መነሻ
ጉዳዩ ብዙ ንትርኮችን ያስነሳ ሲሆን፤ በግራ እና በቀኝ መቆራቆዝ፤ ከሁለቱም ወገን ሕጋዊ አሠራር ይከበር የሚል ድምፀት የሚሰማበት ነው፡፡ በዳይ እና ተበዳይ ነን ያሉት አካላት በየፊናቸው የተለያዩ መረጃዎችን ዋቢ አድርገው ለማቅረብ ሞክረዋል፡፡ የጉዳዩ መነሻ ኒው ጀነሬሽን የሎጅስቲክና የሰው ሀብት ሥራ አመራር ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር የተሰኘ ድርጅት እና በዚህ ድርጅት አማካኝነት ተቀጥረው ሲሠሩ በነበሩ ሠራተኞች መካከል የተፈጠረ አለመግባባት ነው፡፡
ድርጅቱ ያለ አግባብ ጉልበታችንን ለመበዝበዝ እና ሕጋዊ ሥርዓትን ባለመከተል የሠራተኛን መብትም ሆነ የሀገሪቱን ሕግ የሚፃረር አካሄድ የሚከተል ስለመሆኑ ይናገራሉ፡፡ በተለይም የሠራተኞችን መብት አለማክበር፤ የሥራ ልምድ ለመስጠት እና የአገልግሎት ክፍያ ለመፈፀም ፈቃደኛ አለመሆንና የመሳሰሉት ናቸው ይላሉ፡፡ ይህም በመሆኑ በእኛ ላይ ግፍ ተሠርቶብናል ሲሉ ነበር ለዝግጅት ክፍላችን ቅሬታቸውን ያቀረቡት፡፡
ኒው ጀነሬሽን የሎጅስቲክና የሰው ሀብት ሥራ አመራር ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር በበኩሉ፤ እኛ ሕግና ሥርዓን ተከትለን የምንሠራ፤ በድሃ ጉልበት የምንነገድ ሳይሆን ይልቁንም ለሥራ አጥ ዜጎች የሥራ ዕድል የፈጠርን በሕጋዊ አግባብ የምንመራ እና ለድርጅታችን መልካም ሥምና የምንጠነቀቅ ነን ይላል። የሚቀርቡ ቅሬታዎችም ሕጋዊ መሠረትን የጣሱ ከመሆናቸው በዘለለ አንዳንዶቹ እውነታውን ሆን ብሎ በማዛነፍ የሥም ማጥፋት ዘመቻ መሆኑ ይታወቅልን ሲሉ ነበር ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት አቋማቸውን የገለፁት፡፡
ቅሬታ አቅራቢዎች ምን ይላሉ?
አቶ አበራ አሼቦ እና አቶ ኃይሉ አስፋው ኒው ጀነሬሽን የሎጅስቲክና የሰው ሀብት ሥራ አመራር ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር የሚከተላቸው አካሄዶች የድሃን ጉልበት መበዝበዝ እና ፍትሃዊ አሠራርን መጣስ ነው ይላሉ፡፡ ለዚህም እንደማሳያ የሚያነሷቸው ነጥቦች አንድ ግለሰብ አንድ ድርጅት ላይ አምስት ዓመትና ከዚያ በላይ ከሠራ የአገልግሎት ክፍያ ይጠይቀናል በሚል እሳቤ ለአምስት ዓመት የተወሰነ ጊዜ ሲቀር ከአንድ ድርጅት ወደ ሌላ ድርጅት ያዛውረናል ባይ ናቸው፡፡ ይህ ደግሞ አጋጣሚዎችን ለመጠቀም የታሰበ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ ለዚህ ማሳያ ደግሞ እኛ ላይ የደረሰውን ብቻ ማገናዘብ በቂ ነው ባይ ናቸው፡፡ መሰል በደሎችን በርካታ ኤጀንሲዎች የሚያደርሱት ሲሆን ይህም ከእነዚያ ውስጥ አንዱ ነው ሲሉ ይወቅሱታል፡፡
አቶ አበራ እና አቶ ኃይሉ እንደሚሉት፤ ኒው ጀነሬሽን የሎጅስቲክና የሰው ሀብት ሥራ አመራር ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር የሥራ ልምድ በሚጠየቅበት ወቅት ለመስጠት ፈቃደኛ አይደለም። የአገልግሎት ክፍያ መጠየቅ ደግሞ እንደ ወንጀል የሚቆጠርበት ድርጅት እንደሆነ ያስገነዝባሉ፡፡
የሰነድ ማስረጃዎች
ኒው ጀነሬሽን የሎጅስቲክና የሰው ሀብት ሥራ አመራር ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር አቶ አበራ የሚያነሷቸው ነጥቦች ውሃ የማያነሱ ይልቁን ተራ ውንጀላዎች ናቸው ሲሉ ያጣጥሉታል፡፡ በተለይም ደግሞ ሥራ ልምድ ለአንድ ተቀጣሪ መስጠት የውዴታ ግዴታ መሆኑ እየታወቀ እኛን በዚህ መክሰሳቸው አግባብ አይደለም ባይ ናቸው ዋቢ ይሆናሉ ያሉትን ማስረጃዎች በመጠቀስ ጭምር፡፡
መረጃዎችን በፍጥት እንደሚሰጡ በመጠቆም ጭምር፤ በቀን 8/03/23 ለሚመለከተው ሁሉ ብሎ በጻፈው ደብዳቤ፤ የድርጅታችን ሠራተኛ የነበሩት አቶ አበራ አሼቦ የድርጅታችን ሠራተኛ መሆናቸውን ጠቅሰን የሥራ ልምድ እንድንጽፍላቸው ጠይቀውናል። ስለሆነም በጥያቄያቸው መሠረት ተጠቃሹ ግለሰብ ድርጅታችን ከተለያዩ ድርጅቶች ጋር በገባው የሥራ ውል መሠረት፤ እ.ኤ.አ ከ11/03/2017 ጀምሮ እስከ እ.ኤ.አ 31/07/2021 ድረስ ከጂአይዜድ ጋር በገባ የሥራ ውል መሠረት በየዓመቱ በሚታደስ ኮንትራት በወር ተከፋይነት በጥበቃ ሠራተኝነት ማገልገላቸውን ጠቅሰን ጽፈናል፡፡
በተጨማሪም እ.ኤ.አ ከ06/08/2021 ጀምሮ እስከ እ.ኤ.አ 28/02/2023 ድረስ ድርጅታችን ከኢትዮጵያ ምርት ገበያ ጋር በገባው የሥራ ውል መሠረት በአዲስ አበባ (ሜክሲኮ) ቅርንጫፍ በጥበቃ ሥራ መደብ በየዓመቱ በሚታደስ ኮንትራት በወር ተከፋይነት በወር ብር 1,983.52 (አንድ ሺህ ዘጠኝ መቶ ሰማንያ ሦስት ብር ከ52/100) እና የትራንስፖርት አበል ብር 354.20 (ሦስት መቶ ሃምሳ አራት ብር ከ20/100) እየተከፈላቸው ሥራቸንውን በማከናወን ላይ የነበሩ መሆናቸውን እየገለጽን ከደመወዛቸው ላይ ተገቢው የሥራ ግብርና የጡረታ መዋጮ እየተቀነሰ ለሚመለከተው መንግሥታዊ መሥሪያ ቤት ገቢ የተደረገ መሆኑን ገልጸው፤ ድርጅቱ ሕጋዊ አግባብ የተከተለ ሥራ እየሠራ መሆኑን ይናገራሉ። በመሆኑም አግባብ የሆነ የሥራ ልምድም ለመስጠት ፈቃደኛ አይደለም ተብሎ ድርጅቱ መወንጀሉ አግባብ አይደለም ሲል በደብዳቤው ለማስረገጥ ሞክሯል፡፡
ኒው ጀነሬሽን የሎጅስቲክና የሰው ሀብት ሥራ አመራር ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ለአቶ አበራ አሼቦ፤ ጉዳዩ፡- በቀን 21/06/2015 ዓ.ም ጽፈው ላቀረቡት የሥራ መፈለጊያና የአገልግሎት ክፍያ ጥያቄ ምላሽ ይመለከታል፤ በሚለው በፃፈው ደብዳቤ፤ ‹‹እርስዎ በድርጅታችን ውስጥ በጥበቃ የሥራ መደብ እ.ኤ.አ 11/03/2017 ጀምሮ ሲያገለግሉ ቆይተው በራስዎ ፍላጎት ሥራ የለቀቁ በመሆኑ የሥራ መፈለጊያና የአገልግሎት ክፍያ እንዲከፈልዎ ጠይቀዋል፡፡ ከድርጅታችን ጋር በነበረዎት ቆይታ በተለያዩ ጊዜያት በኮንትራት የገቡት ውል ተጠናቆ የሥራ ውልዎ ከተቋረጠ በኋላ በድጋሜ ተቀጥረው ያገለገሉ በመሆንዎ የአገልግሎት ክፍያ ጥያቄዎትን ለማስተናገድ እንቸገራለን›› ሲል ነበር ምላሽ የሰጠው፡፡
ታዲያ አቶ አበራ አሼቦ ኒው ጀነሬሽን የሎጅስቲክና የሰው ሀብት ሥራ አመራር ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ሥራ ማፈላለጊያ አይገባህም ሲል በተሰጣቸው ምላሽ ደስተኛ አልሆኑም፡፡ ይህ አግባብ አይደለም ሲሉም ወደ መንግሥት ተቋም አቤት ብለዋል፡፡
መንግሥታዊ ተቋማት
የመንግሥት ተቋማትም ጉዳዩን በመመርመር እና የአቶ አበራን ቅሬታ በመመልከት ለኒው ጀነሬሽን የሎጅስቲክና የሰው ሀብት ሥራ አመራር ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ደብዳቤ ጽፏል፡፡ በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ አስተዳደር የሥራ፣ ኢንተርፕራይዝና ኢንዱስትሪ ልማት ጽሕፈት ቤት በቀን 29/06/2015 ዓ.ም በቁጥር ን/ስ/ላ/ክ/ከ/ስ/ኢ/ል/ጽ/ቤት/የኢ/ሰ/ሙ/ደ/2766/ 2015 ጉዳዩ የሥራ ልምድን እና የሥራ ስንብት ክፍያን ይመለከታል፤ በሚል ለኒው ጀነሬሽን የሎጅስቲክና የሰው ሀብት ሥራ አመራር ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር በፃፈው ደብዳቤ እንዲህ ሲል ጠይቋል፡፡
አቶ አበራ አሼቦ የተባሉ የድርጅታችሁ ሠራተኛ እንደሆኑ በመግለጽ በቀን 29/06/2015 ዓ.ም በመስሪያ ቤታችን በመገኘት የምሠራበት መስሪያ ቤት ተገቢውን የሥራ ልምድ እንዲሰጠኝ እንዲሁም የሥራ ስንብት ክፍያ እንዲከፈለኝ ብጠይቅም በአግባቡ ሊመልሱልኝ አልቻሉም በማለት ቅሬታቸውን አቅርበዋል።
ስለዚህም ቅሬታውን ላቀረቡት አመልካች የግል ድርጅት ሠራተኞች ጡረታ አዋጅ ቁጥር 1268/2014 እና በአሰሪና ሠራተኛ ሕግ አዋጅ ቁጥር 1156/2011 አንቀጽ 12/8/ መሠረት አንድ አሰሪ ሠራተኞች የሥራ ልምድ እንዲሰጣቸው ሲጠይቁ ተገቢው የሥራ ልምድ ማለትም የመንግሥት ግብር እና ጡረታ መቆረጡን የሚያሳይ የሥራ ልምድ የምስክር ወረቀት ያለምንም ቅድመ ሁኔታ መስጠት እንዳለበት እንዲሁም በአሰሪና ሠራተኛ አዋጅ ቁጥር 1156/2011 አንቀጽ 39/ሸ/ መሠረት አንድ ሠራተኛ አምስት ዓመትና ከዚያ በላይ በድርጅቱ የሠራ ከሆነ እና በገዛ ፈቃዱ ሥራውን ሲለቅ ክፍያ እንደሚያገኝ ይደነግጋል፡፡
ስለሆነም አመልካች ያቀረቡትን ቅሬታ ከላይ በተጠቀሰው የሕግ ድንጋጌ መሠረት በሁለት የሥራ ቀናት ውስጥ ቢስተናገዱ እያልን ስንጠይቅ በፃፍነው ደብዳቤ ላይ ቅሬታ ባላችሁ በሁለት ተከታታይ የሥራ ቀናት ውስጥ በደብዳቤ ማሳወቅ የምትችሉ መሆኑን እንገልፃለን ሲል በደብዳቤ መጠየቁ ይታወሳል፡፡ ታዲያ ይህን ደብዳቤ መሠረት በማድረግም ድርጅቱ የሥራ ልምድ መስጠቱን ጠቅሶ ክፍያ ለመፈጸም ግን አለመቻሉን ያሳውቃል፡፡
የኒው ጀነሬሽን የሰጠው ምላሽ
በዚህም መሠረት ኒው ጀነሬሽን የሎጅስቲክና የሰው ሀብት ሥራ አመራር እና ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር በቁጥር ኒጀ/የሰሀ/ሰሀአ/339914 በቀን 13/03/14 ለአቶ አበራ አሼቦ ጉዳዩ፡- የሥራ ልምድ ማስረጃ መስጠትን ይመለከታል በሚለው ደብዳቤው፤ የድርጅታችን ሠራተኛ የሆኑት አቶ አበራ አሼቦ በድርጅታችን ውስጥ የሠሩበትን የሥራ ልምድ ደብዳቤ እንድንጽፍላቸው በቀን 13/03/2014 ዓ.ም በተጻፈ ማመልከቻ ጠይቀውናል፡፡
ስለሆነም በጥያቄያቸው መሠረት ተጠቃሹ ግለሰብ ድርጅታችን ከጂአይዜድ ጋር በገባው የሥራ ውል መሠረት በአዲስ አበባ በካዛንችስ ቅርንጫፍ እ.ኤ.አ ከ1/03/2017 እስከ 3/07/2021 ድረስ፤ እንዲሁም ድርጅታችን ከኢትዮጵያ ምርት ገበያ ጋር በገባው የሥራ ውል መሠረት በአዲስ አበባ (ሜክሲኮ)ቅርንጫፍ (ጥበቃ የሥራ መደብ በየአመቱ በሚታደስ ኮንትራት በወር ተከፋይነት እ.ኤ.አ ከ06/08/2021 ጀምሮ ይህ የሥራ ልምድ ማስረጃ እስከተሰጠበት ቀን ድረስ በወር ብር 1771.00(አንድ ሺህ ሰባት መቶ ሰባ አንድ ብር) ደመወዝ እና 354.20(ሦስት መቶ ሃምሳ አራት ብር ከሃያ ሳንቲም) የትራንስፖርት አበል እየተከፈላቸው ሥራቸውን በማከናወን ላይ ሲሆኑ ከደመወዛቸው ላይ ተገቢውን ሥራ ግብርና የጡረታ መዋጮ እየተቀነሰ ለሚመለከተው መንግሥታዊ መ/ቤት ገቢ የተደረገ መሆኑን እናሳውቃለን ሲል ምላሽ ሰጥቷል፡፡
ኒው ጀነሬሽን የሎጅስቲክና የሰው ሀብት ሥራ አመራር ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበርም ይህንኑ የተመለከተ ደብዳቤ ለንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ አስተዳደር የሥራ፣ ኢንተርፕራይዝና ኢንዱስትሪ ልማት ጽሕፈት ቤትም ምላሽ ሰጥቷል፡፡ ጉዳዩ መረጃ መስጠትን ይመለከታል በሚለው ደብዳቤው፤ እንደሚታወቀው በደብዳቤ ቁጥር ን/ስ/ላ/ክ/ከ/ስ/ኢ/ል/ጽ/ቤት/የኢ/ሰ/ሙ ደ/2766/2015 በቀን 29/6/2015ዓ.ም በተፃፈ ደብዳቤ የድርጅታችን ሠራተኛ የነበሩት አቶ አበራ አሼቦ ለድርጅታችሁ በቀን 29/6/2015 ዓ.ም ላይ ቅሬታ እንዳስገቡ ገልፃችሁ ለድርጅታችን ደብዳቤ መፃፋችሁ የሚታወቅ ነው፡፡
ሆኖም በተፃፈው ደብዳቤ መሠረት አቶ አበራ አሼቦ እናንተ ጋር ቅሬታ ባስገቡበት ቀን በድርጅታችን ተገኝተው የጠየቁትን የሥራ ልምድ የወሰዱ ሲሆን የአገልግሎት ክፍያን በተመለከተ አቶ አበራ አሼቦ ከድርጅታችን ጋር በነበራቸው ቆይታ በተለያዩ ጊዜያት በኮንትራት የገቡት የሥራ ውል ተጠናቆ የሥራ ውላቸው ከተቋረጠ በኋላ በአዲስ የሥራ ውል ድርጅታችን ከኢትዮጵያ ምርት ገበያ ጋር ባለው የራስ ውል መሠረት ከእ.ኤ.አ 06/08/2021 ጀምሮ ተቀጥረው ያገለገሉ በመሆናቸው የአገልግሎት ክፍያ ጥያቄያቸውን በአሰሪና ሠራተኛ አዋጅ ቁጥር 1156/2011 አንቀጽ 39/1/ሸ/ መሠረት አምስት ዓመት ያልሞላቸው ስለሆነ የአገልግሎት ክፍያ አይገባቸውም፡፡ ለዚሁ ይረዳ ዘንድ በተለያየ ጊዜ የፈፀሙትን የቅጥር ውል ኮፒ እና የተሰጣቸውን የሥራ ልምድ አያይዘን የላክን መሆኑን እንገልፃለን ይላል፡፡
አቶ አበራ አሼቦ የደረሰባቸው በደል እኔንም ደርሶብኛል የሚሉት ሌላኛው ሰው ደግሞ ኃይሉ አስፋው ናቸው፡፡ አቶ ኃይሉ አስፋው ከሚያነሷቸው ቅሬታዎች መካከል አንደኛው ሥራ ልምድ ለመስጠት ፈቀደኛ ያልሆነ ድርጅት ስለመሆኑ ይናገራሉ፡፡ ዳሩ ግን ይህ ስም የማጥፋት ዘመቻ ነው ሲል ኒው ጀኔሬሽን የሎጅስቲክና የሰው ሀብት ሥራ አመራር ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር በማስረጃ ይከራከራል፡፡
ኒው ጀነሬሽን የሎጅስቲክና የሰው ሀብት ሥራ አመራር ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ጉዳዩ- የሥራ ልምድ ማስረጃ መስጠትን ይመለከታል በሚል በቁጥር ኒጀ/የሰሀ/ሰሀአ/እና አፕ/ዳ/3490/ 14 በቀን በ23/3/14 በፃፈው ደብዳቤም ለአቶ ኃይሉ የተከለከለ መረጃ የለም የሥራ ልምዳቸውም የሚመለከተው ነው ይላሉ፡፡
የድርጅታችን ሠራተኛ የነበሩት አቶ ኃይሉ አስፋው የድርጅታችን ሠራተኛ መሆናቸውን ጠቅሰን የሥራ ልምድ እንድንጽፍላቸው ጠይቀውናል። በተፃፈው ደብዳቤ መሠረትም በጥያቄያቸው መሠረት ተጠቃሹ ግለሰብ ድርጅታችን ከተለያዩ ካምፓኒዎች ጋር በገባው የሥራ ውል መሠረት እ.ኤ.አ 01/08/2016 ጀምሮ እስከ እ.ኤ.አ 31/07/2021 ድረስ ከጂአይዜድ ጋር በገባው የሥራ ውል መሠረት በየዓመቱ በሚታደስ ኮንትራት በወር ተከፋይነት በጥበቃ ሠራተኝነት አገልግለዋል፡፡
እ.ኤ.አ 06/08/2021 ጀምሮ እስከ እ.ኤ.አ 29/10/2021 ድረስ ድርጅታችን ከኢትዮጵያ ምርት ገበያ ጋር በገባ የሥራ ውል መሠረት አዲስ አበባ (ሜክሲኮ) ቅርንጫፍ በጥበቃ ሥራ መደብ በየዓመቱ በሚታደስ ኮንትራት በወር ተከፋይነት በወር ብር 1,771.00 (አንድ ሺህ ሰባት መቶ ሰባ አንድ ብር) እና የትራንስፖርት አበል ብር 354.20 (ሦስት መቶ ሃምሳ አራት ብር ከ20/100) እየተከፈላቸው ሥራቸውን በማከናወን ላይ የነበሩ መሆናቸውን እየገለጽን ከደሞዛቸው ላይ ተገቢ የሥራ ግብርና የጡረታ መዋጮ እየተቀነሰ ለሚመለከተው መንግሥታዊ መሥሪያ ቤት ገቢ የተደረገ መሆኑን እናሳውቃለን የሚል ደብዳቤ ሰጥቷል።
ለአቶ ኃይሉ አስፋው ሥራ መፈለጊያ እና አገልግሎት ክፍያ ይገባኛል፤ መብቴ ተነፍጓል ብለው በቀን 26/11/2013 ዓ.ም ጽፈው ላቀረቡት ቅሬታም፤ ድርጅቱ እንዲህ ሲል መልሷል፡፡ ሥራ መፈለጊያ እና አገልግሎት ክፍያ ይገባኛል ብለው በቀን 26/11/2013 ዓ.ም ጽፈው ላቀረቡት ቅሬታ በተሰጠው ምላሽም፤ የሥራ መፈለጊያና የአገልግሎት ክፍያ ጥያቄ ምላሽ ይመለከታል በሚለው ደብዳቤ፣እርስዎ በድርጅታችን ውስጥ በጥበቃ የሥራ መደብ ከየካቲት 21/2005 ዓ.ም ጀምሮ ሲያገለግሉ ቆይተው በራስዎ ፍላጎት ሥራ የለቀቁ በመሆኑ የሥራ መፈለጊያና የአገልግሎት ክፍያ እንዲከፈልዎ ጠይቀዋል። ከድርጅታችን ጋር በነበረዎት ቆይታ በተለያዩ ጊዜያት በኮንትራት የገቡት ውል ተጠናቆ የሥራ ውልዎ ከተቋረጠ በኋላ በድጋሜ ተቀጥረው ያገለገሉ በመሆንዎ የአገልግሎት ክፍያ ጥያቄዎትን ለማስተናገድ እንቸገራለን ሲል ምላሽ ይሰጣቸዋል፡፡
አቶ ኃይሉ በዚህ ብቻ አላቆሙም ይልቁንም ወደ ፍርድ ቤት አቅንተዋል፡፡ የክሱ ዝርዝር መግለጫም አንደኛ፤ ከሳሽ በተከሳሽ ድርጅት ውስጥ ከየካቲት 21 ቀን 2005 ዓ.ም ጀምሮ በጥበቃ ሥራ ተቀጥሬ በወር ብር 3500.00 እየተከፈለኝ በድርጅቱ ውስጥ በቅንነትና በታማኝነት ሳገለግል ቆይቼ ሥራዬን በፍቃዴ መስከረም 19 ቀን 2014 ዓ.ም አቋርጫለሁ የሚል ነው፡፡
ሁለተኛው ደግሞ ከሳሽም በተከሳሽ ድርጅት ውስጥ ዘጠኝ ዓመት ያገለገልኩኝና በራሴ ፍቃድ የለቀኩኝ በመሆኑ ከአምስት ዓመት በላይ ያገለገለ ሠራተኛ በራሱ ፍቃድ የሥራ ውሉ ሲቋረጥ የአገልግሎት እንደሚከፈል በግልጽ በሕጉ ላይ የተቀመጠ በመሆኑ የአገልግሎት ክፍያ እንዲከፈለኝ መስከረም 28 ቀን 2014 ዓ.ም በተጻፈ ደብዳቤ ብጠይቅም የኮንትራት ሠራተኛ በመሆንዎ ሊከፈል አይገባም በማለት ምላሽ ተከሳሽ የሰጠኝ ሲሆን ተከሳሽ የኮንትራት ውል ከሳሽን የሚያስፈርመው በአሰሪና ሠራተኛ አዋጅ አንቀጽ 10 ውጪ በመሆኑና ተከሳሽ ድርጅት የተደራጀበት ዋና ዓላማ በተለያየ ድርጅቶች ውስጥ የጥበቃ ሠራተኞችን ማስቀጠር ነው፡፡ ይህ ሥራ ደግሞ ጊዜያዊ ሳይሆን ቋሚና ዘላቂ ሲሆን ሥራውም እስሁን ድረስ የሚሠራ ሲሆን ተከሳሽ ከሳሽን በተለያየ ድርጅት እያዛወረ ሲያሰራ የነበረ ከመሆኑም በላይ ለአንድም ቀን ሳይቋረጥ ከሳሽ በተከሳሽ ድርጅት ውስጥ ለዘጠኝ ዓመት ያህል ማገልገላቸውን በመግለጽ ከሕጉ ውጪ ኮንትራት እያለ ለራሱ ጥቅም ሲል ሲያስፈርመኝ ቆይቶቷል ብለው አቤቱታቸውን አቅርበዋል፡፡
በሦስተኛ ደረጃ ደግሞ ከሳሽም ክሊራንስ የጨረስኩኝ እና በራሴ ፍቃድ የለቀኩኝ በመሆኑ በሕጉ መሠረት ሊከፈል የሚገባው ክፍያ እንዲከፈለኝ በደብዳቤ ብንጠይቅም ድርጅቱ ሊከፍለኝ ፍቃደኛ አይደለም በማለት ለፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ንፋስ ስልክ ላፍቶ ምድብ ሥራ ክርክር ችሎት ጥቅምት 9ቀን 2014 ዓ.ም ክስ አቅርበው ነበር።
ከሳሽ ባቀረቡት ክስም ፍድር ቤቱን የምንጠይቀው ዳኝነት ከሚያዝያ 5 ቀን 2005 ዓ.ም ጀምሮ እስከ መስከረም 19 ቀን 2014 ዓ.ም ድረስ የአገልግሎት ክፍያ ብር 12,833.33 ( አስራ ሁለት ሺህ ስምንት መቶ ሰላሳ ሦስት ብር ከ33/100) እንዲከፍሉ እንዲወሰንልኝ፤ በተጨማሪም ክፍያ እንዲፈጽሙልኝ በተደጋጋሚ ብጠይቅም ለመክፈል ፍቃደኛ ባለመሆናቸው በአንቀጽ 38 መሠረት ከሳሽ የ3 ወር ደመወዝ ብር 10,500.00 (አስር ሺህ አምስት መቶ ብር ) እንዲከፍሉ እንዲወሰን፤ ወጪና ኪሳራ በፍ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 463 እና 464 መሠረት እንዲከፈለኝ ብለው ጠይቀዋል፡፡
የቀረበው ክስም እውነት መሆኑን በፍትሐብሄር ሥነ ሥርዓት ቁጥር 92 መሠረት አረጋግጣለሁ ሲሉ ነበር ወደ ችሎት ያመሩት፡፡
ፍርድ ቤቱም ግራ ቀኙን በማየት ውሳኔ ሰጥቷል። በዚህም መሠረት ከሳሽ ተከሳሽ እንዲከፈላቸው የጠየቁት ክፍያ በሕጉ መሠረት ለማየት ተሞክሯል። በመሆኑም በአሰሪና ሠራተኛ አዋጅ 1156/2011 በሕግ አግባብ የተደረገ የውል ተዋዋዮች ወገኖች ላይ ከውል፣ ከሕግና ከህብረት ስምምነት የሚመነጭ መብት የሚያጎናጽፍ ስለመሆኑ የሚጠቅስ ቢሆንም ግዴታዎችንም ይጥላል። ይህንንም ከግምት ውስጥ በማስገባት ውሳኔ ለመስጠት አንዱ መነሻ ሆኗል፡፡
በተጨማሪም ሕጋዊ ቅድመ ሁኔታዎች አሟልቶ የተደረገ ሥምምነት እንዴት እና መቼ መቋረጥ አለበት? የሚለውም በአንቀፅ 23 መሠረት ታይቷል። የሥራ ስንብት ክፍያን በተመለከትም አንቀፅ 39 እና 41 ላይ የተደነገገ መሆኑን የተመላከተ ሲሆን፤ እነዚህን የሕግ ማጣቀሻዎችን በማየትና በፍርድ ቤቱ በተመለከተው ዝርዝር ምክንያት በአቶ ኃይሉ አስፋው የቀረበው ክስ ውድቅ መደረጉን በመዝገብ ቁጥር 177232 ኅዳር 24 ቀን 2014 ዓ.ም አሳውቋል፡፡
የድርጅቱ ኃላፊዎች
አቶ አንተነህ ታከለ የኒው ጀነሬሽን የሎጅስቲክና የሰው ሀብት ሥራ አመራር ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ዋና ሥራ አስኪጅ ናቸው፡፡ እሳቸው እንደሚሉት በሠራተኛ እና ቀጣሪ ድርጅት መካከል አለመግባባቶች ይጠበቃሉ ዋናው ጉዳይ ቅሬታ መቅረቡ አለመቅረቡ ሳይሆን በወቅቱ ምላሽ መሰጠቱ ላይ ነው ትኩረት መደረግ ያለበት፡፡ እኛም ለግለሰቦቹ ቅሬታ አፋጣኝ መልስ በመስጠት የሚጠበቅብንን በአግባቡ ተወጥተናል፡፡ እኛ ድርጅታችን ሥም በየቦታው እንዲነሳ አንፈልግም፡፡ በመሆኑም ችግሮች ካሉም በአግባቡ መፍትሄ ለመስጠት እንሞክራለን ብለዋል፡፡
ነገር ግን አንዳንድ ግለሰቦች ከሚገባቸው በላይ የመጠቀም ዝንባሌ አላቸው፡፡ የአቶ አበራ እና ኃይሉ አስፋው ሃሳብም ከዚህ ተለየ አይደለም ይላሉ። ሌላው ቀርቶ ችግሮችን በሽምግልና እና በድርድር ለመፍታት ብዙ ጥረት መደረጉን ይጠቁማሉ፡፡ ለአብነትም ለንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ አስተዳደር የሥራ፣ ኢንተርፕራይዝና ኢንዱስትሪ ልማት ፅህፈት በተደጋጋሚ ውይይት መደረጉን ጠቁመዋል፡፡ አለፍ ሲልም የኢንዱስትሪን ሰላም ለማስፈን ሲል የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሥራ፣ ኢንተርፕራይዝና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ድረስ ቅሬታ አቅርበው እንደነበር እና እዚያም ድረስ በአካል በመሄድ ውይይት መደረጉን ያስታውሳሉ፡፡
የኒው ጀነሬሽን የሎጅስቲክና የሰው ሀብት ሥራ አመራር ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር የሰው ሀብትና ኦፕሬሽን ሥራ አስኪያጅ አቶ መስፍን ዘለቀ በበኩላቸው፤ በድርጅቱ ላይ ቅሬታ እያቀረቡ ያሉት እነዚህ ግለሰቦች አካሄዳቸው አግባብ አይደለም፡፡ በተደጋጋሚ ቅሬታቸውን በደብዳቤ የገለፁልን ሲሆን፤ እኛም በዚያው አግባብ ምላሽ ስንሰጥ ቆይተናል። ዳሩ ግን ጉዳዩን ወደ ሚዲያ ማምጣት የተፈለገው በሕጋዊ መስመር ጉዳያቸው መፈፀም የሚያስችላቸው አግባብ ባለመኖሩ እንጂ ትክክለኛ አካሄድ ቢኖር ኖሮ ወደ ፍርድ ቤት እና ሚዲያም መሄድ ባልመረጡ ነበር ይላሉ፡፡ በመሆኑም እነዚህ ግለሰቦች የተቋማችንን ሥም ለማጥፋት ካልሆነ በስተቀር በሕጋዊ አሠራር መሠረት የተበደሉት ነገር የለም፤ እኛም ሕጋዊ አሠራሩን እየተገበርን በመሆኑ እውነታው ሊታወቅልን ይገባል ባይ ናቸው፡፡
ክፍለዮሐንስ አንበርብር
አዲስ ዘመን ሰኔ 28/2015
Having read this I believed it was very informative.
I appreciate you taking the time and effort to put this information together.
I once again find myself spending a lot of time both reading
and commenting. But so what, it was still worthwhile!