ኢትዮጵያውያን ካላቸው ሳይሆን ከሌላቸው በማካፈል የሚታወቁ ሕዝቦች ናቸው። በየተራ ከአንዷ ቤት አንዷ ቤት ቡና ከአቦል እስከ በረካ የሚጠጡት እናቶች በቡናው መሃል ችግራቸውን ተነጋግረው በጋራ መፍትሄ ይፈልጋሉ። ከእነሱም አለፍ ብሎ ስለሌላ ጎረቤታቸው ችግር አብረው ይመክራሉ። ይህ ቅርበት የፈጠረው ውህደት ከአንዱ ቤት እንጀራ ከአንዱ ቤት ወጥ አዋጥቶ ክፉ ቀንን ሲያሳልፍም ቆይቷል።
ምዕራባውያን ችግራቸውን ለጎረቤት ባያዋዩም ለሥነ-ልቦና ባለሙያ በሆዳቸው ያመቁትን በሙሉ ተናግረው ከጭንቀታቸው የሚገላገሉበት አማራጭን ይጠቀሙበታል። የኢኮኖሚ ችግር ሲገጥማቸውም ድጋፍ የሚያደርጉ ብዛት ያላቸው መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች አሏቸው።
በሀገራችን በችግር ውስጥ የሚገኙ ዜጎቻችንን በስነ ልቦና ባለሙያዎች ሆነ ፤ በመንግስታዊና መንግስታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች በሚፈለገው ደረጃ መርዳት የሚያስችል አቅም የለም። በተለይም በስነ ልቦና ባለሙያዎች ችግሮችን የመፍታቱ ባህል ብዙም የተለመደ አይደለም።
ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ይህንን ክፍተት ለመሙላት ያለመ ወጣቶችን በስፋት ያሳተፈ የክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተጀምሯል። እኔ ተማሪ ሳለሁ ሰኔ 30 ትምህርት ይዘጋል። ያኔ ተማሪዎች ሰፈር ውስጥ እንደልብ ለመጫወት በቂ ጊዜ ይኖራቸዋል። ከዛ አለፍ ካለ ቤተሰብን በሥራ በማገዝ ክረምቱ ያልቃል።
የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች፣ የኮሌጅ እንዲሁም የሁለተኛና የመሰናዶ ተማሪዎች ከሁለት ወር በላይ የእረፍት ጊዜ ቢኖራቸውም ከቤተሰብና ከጓደኛ ጋር ጊዜን ከማሳለፍ የዘለለ ተግባር አይከውኑበትም ነበር።
አሁን ግን ያ ታሪክ ተቀይሯል፤ በጎነት ለኢትዮጵያ ከፍታ በሚል መርህ በተደራጀ አግባብ የክረምት ወጣቶች የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ዘንድሮ ሁለት ዓመት ሞላው። የዘንድሮ የወጣቶች የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር አስተባባሪነት ተጀምሯል።
በክረምት የወጣቶች የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ላይ ከ20 ሚሊዮን በላይ ወጣቶች፣ በ13 የሥምሪት መስኮች በመሰማራት ለማህበረሰባቸው የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንደሚያበረክቱም ይጠበቃል።
ከዚህ በተጨማሪ ከየክልሉ የተውጣጡ ወጣቶች ወደ ሁሉም ክልል ተሰማርተው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የሚሰጡ ሲሆን ይህም ከርቀት በቁንጽል ያወቋትን ሀገራቸውንና ማህበረሰብ ቀርበው ማየት ብሎም መረዳት ይፈጥርላቸዋል። ይህ ሲሆን ነገ ማህበራዊ ሚዲያ ላይ አንዱ ማህበረሰብ አንቂ ተብዬ ተነስቶ እከሌ ብሔረሰብ እከሌን ጨቆነ ሲል እኛ ያየነው እውነቱ ይሄ አይደለም ብለው ሀገር የሚያፀኑ ወጣቶች ይሆናሉ።
አሁን ላይ ሁሉም ቤቱን ዘግቶ በተቀመጠበት በጎ አድራጊ ወጣቶች በየሰፈሩ ጉራንጉር እየገቡ የሰው ዓይን የናፈቃቸውን አረጋውያን ከሰው እያገናኙ ነው።‹‹መርዳት እፈልጋለሁ ››ግን አጭበርባሪውን ከእውነተኛው እንዴት ልለይ ብሎ ግራ ለተጋባው መፍትሄ ሆነዋል።
ሰውን ለመርዳት ደሞዝተኛ መሆንም ሆነ ባለገንዘብ መሆን የግድ እንዳልሆነ እያሳዩም ናቸው። በወጣቶች እርዳታ በጤና ተቋማት ከካርድ ክፍል አንስቶ ሀኪሙን ማግኘት ግራ የሆነባቸው በርካታ ታካሚዎች በበጎ ፈቃደኞች እርዳታ በቀላሉ ህክምናቸውን ጨርሰው እየወጡ ነው።
የትራፊክ እንቅስቃሴውን ከማሳለጥ አንስቶ የሀገራችን አረንጓዴ አሻራ በእቅዱ ልክ እንዲሳካ የበጎ ፈቃደኞቹ ሚና ቀላል አይደለም። የአረጋውያንን ቤት በማደስም ቢሆን ከመምረጥ አንስቶ በተግባር እድሳቱን እስከማከናወን ድርሻቸው የጎላ ነው።
በጎ ፈቃድ ከምንም በላይ ክፍያው የህሊና እርካታ መሆኑ ባያጠያይቅም በሌሎች ሀገራት እንዲስፋፋ ያደረገው በጎ ፈቃደኞች በትምህርት ምርጫም ሆነ በሥራ ላይ የተሻለ ተፈላጊ እንደሚሆኑ ማወቃቸው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ላይ እንዲሳተፉ ገፊ ምክንያት ሆኗቸዋል።
በበጎ ፈቃድ አገልግሎቶች መሳተፍ ለነገ የሥራ ሕይወት ከሚያስገኘው የሥራ ልምድ፣ ከሚፈጥረው የግንኙነት እድልና ከምንም በላይ ከሚያጎናጽፈው የህሊና እርካታ በተጨማሪ በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ለመሳተፍ ተነሳሽነት መኖር በራሱ እውቅናና በአንዳንድ እድሎች ላይ ቅድሚያ ሊያሰጥ ይገባል። ምንም እንኳን የሚያገኙትን ጥቅም አስቦ በበጎ ፈቃደኝነት አገልግሎት ላይ መሳተፍ ተገቢ ባይሆንም የተሳታፊውን ቁጥር ይጨምራል ብዬ አስባለሁ።
የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ብሔራዊ የወጣቶች የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ረቂቅ ፖሊሲና ብሔራዊ የወጣቶች የዜግነት አገልግሎት ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጅቶ ለሚመለከተው አካል እንዲጸድቅ መላኩን ያሳያል። ረቂቅ አዋጁ ጸድቆ ተግባራዊ ሲሆን የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ላይ የተሰማሩ በተራቸው አገልግሎት ሲፈልጉ የሚካሱበት ሁኔታ እንደሚኖር አስባለሁ።
የበጎ ፈቃድ አገልጋዮች ያለመሰልቸት አገልግሎት እንዲሰጡ ከሕብረተሰቡ በኩል የሚታየው እነሱ አገልግሎት ሲሰጡ ያለመታዘዝና ዝቅ የሚያደርጉ ንግግሮችን ከመናገር መቆጠብ ይገባል። በአገልጋዮቹ ዘንድም ታምነው እርዳታ በመስጠት ቅድሚያ የሚገባቸውን እንዲለዩ እድል ሲሰጣቸው ከወገንተኝነት በጸዳ መልኩ መስራትን ይሻል።
ይህ ሲሆን ኢትዮጵያዊ የመረዳዳት ባህላችንና ለወገን አለኝታነታችን በተግባር ይገለጻል። ዛሬ በየጉራንጉሩ ገብተው የወደቁትን ያነሱ የወጣቶቹ እጆች ነገ ከፍ ያለ ቦታ ሲደርሱ የትላንት ደጋፊነታቸው አብሮአቸው እንደሚቆይ እምነቴ የጸና ነው።
ይህ አምድ በተለያዩ ፖለቲካዊ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ዜጎች ነፃ ሀሳባቸውን የሚሰጡበት ነው።በዓምዱ ላይ የሚወጡ ጽሁፎች የዝግጅት ክፍሉን አቋም አያመለክቱም።
ከትዝታ ማስታወሻ
አዲስ ዘመን ሰኔ 28/2015