፍጠር ይጠበቅባቸዋል።
በሀገራችንም የፌዴራል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት፤ ዓለም አቀፍ የኦዲት ደረጃዎችን በመከተል ጥራቱን የጠበቀ ኦዲት በማከናወን የፌዴራል መንግሥት ገንዘብና ንብረት ሀገሪቷ ሥራ ላይ ባዋለቻቸው ሕጎችና ደንቦች መሠረት መሰብሰቡን እና በአግባቡ ሥራ ላይ ማዋሉን የማረጋገጥ ሃላፊነት ተሰጥቶት የተቋቋመ የፌዴራል ተቋም ነው።
ተቋሙ በሕገ መንግሥቱ አንቀፅ 101/4 በተሰጠው ሥልጣን መሠረት የፌዴራል ተቋማትን የበጀት አጠቃቀም በመመርመር የደረሰባቸውን የኦዲት ግኝት ሪፖርቶች እና ምክረ ሃሳቦች ፤ የሚመለከታቸው ከፍተኛ የመንግሥት ተቋማት ሃላፊዎች በተገኙበት ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያቀርባል።
በዚህም በበጀት አጠቃቀም ዙሪያ የግልጽነትና የተጠያቂነት አሠራርን በማስፈን መልካም አስተዳደርን ለማረጋገጥ ፤ ሙስናን ለመከላከልና የህዝብ ሀብት ብክነትን ለመቆጣጠር ለሚደረገው ሀገራዊ እንቅስቃሴ ስኬታማነት ከፍተኛ እገዛ ያደርጋል።
ተቋሙ በዚህም ዓመት በምርመራ የደረሰበትን የኦዲት ግኝት ሪፖርቶች እና ምክረ ሃሳቦችን በሕግ አስገዳጅነት መገኘት የነበራቸው የፌዴራል ተቋማት ከፍተኛ አመራሮች በተሟላ መልኩ ባለተገኙበትም ቢሆን ሰሞኑን ለተወካዮች ምክር ቤት አቅርቧል።
በእለቱም በኦዲት ምርመራው ከዚህ ቀደም ተመላሽ እንዲሆን አስተያየት የሰጠባቸው ከስድስት ነጥብ ስምንት ቢሊዮን ብር በላይ ሂሳብ ተመላሽ አለመሆኑን አስታውቋል። በጉዳዩ ዙሪያ ምክር ቤቱ በቂ ትኩረት በመስጠት የእርምት እርምጃዎችን እንዲወስድም ጠይቋል።
መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ፤ የተቋሙ የኦዲት ግኝት ሪፖርት በየዓመቱ የጥሬ ገንዘብ ጉድለት፣ ያልተወራረደ ውዝፍ ሂሳብ እንዲሁም በገቢ ሂሳብ ላይ የሚታዩ ችግሮች እየጨመሩ ይገኛል።
ለዚህም ተቋሙ በየዓመቱ ያወጣቸውን የምርመራ ሪፖርት ማየት ተገቢ ነው ፤ በ2011 ዓ.ም የበጀት ምርመራው አንድ ቢሊዮን 787 ሚሊዮን 421 ሺህ 15 ብር ተመላሽ እንዲሆን አስተያየት ሰጥቷል ፤ ተመላሽ የሆነው ግን 216 ሚሊዮን 823 ሺህ 793 ብር (14 ነጥብ 64 በመቶው) ብቻ ነው፡፡
በ2012 ዓ.ም በተመሳሳይ መልኩ ተመላሽ እንዲሆን አስተያየት ከሰጠበት ሁለት ቢሊዮን 471 ሚሊዮን 480 ሺህ 929 ብር ውስጥ፣ ተመላሽ የሆነው አንድ ቢሊዮን 29 ሚሊዮን 166 ሺህ 927 ብር (41 ነጥብ 64 በመቶው) ነው ፡፡
በ2013 ዓ.ም ስድስት ነጥብ 88 ቢሊዮን ብር ተመላሽ እንዲሆን ቢያሳስብም ፤ ተመላሽ የሆነው ከ44 ነጥብ 99 ሚሊዮን ብር (ዜሮ ነጥብ 65 በመቶው) ያለፈ አይደለም ፡፡ ዋና ኦዲተር ይሄንን ምርመራ እና ግኝት አስመልክቶ በ2014 ዓ.ም የኦዲት ሪፖርቱ ላይ እንዳሰፈረው፤ በ86 መስሪያ ቤቶች ተመላሽ እንዲደረግ ተብሎ አስተያየት ከተሰጠበት ስድስት ቢሊዮን 883 ሚሊዮን 555 ሺህ 669 ብር ውስጥ፤ 44 ሚሊዮን 995 ሺህ 283 ብር ብቻ ተመላሽ መደረጉን አመልክቷል፡፡
ችግሮቹን ለማረም የሚያስችሉ ሕጋዊና አስተዳደራዊ ርምጃዎች በአግባቡ አለመወሰዳቸው ለችግሮቹ በየዓመቱ መባባስ ዋነኛ ምክንያቶች እንደሆኑም ይታመናል፡፡ የሚመለከታቸው አካላት በቂ ትኩረት አለመስጠታቸው ፤ በጊዜው ተመላሽ መሆን ያልቻሉ ጥሬ ብሮችም ሆኑ፣ በወቅቱ መወራረድ እና መሰብሰብ ያለባቸው ውዝፍ ሂሳቦችና ገቢዎች የመሰብሰባቸውን እድል ጥያቄ ውስጥ የሚከት ሆኗል፡፡
በመሆኑም ሀገሪቱ ከጀመረችው ለውጥና ለውጡ ከተሸከማቸው ከፍ ያሉ የልማት ውጥኖች አንጻር፤ ያለንን ውስን ሀብት በቁጠባ ለታለመለት ዓላማ በአግባቡ በመጠቀም ውጤታማ እንዲሆኑ፤ ለዋና ኦዲተር የኦዲት ግኝት ሪፖርቶችና ምክረሃሳቦች ተገቢውን ትኩረት በመስጠት ፈጣን የእርምት ርምጃዎች መውሰድ ተገቢነው ።
በተለይም የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ካለበት ሃላፊነት አንጻር ፤ በመንግሥት የበጀት አጠቃቀም ዙሪያ እየተስተዋለ ያለውን ችግር አግባብ ባለው መንገድ ለመፍታት ፈጥኖ መንቀሳቀስ ይጠበቅበታል፡፡ ለዚህም የሕግ እና የሞራል ግዴታም አለበት፡፡
ይሄን ማድረግ ሲቻል ብቻ ነው እንደ ሀገር ለመንግሥት ሥራዎች የሚመደበው ሀብት ለታለመለት ዓላማ /ለልማት/ መዋሉን እርግጠኛ መሆን የሚቻለው። ሀገር እንደ ሀገር ከሀብቷ ፣ ዜጎችም ሀብቱ ከሚፈጥረው ሁለንተናዊ ልማት ተጠቃሚ ሊሆኑ የሚችሉት፡፡
አዲስ ዘመን ሰኔ 29/2015