ጤና የሁሉም ነገር መሠረት ነው። በተለይም ጤናው የተጠበቀ ሕዝብ ለአንድ ሀገር ማኅበራዊ፤ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ዕድገት የሚጫወተው ሚና መተኪያ የሌለው መሆኑ እሙን ነው።
ይህንኑ መሠረት በማድረግም ሀገራችን ኢትዮጵያ መከላከልን መሠረት ያደረገ የጤና ፖሊሲ እና ስትራቴጂ በመቅረጽ እና በመተግበር በጤናው ዘርፍ አበረታች ለውጥ ለማምጣት በቅታለች። ጤና ኢትዮጵያ ከተቀበለቻቸው ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች አንዱ መሆኑ በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገ መንግሥት በተለያዩ አንቀፆች ተደንግጓል።
በሕገ መንግሥቱ አንቀፅ 90 ንዑስ አንቀፅ 1 “የሀገሪቱ አቅም በፈቀደ መጠን ሁሉም ኢትዮጵያዊ የትምህርት፣ የጤና አገልግሎት፣ የንጹሕ ውሃ፣ የመኖሪያ፣ የምግብና የማኅበራዊ ዋስትና እንዲኖረው ይደረጋል“ ሲል የደነገገ ሲሆን በአንቀፅ 92 ንዑስ አንቀፅ 1 ደግሞ መንግሥት ሁሉም ኢትዮጵያዊ ንጹሕና ጤናማ አካባቢ እንዲኖረው የመሥራት ኃላፊነት እንዳለበት በግልፅ ተደንግጓል።
በተጨማሪም በሕገ መንግሥቱ አንቀፅ 35 ንዑስ አንቀፅ 9 ሴቶች በእርግዝናና በወሊድ ምክንያት የሚደርስባቸውን ጉዳት ለመከላከልና ጤንነታቸውን ለማስጠበቅ የሚያስችል መብት ያስቀመጠ ሲሆን እንደዚሁም በአንቀፅ 36 ንዑስ አንቀፅ 1 ስለ ሕፃናት በሕይወት የመኖር እና ጤንነት መጠበቅን ይደነግጋል። በአንቀፅ 44 ንዑስ አንቀፅ 1 ደግሞ ሁሉም ሰዎች ንጹሕና ጤናማ በሆነ አካባቢ የመኖር መብት እንዳላቸው ይጠቅሳል። ስለሆነም በሕገ መንግሥቱ ድንጋጌዎች መሠረት እያንዳንዱ ዜጋ የጤና አገልግሎት የማግኘት መብት አለው። መንግሥትም እነዚህን ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌዎች ወደ ተግባር ለመቀየር የጤና ፖሊሲ በመቅረፅና ስትራቴጂዎችን በመንደፍ ሲንቀሳቀስ ቆይቷል። በዚህም ተጨባጭ ለውጦች መጥተዋል።
እየጨመረ ከሚመጣው የሕዝብ ቁጥርን ከበሽታዎች መስፋፋት አንጻር አሁንም የጤና አገልግሎቱ ጥራትና ፍትሐዊነት በከፍተኛ ሁኔታ መሻሻል ያለበት ነው። ከዚህ አንጻር የአዲስ አበባ ከተማ አስተደዳር የጤና ዘርፉን ተደራሽነት እና ፍትሐዊነት ለማረጋገጥ የሠራቸው ሥራዎች በምሳሌነት የሚጠቀሱ ናቸው።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የጤና ፍትሐዊነትን ለማረጋገጥ እያንዳንዳቸው ከሦስት ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ የተያዘላቸው ሦስት ሆስፒታሎችን እየገነባ መሆኑን ገልጿል። ከዚህም በተጨማሪ አስተዳደሩ ከፍለው መታከም ለማይችሉ ዜጎችም 300 ሚሊዮን ብር በበጀት ዓመቱ መደጎሙንም አስታውቋል።
አስተዳደሩ ያከናወናቸው ተግባራት በሕገ መንግሥቱ የተቀመጡት ድንጋጌዎች በአግባቡ መሬት እንዲረግጡ የሚያስችልና የጤና ተቋማትን ተደራሽነትና ፍትሐዊነትን በማረጋገጥ ኅብረተሰቡ በአቅራቢያው የጤና አገልግሎት እንዲያገኝ የሚያስችል ነው።
በአዲስ አበባ ብዙዎቹ ነባር ሆስፒታሎች የሚገኙት መሐል ከተማዋ ላይ በመሆኑ ከተማዋ ዳር ላይ የሚገኙት ክፍለ ከተሞች ሆስፒታል የላቸውም። በመሆኑም በእነዚህ አካባቢ ያሉ ዜጎች የሆስፒታል አገልግሎት ለማግኘት ረጅም ርቀት መጓዝ ግድ ሲላቸው ቆይቷል። ይህንን የፍትሐዊነት ችግር ለመፍታት ከተማ አስተዳደሩ ከዘጠኝ ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ በንፋስ ስልክ ላፍቶ፣ በቦሌና ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተሞች ትላልቅ ሆስፒታሎችን እንዲገነቡ ማድረጉ ኅብረተሰቡን ከውጣ ውረድ እና እንግልት የሚታደግና ጤናው እንዲጠበቅ የሚያደርግ ተግባር ነው።
በሌላ በኩል ዜጎች በአቅም ማነስ ምክንያት የሕክምና አገልግሎት ሳያገኙ እንዳይቀሩ የከተማ አስተዳደሩ ማኅበረሰብ አቀፍ የጤና መድሕን አገልግሎት ተግባራዊ በማድረግ በከተማዋ ያሉ ሁሉም ወረዳዎች በዚህ ማዕቀፍ ውስጥ እንዲገቡ በማድረግ ከፍለው መታከም ለማይችሉ ዜጎች 300 ሚሊዮን ብር በዚህ ዓመት ድጎማ ማድረጉ ዜጎች በፍትሐዊነት የጤና አገልግሎት እንዲያገኙ ያለውን ቁርጠኛ አቋም ያመላክታል።
ከዚሁ ጎን ለጎንም የከተማ አስተዳደሩ ላለፉት ሦስት ዓመታት በዳግማዊ ምኒልክ፣ በዘውዲቱና ጳውሎስ ሆስፒታሎች የኩላሊት እጥበት ለሚደረግላቸውና መክፈል ለማይችሉ ዜጎች ከ25 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ሸፍኖ እንዲታከሙ በማድረግ ዜጎችን መታደግ ችሏል።
በአጠቃላይ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለጤና ዘርፍ የሰጠው ትኩረት ለሌሎች ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ትልቅ ምሳሌ የሚሆንና ዜጎች በያሉበት አካባቢም ፍትሐዊ የጤና አገልግሎት እንዲያገኙ የሚያስችል ነው። ስለዚህም አስተዳደሩ ለጤና ዘርፍ የሰጠው ትኩረት በአርዓያነቱ የሚጠቀስና ተጠናክሮ ሊቀጥል የሚገባው ነው!
አዲስ ዘመን ሰኔ 28/2015